ለሰው ልጆች ደህንነት የሰው ሰራሽ አስተውህሎ ልጓም ማበጀት!!

ዓለም በማይገመት የቴክኖሎጂ ለውጥ አብዮት ውስጥ ይገኛል። የሰው ሠራሽ አስተውህሎ፣ የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ እና የበይነ-መረብ ቁሶች አዲስ የቴክኖሎጂ አብዮት እየፈጠሩ ነው። በተለይ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ብዙዎች ስለ ወደፊት እጣ ፈንታቸውና ሰብዓዊነት እንዲያስቡ ሳያደርጋቸው አልቀረም።

የሰው ሠራሽ አስተውህሎ እያደገ እና ጥቅም ላይ እየዋለ ያለበት ፍጥነት ልጓም ስለማበጀት እንድናስብ ያስገድደናል። ቴክኖሎጂው ወደፊት የሰዎችን ሥራ በመቀማት ሥራ አጥ ሊያደርጋቸው “ይችላል” ወይስ “አይችልም” እንዲሁም ደግሞ ሰዎችን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ሰብዓዊነት ላይ አደጋ ሊደቅን “ይችላል” ወይስ “አይችልም” የሚለው ጉዳይ የብዙዎች ስጋት እየሆነ መጥቷል። ፒው የተሰኘ የምርምር ተቋም በአሜሪካ ሀገር ባጠናው ጥናት በሀገሪቱ ከ52 ከመቶ በላይ ሰዎች ቴክኖሎጂው ሰዎችን በመቆጣጠር አደጋ ይደቅናል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ርግጥ ነው ቴክኖሎጂው በአስደንጋጭ ሁኔታ የሰዎችን አዕምሮ ቀድቶና ተምሮ ሰዎችን ሊበልጥ እየተገዳደረ ነው። አንዳንድ ባለሙያዎች በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ የሰዎችን የማሰብ ችሎታ ይበልጣል የሚል ግምት ያስቀምጣሉ። ዛሬ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ የተገጠመለት ሮቦት ቀዶ ጥገና እየሰራ ነው፡፡ መኪናዎች በሰው ሠራሽ አስተውህሎ በታገዘ ቴክኖሎጂ ሹፌር ሳያስፈልግ ሰዎችን ከቦታ ወደ ቦታ ማንቀሳቀስ ጀምረዋል።

የሰው ሠራሽ አስተውህሎ የቋንቋ ሞዴል ጥናታዊ ጽሑፎችን ጥንቅቅ አድርጎ እስከ ማዘጋጀት ደርሷል። በሰው ሠራሽ አስተውህሎ የሚሳሉ ስዕሎች አጃኢብ የሚያሰኙ ናቸው። “ሶራ” የተሰኘው የሰው ሠራሽ አስተውህሎ፣ ሃሳብ ብቻ ሰጥተነው ጥንቅቅ ያለ ፊልም ሰርቶ ያስረክበናል። የሰዎችን ሥራ ሁሉ መሥራት የተማረ ማሽን ከሰው አስበልጦ ነገሮችን መከወን ደረጃ ላይ ደርሷል።

ሰሞኑን ደግሞ ቻት ጂ ፒ ቲ 4 ኦ (ChatGPT 4O) ደረጃውን ከፍ አድርጎ በጽሁፍ፣ በድምፅ እና በምስል ከሰዎች ጋር መግባባት ጀምሯል። አንድ ሰው ያለበትን ቦታ፣ የለበሰውን ልብስ፣ በአካባቢው ያሉ ቁሶችን ጥንቅቅ አድርጎ በመመልከት ማብራራት የቻለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ከጎናችን እንዳለ አንድ ሰው ሆኖ በትክክል ማዋራት ጀምሯል። ለዚህ ነው ቴክኖሎጂው በብዙዎች ዘንድ ስጋትን የፈጠረው እና ስለ ሕግ እንዲያስቡ እያስገደደ ያለው።

ርግጥ ነው ቴክኖሎጂው ተመሳሳይ እና በሰዎች ዘንድ አሰልቺ የሆኑ ሥራዎችን በማቀላጠፍ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ ነው። የሰዎችን ሕይወት በእጅጉ እያቀለለ ነው። በጣም ባጠረ ጊዜ እና ወጪ በሚቆጥብ ሁኔታ ለሰው ልጅ ግልጋሎት እየሰጠ ነው። ለሰው ልጅ አደጋ የሆኑ ሥራዎችን ተክቶ በመሥራት ሰዎችን ከአደጋ መጠበቅ አስችሏል።

በቴክኖሎጂው ዙሪያ የሚነሳው ሌላኛው ስጋት የሰው ሠራሽ አስተውህሎ መድሎ ነው። ሶፍትዌር የሰጡትን ይቀበላል። ሰው ያዘዘውን ይፈፅማል። በተሰጠው መረጃ ልክ ሥራዎችን ይከውናል። ነገር ግን ሰው መረጃ ሲሰጠው በሰውየው ፍላጎት መሠረት አድልዎ እንዲሰራ አድርጎ መረጃ ሊመግበው ይችላል። አድልዎው በፆታ፣ በእድሜ፣ በቆዳ ቀለም እና በሌሎችም ምክንያቶች እንዲሰራ ተደርጎ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ባደጉት ሀገራት የቆዳ ቀለም ልዩነት በተለያዩ አካባቢዎች ዛሬም አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል። አንድ መሥሪያ ቤት የሥራ ማስታወቂያ ቢያወጣ እና የቅጥር ሂደቱ ሲስተም እንዲፈፅመው ቢደረግ የፈተናውን ሂደት ለተፈለገው አካል እንዲያዳላ አድርጎ ማዘዝ ይቻላል። ለሴት ወይም ለወንድ፣ ለቀይ ወይም ለጥቁር፣ እድሜያቸው ወጣት ለሆኑ ወይንም ትንሽ ገፋ ላሉ ተደርጎ ወዘተ ሊዘጋጅ ይችላል። ይህ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ አድሎ የብዙዎች ስጋት ነው። ይህም አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል።

የሰው ሠራሽ አስተውህሎ የሰዎችን ግላዊ ደህንነት በመጋፋት ረገድም ስሙ ጎልቶ ይነሳል። በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ለሰው የተለያዩ የሕግ ከለላዎች ይሰጡታል። ከቦታ ቦታ ያለገደብ የመንቀሳቀስ መብት አንዱ ነው። ነገር ግን አሁን እየመጡ ያሉ የደህንነት ካሜራዎች የሰዎችን ነፃነት እስከ መጋፋት ደርሰዋል። ይህ ጉዳይ ሕግ ሊበጅለት ይገባል። የት የት አካባቢ እንዲህ ያሉ ሥርዓቶች መዘርጋት እንዳለባቸው፣ የትኞቹ ቦታዎች ላይ ደግሞ መገጠም እንደሌለባቸው በሕግ ሊደነገግ ይገባል።

የአውሮፓ ህብረትም ባፀደቀው የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ሕግ ላይ በጣም ከፍተኛ ጥበቃ ከሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ውጭ የሰዎችን የፊት ገፅታ መመዝገብን ከልክሏል። ይህ ከሰዎች ደህንነት ጋር የተያያዘ ነው። እኛ ሀገር ግን አሳንሰር ወይም ሊፍት ላይ ሳይቀር ካሜራዎችን የመግጠም ልምድ እየታየ ነው። እነዚህ ችግሮች የሚቀረፉት በሕግ ነው።

ቴክኖሎጂ በማያቋርጥ የለውጥ ጉዞ ውስጥ የሚያልፍ እና እድሜውም በጣም አጭር ነው። ይህ ማለት ዛሬ የተፈጠረ አዲስ ቴክኖሎጂ በቀጣዩ ዓመት አዳዲስ ነገሮች ተጨምረውበት አድጎ እና ተለውጦ ሌላ ታሪክ ውስጥ ገብቶ ነው የሚገኘው። በዚህ ተለዋዋጭ የቴክኖሎጂ ዓለም ውስጥ ሀገራት የዜጎቻቸውን መብት ለማስጠበቅ ሲባል ቢችሉ የቴክኖሎጂውን የእድገት ደረጃ አስቀድመው በመተንበይ ካልሆነም ደግሞ ከቴክኖሎጂው እኩል በመራመድ “ሕግ” የተሰኘ ልጓም ሊያበጁለት ግድ ይላቸዋል።

አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂን እድገት ሊገድብ ስለሚችል ቴክኖሎጂ የሚመራበት ሕግ ቀድሞ መውጣት የለበትም ብለው ይከራከራሉ። ተገቢው አካሄድ ቴክኖሎጂውን እየተከተሉ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሆነ ያምናሉ። ሕግ ቅድሚያ ከተዘጋጀ ቴክኖሎጂው የሚያመጣቸውን አዳዲስ ግኝቶች እየገደበ ተጠቃሚነትን ያስቀራል ብለው ይከራከራሉ። እንዲህ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ቦታ ተከልሎላቸው እዚያ ውስጥ እየዳበሩ መሄድ አለባቸው ብለው የሚከራከሩም አሉ። ያም ሆነ ይህ ግን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ላይ ሁሉም ይስማማሉ።

የሰው ሠራሽ አስተውህሎ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ተደጋጋሚና አስልቺ ሥራዎችን ከመተካት ጀምሮ በጣም ጥንቃቄ በሚጠይቀው የሕክምና ዓለም ውስጥ ሳይቀር ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል። ቴክኖሎጂው በመከላከያ፣ በትምህርት፣ በፍትህ ሥርዓት፣ በመዝናኛ፣ ወዘተ በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

ሀገራት የቴክኖሎጂውን አዝማሚያ እና እየተጓዘበት ያለውን ፍጥነት በማየት የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማው አቅርቦ አፀድቋል። ሕጉ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ቴክኖሎጂን የማይፈቀዱ፣ ከፍተኛ አደጋ ያላቸው እና ዝቅተኛ አደጋ ያላቸው በሚል በሶስት ምድቦች አስቀምጧል። የማይፈቀዱ ያላቸው በማህበረሰቡ ውስጥ እንደ ስጋት የሚቆጠሩትን ነው። ሕፃናት አደገኛ ባህሪ እንዲላበሱ የሚያደርጉትን በዚህ ምድብ ውስጥ አካትቶታል።

ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚባሉት ደግሞ ወደ ገበያ ከመውጣታቸው በፊት የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ፍቃድ የሚጠይቅ ተብሎ ተለይቷል። የቅጥር ምልመላ፣ የሕግ ማስከበር፣ የድንበር ጥበቃ እና በመሳሰሉት ላይ የሚተገበሩ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ውጤቶች በዚህ ምድብ ውስጥ የተካተቱ ናቸው። ሕጉ ቀጣዮቹን ሂደቶች ሲያልፍ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ብራዚል በረቂቅ ደረጃ ባዘጋጀችው የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ሕግ ተጠቃሚዎች ከሰው ሠራሽ አስተውህሎ ጋር እየተመላለሱ መሆናቸውን፣ ውሳኔ እንዴት እንዴት እንደሚሰጥና ምክረ ሃሳቦችን በምን መልኩ እንደሚያቀርብ የማወቅ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ውሳኔዎች በሰው ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ከሆኑ (ለምሳሌ ራሳቸውን የሚነዱ መኪኖች፣ ቅጥር፣ የሂሳብ ጉዳዮች) የሰዎችን ጣልቃ ገብነት መጠየቅ የሚያስችል መብት ይሰጣቸዋል። ቴክኖሎጂውን የሚያለሙ አካላት ደግሞ የጉዳት ትንተና እንዲሰሩና እንዲከታተሉ ያስገድዳል። በሰዎች ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮችን ልዩ ትኩረት ይሰጣል።

ቻይና የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ረቂቅ ሕግ አሳትማ ለሕዝብ አስተያየት ክፍት አድርጋለች። ቴክኖሎጂው እውነተኛ እና ትክክለኛ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ላይ ያተኮረ ሲሆን የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም እሴቶችን ማንፀባረቅ አለበትም ይላል። የሰው ሠራሽ አስተውህሎው ለሰራቸው ሥራዎች ውጤት (output) አበልፃጊው ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድም ይደነግጋል። ከአዕምሯዊ ንብረት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

ጣልያን፣ ጃፓን፣ እስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሀገራቸው ሁኔታ ልክ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ሕግ እያረቀቁ ይገኛሉ። ጣልያን በዲጂታላይዜሽን ምክንያት ሥራቸውን ያጡ ዜጎችን ለመደጎም የሚያስችል አሠራር እየዘረጋችም ትገኛለች። ሁሉም ሀገራት ግን የዳታ ጥበቃ (Data) ላይ ትኩረታቸውን ያደረጋሉ።

ኢትዮጵያም የቴክኖሎጂውን ጠቃሚነት ታሳቢ በማድረግ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ኢንስቲትዩት አቋቁማ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች። በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ የማዘመን ሥራ ይጠይቃቸዋል። የጤናው ዘርፍ፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ መከላከያ፣ ትራንስፖርት፣ ፋይናንስ እና ሌሎችም ዘርፎች ይህንን ቴክኖሎጂ ይፈልጋሉ።

በርካታ ሥራዎች በሰው ሠራሽ አስተውህሎ የተደገፈ የኦቶሜሽን ሠራ ካልተሰራላቸው ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት፣ ምርትን ማሳደግ እና በጥቅሉ ሁለንተናዊ እድገት ማስመዝገብ አዳጋች ይሆናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሉላዊው ዓለም እየተራመደበት ካለው የቴክኖሎጂ መንገድ መነጠል አዳጋች በመሆኑ በተቻለ ፍጥነት በራስ አቅም ከቴክኖሎጂ እኩል መጓዝ የግድ ይላል። ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያ ከሌሎች ተቋማት ጋር በተደራቢነት መሥራት እየተቻለ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ተቋም ያቋቋመችው።

ይህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፣ ባለቤት ተሰጥቶት ቴክኖሎጂውን ለማሳደግ፣ ለመጠቀምና ለመቆጣጠር የሚያስችል እድል ይፈጥራል። ሀገራት በዚህ ዘርፍ ለዜጎች የግል ዳታ ጥበቃ ልዩ ትኩረት የሚሰጡ ሲሆን ኢትዮጵያም የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅን በማርቀቅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ አድርጋለች።

ይህ በዘርፉ የተደረገ ትልቅ ርምጃ ሲሆን ዜጎች በኤሌክትሮኒክ የተመዘገቡ መረጃዎቻቸው ወደ ሶስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ ጥበቃ እንደሚደረግላቸውና እምነት እንዲኖራቸው ያስችላል። በዲጂታል ዓለም ውስጥ የዲጂታል እምነት መፍጠር ትልቁ ሥራ ነው።

ቴክኖሎጂውን ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት ክፍተት ይስተዋላል። በአንድ በኩል በዘርፉ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ያለ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ቴክኖሎጂው ከነመፈጠሩም ያለማወቅ ክፍተቶች ይስተዋላሉ።

ይህንን ክፍተት ለመሙላት በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ከማካተት ጀምሮ የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ የክህሎት ክፍተቱን መሙላት አስፈላጊ ሲሆን የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትም ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው። ሕግ ሲዘጋጅም ማህበረሰቡ ያለበትን ደረጃ ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ይህንን የዲጂታል ክህሎት ክፍተት ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውህሎ ተቋም (የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንስቲትዩት) የሰው ሠራሽ አስተህውሎ ፖሊሲ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ላይ ነው። ፖሊሲው እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሚዘጋጅ ተስፋ እናደርጋለን።

አዲስ መኮንን

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You