የፈጠራ ሥራ፣ ጥናትና ምርምር ከመደርደሪያ ወርዶ እንዲተገበር

የሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ተማሪዎችን ከማስተማር ጎን ለጎን ጥናትና ምርምር በማድረግ እና ለኅብረተሰቡ ሥራ አጋዥ የሆኑ አዳዲስ ፈጠራዎች ጊዜ እና ጉልበትን የሚቆጥቡ ሥራዎች ይሠራሉ።

ነገር ግን የሚወጡ ጥናትና ምርምሮች ተማሪዎቹ ለመመረቂያ ጽሑፍ ከማሟላት በዘለለ ኅብረተሰቡን ሊያግዙ በሚችሉ መልኩ ሲተገበሩ አይታይም። በብዛት የሚወጡ ጥናትና ምርምሮች በመደርደሪያ ተቆልለው የተረሱ ናቸው። ጥናትና ምርምሮቹ ካልተተገበሩ ሰዎች ሊያነቡዋቸው የሚችሉበት መንገድ ካልተመቻቸ ‹‹የጋን ውስጥ መብራት›› ሆነው ይቀራሉ ማለት ነው።

እንደ ምሳሌ በአንድ ወቅት በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በተካሔደ ዐውደ ጥናት እንቦጭ እንደ ከሰል ሊያገለግል እንደሚችል እና ጣና ሐይቅ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች እንደከሰል ሊጠቀሙበት እንደሚችል በምርምር ጠቁመው ነበር። ነገር ግን ይህንን ምርምር በመተግበር ስጋት የሆነው እንቦጭ ለማስወገድ የቻለ ድርጅት የለም። ሰውየው በጋዜጠኞች ሲጠየቁም፤ የእኛ ድርሻ ጥናትና ምርምሩን ማቅረብ ነው። አቅም ያላቸው ደግሞ በገንዘብ ይሠሩታል ብለው ነበር።

እንደዚህ ዓይነት ሕዝብንና ሀገርን የሚጠቅም የምርምር ሥራ ሲሠራ ‹‹ፕሮፓዛሉ››ን ይዞ ባንክ ብድር ሰጥቶ ሊተገበር ቢችል ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል በፈጠረ ነበር። ችግሩ የጥናት ፕሮፖዛል ተመርኮዙ አዋጭነትን አጥንቶ የሚያበድር ባንክ የለንም። የምዕራባውያን ባንኮች ግን የዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ተመራቂዎችን እና ጥናት አቅራቢ ምሁራንን ጽሑፍ ገምግመው አዋጭነቱንና ለሀገር የሚበጅ መሆኑን ተረድተው ብድር እንደሚሰጡ ሰነዶች ያሳያሉ። የፈጠራ ሥራዎች በግለሰብ ሲሠሩ ባንኮች አዋጪነታቸውን ገምግመው ያበድራሉ።

‹‹ፈረስና ፈረሰኞች›› በሚል በአዲስ ዘመን የወጣ ዘገባ፤ ኢትዮጵያ ፈረስ በማርባት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗዋን ይጠቅስና በዓለም ለማዳ ያልሆኑ ፈረሶች (feral horses) በአሜሪካ አትላንቲክ ጠረፍ፣ በአውስትራሊያ፣ በፖርቱጋልና ስኮትላንድ፣በአፍሪካ በናሚቢያ ብቻ ይገኛሉ ቢባልም በኢትዮጵያም በምሥራቅ ሐረርጌ 3000 ሜትር ከፍታ ባለው በቁንዱዶ ተራራ የዱር ፈረሶች መገኘታቸውን፤ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ከፈና ኢፋ በጥናታቸው ማውጣታቸውን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዘግቦ ነበር።

ከላይ የጠቀስናቸው የጥናት ጽሑፎች ታትመው ወይም በመገናኛ ብዙኃን ካልተዘገቡ ጥናትና ምርምሩ የጋን ውስጥ መብራት ይሆናል። ማንም ኢትዮጵያዊ የዱር ፈረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይ? ቢባል በሙሉ ልቡ የለም ነው የሚለው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በተለያዩ ወቅቶች የጥናት ምርምር ሥራዎች እያሳተመ ገበያ ይሠራጭ ነበር። ጥናትን ምርምሩ ለተማሪዎችና ለመምህራን ብሎም ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ መሆናቸው እሙን ነው።

እርግጥ ነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ አልፎ አልፎ ሲያሳትማቸው የነበሩ የምርምር ጽሑፎች ነበሩ። አሁንም ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ምሁራን የተጻፉ ጥናታዊ ጽሑፎች የማሳተም ልምዱ ቢቀንስም፤ የሚታተሙ መጽሐፎች አሉ። ሌሎች የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎችም ይህን ልምድ በማየት ጥናታዊ ጽሑፎችን ለማሳተም መጣር አለባቸው። ጥናታዊ ጽሑፎቹ ሲወጡ ከፍተኛ አበርክቶ ይኖራቸዋል።

ከላይ እንደ መግቢያ የጠቀስናቸው ሆኑ ሌሎች የጥናትና ምርምር ሥራዎች፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች ለአካባቢያቸው ማሕበረሰብ ብሎም ለሀገሪቱ የምርምር አበርክቶ ሲኖራቸው አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው የሚያሳዩ ናቸው።

መንግሥት ይህንኑ ከግምት በመክተት፤ የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፪፻፺፰/፪ሺ፲፭ አውጥቷል። ሥራው የበለጠ ከኅብረተሰቡና ከኢንዱስትሪዎች ከባለሀብቶች ጋር ትስስር እንዲኖረውና እንዲተገበርም የሚረዳና በትምህርት ሚኒስቴርና በመንግሥትም የተሰጠውንም ትኩረት የሚያሳይ ነው።

አዋጁ በኢንዱስትሪዎች፣ በከፍተኛ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ፣ በምርምር ተቋማት እና በሌሎች በመንግሥትና በግል ተቋማት መካከል የሚደረግ የሙያ፣ የእውቀት፣ የቴክኖሎጂ፣ የአመራረት ዘይቤዎችን፣ ምርት ናሙናዎችን የመለዋወጥ ሂደት ሆኖ በውጤቱም ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂካዊ ዕድገቶች ለተጠቃሚ የሚደርሱበትና ተጠቃሚውም ቴክኖሎጂውን ወደ አዲስ ምርት፣ ሂደት፣ ጥቅም፣ ቁሳቁስ ወይም አገልግሎት የሚቀይርበት ‹‹የቴክኖሎጂ ሽግግር›› ሂደት መሆኑንም ይኸው አዋጅ ያስረዳል።

ሰሞኑን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በወጣ ዘገባ የጥናትና የምርምር ሥራዎች ወደ ተግባር የሚቀየሩበት አቅጣጫ መቀመጡን ያስረዳል። የትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሠሩ አብዛኛው የምርምርና የጥናት ሥራዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የተለያዩ የትኩረት አቅጣጫዎች ተለይተው እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል።

በዩኒቨርሲቲዎች በርካታ የምርምርና የጥናት ሥራዎች ቢሠሩም አብዛኞቹ ተግባር ላይ እንደማይውሉ ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፤ ዩኒቨርሲቲዎቹ ልምድ ካላቸው የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እንዲሠሩ እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የሚታተሙ ጥናቶች ለፖሊሲ ግብዓት የሚውሉና ለውሳኔ ሰጪዎች የሚያገለግሉ ከማድረግ አኳያ ጥሩ ጅምር ቢኖርም ከሚፈለገው አንጻር ዝቅተኛ የሚኒስቴሩ መግለጫ ያሳያል። ይህንንም ውስንነት ለመቅረፍ የምርምር ውጤቶች ወደ ማበልፀጊያ ማዕከላት ገብተው ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዲቀየሩ እየተደረገ ይገኛል።

ከላይ እንደተጠቀሰው፤ የፈጠራ ሥራዎች ጥናት ምርምሮች ከመመረቂያ ባለፈ ሀገርና ሕዝብ ሊጠቀምበት የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል። በማንኛውም ደረጃ ያሉ የብድርና ቁጠባ ተቋማትም ሆኑ ባንኮች ቢተገበሩ አዋጪ ሊሆኑ ለሚችሉ ጥናትና ምርምር ለፈጠራ ሥራዎች ብድር ሊሰጡ የሚችሉበትን አሰራር ቢዘረጉ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ ነው።

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You