መዲናዋን ከትምባሆ ጭስ ለመታደግ

በትምባሆ ውስጥ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ያሉ ሲሆን፤ ዋናውና የማነቃቃት ኃይል ያለው ኒኮቲን (Nicotine) ይባላል። ከዚህ በተጨማሪ ታር (Tar) የሚባል ዝቃጭ ነገር የሚገኝበት ሲሆን፤ በዚህም ውስጥ እስከ 4000 የሚደርሱ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከ250 የማያንሱት ለሰው ልጅ ጎጂዎች ሲሆኑ፤ 50 የሚሆኑት ለካንሰር በሽታ ያጋልጣሉ። በተለይ አርሰኒክ (Arsenic) እና ቤንዞፕሪን (Benzoprine) የሚባሉት ንጥረ ነገሮች ዋና ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገሮች ናቸው።

በዚህም ትምባሆ የሚያስከትለው ውስብስብ ችግር ዓለም አቀፍ አጀንዳ ከሆነ ረጅም ዓመታት አስቆጥሯል። በዓለማችን በየዓመቱ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በትምባሆ ሕይወታቸውን ያጣሉ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑት ከአጫሽ ሰዎች በሚመነጭ ጭስ ሕይወታቸውን የሚያጡ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል። በኢትዮጵያም በየዓመቱ ከ16,800 በላይ ሰዎች በትምባሆ ጭስ ምክንያት ለህልፈት እንደሚዳረጉ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል።

በኢትዮጵያ በ2022 በተደረገው ሀገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት 12 ነጥብ 3 በመቶ ሰዎች ብቻ ከትምባሆ ጭስ ነፃ በሆነ አካባቢ ይኖራሉ። በአንጻሩ 87 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በተለያየ መንገድ ለትምባሆ ጭስ ተጋላጭ መሆናቸውን ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ ያሳያል። ይህንን የዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ “አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ ነፃ የማድረግ ኢንሼቲቭ” በይፋ ሚያዚያ 2013 ዓ.ም ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛል።

ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ሕዝብ በሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች ማለትም መዝናኛ ቦታዎች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ … ወዘተ ሲጋራ የማይጨስባቸው እንዲሆኑ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለምግብና መጠጥ ተቋማት፣ ለትምባሆ ምርት አከፋፋዮች፣ ለሸቀጣ ሸቀጥ ባለቤቶች እና ለሱቅ በደረቴ አዟሪዎች እንዲሁም ለተለያዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች፣ ለተማሪዎች እና የትምህርት ማህበረሰብ ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል። በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በቀጥታ ሥርጭት እና በተለያየ መንገድ የሚገለጽ የሚዲያ ሽፋን ተሠርቷል። ታትመው የተሰራጩ የህትመት ውጤቶችም አሉ።

ከቁጥጥርና ክትትል ሥራ አንጻር ደግሞ በልዩ ሁኔታ ከሲቪክ ማህበራት ጋር በመተባበር በምግብና መጠጥ ተቋማት የቀንና የማታ የትምባሆ ቁጥጥር ሥራ ተሠርቷል። የድንገተኛ ምልከታም ተደርጓል። በዚህ ክንውን በተገኙ ግኝቶች መጠን የቃልና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም ቤቶቹን እስከማሸግና ከፖሊስ ጋር በመተባበር ክስ እስከ መመስረት ተከናውኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዚህ ተግባር የመጡ ተስፋ ሰጪ ለውጦች አሉ። በአዋጅ 1112/2011 የተቀመጡ ክልከላዎችን የንግድ ማህበረሰቡ ግንዛቤ እያደገ መምጣቱ፣ የኅብረተሰቡ የትምባሆ ቁጥጥር ባለቤትነት መጨመሩ፣ ጥቆማዎችና አስተያየቶች በባለቤትነት ስሜት የሚሰጡ ዜጎች መበራከታቸው፣ ከትምባሆ ጭስ ነፃ የሆኑ ተቋማት መበራከታቸው (ከነበረበት 42 በመቶ ወደ 75 በመቶ አካባቢ መድረሱ) እንዲሁም ሞዴል ተቋማት ቁጥራቸው መጨመሩን (ከ240 በላይ ባርና ሬስቶራንት እንዲሁም ከ2000 በላይ ሱቆች) ያስረዳል።

ይሁን እንጂ የግንዛቤ ማስረጽም ሆነ የቁጥጥርና የእርምጃ ሥራው ልክ ኢንሼቲቩ ሲጀመር እንደነበረው ተጠናክሮ ባለመቀጠሉ፤ አሁንም ክልከላ በሚደረግባቸው ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ሲጋራ እንዳይጨስ ማድረግ አልተቻለም። ባለሱቆችም በፍሬ አንሸጥም ብለው ደንበኛ አይመልሱም፤ አጫሾችም በፍሬ ለመግዛት እና ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ለማጨስ ሲሳቀቁ አይስተዋሉም። ማህበረሰቡም አጫሾች በተከለከለ ቦታ ሲያጨሱ ተቆጣጣሪ አካላትን ሳይጠብቅ ለምን ብሎ ከማስቆም አንጻር አሁንም ሰፊ ክፍተት ይስተዋላል።

ስለዚህ አሁን አሁን አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ የመታደግ እንቅስቃሴ ሥራው እንደአጀማመሩ አለመሆኑን፤ ኢንሼቲቩን በበላይነት የሚያስተባብረው ከንቲባ ጽህፈት ቤቱ እራሱ የማያስተባብለው ሀቅ ነው። ስለሆነም በቀጣይ ምን ቢሠራ መልካም ነው የሚለው ላይ የግሌን አስተያየት እንደሚከተለው እሰነዝራለሁ።

ይኸውም፣ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ‹‹ሕፃናትን ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት እንከላከል›› በሚል መሪ ቃል ለሚከበረው የፀረ ትምባሆ ቀን የተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። እነዚህ የንቅናቄ ሥራዎች ዕለቱ ከተከበረ በኋላም በዚያው እንዲቀጥሉ ማድረግ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ የግንዛቤ ማስረጽ፣ የቁጥጥር እና የእርምጃ አወሳሰዱን የሚያግዙ ተግባራትን በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል።

ይህን ተግባር ያዝ ለቀቅ በማድረግ ሳይሆን አጫሾች የሚያጨሱበት ቦታ አጥተው እስኪቸገሩ ድረስ፤ አጫሾች በፍሬ የሚሸጥላቸው አጥተው ማጨሳቸውን እንዲያዘገዩ እስከማድረግ ድረስ፤ ከተቻለ ደግሞ ማጨሳቸውን እስኪያቆሙ ድረስ ሥራዎችን መሥራት ይገባል እላለሁ።

ለዚህ ተግባር ደግሞ የከተማው ሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ስለሆነ በተለያዩ አደረጃጀቶችና አማራጮች ኅብረተሰቡም አጋዥ እንዲሆን የግንዛቤ ማስረጽ ሥራ መሥራት ይገባል። “ማጨስ ክልክል ነው” የሚለው ማስታወቂያም በተገቢ ቦታዎች ሁሉ ቢለጠፉ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም።

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 150/2015 እንዲያስፈጽማቸው ከተሰጡት ለደንብ መተላለፎች የወጡ የቅጣት ሰንጠረዦች ላይ አዋኪ ድርጊትና መሰል ተግባራትን መፈጸም በሚለው ስር ጫት መቃምና ሺሻ ማጨስ ተካቷል። ይሁን እንጂ ስለ ሲጋራ ማጨስ የተባለ ነገር ስለሌለ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች እርምጃ ለመውሰድ ሲቸገሩ ይስተዋላል። ስለሆነም በቀጣይ እንደ ጫቱና ሺሻው ሁሉ በአዋጁ ሲጋራ ማጨስ በደንብ መተላለፍ የሚካተትበት ሁኔታ ተፈጥሮ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ቁጥጥርና እርምጃ የሚወስዱበት አግባብ ሊፈጠር ይገባል።

ሌላው ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ሲጋራ ማጨስን በተመለከተ የሚያሳዩትን የተለያየ ሃሳብ አጥብበው አንድ ማድረግ ይገባቸዋል። ይህ የተለያየ ሃሳብ የሚከተለውን ይመስላል፤ ቢሮ ሆቴሎችና መሰል ተቋማት ለአጫሾች ለብቻቸው የተከለለ ቦታ እንዲዘጋጁላቸው ተደርጎ ያጭሱ የሚል አቋም አለው። ባለስልጣኑ ደግሞ የዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ በሆቴሎችና መሰል የመዝናኛ ቦታዎች በግቢው ውስጥም ሆነ ከግቢው ውጭ ሰው ባለበት አስር ሜትር ራዲያስ ውስጥ ማጨስ አይፈቀድም ይላል። ይሄን ልዩነት በአጭር ጊዜ ተቋማቱ ማጥበብና የደረሱበትን ውሳኔ ለሆቴሎችና መሰል ተቋማት ማሳወቅ ይገባቸዋል።

እንደእኔ አስተያየት የባለስልጣኑን ሃሳብ እደግፋለሁ። ምክንያቱም አጫሾች የሚያጨሱበት ቦታ ሲያጡ የሚያጨሱት መጠን ይቀንሳል። በዚህም የዜጎች ተጋላጭነት ቁጥር ይቀንሳል። መዲናዋን ከትምባሆ ጭስ የፀዳች ለማድረግ አንድ ዜዴ ነው። ስለሆነም እነዚህን የመሳሰሉ ተግባራት ቀጣይነት ባለው መንገድ በትብብር የሚተገበር ከሆነ መዲናዋን ከትምባሆ ጭስ ነፃ ማድረግ ይቻላል ባይ ነኝ።

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You