የለውጡ መንግሥት በሕዝብ ድምፅና ይሁንታ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ እነሆ አራት ዓመት ሊሞላው ነው። በነዚህ ዓመታትም በተቻለው አቅም የሕዝቡን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። በነዚህ አጭር ጊዜያት ውስጥ በተሠሩ ሥራዎች በርካታ ለውጦች ሊመጡ ችለዋል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ተመልሰዋል ማለት አይቻልም።
በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ውስብስብና ውጥንቅጡ የበዛ የሕዝብ ጥያቄን መመለስ እንደማይቻል ልብ ማለት ይገባል። ምክንያቱም በየትኛውም ሀገር ውስጥ ቢሆን አዲስ የለውጥ መንግሥት ሲመጣ እነዚህን ሁሉ የተለያዩ የሕዝብ ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ መመለስ ስለማይቻል እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ጊዜ፣ ሂደትና ከሕዝቡ በኩል ደግሞ ትእግስት ይጠይቃል፡፡ ይህ ሲባል ግን እንደው የለውጡ መንግሥት እድሜው አጭር ቢሆንም ሕዝቡ አይጠይቅ ማለት አይደለም።
የሕዝብ ጥያቄ ዲሞክራሲያዊም፤ ሰብአዊም መብት ነው። መንግሥትም ቢሆን የሕዝቡን ጥያቄዎች መቀበልና ለመመለስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል። በተመሳሳይ ሕዝቡም ጥያቄዎቹን በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ያኔ መንግሥት መሠረታዊና አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ጥረት ያደርጋል። ሕዝቡም ለጥያቄዎቹ በቂ መልስ እያገኘ ይመጣል።
ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የኃይል አማራጭን ወስደውና ትጥቅ አንግበው ለጥያቄያቸው መልስ ለማግኘት የሚታትሩ በየአቅጣጫው ተፈጥረዋል። ዲሞክራሲያዊ መንገድን ትተው በምርጫ ወደስልጣን የመጣን መንግሥት በኃይል ለመጣል ላይ ታች የሚሉ ጥቂት አይደሉም። ከነዚህ ውስጥ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውና ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን በዋናነት ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ቡድኖች መንግሥት በተደጋጋሚ ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ወደጎን በመተውና የኃይል አማራጭን ወስደው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። በዚህም መሸሸጊያቸው ባደረጉት ሕዝብ ላይ ይህ ነው የማይባል በደል ሲያደርሱና ሰላሙን ሲያደፈርሱ ቆይተዋል፤ አሁንም በዚህ ተግባራቸው ቀጥለዋል። በዚህም የኅብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ከማናጋት ውጪ አንድም የፈየዱት ነገር የለም፡፡
በዚሁ ሥራቸው ምክንያት ነው እንግዲህ መንግሥት የኅብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ሲል የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ የቆየው፡፡ በመጀመሪያ መንግሥት እነዚህ ቡድኖች ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡና ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ በሩን ክፍት አድርጓል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ታጣቂ ቡድኖች የኅብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ከማወክ፣ ከመግደልና ከማሰቃየት ወደኋላ አላሉም፡፡ ለዛም ነው መንግሥት እስካሁን ድረስ እነዚህ ቡድኖች ላይ ርምጃ እየወሰደ የሚገኘው፡፡
በዚህም በርካታ የቡድኑ አባላት በየጊዜው እየተደመሰሱና ገሚሶቹም እጃቸውን ለመንግሥት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ይህም በሁለቱም ክልሎች አንፃራዊ ሰላም እየሰፈነ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ለሕዝቡ ራስ ምታት የሆኑ ታጣቂ ቡድኖችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ በክልሎቹ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ከመንግሥት በኩል ጠንካራና የተደራጁ ሥራዎችን መስራት ያስፈልጋል፡፡
ከነዚህ ውስጥ አንዱና አሁንም መንግሥት እያከናወነ ያለው ተግባር ሰላማዊ መንገድን መርጠውና ሲሠሩት በነበረው እኩይ ሥራ የተፀፀቱ የታጣቂ ቡድኖች አባላትን ወደ ተሃድሶ ማእከላት በማስገባትና በቂ ስልጠና በመስጠት ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሥራም በርካታ የታጣቂ ቡድኖቹ አባላት እጃቸውን በሰላም ለመከላከያ ሠራዊት በመስጠት ወደ ተሃድሶ ማእከላት እየገቡ ነው፡፡ ይህንኑ ተግባር በማየት ሌሎችም ወደ ተሃድሶ ማእከላት እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
መንግሥት ባደረገው የሰላም ጥሪ በርካታ የታጣቂ ቡድኖቹ አባላት ወደ ተሃድሶ ማእከላት እየገቡ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ታዲያ መንግሥት አሁንም ቢሆን ለሰላም በሩ ክፍት መሆኑን በተደጋጋሚ በመግለፁና በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ጠንካራ ሥራዎችን በመሥራቱ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የቡድኑ አባላትም ቢሆኑ ወደተሃድሶ ማእከላት በብዛት እየገቡ ያሉት ይህ የሰላም አማራጭ አዋጭ እንጂ አክሳሪ አለመሆኑን በመረዳት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም ይህን የሰላም አማራጭ እድል ተጠቅመው ወደ ተሃድሶ ማእከላት በርካታ የታጣቂ ቡድኖቹ አባላት እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
አገናዝቦና በብስለት ወስኖ ወደ ተሃድሶ መግባት በብዙ መልኩ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ ይህን ወስነው ወደ ተሃድሶ ማእከላት የሚቀላቀሉ የቡድኑ አባላት ተገቢውን ስልጠናና ትምህርት ወስደው ከጥፋታቸው ተምረው ዳግም ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለው የበደሉትን ሕዝብና መንግሥት ዳግም መካስ እድል ይፈጠርላቸዋል። ካላስፈላጊ የህይወት መስዋእትነትም ይድናሉ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ልክ እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በመረጡት የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ጥረው ግረው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመቀየር ምቹ አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል፡፡ የልማቱ ተሳታፊ በመሆንም ጭምር የራሳቸውን አስተዋፅኦ የሚያበረክቱበት እድል ሰፊ ነው።
ስለዚህ የታጣቂ ቡድኖቹ አባላት በስፋት ወደ ተሃድሶ ማእከላት እንዲገቡና ለእነርሱም ሆነ ለኅብረተሰቡ ሰላማዊ ምህዳር እንዲፈጠር ከራሳቸው ከታጣቂ ቡድኑ አባላት፣ ከሕዝቡና ከመንግሥት ብዙ ሥራዎች ይጠበቃሉ። የታጣቂ ቡድኑ አባላት እያደረጉት ያለው የኃይል እንቅስቃሴ የህይወት ዋጋ እንደሚያስከፍልና በዚህ መንገድ ስልጣን መያዝ እንደማይቻል ልብ ሊሉ ይገባል፡፡ ጊዜው የውይይትና በሃሳብ የማሸነፍ ነውና ይህንኑ የሰላም አካሄድ በመከተል በሃሳብ የበላይነት በማመን በዚሁ መንገድ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ያኔ ተገቢውን ስልጠናና ምክር አግኝተው ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላሉ።
በዲሞክራሲና በሰለጠነ መንገድ ጥያቄያቸውን ማቅረብና አላማም ካላቸው አላማቸውን ለማሳካት በዚሁ መንገድ መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ሕዝቡም ቢሆን ፖለቲካዊ አካሄዳቸውን፣ ዓላማቸውንና ሃሳባቸውን ለማዳመጥ ዝግጁ ይሆናል፡፡
ኅብረተሰቡም ቢሆን እነዚህ ታጣቂ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ሰጥተው ወደ ተሃድሶ ማእከላት እንዲገቡ በየትኛውም አጋጣሚ ቢሆን ከመንግሥት ጋር በትብብር መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህ ታጣቂ ቡድኖች መሸሸጊያቸው በአብዛኛው ሕዝቡ ነውና አባላቱን መንጥሮ በማውጣቱ ሥራ ኅብረተሰቡ ቀና ትብብር ሊያደርግ ይገባል። አባላቱ ለመከላከያ ሠራዊቱ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ መጠቆምም ይኖርበታል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የታጣቂ ቡድኖቹ አባላት ወደ ተሃድሶ ማእከል እንዲገቡና በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ምክር መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
መንግሥትም እስካሁን ድረስ እየሠራው ያለው ሥራ እንዳለ ሆኖ የታጣቂ ቡድኑ አባላት አሁንም ወደ ተሃድሶ ማእከላት በብዛት እንዲገቡ ተጨማሪ የቤት ሥራዎችን መሥራት ይኖርበታል፡፡ በተለይ ደግሞ ይህ አካሄድ አዋጭና አላስፈላጊ የህይወት መስዋእትነትን የሚቀንስ መሆኑን በመረዳት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት፡ ፡ በተለይ ደግሞ አባላቱ ወደ ተሃድሶ ማእከላት እንዲገቡ በማድረጉ ሂደት ሕዝቡ ቁልፍ ሚና ስለሚጫወት ከሕዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
በሌላ በኩል የታጣቂ ቡድኖቹ አባላት ወደ ተሃድሶ ማእካላት ከገቡ በኋላ ተገቢውን ስልጠናና ትምህርት አግኝተው ወደ ኅብረተሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላ ፍፁም ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና ተመልሰው ወደ በፊቱ እንቅስቃሴያቸው እንዳይገቡ የማያቋርጥና ተከታታይነት ያለው ሥራ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ማከናወን አለበት፡፡ ለዚህ ስራ ታዲያ በሁለቱም ክልሎች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ አመራሮች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
የተሃድሶ ሥራውን በቅንጅትና በትብብር መሥራት የሚቻል ከሆነ አላስፈላጊ የህይወት መስዋእትነትን በመቀነስ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ ይቻላል፡፡ ይህ ሰላማዊ ሁኔታ ደግሞ የሚፈለገውን ልማት ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ያኔ በሁለቱም ክልሎች ያሉ ሕዝቦች የሰላም አየር ተንፍሰው በልማታዊ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
የታጣቂ ቡድኖቹ አባላት መንግሥት ያቀረበላችሁን የሰላም አማራጭ መንገድ በመከተል ወደዚሁ መስመር እንደሚቀላቀሉ ተስፋ ይደረጋል፡፡ ወደተሃድሶ እየተቀላቀሉ ያሉትም ተገቢውን ስልጠናና ትምህርት ወስደው ሀገራቸውን ለመካስ ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ አለባቸው፡፡
ሙዘይን ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም