በአረንጓዴ አብዮት ሒደት

በአለማችን ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ጋር ከተያያዙ ኩባንያዎች በማስከተል ኢኮኖሚውን ይመራል ተብሎ የሚጠበቀው ግብርና ዘርፍ ነው።ቻይናንና ሕንድን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ዜጎች መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ጎራ መቀላቀል የምግብ ፍላጎትን በብዙ እጥፍ ስለሚያሳድገው እና በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ የግብርና ምርት እየተዛባ መሆን፤አረንጓዴ አሻራንና የግብርና ምርታማነትን መሳ ለመሳ ለምታካሂደው ሀገራችን ጥሩ አጋጣሚ ነው።በተለይ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት መጨመር ብንችል በኢኮኖሚያችን ላይ መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት እምቅ አቅም አለው።ሰፊ መሬትና ከአመት እስከ አመት የሚገማሸሩ ወንዞች፤ለግብርና ምቹ የአየር ንብረትና ወጣት አምራች ኃይል ላላት ሀገር ግብርናን መሠረት አድርጋ አብዮት ማካሄዷ ይበል የሚያሰኝ ነው።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሦስት ሚሊዮን 385 ሺህ 137 የግብርና ማሽነሪዎች ከቀረጥና ከታክስ ነጻ ወደ ሀገር እንዲገቡ መደረጉን፤ማሽነሪዎችን ከማስገባት ጎን ለጎን የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም የማጠናከር ሥራ መከናወኑን ወዲህ ሳነብ፤በሌላ በኩል በ2016 የስንዴ ምርትን ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ባለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስከ ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከ99 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን፤በሁሉም ክልሎች በ2016 በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ሳጤን፤በሌላ ገጽ ለአረንጓዴ አሻራ የተሰጠውን ትኩረት እንዲህ ስመለከተ ሀገር አረንጓዴ አብዮት ላይ መሆኗን አረጋገጥሁ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤አረንጓዴ አሻራ ለኢትዮያውያን እንደ ባህል እስኪቆጠር ተግተን በመሥራት አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን እውን አናደርጋለን ብሎናል።ለእኔ “አረንጓዴ አሻራ” ባህል ከማድረግም ሆነ ሀገርን አረንጓዴ ከማልበስ የተሻገረ ነው።ሀገርን ከድህነትና ኋላቀርነት በአንድነት ይዞ የሚነሳ፣ከተረጅነትና ከተመጽዋችነት በማላቀቅ ነጻነቷንና ሉዓላዊነቷን ሙሉኡ የሚያደርግ፤ወዘተረፈ ስለሆነ ችግኝ ተከላን ባህል ከማድረግም ሆነ ሀገርን አረንጓዴ ከማልበስ በከባዱ የተሻገረ ነው።

ባለፉት ዓመታት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ32 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የተተከሉት ችግኞችም በዘርፉ ሙያተኞች በተደረጉት ክትትል 90 በመቶ ለመፅደቅ ችለዋል፡፡የተፈጥሮ ሃብትና የሕይወታዊ ሃብት ጥበቃ ሥራ ሲጠናከርና ተከታታይነት ባለው መንገድ ሲሰራ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ነጻ የሆነና መልካምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ አካባቢያዊ የአየር ንብረት እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ዕድል ይሰጣል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመላ ሃገሪቱ በተተከሉ ችግኞች ቀደም ሲል ተራቁተው የነበሩና የአፈር መሸርሸር አጋጥሟቸው የነበሩ አከባቢዎች በአሁኑ ወቅት ወደ ቀድሞ ገጽታቸው እየተመለሱና መሬቱም እያገገመ መሆኑን የግብርና ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው፡፡የአረንጓዴ አሻራ ሥራችን በተለያዩ ዘርፎች ውጤቶችን እያሳየን ነው፡፡

ተደጋጋሚ ድርቅ ሲያጠቃቸው የነበሩ አካባቢዎች ዝናብ ማግኘት ጀምረዋል፣ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ተችሏል፣ የደረቁ ምንጮችና ሀይቆች እንደገና ቀድሞ ወደ ነበሩበት መመለስ ችለዋል፣ ለበጋና የመኽር እርሻ ተስማሚ የሆነ ዝናብ ማግኘት ተችሏል፡፡ከሥራ እድል ፈጠራነት አንጻር ለእንስሳት መኖነት፤ ለንብ ማነብ ፤ ለካርቦን ሽያጭና ለጎረቤት ሀገራት መልካም ጉርብትና እና የዲፕሎማሲ ግንኝነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በዘንድሮ 2016/17 በ132 ሺህ 144 ችግኝ ጣቢያዎች ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩ ችግኝ ተዘጋጅቶ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የቅድመ-ተከላ ዝግጅቶች በሁሉም አካባቢዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ 25 በመቶ የሚሆነው በአባይ ተፋሰሶች የሚተከል ይሆናል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅትና ተከላ ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የስራ እድል እየፈጠረ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በ6 ሺህ 200 ተፋሰሶች የስነ-አካላዊ ስራ በመስራት በስነ-ህይወታዊ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ገቢ የሚየስገኙ አትክልትና ፍራፍሬ፤ ጥምር ደን፤ ለከተሜነት ውበት የሚዉሉ እና ለደን የሚውሉ ናቸዉ፡፡ ለሁለተኛው አረንጓዴ አሻራ ሁለተኛ ዓመት የአረንጓድ አሻራ ስኬት የሁላችንም ተሳትፎና ዝግጁነት ከወዲሁ ይጠበቃል ይለናል የአገልግሎቱ መልዕክት፡፡ወደ ነገረ አብዮት ስመለስ፤

ዓለማችን ከፓለቲካዊ አብዮቶች (መነሻ ቃል፡ አበየ- ‘እምቢ አለ’) በተጨማሪ ሌሎች ዘመን ቀያሪ፤ ሂደት ለዋጭ አብዮቶችን አስተናግዳለች – የግብርና አብዮት፤ የኢንዱስትሪ አብዮት ፤ የሳይንስ አብዮት፤ የዲጂታል አብዮት። እነዚህ አብዮቶች ‘አብዮት’ ያሰኛቸው ከዛ በፊት ግብርና ወይም ኢንዱስትሪ ወይም ሳይንስ ወይም ዲጂታላዊ እንቅስቃሴ ወይም ስራ ስላልነበረ አይደለም። በመጠናቸውና በአይነታቸው ከተለመደውና ከነበረው አሰራርና አካሄድ ለየት ባለ መልኩ ሁኔታ ቀያሪ በሆነ መገለጫ ግብርናው፤ ኢንዱስትሪው፤ ሳይንሱና የመረጃ ቴክኖሎጂው ስለተስፋፋና አገሮች ከተለመደው መንገድ ‘በእምቢታ’ ወጥተው ወደ አዲሱ መንገድ ስለገቡ ነው ከአብዮት ጋር ተያይዞ የሚነገርላቸው። ይሉናል ጌታቸው አሰፋ በአዲስ ጉዳይ ላይ ባስነበቡን ቆየት ባለ መጣጥፋቸው።

ከአንድ ሄክታር ይገኝ የነበረውን የምርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ ከማሳደግ ጋር በተያያዘ የተገኘውን የለውጥ እምርታ የግብርና አብዮት እንለዋለን። የግብርና አብዮት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተለያየ ወቅት ተካሄዷል። ለምሳሌ በእንግሊዝ ከአስራ አምስተኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ለአራት ክፍለዘመናት ከኢንዱስትሪ አብዮትና ከሳይንስ አብዮት ጋር መነሻና መድረሻ እየሆነ ተከስቷል። በአረቡ ዓለምም ከዚህ በጣም ቀድም ብሎ ከስምንተኛው ክፍለዘመን እስከ አስራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የዘለቀ አብዮት ነበር።

በንጽጽር በቅርቡ በኤዥያና (በተለይ በህንድ) በላቲን አሜሪካ (በዋናነት በሜክሲኮ) የተካሄዱትን የግብርና አብዮቶች ነው አረንጓዴ አብዮት ተብለው የሚጠሩት።በ1960ዎቹ 1970ዎቹ በህንድና ሜክሲኮ የተከሰተውን አረንጓዴ አብዮት እውን እንዲሆን የደገፉ የሮክፌለር ፋውንዴሽን ፤ የፎርድ ፋውንዴሽን እንዲሁም የዓለም ባንክ ነበሩ። እነዚህ ድርጅቶች ይህን አረንጓዴ አብዮት በ1980ዎቹ በአፍሪካም እንዲከሰት ሊያደርጉ ሲሞክሩ የዓለም አቀፍ አካባቢ ተቆርቋሪዎች ተቃውሞ በማሰማታቸው ይህን ድጋፍ ለመስጠት አልፈቀዱም። የተቃውሞው ምንጭ በነዚህ አብዮቶች ተጠቃሚ ለምርት መጨመሩ ግብአት የሚሆኑትን ነገሮች የሚያቀርቡት የምዕራብ አገሮች ትልልቅ ኩባንያዎች ናቸው እንጂ ገበሬው አይደለም የሚል ነው። ጉዳቱ በአካባቢም በዘላቂ ምርታማነትም በኩል ከፍተኛ ነው የሚል ነው።

ይህ ከሆነ ሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ካለፈ በኋላ እነሆ አፍሪካ በተቃውሞው ምክንያት የዘገየው አረንጓዴ አብዮት መፈንጃ ልት ሆን እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ሲጀመር ‘አረንጓዴ አብዮት’ የሚለው ስም አሳሳች ነው። ‘ለምን?’ ቢባል ለምሳሌ ይህ ስም ‘አረንጓዴ ኢኮኖሚ’ ከሚለው ጋር ዝምድና የሌለውና አረንጓዴነቱ ከአካባቢ ተጽእኖ አለመኖር ወይም አነስተኛ መሆን ጋር የማይገናኝ ነው። የስም አወጣጡም አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን ንግግር ሲያደርጉ “በነህንድና ሜክሲኮ የተካሄደው አብዮት በሶቭዮት ህብረት የነበረውን ቀይ አብዮት ያይደለ፤ የአረቦች አይነት ነጭ አብዮት ያይደለ አብዮት ነው። ይህን አብዮት አረንጓዴ አብዮት ብየዋለሁ” ያሉትን መነሻ በማድረግ ነው።

ከዛን ጊዜ ጀምሮ የግብርና ምርት መጠን ላይ ከፍተኛ እምርታ ማምጣት ‘አረንጓዴ አብዮት’ ተብሎ ከመጠራቱ አኳያ ነው አፍሪካ ማካሄድ አለባት የሚባለው የራሷ የግብርና አብዮትም ‘የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት’ የሚል ስያሜ ያገኘው። ይህ የአፍሪካ አብዮት እውን እንዲሆንም የአፍሪካ መንግሥታት ጥረት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ እና እንዲሁም የታወቁ ግለሰቦችና ባለጸጎች እንቅስቃሴ እየታየ ነው። ከአዲሱ የአፍሪካ አረንጓዴ የግብርና አብዮት ጀርባ የተከበሩ ሰዎች አሉ- የቀድሞው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን እና ቢል ጌትስ የመሳሰሉት።ወደ ሀገራችን ስንመለስ፤

የአገራችን ደጋማው ክፍል ለዘመናት በመታረሱ ምክንያት በሄክታር የሚገኘው ምርት በጣም አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ተጨማሪ አዲስ መሬት ወደ ግብርናው እስካልተቀላቀለ ድረስ በቂ ምርት ማግኘት ከባድ ከሆነ ቆይቷል። በየጊዜው ደግሞ ሊጨመር የሚችል አዲስ መሬት ሊኖር አይችልም። በመሆኑም ካለው መሬት የምናገኘውን ምርት መጨመር የምንችልበት መንገድ መፈለግ የግድ ነው። መንግሥት በግብርና ኤክስቴንሽን ባደረገው ጥረት አበረታች ውጤትም ተገኝቷል። ለምርት መጨመር ምክንያት የሆነው ማዳበሪያን ከውጪ በውጪ ምንዛሪ በማስገባት በመሆኑ ውሎ አድሮ አቅሙ ከተገኘ ሁኔታዎች ከተመቻቹ ማዳበሪያም ሆነ ሌላው የግብርና ግብአት በአገር ውስጥ ማምረት የምንችልበትን እድል መጠቀም ወሳኝ ነበር።

‘ምን ያህል መሬት? በምን ያህል መጠን? ለምን ያህል ጊዜ ነው በግብአቶች ጣራ ስር ማዋል ያለብን? ይህን ስናደርግ የሚፈጠሩ የጎንዮሽ ተጽእኖዎች እንዴት ነው የምንመክታቸው? የግብአቶች ምርጥ የአጠቃቀም ባህልስ የምንፈጥረው እንዴት ነው?’ የሚሉትን ጥያቄዎች በሁለንተናዊ ግምገማ ስልት የየዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መመለስ አለባቸው።

በዚህ በኩል የህንድ ልምድ በበጎም በመጥፎም ጥሩ መነሻ ሊሆነን ይችላል። ‘ህንድ ራሷን መመገብ አትችልም። ከአሁን በኋላ ካላት የህዝብ ብዛት አንጻር መጪው ጊዜ ለህንድ መጥፎ ነው።’ ተብሎ በተተነበየ በስድስት ዓመት ውስጥ እድሜ በዋናነት ሩዝ ላይ መሰረት ላደረገ አረንጓዴው አብዮት ራሷን ከመመገብ አልፋም በስፋት ወደ ውጪ ለመላክ በቅታለች። ይህ በጎው ነው። በመጥፎ ጎኑ ደግሞ መጠነ ሰፊና ያልተመረጠ የማዳበሪያና የጸረ ተባይ አጠቃቀም ጋር የሚያያዝ የአረንጓዴ አብዮት ሰርቶ ማሳያ የሆነችው የህንዷ ፑንጃብ ግዛት የታየው እየጨመረ የመጣ የበሽታና (ለምሳሌ ከጸረ ተባይ ጋር የተያያዘ ካንሰር) የአካባቢ ተጽእኖ (የክርሰ ምድር ውኃ ብክለት እና የመሳሰሉት) በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው።

ሌላው ከምርጥ ዘሩ አይነት ጋር የሚያያዝ የጎንዮሽ ጠንቅ አለ። በሩዝም ሆነ በስንዴ ላይ የተደረገው የምርት ጭማሪ እምርታ የተከሰተው በግንዱ ላይ ይውል የነበረው መዋዕለ ህይወት ፍሰት ተቀንሶ ፍሬ መጨመር ላይ እንዲውል በማድረግ ድንክዬ ስንዴና ድንክዬ ሩዝ ግን ከመደበኛው ዝርያ የበለጠ የሚያፈሩ እንዲሁን በማድረግ ነው። ይሁንና ይህ ዘዴ ከምርት ሂደት በኋላ ከፍሬው በተጨማሪ ለሌላም አገልግሎት (ለምሳሌ ለከብት መኖ) የሚውለው አጠቃላይ የቃርሚያ መጠን የሚቀንስ ነው።

ይህ ደግሞ እኛን በመሳሰሉ አገሮች ከጠቅላላ የቃርሚያ መጠኑ ያገኙት የነበረው ጥቅም ያሳንስብናል። በዛ ላይ ደግሞ እነዚህ ምርጥ ዘሮች ከፍተኛ የማዳበሪያ፤ የውኃ እና የጸረ ተባይ ግብአት የሚጠይቁ ናቸው። እንዲያውም በቂ ግብአት ካላገኙ ከመደበኛ ዘሮች ያነሰ ምርት ነው የሚሰጡት። ይህ ጉዳት ነው። እንደዛም ሆኖ ግን ‘የተመረጠውና አዛላቂ የሆነው መንገድ የትኛው ነው?’ ብለን የአጭሩንና የረጅሙን ዘመን ተግዳሮቶችንና ጸጋዎችን ለማጣጣም ከአሁኑ ማሰብና ማሰላሰል ይጠበቅብናል። ይህ ሲሆን በአገራችን አሁን ያሉት በጎ ጅምሮች ባለ-ብዙ ዘርፍ አብዮት የማምጣት እድላቸውን ሰፊ ማድረግ እንችላለን ይሉናል ጸሐፊው።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You