አንዳንድ ሰዎች ለበጎ ስራ የተፈጠሩ ናቸው። ከተወለዱባት ቅጽበት ጀምሮ ይህቺን አለም በመልካም ባህሪና ተግባራቸው የሚፈውሱና የዚህች አለም ገጸ በረከት ተደርገው የሚወሰዱ ሰዎች ጥቂትም ቢሆኑ በየአካባቢው አሉ።የዛሬው የድሬደዋ በጎነት ተምሳሌት ወ/ሮ አሰገደች አስፋው ለዚህ አባባላችን አብነት የሚሆኑ ናቸው።
ወይዘሮ አሰገደች አስፋው የ90 አመት አረጋዊ ናቸው። የዕድሜያቸውን ዕኩሌታ ያሳለፉት ነድያንን እና አረጋውያንን በመንከባከብ ነው። ከልጅነታቸው ጀምሮ ሰዎችን መርዳት ይወዱ ነበር። በኋላም አድገው የራሳቸውን ኑሮ ሲመሰርቱ ነዳያንን በቤታቸው እያስጠጉ መርዳት ጀመሩ። የትዳር አጋራቸው በሞት ሲለዩዋቸውና ልጆቻቸውም ራሳቸውን እየቻሉ ከቤት ሲወጡ፣ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ለበጎ አድራጎት ስራ ሠጡ።ከ50 አመታት ላላነሰ ጊዜ በጎ እያደረጉ ለብዙዎች መከታ መሆን ቻሉ።
ወይዘሮ አሰገደች አስፋው የዕድሜያቸውን ዕኩሌታ ለከፈሉበት የበጎ አድራጎት ስራቸው ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል። እናት ባንክ ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ በስማቸው አንድ ቅርንጫፍ ሰይሞላቸዋል።
ለብዙዎች መከታ የሆነው ተቋም
በእኒህ ብርቱ ሰው የተቋቋመው ድርጅት አሰገደች የአረጋውያን ማቋቋሚያና መንከባከቢያ ይባላል። በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያውና አንጋፋ ድርጅት ነው። ዶክተር አሰገደች ህይወታቸውን ሙሉ ለዚህ ድርጅት መስዋዕት አድርገዋል።የተመሰረተውም የዛሬ 30 አመት አካባቢ ነው። አካባቢውን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች እንደሚናገሩት አሁን ድርጅቱ ያለበት ሰፈር ከዚህ ቀደም ጫካ የነበረ ነው። ሰፈሩን በማስተካከል ለአረጋውያን ምቹ እንዲሆን ያደረጉት ወ/ሮ አሰገደች ናቸው።
ወ/ሮ አሰገደች ይህንን የአረጋውያን ማቋቋሚያና መንከባከቢያ ድርጅቱ ከማቋቋማቸው በፊት አረጋውያንን ይረዱ የነበሩት በወላጅ አባታቸው ቤት ነበር።ከዚሁ ጎን ለጎንም በየሆስፒታሉ እየሄዱ የታመሙ ሰዎችን ያጽናኑ ነበር።
የወ/ሮ አሰገደች ልጅ የሆነችው ወይዘሮ እመቤት፤ እንደምትናገረው ወ/ሮ አሰገደች ገና ከጅምሩ ሁለት አላማ ነበራቸው። የመጀመሪያው አረጋውያንን መሰብሰብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ አገልግሎት ሰጥተው ሜዳ ላይ የሚጣሉ ፈረሶችን ሰብስበው ከአደጋ የመከለል አላማ ነበራቸው። ነገር ግን ከጎረቤት ጋር በዚህ ጉዳይ መስማማት ስላልቻሉ ፈረሶችን የመሰብሰቡ ነገር አልተሳካላቸውም።
ወይዘሮ እመቤት እንደምትናገረው ወ/ሮ አሰገደች ሥራውን የጀመሩት በእናትና በአባታቸው መኖሪያ ቤት ነው።ያለምንም የኃይማኖትና የዘር ልዩነት የተቸገሩ አረጋውያንን ከመንገድ በማንሳት ለብዙዎች አለኝታ መሆን የቻሉ ብርቱ ሴት ናቸው። በእናትና በአባታቸው መኖርያ ቤት አረጋውያንን በማሰባሰብ ከሰላሳ አምስት አመት በፊት ሥራውን የጀመሩ ሲሆን እስከአሁንም ድረስ ይህው በጎ ተግባር ቀጥሎ ብዙዎችን ማቀፍ ችሏል።በአሁኑ ወቅት በአረጋውያን ማቋቋሚያና መንከባከቢያ ድርጅቱ ውስጥ ለሀገራቸው በተለያየ መስክ አገልገሎት የሰጡ አረጋውያን የሀገር ባለውለታዎች እየተደገፉ ይገኛሉ።
የ120 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ሰውን ጨምሮ ባለፉት ዘመናት በሀገሪቱ ስልጣን ላይ የነበሩ፣ ባለሀብት የነበሩ ግለሰቦች በዚህ ድርጅት አማካኝነት ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛሉ።እንደሀገር በርካታ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎች እንደዘበት ጎዳና ወድቀው ሲገኙም ይህ ድርጅት ሰብስቦ ተስፋ ሆኗቸዋል።
ይህ በጎ ተግባር ዕውቅና አግኝቶ ለማዕከሉ መስራች ለወይዘሮ አሰገደች አስፋው ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።
ድርጅቱ ስለሚተዳደርበት ሁኔታ
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ የሚተዳደረው ዘጠና ዘጠኝ በመቶ በኢትዮጵያ ህዝብ መዋጮ ነው። የመንፈሳዊ በዓላት ሲኖሩ ሰዎች ይመጡና አረጋውያንን ይመግባሉ። የመንግሥት ተቋማትም የተቻላቸውን ድጋፍ በማድረግ ይህ ድርጅት በሁለት እግሩ እንዲቆም አድርገዋል። በተጨማሪም ድርጅቱ ያሉትን የወተት ላሞች በመጠቀም ለአረጋውያን ወተት ከማቅረብ በተጨማሪ ከወተት ኪራይ ከሚገኝ ገቢ ሌሎች ወጪዎችን በመሸፈን ይተዳደራል።
በተጨማሪም ድርጅቱ ሰፊ የሆነ የእርሻ ቦታ አለው። ጊቢው ገነት በምድር የሚያስብል በአረንጓዴ ተክል ያማረ ከመሆኑ ባሻገር ቲማቲም፣ ጎመን፣ ቆስጣ፣ የቻይና ቆስጣ፣ ሰላጣ እና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን እንዲሁም ፍራፍሬዎች አፕል ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ኮምጣጤ እና ሎሚን ተክለው ለገበያ ያቀርባሉ። በተጨማሪ የሽንኩርት ማሳ እና ዶሮ ከማርባት ጎን ለጎን አሳዎችም ይረባሉ። ከእነዚህ በሚገኘው ገቢ እራሱን ይደጉማል።
በእርሻ ማሳው ላይ የተለያዩ ፍራፍሬ አትክልቶችን በመትከልም ለድርጅቱ ለምግብነት ከማዋል ባለፈ ለህብረተሰቡ በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ያገኛል። ለወተት ከብቶች መኖ የአጨዳ ወጪን ጨምሮ በመሸፈን የኢትዮጵያ አየር ሀይልና ሌሎች ግለሰቦች በሚያደርጉት ትብብር መኖ ይሰበሰባል።ለአካባቢው ማህበረሰብም ወተት በተመጣጠኝ ዋጋ በማቅረብ ይታወቃል። በድሬዳዋ ከተማ አንድ ሊትር ወተት 110 ብር ሲሆን ይህ ድርጅት ግን በ70 ብር በማቅረብ በተጓዳኝ ለህብረተሰቡ ጥቅም በማስገኘት ላይ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ በድርጅቱ ባለቤትነት የሚተዳደር ባለሶስት ወለል ህንፃን በማከራየት ገቢውን ለአረጋውያን የእለት ወጪ ያውላል።
የወ/ሮ አሰገደች ልጅ የሆነችው ወ/ሮ እመቤት እንደምትናገረው ከዚህ በፊት የነበሩ አረጋውያን ጥቂትም ቢሆን ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ይሰሩ ነበር።አረጋውያኑ ፈትል በመፍተል፤ ነጠላ በመቋጨት፣ ሽመና በመስራት ገቢ ያገኙ ነበር። አንዳንዶቹም በርበሬ በመዝራት የተሻለ ገቢ ነበራቸው። አሁን ያሉ አረጋውያን ግን እድሜያቸው የገፋና አቅመ ደካማ በመሆናቸው ምንም አይነት ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ አይሰሩም።ይህም በድርጅቱ ላይ ጫና ማሳዳሩን ትገልጻለች።
ማዕከሉ አሁንም ለአረጋውያኑ የምግብ ማብሰያ የሚጠቀመው በእንጨት ነው። በቀጣይ በሰዎች እና በከብት እዳሪ በባዮጋዝ ለመጠቀም፤ አምፖልም ቢሆን በሶላር የሚሠሩትን ለመገልገል አቅደዋል።
ከሁሉ የከፋው ግን የአረጋውያኑ መጸዳጃ ቤትና መኝታ ክፍል ሁኔታ ነው።በርካታ አረጋውያን የሚጠቀሙት በአንድ መጻዳጃ ቤት ነው።ይህ ከእድሜያቸው መግፋትና ከጤንነት አንጻር ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህም በቀጣይ እያንዳንዱ የአረጋውያን ክፍል ከኋላ ዘመናዊ ሽንት ቤት እንዲኖራቸው ማቀዳቸውን ትናገራለች።
መኝታ ቤትን በተመለከተ አረጋውያኑ በአንድ ክፍል አራት ሆነው ተጨናንቀው የሚኖሩበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህ ተሻሽሎ እያንዳንዱ አረጋዊ ለየብቻ ምቹ በሆነ መልኩ የመጨረሻ ሕይወታቸውን እንዲያሳልፉ እንደሚፈልጉም ይናገራሉ።
በማዕከሉ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ባላቸው ተነሳሽነት ጫማ ጠርገው እና በተለያየ መንገድ ገንዘብ ሰብስበው በጊቢው አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ ተቋቁሟል። በጎ ፈቃደኛ ሓኪሞችም ክሊኒኩ ድረስ በመሔድ የሚያክሙላቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ድርጅቱ በእስከዛሬው ጉዞ ምን ያህል ሰዎች ረድቷል?
የወ/ሮ አሰገደች ልጅ የሆነችው ወይዘሮ እመቤት እንደምትናገረው አሰገደች የአረጋውያን ማቋቋሚያና መንከባከቢያ ድርጅት ከመቋቋሙ በፊትም ሆነ በኋላ በርካታ ሰዎችን ሲደግፍ ቆይቷል።ሆኖም ትክክለኛውን አሃዝ አስረግጦ መናገር ባይቻልም ከቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጀምሮ ባለሀብቶች እንዲሁም የውጭ ሀገር ዜጎች ድረስ በዚህ ድርጅት አማካኝነት ድጋፍ አግኝተዋል።
እንደ ወይዘሮ እመቤት ገለፃ፤ አሁን በግቢ ውስጥ በቁጥር ዘጠና የሚደርሱ ሰዎች አሉ፤ ከዚህ ውስጥ 20 የሚሆኑት የድርጅቱ ሰራተኞች ናቸው። በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግላቸው ደግሞ 70 አረጋውያን ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ እየተመላለሱ ቁርስ ምሳ እራት የሚያገኙ አሉ። በራሳቸው መኖሪያ ቤትም እየኖሩ በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግላቸው 20 አረጋውያንም አሉ።
ድርጅቱ አሁን ያለበት ሁኔታ
አሰገደች የአረጋውያን ማቋቋሚያና መንከባከቢያ ድርጅት አሁንም ለበርካቶች መድህን ሆኖ የቀጠለ ቢሆንም ዋናዋ መስራች የሆኑት ወ/ሮ አሰገደች በእድሜ መግፋት ድርጅቱን እንደቀድሞው መምራት ስላልቻሉ በእሳቸው ምትክ ልጃቸውን ተክተዋል።
ልጃቸው ወ/ሮ እመቤት ኑሯቸውን በካናዳ ሀገር ያደረጉ ቢሆንም በእረፍት እናታቸውን ለመጠየቅ ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ወቅት በሚያዩት በጎነት የተነሳ የበጎነት ሥራውን እንደቀጠሉ ይናገራሉ።
‹‹እናታችን እያስተማረች ያሳደገችን ቅንነትን ነው›› የሚሉት ወይዘሮ እመቤት፤ ‹‹እኔም ይህንኑ ተከትዩ በእናቴ መንገድ ህዝቤን ለማገልገል እየሞከርኩ ነው›› ሲሉ ነግረውናል።
ወ/ሮ እመቤት እንደሚሉትም‹‹ህይወት ማለት አንድ እጅህን ለሌላ ሰው መዘርጋት ነው። የህይወትን ጣዕም ማወቅ የሚቻለው ያኔ ነው። አለበለዚያ መኖር ትርጉም የለውም። ሰው ሁልጊዜ ይህንን አደርጋለሁ፤ እንዲህ እሆናለሁ ይላል እንጂ መቼ እንደሚሞት አያውቅም፤ ሰውን በገንዘብ ብቻ አይደለም መርዳት የሚቻለው ፤ግዜ መስጠት በራሱ ትልቅ እርዳታ ነው›› ይላሉ።
ሰው ከራሱ በላይ ያለውን እንጂ የበታቹን አያይም የሚሉት ወይዘሮ እመቤት፤ሁልጊዜ የራስን ስሜት እየተከተሉ መኖር እርካታ እንደማይሰጥ ይናገራሉ።ከእናታቸውም የተማሩት ከራስ ይልቅ ለሰው መኖር መሆኑን ያስረዳሉ።
በመኖር ውስጥ የሚገኘው ትልቁ ስኬት ለሌሎች መድረስ መቻል ነው ይላሉ። አንድን ሰው በህመሙ ግዜ ሳንጠይቀው በሞተ ግዜ የገንዘብ መዋጮ ብናደርግ ትርጉም እንደሌለው ይናገራሉ።
ሰዎች ምን ይላሉ
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ይሠሩ የነበሩት ታችዘሩ አበበ የኦዲት ሥራ ላይ ሲሰሩ ወይዘሮ አሰገደችን እንደተዋወቋቸው ይናገራሉ። በ2000 ዓ.ም አካባቢ ወደ ማዕከሉ ገብተው ሥራ የጀመሩ ሲሆን፤ ከ15 ዓመት በላይ መቆየታቸውን ያብራራሉ።
በዛ ጊዜ ወይዘሮ ታችዘሩ ወይዘሮ አሰገደችን በድሬዳዋ ሀሩር ፀሃይ በእግራቸው እየሔዱ በየቢሮ ገንዘብ ሲሠበስቡ ተመልክተው፤ ‹‹ 25 ሳንቲም ከፍለሽ ለምን በታክሲ አትሔጂም? ›› ብለው ወይዘሮ አሰገደች ሲጠይቁ፤ ‹‹ሳንቲሙ ለሁለት አረጋዊ ዳቦ ይገዛልኛል›› ብለው መልስ እንደሰጧቸው ያስታውሳሉ።
‹‹የወይዘሮ አሰገደች ቤተሰቦች ከ30 ዓመት በላይ ካናዳ ኖረዋል። ነገር ግን ያንን ትተው መጥተው፤ ሰዎችን እያገለገሉ ነው።›› የሚሉት ወይዘሮ ታችዘሩ፤ ሰዎች ለራሳቸው ቤተሰብ እንኳን ጥያቄ ምላሽ መስጠት እና መታዘዝ ሲሰለቻቸው እነወይዘሮ አሰገደች እና ቤተሰቦቻቸው ብዙዎችን መርዳታቸው እና ለብዙዎች ጥያቄ መልስ መስጠታቸው እጅግ እንደሚያስገርማቸው ይናገራሉ።
እንደወይዘሮ ታችዘር ገለፃ፤ ወይዘሮ አሰገደች ግን ሰው ሲታመም ሃኪም ቤት ይዘው ይሔዳሉ። ከብት ሲታመም ያሳክማሉ፤ ግብርናው ሲበላሽ ወደ እዛም ይሔዳሉ። ምንም እረፍት የላቸውም።
በማዕከሉ የሚያዩትን አሳዛኝ ነገር ሲገልፁ፤ ‹‹ ለአረጋውያኑ መርጃ የተጀመረው ህንፃ ከቆመ 15 ዓመት አልፎታል። ያም ቢሆን በከፊል ለንግድ ተከራይቷል፤ ገቢው ለአረጋውያኑ እርዳታ ይደረግበታል። ነገር ግን አጠናቆ የተሻላ ገቢ ማግኘት አልተቻለም። ሰሞኑን በመከላከያ ድጋፍ እየተሠራ ነው። ነገር ግን የድሬዳዋ ሕዝብም ሆነ መንግስት አግዞ ህንፃው ቢጠናቀቅ ለማዕከሉ ትልቅ አቅም።›› ይሆናል ይላሉ።
በማእከሉ ሰላሳ አመታት ያገለገለችው ሴት
ወይዘሮ መቅደስ ታደሰ ትባላለች። ባለ ትዳርና የልጆች እናት የሆነችው ይህች ሴት ከወይዘሮ አሰገደች ጋር የተገናኙበትን አጋጣሚ በዚህ መልኩ ትናገራለች። “ ድሬዳዋ ውስጥ እናቴን ወ/ሮ አሰገደችን ሳቃት ከሰላሳ አመት በላይ ሆነኝ። እናቴ የምላት ወልዳኝ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ እናት አድርጌ ስለማያት ነው ።
እኔም በተፈጥሮዬ ድሃ እወድ ስለነበር ከሷ ጋር አንድ አይነት የነፍስ ጥሪ ስላለን ተገናኝተናል። በአንድ ወቅት ታዲያ እናቴ ወይዘሮ አሰገደች ድል ጮራ ሆስፒታል አካባቢ የወደቁ አረጋዊት ለማንሳት ሲሞክሩ ከእኔ ጋር ተገናኘን።በጊዜው አግዣት ወደ ቤቷ በወሰድኩበት አጋጣሚ ነበር የተገናኘነው። ከዛ በኋላ ነው አንግዲህ እናቴን ተከትዬ መጣሁ ። አብሪያት ከሆንኩም ከሀያ አመት በላይ ሆኖኛል።
መጀመሪያ ድሆችን በቤቷ ነበር የምትሰበስበው ፤ከዛ በኋላ ጫካ በመመንጠር የአረጋዊያን መሰብሰቢያ ተቋም እንዲቋቋም ያደረገች ብርቱ ሴት ናት። እናቴ በጣም ደከመኝ ሰለቸኝ የማታውቅ ሰው ናት። ለራሷ ምቾት የማትጨነቅ፤ የማይርባት፤ የማይደክማት ሴት ናት። የምትተኛው እንኳን ኬሻ ላይ ነበር ።
ለአረጋውያን የሚቀርበው ምግብ የሚዘጋጀው በጥንቃቄ ነው።የሚቀርበው ምግብ ሁሉ የሚዘጋጀው ቤት ውስጥ ነው። አረጋዊያኑ የሚበሉት ምግብ ጣእሙ እንዳይቀያየር እንኳን ከፍ ያለ ጥንቃቄ ታደርጋለች።
እናቴ በጣም የእምነት ሰው ናት ።አንዴ ታማ ቤቱን እያስተዳደርኩ አያለ ጤፍ ያልቃል። ወዲያው እናቴ ጋር ገብቼ ለሁለት ጊዜ ቡኮ የሚሆን ነው የቀረው ስላት እኔ ምን አግብቶኝ ነው፤ የሰማይ አምላክ እራሱ አረጋዊያኑን ይመግባቸዋል አለችኝ። ይህን ባለች ቅፅበት ውስጥ አንድ ድርጅት ሁለት መቶ ኪሎ ነጭ ጤፍ ላከለን። በእምነት በረከትን የምታገኝ ታላቅ ሰው ናት። ከእሷ በእምነት መፅናትን ተምሪያለሁ “ ትላለ ች።
የድሬደዋ ሰው መስጠት የሚችለው ነገር እንኳን ቢያጣ መጥቶ የአረጋውያን ገላ ያጥባል፤ጸጉራቸውን ይቆርጣል፤ይላጫል።የታይዋን ሰዎች በአል ጠብቀው አዳዲስ ልብስ አረጋዊያኑን ያለብሳሉ። ሰርግ ልደት አና ዝክር በጊቢው ስለሚከበር አንድም ቀን ጎድሎ እንደማያውቅ ወይዘሮ መቅደስ ትናገራለች።።
ወይዘሮ መቅደስ አክላም ቤቱ በርካታ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች የሚመረትበት፤ ላም ረብቶ ወተት ከግቢው ነዋሪዎች ፍጆታ የተረፈውነ በመሸጥ ጎዶሎ የመሙላት ሰራ ይሰራል።
ወይዘሮ አሰገደች ለአረጋዊያኑ ፍጆታ የሚውል ነገር ለመለመን ስትሄድ ቁጭ በይ እንኳን ሲሏት “የኔ ቢጤ ቆሞ ነው የሚለምነው ፤ሲደረግለት ነው ቁጭ የሚለው” በማለት ተማፅና በግቢዋ ያስጠለለቻቸውን አረጋዊያን ትመግባለች።
መቀመጥ እርጅናን ያብሳል የምትለው ወይዘሮ አሰገደች አቅም የላቸው አረጋዊያን በሚችሉት ሁሉ የገቢውን ስራ እንዲረዱ ያደርጉ ነበር።አረጋውያን በሞት እስኪለዩ ድረስ መጦርያ ቤታቸውነ ወደውት እንደ ቤተሰብ እንደሚኖሩ ብዙዎች ይናገራሉ።
በማእከሉ የሚገኙ አረጋዊያን ምስክርነት
በአረጋዊያን ማእከሉ የሚኖሩት ወይዘሮ አፀደ ተሰማ የተወለዱት ወሎ እንደሆነ ይናገራሉ። ከወሎ ወደ ድሬደዋ የመጡት ከባላቸው ጋር ሲሆን ልጅ ባለመውለዳቸው ምክንያት ከባላቸው ጋር ተለያይተው ሳብያን የተባለ አካባቢ ይኖሩ እንደ ነበር ይናገራሉ። አቅመ ደካማ ጧሪ ሲያጡ ግን ወደ አረጋዊያን ማእከሉ የመጡት እኝህ ሴት በማእከሉ ሶሰት አመታትን አሳልፈዋል።
ልጅ ባለመውለዳቸው ምክንያት ሲከፉ የነበሩት እማማ አፀደ የወንድማቸውን ልጅ በሶሰት አመቷ አምጥተው ያሳደጉና ያስተማሩ ሲሆን ያላቸውን ንብረትና ጌጥ ሸጠው ቤታቸውንም ጭምር ከሞቱ በኋላ እንደትወርስ ይሰጧታል። ልጅቷ ባል ሰታገባ ቤት ንብረታቸው አንዴ በስሟ ሰለሆነ እማማ አፀደን አውጥታ ጎዳና በመጣል ቤቱን ሸጣ አዲስ አበባ ገባች።
ጎዳና መውጣታቸውን የተመለከተች አንዲት የጎረቤት ልጅ ይዛቸው ብትቆይም እሷ አሜሪካ ሀገር በመሄዷ የተነሳ ወ/ሮ አሰገደች ወደ አቋቋሙት ማእከል እንደመጡ ይናገራሉ። በተቋሙ መንፈሳዊ ህይወታቸውን እያካሄዱ በልጆች እንደሚደረግላቸው አይነት አንክብካቤ እየተደረገላቸው በመኖር ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።
ሌላዋ በደርጅቱ የሚኖሩ አረጋዊት ወይዘሮ አለሚቱ መኮንን ይባላሉ። እማማ አለሚቱ ወሎ ስጎን የተባለ ቦታ የተወለዱ ሲሆን አግብተው የወለዱና አንድ ልጃቸው የሞቱባቸው ሲሆን ወደ ድሬደዋ ሰው ተከትለው መጥተው ለመሰራት እየሞከሩ ነበር። በጦርነት በፈንጂ አግራቸውን ያጡት በዚሁ ምክንያት ወደ ተቋሙ መጥተው የሚረዱ እናት ናቸው።
እግር አልባዋ እናት በደርግ ጦርነት ወቅት የአካል ጉዳት የገጠማቸው ሲሆን እርጅና መጥቶ ሳይጫናቸው በፊት የአረጋዊያን ማእከል ውስጥ ተቀምጠው መስራት የሚችሉትን ስራ በሙሉ ይሰሩ እንደ ነበረ ያስታውሳሉ።
ከሰላሳ አምሰት አመት በላይ በማእከሉ የቆዩት እናት ምሰር መልቀም ፤ሽንኩርት መላጥ የመሳሰሉ ስራዎችን ይሰሩ እንደ ነበር ያስታወሳሉ። በማእከሉ ምንም ሳይጎልባቸው ፤ ፅዳታቸው ተጠብቆ፤ በልተው፤ ጠጥተው፤ የእርጅና ዘመናቸውን መቆየታቸው ወይዘሮ አሰገደችን እያመሰገኑ እንዲኖሩ አንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
ሌላው በአረጋዊያን ማእከል የሚኖሩ አባት አቶ ገዛሄኝ ሄርፖ ይባላሉ። አቶ ገዛሄኝ የተወለዱት ሂርና ሲሆን እስከ ስምንተኛ ክፍል በተወለዱበት አካባቢ ተምረዋል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአሰበ ተፈሪ መማራቸውን ያስታውሳሉ።
በወቅቱ በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት የተነሳ ትምህርታቸውን አቁመው ወደ ጦርነት ከገቡት ዘጠኝ ጓደኞቻቸው መካክል አሳቸው ሲተርፉ ወደ ግብርና ስራ መሰማራታቸውን ይናገራሉ። ከአስረኛ ክፍል አቋርጠው እርሻ የገቡት አባት ስራቸውን እየሰሩ የተወሰነ ጥሪት እያፈሩ ከቆዩ በኋላ በዱር በገደሉ ያለህ ወገን ሰራዊቱን ተቀላቀል ሲባል የእናት ሀገር ጥሪን ተቀብለው ወደ ውትድርና መግባታቸውን ይናገራሉ።
ድሬደዋ በ1972 የመጡት እኚህ ሰው በጥበቃም በጉልበትም ሰራ ሲሰሩ ቆዩ ። ለአመታት ያገኙትን እየሰሩ የሰው እጅ ሳይጠብቁ ቢኖሩም በቅርብ ጊዜ ቤታቸው በጎርፍ በመወሰዱ የተነሳ ተረጂ ሆነው ወደ ማእከሉ መምጣታቸውን ይናገራሉ።
በተቋሙ መግባታቸው ቡናው ጫወታው ደስ የሚል እረፍት እንደሰጣቸው ይናገራሉ። ሰው እንደ ቤተሰብ ስለሚጠየቅ ይደሰታሉ። ንፁህ አልባሳትን በማግኘታቸው ደስታ እንደተሰማቸው ይናገራሉ።ለዚህ ሁሉ መሰረት የሆኑትን ወይዘሮ አሰገደች አስፋውን ያመሰግናሉ፤ረጅም ዕድሜም ይመኛሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም