የሰፌዱ ጦስ

የተወለዱባት ቀዬ እጅግ ነፋሻማ በተፈጥሮ የተዋበች መንደር ነበረች። በተራሮች የተከበበችው መንደር ብዙም ሰፊ የሚባል የእርሻ መሬት ባይኖርም ባለቻቸው መሬት ጥሩ ምርትን የሚያገኙ ገበሬ ቤተሰቦች መካከል ነበር ያደጉት። በቀየዋ በየቦታው የፈለቁት ምንጮች የአካባቢዋን ልምላሜ ያደመቁ ነበሩ። ቤቶቹ የተጠጋጉና የቀረው መሬት ደግሞ የእርሻ በመሆኑ የተነሳ ከብቶችን ለማስጋጥ እንኳን ተራራውን ወጥተው ሌላ መንደር መሄድ ግድ ይላቸው ነበር።

ውሃ እንደ ልብ የሆነባት ይህች መንደር በየጓሮው የተተከሉት የጓሮ አትክልቶች ሁሌም አረንጓዴ ሆና እንድትኖር አድርገዋታል። ዛሬ በዶሴ አምዳችን የምንቃኛቸው ወጣቶች ከዚህች ውብ መንደር የወጡ የገበሬ ልጆች ናቸው።

ቤተሰቦቻቸው በአናት በአናቱ ልጆች በመውለዳቸው ልጆቻቸውን ባለቻቸው መሬት ለማስተዳደር ተሳናቸው። ሕፃን እያሉ በእረኝነቱም እና በመላላክ ጭምር ቢያድጉም ከፍ ሲሉ ግን የቤተሰቦቻቸውን የእርሻ መሬት ከመቀራመት ይልቅ ከተማ ገብቶ መሥራት ምርጫቸው አደረጉ። ወጣቶቹ ከተማ ከገቡ በኋላ ያገኙትን ሥራ ሰርተው በጋራ በማደር ጥሪት ለማጠራቀም ይታትሩ ጀመር።

በየእለቱ ለእድገት የሚጥሩት እነዚህ ወጣቶቸ ያች ውብ መንደራቸው በዓይናቸው ላይ እየተሽከረከረች ናፍቆት ቢቀጣቸውም ጠንከር ብሎ በመሥራት የተሻለ ሰው ለመሆን ይጥሩ ነበር። ስኬት ለማግኘትም አሉ የተባሉ በአቅማቸው ሊሰሯቸው የሚችሉ ሥራዎችን በሙሉ ለመሥራት መሞከር የየእለት ተግባራቸው ነበር።

ሠራተኞቹ ወጣቶች

ወጣቶቹ ከተወለዱባት ቀዬ ከወጡ በኋላ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው በጋራ አንድ ቤት ተከራይተው ይኖሩ ጀመር። አብረው ወጥተው አብረው መግባት ልዩ ምልክታቸው እስኪሆን ደረስ ሳይለያዩ ይውሉ ነበር። የሸክም ሥራ ሲሰሩ እንኳን እየተጋገዙ አብረው ነበር የሚውሉት። ደስታቸውም ሀዘናቸውም በጋራ የሆኑት እነዚህ ልጆች ከቅርርባቸው የተነሳ የአንድ እናት ልጆች እንጂ ከተለያየ ቤተሰብ የተገኙ አይመሰሉም ነበር። የሰሩትን ሰርተው በሚያገኟት ገንዘብ የሚቃመሱትን ገዝተው ወደ ማደሪያቸው በጊዜ ይገቡ ነበር። መተጋገዛቸውን የተመለከተ ሰው በሙሉ ነፋስ መካከላችሁ አይግባ እያለ ይመርቃቸው ነበር።

ከተማውን ሲለምዱት ግን የተሻለ የሥራ አማራጭ መመለከት ፈለጉ። በዚህም አጋጣሚ የተወለዱበት አካባቢ ልጆች የሚሰሩበት ወፍጮ ቤት ሰው እንደሚፈልግ ተነገራቸው። ወፍጮ ቤት ውስጥ እህል አበጥሮ አስፈጭቶ ደንበኞች ጋር የማድረስ ሥራና፤ ከወፍጮ ቤቱ ጎን ለጎን እንጀራ ጋግሮ የማስረከብ ሥራ ነበር በክፍት የሥራ ቦታነት ያገኙት።

በዚህም ወጣቶቹ ከወፍጮው አረፍ ሲሉ እንጀራ ለተረካቢዎች በማድረስ ሥራ ላይ ይሰማራሉ። ይህ ሥራ ምግብና መኝታም ስለሰጣቸው ያገኙትን ገንዘብ ለማጠራቀም ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸው ነበር። ለለውጥ የተነሱት ወጣቶች ገቢያቸውን ከፍ የሚያደርግላቸው ምንም ወጪ የሌለበት ሥራ በማግኘታቸው ደስተኛ ሆነው ነበር።

ማልደው ተነስተው እስከ ምሽት ሲሰሩ የሚወሉት ወጣቶች እጅግ በጣም ታታሪ ስለነበሩ ሶሰቱንም አዲሱ አሰሪያቸው ወዷቸው ነበር። በዚህም የተነሳ ቀደመው በወፍጮ ቤቱ ሲሰሩ የነበሩት ወጣቶች ይቀኑባቸው ጀመር። በዚህም የተነሳ በጣም የሚወደዱት ጓደኛሞች መካከል አንዳንድ ነገር እያነሱ እንዲጣሉ ያደረጓቸው ጀመር።

የጠቡ መነሻ

በትንሹም በትልቁም መኳረፍ ልማዳቸው የሆኑት የቀድሞ ጓደኛሞች የነበረ ፍቅራቸው ቀዝቅዞ ፊት መነሳሳት ጀመሩ። ከሶስቱ ጓደኛሞች መካከል በእድሜ አነስ የሚለው ልጅ በየሰበቡ ስለሚናገሩት ቅያሜው በዝቶ ጥሏቸው ለመሄድ ተነሳ።

ልጁ እንጀራ እንዲያደርስ ተልኮ ሲመለስ እግረ መንገዱ አንድ ወፍጮ ቤት ሥራ መኖሩን ይጠይቃል። ያኔ ሰዎቹ እንጀራ መጋገሪያ ቤት ሥራ መኖሩን ነግረውት ሳይመልስ በዛው ተቀጥሮ ያድራል። ያ ወጣት እንጀራ ሊያደርስበት ይዞት የወጣውን ሰፌድ እንኳን ሳይመለስ በዛ እንደወጣ ይቀራል።

በእለቱ ልጁ ከመጥፋቱ በላይ ሰፌዱን ይዞ መቅረቱ ያንገበገበው አሰሪያቸው ጓደኞቹን ሰፌዱን ካላስመለሳችሁ ከሥራ አባርራቸኋለሁ በማለት ያስፈራረቸዋል። ልጁ ማንም ሰው ሳያየው ሹልክ ብሎ ልብሱን መውሰዱን የጠፋው የደሞዝ ሰሞን በመሆኑ ለክፍያ ሲል ወደ ወፍጮ ቤቱ ባለመመለሱ ሁሉም ተናደዱበት።

ስልክ ሲደውሉለት አላነሳም ማለቱ ያበሳጫቸው ጓደኞቹ ከበፊቱ ፀባቸው በላይ አሁን ሳይናገር መሄዱ እጅግ በጣም አንገበገባቸው። በዚህም ምክንያት የልጁን መገኛ ማፈላለግ ጀመሩ። በእረፍት ቀናቸው እሁድ እለት እየተነሱ ቂም የያዙበትን አብሮ አደግ ጓደኛቸውን ለመፈለግ ታየ የተባለበት ቦታ በሙሉ ረገጡ።

ከብዙ ፍለጋ በኋላ እነሱ ከሚሰሩበት ወፍጮ ቤት በቅርብ ርቀት የሚገኝ እንጀራ መጋገሪያ ውስጥ የሚሰራ ተወዳጅ ሠራተኛ መሆኑን ሰሙ፤ ስለዚህ ከጓደኞቹ ተለይቶ ሌላ ሥራ ከመግባቱም በላይ እነሱን በወሰደው ሰፌድ ምክንያት ከአሰሪያቸው ጋር ፊትና ጀርባ እንዲሆኑ ማደረጉ ሆዳቸውን አሻክሮታል።

መዘዘኛው ሰፌድ

ልጁን እንዳገኙት ይዘው ከመጠየቅ ይልቅ ተዘጋጅተውና ቀን ጠብቀው መመለስ መርጫቸው ያደረጉት ጓደኛሞቹ ቢምረው(አንዱአለም) ዓለሙ ይግዛው፣ አቤው(መኮንን) ያለው ፈለቀ ልጁን የሚጎዱበትን አማራጭ በሙሉ መመልከት ጀመሩ። ከብዙ ሃሳብና አቅድ በኋላ አንድ ቀን በቀጥታ ሄደው ከጓደኛቸው ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ ጀመሩ።

ቀኑ ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር። በግምት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ሲሆን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ቄስ ሰፈር እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ጓደኛቸው ግንቦት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ሰፌድ ወሰደብኝ በሚል ምክንያት አብሮ አደግ ጓደኛሞቹ መሀል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር።

በወቅቱ ጓድኛሞቹ መቀያየማቸወን የሰሙ ሌሎች የትውልድ ቀያቸው ልጆች ይሄን አለመግባባት በእርቅ ለመጨረስ በሂደት ላይ ነበሩ። ቂም የተያያዙት ጓደኛሞች ግን አስታረቂን ወደጎን በማለት ዱላ፣ አካፋ እና ድንጋይ በመያዝ ወደ ልጁ የሥራ ቦታ በመሄድ ቤቱ ላይ ድንጋይ በመወርወር እንዲወጡ ካደረጉ በኋላ ጨካኝነታቸውን እና ነውረኝነታቸውን በሚያሳይ ሁኔታ 1ኛው ተከሳሽ ድንጋይ ወርውሮ ሟች አወቀ መቆየቴን ቅንድቡን ሲመታው 2ኛው ተከሳሽ በአካፋ ማጅራቱን መቶ በመጣል ሕይወቱ እንዲያልፍ ያደረጉ በመሆኑ በፈፀሙት በዋና ወንጀል አድራጊነት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል እንዲያዙና ክስ እንዲቀርብባቸው ሆኗል።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ ወንጀል ፈጻሚዎቹን ድርጊቱን ከፈፀሙበት ቦታ በቁጥጥር ሰር ያዋላችው ሲሆን ወጣቶቹ ጓደኛቸውን በጭካኔና ነውረኝነት በተሞላው መልኩ መግደላቸውን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል። የተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃል፤ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል፤ የፌረንሲክ ምርመራውን አካቶ ማስረጃውን ያጠናቀረው ፖሊስ በፈፀሙት አስነዋሪ ተግባር የተነሳ በዋና ወንጀል አድራጊነት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል እንዲያዙና ክስ እንዲመሰርትባቸው በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዓቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸዋል።

የዓቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዓቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በዚህ መልኩ የክስ ዝርዝር አቅርቧል።

በዓቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ቢምረው(አንዱአለም) ዓለሙ ይግዛው፣ 2ኛ

አቤው(መኮንን) ያለው ፈለቀ የተባሉ ተከሳሾች ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ሲሆን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ቄስ ሰፈር እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ግንቦት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ሰፌድ ወሰደብኝ በሚል በአንድ የዓቃቤ ሕግ ምስክር እና በተከሳሾች መሀል አለመግባባት ተፈጥሮ፣ ይሄን አለመግባባት በእርቅ ለመጨረስ በሂደት ላይ እያለ ተጠርጣሪዎች ዱላ፣ አካፋ እና ድንጋይ በመያዝ ወደ አንደኛው የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሥራ ቦታ በመሄድ ቤቱ ላይ ድንጋይ በመወርወር እንዲወጡ ካደረጉ በኋላ ጨካኝነታቸውን እና ነውረኝነታቸውን በሚያሳይ ሁኔታ 1ኛ ተከሳሽ ድንጋይ ወርውሮ ሟች አወቀ መቆየቴን ቅንድቡን ሲመታው 2ኛ ተከሳሽ በአካፋ ማጅራቱን መቶ በመጣል ሕይወቱ እንዲያልፍ ያደረጉ በመሆኑ በፈፀሙት በዋና ወንጀል አድራጊነት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዓቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል።

ውሳኔ

በክርክሩ ሂደትም 1ኛ ተከሳሽ በማረሚያ ቤት ሆኖ፣ 2ኛ ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ እንዲቀጥል ተወስኖ የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ 1ኛ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዓቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ፣ 2ኛ ተከሳሽም የመከላከያ ምስክር ባለማቅረቡ ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ2ኛ ተከሳሽ ላይ በሌለበት በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You