ተፈላጊነታቸው የጨመረው የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ግብዓት ማዕድናት

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ከተለገሰቻቸው በርካታ ማዕድናት መካከል ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ካኦሊን፣ ዶሎማይት፣ ኳርትዝ፣ ፊልድስባር፣ ዳያቶማይት፣ ቤንቶናይት ያሉት ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት የሚያገለግሉ ማዕድናት ከክምችት አኳያ ሲታዩም እንዲሁ በርካታ ናቸው፡፡

እነዚህ ማዕድናት እያሉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሀገሪቱ ፋብሪካዎች አብዛኛዎቹን ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት ከውጭ ሀገር እያስመጡ ይጠቀሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እነዚህ ማዕድናት ሀገር ውስጥ መመረት ከጀመሩ ወዲህ ግን በርካታ ፋብሪካዎች ፊታቸውን ወደ ሀገር ውስጥ ምርቶች መመለስ ጀምረዋል፡፡ የድንጋይ ከሰልን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በድንጋይ ከሰል ምርት ሀገሪቱ ራሷን መቻል ጀምራለች፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የድንጋይ ከሰልን በብዛት ይጠቀማሉ፤ የካኦሊን ማዕድን፣ በውሃ ፋብሪካዎች ይፈለጋል። ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ባሉበት በዚህ ወቅት የማዕድናቱ ተፈላጊነት እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የኢንዱስትሪ ማዕድን ኮርፖሬሽንም ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድናትን ለረዥም ጊዜያት በማምረት ይታወቃል፡፡ በኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የማዕድን ባለሙያና የሥነ ምድር ተመራማሪ (ጂኦሎጂስት) አቶ ሳዲቅ ከቢር እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ብዙ ዓይነት የኢንዱስትሪ ማዕድናት አሏት። ኮርፖሬሽኑ ከእነዚህ መካከል በካኦሊን፣ ዶሎማይት፣ ኳርትዝ፣ ፊልድስባር፣ ዳያቶማይትና ቤንቶናይት ላይ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ጎጂ ዞን አርዳጅላ ወረዳ ፋብሪካ በመገንባት ካኦሊን የተሰኘውን የኢንዱስትሪ ማዕድን በፋብሪካ ደረጃ በማምረት ገቢ እያስገኘ ነው፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የካኦሊን ማዕድን ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ በዋናነት የሀገሪቱ የውሃ የማጣራት ሥራ የሚከናወነው በዚህ ማዕድን ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በሀገሪቱ ብቸኛ የካኦሊን ማዕድን አምራችና አቅራቢ ሲሆን፣ ማዕድኑ ከተመረተ በኋላ አዋሽ መልካሳ አልሙኒየም ሰልፊት ለተባለ ድርጅት ይቀርባል፡፡ ይህ ድርጅትም በማዕድኑ ላይ እሴት በመጨመር ምርቱን ለመጠጥ ውሃ አምራቾች ያቀርባል፡፡

‹‹ዋናው የካኦሊን ማዕድን አገልግሎት ግን የመጠጥ ውሃ ማጣራት ነው፡፡ የካኦሊን ማዕድንን ማምረት ከቆመ፤ የመጠጥ ውሃም ሥራው እንደቆመ ይቆጠራል፡፡ ለዚህም ነው ኮርፖሬሽኑ ትልቅ ኃላፊነት ወስዶ በካኦሊን ላይ እየሰራ የሚገኘው፡፡ ካኦሊን ማዕድን ውሃን ከማጣራት በተጨማሪም ለወረቀት እና ለሴራሚክ ፋብሪካዎች ግብዓትነት ይውላል፡፡

ቀደም ሲል ኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ዶሎማይት፣ ኳርትዝ፣ ፊልድስባርና፣ ታንታለም እያመረተ ያቀርብ እንደነበር አስታውሰው፤ በተለይ የታንታለምና የዶሎማይት ማዕድንን ቀንጤቻ አካባቢ ፋብሪካ ተቋቁሞ በፋብሪካ ደረጃ ይመረት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ታንታለም የማምረቱ ሥራ ሲቆም ዶሎማይት የማምረት ሥራ አብሮ መቆሙን ይገልፃሉ፡፡ እንደ ዶሎማይት፣ ኳርትዝና ፊልድስባር ዓይነቶቹ ማዕድናት በአነስተኛ ማህበራት ደረጃ ብቻ እንዲመረቱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ማህበራት ተደራጀተው እንዲያመርቱ መደረጉን ያስረዳሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ታንታለም የማምረቱን ሥራ እንደገና ለመጀመር እየተሰራ ነው። ታንታለም ሲመረት ኳርትዝና ፊልድስባር፣ አብሮ በማምረት እሴት በመጨመር ለገበያ ይቀርቡ ነበር። በአሁኑ ወቅትም እነዚህ ማዕድናት ለብረትና መሰል ፋብሪካዎች ግብዓት የሚውሉ ሲሆን፣ ጥሬ እቃዎቹን ከአምራቾች በመግዛት እሴት በመጨመር ለማቅረብ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ በተመሳሳይ ካኦሊን ማዕድን የሚያመርተው ፋብሪካ በማዘመን ፋብሪካው በተሻለ ደረጃ እንዲያመርትና ለተለያየ ግብዓት እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ለእዚህም የማስፋፊያ በጀት ተይዞለት እየተሰራ ነው፡፡

በዝዋይ አካባቢ የሚገኘውን ዳያቶማይት የተሰኘ ማዕድን ለማምረትም የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማን መካሄዱን ጠቅሰው፣ ከኦሮሚያ ክልል ፈቃድ ለመወሰድ ጥያቄ እየቀረበ መሆኑንና ወደ ሥራ ለመሰማራት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ይገልጻሉ።

‹‹የዳያቶማይት ማዕድን ብዙ አገልግሎቶች አሉት። ለቢራ፣ ለስላሳ እና ጁስ ፋብሪካዎች ለማጣሪያነት ይውላል፡፡ ይህ ማዕድን አሁን ከቻይና እና ከተለያዩ የውጭ ሀገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይመጣል›› ሲሉም ጠቅሰው፣ ማዕድኑን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ለመተካት ያለመ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑም የማምረት ፈቃዱን እንዳገኘ ወደ ማምረቱ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የዳያቶማይት ማዕድን ፀረ-ተባይ ኬሚካል ለማምረት እንደሚጠቅም ጠቅሰው፤ ኮርፖሬሽኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት ይህን ማዕድን በማምረት የጸረ ተባይ ኬሚካሎችን ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች ያቀርብ እንደነበር ያስታውሳሉ። ማዕድኑን የማምረቱ ሥራ አሁን ላይ በአነስተኛ አምራችነት ለተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች መሰጠቱን ይገልጻሉ። ኮርፖሬሽኑ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ማዕድኑን በከፍተኛ ደረጃ ለማምረት የሚያስችል ሥራ እየሰራ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡

እንደ አቶ ሳዲቅ ማብራሪያ፤ ኮርፖሬሽኑ የካኦሊን ማዕድን ማምረት ከጀመረ ረዘም ያሉ ጊዜያትን ያስቆጠረና ለፋብሪካዎች እያቀረበ ያለ ነው። ምርቱንም ለአዋሽ መልካሳ የአልሙኒየም ሰልፊት ፋብሪካ ስለሚያቀርብ እሴት ተጨምሮበት ለመጠጥ ውሃ ማጣሪያነት ይውላል፡፡ አሁን ፋብሪካ በዓመት 3ሺ500 እስከ አምስት ሺ ቶን የካኦሊን ማዕድን ያመርታል፡፡ ፋብሪካው ሀገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችል ምርቶች እያመረተ ይገኛል። በዚህ ዘርፍ 130 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡

አሁን ላይ ፋብሪካው የሚያመርተው የኮኦሊን ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ በቂ ቢሆንም፣ ግብዓቱን የወረቀትና ሴራሚክ ፋብሪካዎች ከውጭ ሀገራት የሚያስመጡበት ሁኔታ ይታያል ሲሉ አመልክተዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ የሀገር ውስጡን ምርት የማይጠቀሙበትን ምክንያት ሲያብራሩም ፋብሪካ ከአዲስ አበባ 430 ኪሎ ሜትር ርቀት መገኘቱን በሩቅነት እንደሚጠቅሱ ይገልጻሉ፡፡

በሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ማሟላት የሚችል የካኦሊን ማዕድን ከፍተኛ ክምችት እንዳለም ጠቅሰው፣ ኮርፖሬሽኑ ይህን ታሳቢ በማድረግ ዘመናዊ ፋብሪካ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን አቶ ሳዲቅ ያመለክታሉ። የዳያቶማይት ማዕድንን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ሀገራት ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ከፍተኛ ክምችት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የቢራ፣ የለስላሳ ፋብሪካዎች አሁን እየተጠቀሙ ያሉትን የዳያቶማይት ማዕድን በሀገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ ከውጭ እያስመጡ ነው፡፡ ይሁንና ፋብሪካዎቹ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲሉ ዳያቶማይት የዳያቶማይትን ይዘት ሲጠየቁ ለመናገር ፈቃደኛ አይደሉም ሲሉ ጠቅሰው፣ የሀገር ውስጡን ምርት አያበረታቱም ይላሉ፤ ጥቅሙን ከራሳቸው እንጂ ሀገሪቱ ከምታወጣው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አንጻር እንደማያዩ አመልክተው፣ ከውጭ የሚመጣውን ምርት ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት አይደግፉም ብለዋል፡፡ ወደፊት በዳያቶማይት ማዕድናት ላይ ኮርፖሬሽኑ እየሰራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል ከተቻለ በቂ ምርት ማምረት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የካኦሊን ምርት ከፍተኛውን የኮርፖሬሽኑን ገቢ የያዘ ሲሆን፤ አንድ ቶን የኮኦሊን ምርት ከ13ሺ እስከ 15ሺብር ድረስ ይሸጣል። በዘንድሮው በጀት ዓመት 5ሺ ቶን የካኦሊን ምርት ለማምረት ታቀዶ እስካሁን ከእቅድ በላይ ማምረት ተችሏል፡፡

‹‹የኢንዱስትሪ ማዕድናት ተፈላጊነት በጣም እየጨመረ ነው፡፡ ትላልቅ ፋብሪካዎች በተገነቡ ቁጥር የኢንዱስትሪ ማዕድናት ፍላጎት እየጨመረ ይመጣል›› ያሉት አቶ ሳዲቅ፤ ድሮ የማይጠየቁ (የማይፈለጉ ማዕድናት) ተፈላጊ እየሆኑ መምጣታቸው ይናገራሉ፡፡ ለእዚህም የድንጋይ ከሰል ምርት ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣትን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ የፋብሪካዎች መብዛት የኢንዱስትሪ ማዕድናት ተፈላጊነት እንዲጨምር የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ማዕድናት ምርት እንደሚታወቅ ተናግረው፣ በርካታ ፋብሪካዎች ወደ ኮርፖሬሽኑ በመምጣት የሚያስፈልጋቸውን ማዕድን ታመርታላችሁ ወይ በማለት እስከመጠየቅ ደርሰዋል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

ኮርፖሬሽኑም የፋብሪካዎችን የማዕድን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ከሚያመርታቸው ማዕድናት በተጨማሪ የሚፈለጉ ሌሎች ማዕድናት ፍለጋ ላይ እየተሰማራ መሆኑንም አስታውቀዋል። የኢንዱስትሪዎች የማዕድናት ፍላጎት እየጨመረ በመጣ ቁጥር ኮርፖሬሽኑ የሚያመርታቸውን የማዕድናት ምርት ብዛት ለመጨመር ይሰራል ብለዋል፡፡ በተለያዩ የማዕድናት ልማቶች ላይ ለመስማራት የሚያስችሉ ሥራዎች ከወዲሁ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ማዕድናት ልማቱ ላይ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚታዩም አቶ ሳዲቅ ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ከእነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ ኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ማዕድናት በቀጥታ ማምረት አለመቻሉ ነው፡፡ ቀደም ሲል ማዕድናቱን ከሚያመርቱ ማህበራት ጋር ክፍተቶች ነበሩበት፤ በአሁኑ ወቅት መሻሻሎች እየታዩ ናቸው። ማዕድናቱን በማምረት ሥራ ላይ ከተሰማሩ በአነስተኛ ደረጃ ከተደራጁ ማህበራት ጋር አብሮ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ከማህበራት ጋር አብሮ መሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች በመፍጠር ማህበራቱን በማገዝ፣ ለማህበራቱ ድጎማ በማድረግና በመቶኛ በማጋራት ድጋፍ እያደረገ እያመረተ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ማዕድናቱን በቴክኖሎጂ በመጠቀም ማምረት የሚቻልበት ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት አቶ ሳዲቅ አስታውቀዋል፤ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፋ መምጣት የፍላጎት መጨመሩን ከፍተኛ ደረጃ እንዳደረሰው ጠቅሰው፤ በኢንዱስትሪ ማዕድናት ላይ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ያመለክታሉ፡፡

ከገበያ አንጻርም ሲያብራሩ ኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት አካሄዶ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸው፣ ፋብሪካዎቹ የሚፈልጉት የማዕድን ዓይነት ጥራትና ብዛት ከተለየ በኋላ ማዕድናቱን ወደ ማምረት እንደሚገባ ያብራራሉ፡፡ ፋብሪካዎች የሚጠይቁት የጥራት ዓይነት እንደሚለያይ አመልክተው፣ በጠየቁት የጥራት መጠን ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

አቶ ሳዲቅ እንደገለጹት፤ ማዕድናት በተፈጥሮ እኩል የሆነ ጥራት የላቸውም፤ አንድ ዓይነት ማዕድን ሆኖ አንድ ቦታ ላይ ያለው ማዕድን ጥራት ፤ ሌላ ቦታ ላይ ካለው ማዕድን ጋር በጥራት ሊለያይ ይችላል። ማዕድናቱ በላቦራቶሪ ከተፈተሹ በኋላ ያላቸው ጥራት መጠን ይለያል፤ ማዕድኑ ያለው የጥራት ደረጃ ለየፋብሪካዎቹ እየገለጸ አቅርቦቱ ይፈጸማል፡፡

የማዕድናትን ጥራት ከፍ ለማድረግ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል። ሀገር ውስጥ የሚመረቱት ማዕድናት ጥራት ላይ የሚነሳው ችግር ከእጥበት ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከውጭ የሚመጡት ማዕድናት በቴክኖሎጂ በመጠቀም እንደሚታጠቡ ተናግረዋል፡፡ ማዕድናት እንደተመረተ ለገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታ ጥራት ላይ ችግር እንዲኖር እንደሚያደርግ አመልክተው፣ እሴት ተጨምሮበት፣ በቴክኖሎጂ ታግዞ ከተመረተ ተፈላጊነቱ እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የድንጋይ ከሰል ለአብነት ቢወሰድ ሀገር ውስጥ የሚመረተው የድንጋይ ከሰል ከውጭ ያነሰ ጥራት የለውም፡፡ ከውጭ የሚመጣው ታጥቦ ስለሚመጣ የካሎሪ መጠኑ ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ አሁን ላይ ሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ እየተቋቋመ ነው፤ በዚህም የድንጋይ ከሰል እየታጠበ ለፋብሪካዎች እያቀረበ ይገኛል። እንደዚህ ዓይነት ፋብሪካዎች መኖር የማዕድናት ምርቶችን የጥራት መጠን ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ አቶ ሳዲቅ አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በኢንዱስትሪ ማዕድናት ላይ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ የካኦሊን ፋብሪካን በማዘመን በቴክኖሎጂ የታገዝ ምርት ለማምረት የሚያስችል ሥራ ይሰራል። ድንጋይ ከሰል ማምረት ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡ እንደ ማርበል ያሉ ሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕድናት ለማምረት ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡

በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ በሀገሪቱ ላይ አሉ የተባሉ ማዕድናት ላይ ለመስማራት የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ስለሚጠበቅበት በዚያ ልክ አቅምን የመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በማዕድኑ ዘርፍ መንግሥትም እገዛ እያደረገ ስለሆነ በኢንዱስትሪ እና በሜታሊክ ማዕድናት ዘርፍ ብዙ ሥራዎች ለመሥራት ታቅዶ፤ የሰው ኃይል በማደራጀት የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ ነው፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ግንቦት 23 ዓርብ ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You