ጽዱ ከተማ የሕዝቦች የሥልጣኔ ገላጭ ምስል ነው

ዘመናዊነት ከሚገለጽባቸውና የሥልጣኔ ማሳያ ተደርገው ከሚወሰዱ አበይት ክንዋኔዎች ውስጥ የከተማ ጽዱነት አንዱ ነው፡፡ ጽዳት ሕይወትና እድገት የተቆራኙበት የአንድ ወሳኝ ኩነት መጀመሪያና ማብቂያ ነው፡፡ በመርህ እና በአስገዳጅ ሕግ አይቀመጥ እንጂ ሁሉንም የሚያግባባ የጋራ እውነት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ በዚህም መነሻ ጽዱ ከተማ የሕዝቦች የመኖር ዋስትና የሚረጋገጥበት፣ የሥራ ተነሳሽነት የሚፈጥር፣ የውጪ ጎብኚዎችን የሚስብ፣ ከጤና አኳያ የማይናቅ ሚና ያለው፣ በኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ዐሻራው የገዘፈ እንደሆነ በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል፡፡

የጽዳት ጽንሰ ሃሳብ እጅግ ሰፊና ግዙፍ ነው። እንደሀገርም ሆነ እንደግለሰብ ሥልጣኔን በበቂ ሁኔታ ይገልጻሉ ተብለው ከሚታሰቡት ውስጥ ጽዳት የሚለው ቃል ቀዳሚው ነው፡፡ ጽዳት ለምንም ነገር መነሻ ነው፡፡ ንጽህና በጥላው እንዳማረ፣ በቅርንጫፎቹ እንደተሞገሰ እንደአንድ ለምለም ዛፍ የሚታሰብ ነው፡፡ ይሄን ዛፍ ሁሉም ይቀመጥበታል፣ ብዙዎች ፎቶ ይነሱበታል፣ ከከንፈር ወዳጃቸው ጋር የሚቀጣጠሩበትም አይጠፉም፡፡ ደክሞን የምናርፍበት፣ ተጣልተን የምንታረቅበት የእርቅ ጉባዔያችንም መሆን ይችላል፡፡ ለምለምና ሳቢ ባይሆን ግን ለዚህ ሁሉ ክብር አንመርጠውም፡፡

ይሄ እውነት የሚገባን ግን ከነበርንበትና ለብዙ ጊዜ ከተለማመድንው ማህበራዊ ልምምድ ስንርቅ ነው። የአንድን ነገር አስፈላጊነት ካልተረዳነው በመሆንና ባለመሆኑ ውስጥ ያለውን ልዩነት አንረዳውም፡፡ የጽዳትን አስፈላጊነት ለመረዳት ከቆሻሻ አካባቢ ጋር የነበረንን ቁርኝት መሻር ያስፈልጋል፡፡ ዋና ከተማችን አዲስ አበባ እንደስሟ ውብና ማራኪ አልነበረችም፡ ፡ከዚም ከዛም በሚጣሉ ቆሻሻዎች፣ በሽንት በሰገራ፣ ሃላፊነት በማይሰማቸው አንዳንድ ሰዎች ውበቷን አጥታ ‹ሽታዬ› በሚል የማላገጫ ስም እስከመጠራት ደርሳ ነበር፡፡

አሁን ባለው ንቅናቄ ከቆሻሻ አስተሳሰብ ወጥተን ወደጽዱና ምቹ አስተሳሰብ ለመሸጋገር በመንግሥት በኩል ቁርጠኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከተማችንን ስማርት ሲቲ ከማድረግ ጀምሮ በንጽህናዋ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀውን አዲስ አበባ ለመፍጠር በከፍተኛ ርብርብ ላይ እንገኛለን፡፡ ሁሉን ትተን እንኳን ባለፉት ወራት ውስጥ እየተከናወነ ያለውን የኮሊደር ልማት ብንቃኝ በብዙ ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች የታጀበ ነው ፡፡ በቀን ለሃያ አራት ሰአት፣ በሳምንት ለሰባት ቀናት እጅግ በበረቱና ለለውጥ በታተሩ ሠራተኞች ከተማችን ስሟን ለማደስና ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ጥረት በሁሉም አካባቢ እየታየ ያለ እውነታ ነው፡፡

ሂደቱ ቀጣይነት ያለውና ከቆሻሻ ጋር የነበረንን ትስስር እስከወዲያኛው የሚሽር ነው፡፡ ከእንጦጦ ፓርክና ከወዳጅነት አደባባይ፣ ከአንድነት ፓርክ እስከ መስቀል አደባባይ ከዛም ከፍ ብሎ እስከዓድዋ ሙዚየም ድረስ የተሻገረው የከተማ ውበት ዋና ከተማችን ላይ አርፎ ሁላችንም የነገዋን አዲስ አበባ እንድንናፍቅ እያደረገን ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቀው የኮሊደር ልማት ሥራ ለብዙዎች የሥራ እድል ከመፍጠር ጎን ለጎን ማህበረሰቡ ስለምቹ አካባቢ ያለውን ግንዛቤ እንዲሳድግ መንገድ የከፈተም ነው፡፡

ባደጉትና በማደግ ላይ ባለንም እኛ መሀከል የሀገር እድገትን በተመለከተ የአረዳድ ልዩነት አለ፡ ፡ ያደጉት ሀገራት ለየትኛውም እድገትና ለውጥ እንደዋነኛ ምክንያት የሚያነሱት የግልና የአካባቢ ከፍ ካለም የከተማን ጽዳት ነው፡፡ እኛ ግን እንደዚህ አናስብም እድገት የሚሉትን ጽንሰ ሃሳብ ከሥራና ሥራ ጋር ብቻ አያይዘን ያለን ነን፡፡ አእምሮ እንዲሠራ፣ እንዲፈጥር፣ እንዲነቃቃ፣ ሰው በትጋት ህልሙን እንዲያሳካ እንደምቹ ከባቢ ያሉ እንደቅድመ ሁኔታ የሚቀመጡ ነገሮች እንዳሉ አንረዳም፡፡

ለሥራ በማያነቃቃና ለመኖር ምቹ ባልሆነ አካባቢና ከተማ ላይ ስኬት እምብዛም ነው፡ መጀመሪያ መቀመጫዬን እንዳለችው ዝንጀሮ.. መጀመሪያ ከተማችን፣ መጀመሪያ አካባቢያችንን እናጽዳ፡፡ ከዛ በኋላ በሚገርም ሁኔታ፣ ባልገባን መልኩ ለሥራ፣ ለለውጥ፣ ለስኬት ስንተጋ ራሳችንን እናገኘዋለን፡፡

በጽዳቱ ረገድ ዱባይ ሙንባይ እያልን የሌሎችን ሀገር ከማወደስ የዘለለ ታሪክ አልነበረንም፡ ፡ የኒዮርክንና የጁሀንሰበርግን ከተሞች ከማድነቅ ባለፈ እኔስ ስንል ለከተማችን ጽዳት የበኩላችንን ስናደርግ አንታይም፡፡ ሌሎች ሀገራት ያስደነቁን በተባበረና ለአንድ ዓላማ በተጋ መንፈስ ነው፡፡ እኛም ያስደነቁንን ለማስደነቅ መንግሥት ባዘጋጀው የከተማ ጽዳት ቴሌቶን እና ሥራ ላይ በገንዘብና በጉልበት፣ በእውቀትና በሃሳብ በመሳተፍ አዲስ አበባችንን እንደስሟ አበባ ማድረግ ይቻለናል፡፡

አንድ እንጨት ብቻውን አይነድም.. ሀገር የጋራ መኖሪያ፣ የጋራ መጠሪያ ናት፡፡ ከተማ የጋራ ታሪክ የጋራ ርስት ነው፡፡ በጽዳት ዓላማው ላይ ሁላችንም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ህልማችንን እውን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ አንዳንድ ነገሮች ለአንዳንድ ሰዎች ብቻ የምንተዋቸው አይደሉም፡፡ ዓድዋ ስንል ኢትዮጵያዊነት ነው የሚነሳው፡፡ ህዳሴ ግድብ ስንል ብዙሀነት ነው የሚታወሰው፡፡ በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አብሮነት ነው የሚመጣው ልክ እንደዚህ ሁሉ የከተማ ውበትም የሁላችንም የጋራ ሃላፊነት ነው፡፡ ከእድፍና ከቆሻሻ ጋር የሚነሳ ታሪካችንን አድሰን በጤናማ አካባቢ ሰላማዊ ሕይወት ለመኖር መብት አለን፡፡

እድገትንና ለውጥን በተመለከተ የብዙዎቻችን አረዳድ በኢኮኖሚ ግንባታ በኩል የሚንጸባረቅ ነው፡፡ እውነት ነው የአንድ ሀገር ሃያልነት እውቅና የሚያገኘው በኢኮኖሚዋ በኩል ነው፡፡ ነገር ግን የትኛውም የእድገትና የሥልጣኔ እሳቤ ጽዳትና የኑሮ ምቹነትን ተንተርሶ የሚመጣ ነው፡፡ ጽዱ እና ምቹ አካባቢ የጽዱና ምቹ አስተሳሰብ ነጸብራቅ ነው። ሰው አካባቢውን ይመስላል የሚባለው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ሁላችንም በአካባቢያችን የተሳልንና የተቀረጽን ነን፡፡ ጽዱና ምቹ አካባቢ የመኖር ፍላጎትን ከመጨመርና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ሥልጣኔያችንን፣ ታሪካችንን፣ ማንነታችንን ለሌሎች የምንገልጽበት ምቹ አጋጣሚያችን ነው፡፡

እንደአፍሪካ ህብረት መቀመጫነት፣ እንደዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነታችን እድላችንን ተጠቅመን በከተማችን በኩል የምናንጸባርቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በታሪክና በባህል ለሰፋ ለእንደኛ አይነቱ በብዙሀነት ለተዋበ ማንነት የከተማ ውበት ልዩ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተዘጋጀ ‹የህንጻ ግንባታ ትናንት ዛሬና ነገ› በሚል መርሀ ግብር ላይ ተሳትፌ ነበር፡፡ በፕሮግራሙ ላይ በተነሳ የባለሙያ ሃሳብ የአዲስ አበባ መልከአምድር ለከተማ ውበት፣ ለሕዝቦች መኖሪያነት እጅግ ምቹ እንደሆነና ዓለም ላይ እንዲህ ባለ ተፈጥሮ ስር ያሉ ሀገራት እንደሌሉ አድምጨ ነበር፡፡ ከሁሉም ጎልቶ የተነሳው ሃሳብ ደግሞ መልከአ ምድራችንን አልተጠቀምንበትም እንጂ ከዚህም በላይ በውበትና በጽዳት ስማችንን ማስጠራት እንችል ነበር የሚለው የቁጭት አነጋገር ነው፡፡

ከተማ ማንነት ነው፡፡ ከተማ የሕዝብ መልክ ነው። የትናንትና የዛሬ የነገም አስተሳሰብ ውህድ ነው፡ ፡ ጽዱ ከተማ ለአንድ ሀገር እንደመታወቂያ አርማ ነው፡፡ ከሰንደቅዓላማቸው እኩል በውበታቸው የሚታወቁ ብዙ ሀገራት አሉ፡፡ የከተማ ንጽህናቸው መጠሪያቸው ሆኖ ለዓለም ያስተዋወቃቸው ጥቂቶች አይደሉም። እኛም በዚህ ንቅናቄ ውስጥ ነን፡፡ በውበትና በንጽህና ጽዱ ከባቢን መፍጠር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። በኢኮኖሚ፣ በጤና፣ በትራንስፖርት፣ በትምህርት፣ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ አዎንታዊ ሚዛን የሚደፋ ነው፡፡

ለሠራተኛው ተስማሚ የሥራ ቦታ ሳንፈጥር ስለኢኮኖሚ ብናወራ ትርጉም የለውም፡፡ አካባቢያችንን ጽዱና ምቹ ሳናደርግ ስለጤና ብናወራ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ከተማዎቻችንን ለትራፊክ ፍሰት ሳናዘጋጅ ስለትራፊክ አደጋ ብንዘግብ ዋጋ ቢስ ነው። የግልና የአካባቢ ንጽህናን ቸል ብለን ትምህርት የእድገት ቁልፍ ነው ብንል፣ ለጎብኚዎች ተስማሚ ሁኔታን ሳንፈጥር ስላሉን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ብናወራ ምንም አናመጣም፡፡ ቅድሚያ ለሚገባው ቅድሚያ በመስጠት ውስጥ ነው ነገሮች የሚስተካከሉት፡፡ ተዘበራርቀንና ቅደም ተከተላችንን ሳንጠብቅ ነገሮች እንዲሆኑ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡

ነገር በአይን ነው የሚገባው፡፡ በአይን ያልገባ ልብ ላይ አያርፍም፡፡ አእምሮ ነቅቶና በቅቶ ሥራውን እንዲሠራ የምናየው ተስማሚያችን ሊሆን ይገባል፡፡ ገና ከቤታችን ስንወጣ ሰፈራችን ጸድቶ፣ ከተማችን አምሮ ስናይ ውሏችን ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ከቤት በምንወዳቸው ተስመንና ተሞካሽተን ስንወጣ የሚሰማንን ያህል ቀናችን ተባርኮ እንደሚውል ስ።በት እንደሚጀምር እነግራችኋለሁ፡፡

አበባ ለንብ ነው የተፈጠረው፡፡ ንብ ደግሞ ሁልጊዜም ከአበባ ጎን የቆመ ነው፡፡ ንብና አበባ የውበትና የመልካም ስም ምሳሌዎች ናቸው፡፡ መዲናችን አዲስ አበባ ‹አበባ› የሚለውን ስም ይዛ ስሟንና ክብሯን በሚመጥን ደረጃ አለማማሯና አለመቆንጀቷ ሁሉንም የሚያስቆጭ ሆኖ የሰነበተ መሆኑ ቢታወቅም ክብሯን ለሚመጥን ውበትና ማማር መታጨቷ ደግሞ ሌላው የምስራች ነው። ለተለያየ ዓላማ ከሰባቱም አህጉራት ብዙዎች የሚረግጧት አዲስ አበባ ከዚህ በኋላ እንግዶቿን የምትቀበለው በሽታ በተጨማደደ ፊት ሳይሆን በአድናቆት በተከፈተ አፍ ነው፡፡

ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ከልማት ጎን ለጎን ለከተማ ውበት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ የውበትና የጽዱነት ንቅናቄም የዚህ እንቅስቃሴ አንድ አካል ነው። ለውጥ ተላላፊ ነው፡፡ አዲስ አበባ የጀመረው ገበታ ለሀገር አሌላ ኬላ እና ጎርጎራ ላይ ቀጥሎ በሌሎችም አካባቢዎች እየተዛመተ ነው፡፡ ልክ እንደዚህ የአዲስ አበባ ውበትም ወደሌሎች ከተማ ተዛምቶ በጽዳትና በጤናው ዘርፍ ውጤት እንደምናመጣ መተማመን ይሰጠናል፡፡

በሳይንሱ ዓለም የግልም ሆነ የአካባቢ ንጽህና በሽታን ከመከላከልና ገጽታን ከመገንባት አኳያ እንደቅድመ ሁኔታ ይቀመጣል፡፡ ይሄን ርዕሰ ጉዳይ ወደሀገር ስንቀይረው ደግሞ ትርጉሙ ከዚህም በላይ ላቅ ብሎ ይገኛል፡፡ ትስስራችን ከቤት ወደውጪ፣ ከውጪ ወደ አካባቢ ከዛም ሀገር የሚሏት ግዙፍ እውነት ላይ እናርፋለን፡፡ ከግል ተነስተን ሀገር ላይ ካረፍን እኛ ለሀገር ሀገርም ለእኛ የምትሰጠን አለ ማለት ነው፡፡ እንደሀገር የያዝንው ‹ጽዱ ከተማ ኑሮ በጤና› ንቅናቄ አዲስ አበባን እንደስሟ አበባ ከማድረግ፣ ሕዝቦቹን በደህነኛ አካባቢ ከማኖር፣ ለትውልዱ ጽዱና ጤነኛ ከተማን ከማውረስ ባለፈ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጎ ስምን መትከል ነው፡፡ ይሄ ሂደት የክብር ሥፍራውን ያደረገው እኛን ነው፡፡ ትስስራችን የጠበቀ ነው ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡

ሥልጣኔ አስተሳሰብ ነው፡፡ አስተሳሰብ ደግሞ ራስን ከማፍቀር፣ ለራስ ዋጋ ከመስጠት፣ ሀገርና ትውልድን በምቹ ህልም ውስጥ ከማሳለፍ የሚጀምር ነው፡፡ እንደሀገር በዚህ ሁሉን አቃፊ ህልም ውስጥ እያለፍን ነው፡፡ አሁን ባነሳሁት ሃሳብ ዙሪያ የከተማ ንጽህና የሕዝቦችን የመኖር ዋስትና የሚያረጋግጥ፣ ሰላማዊ አካባቢን የሚፈጥር መሆኑ ንጽህና ለራስ ዋጋ የምንሰጥበት፣ እኛ ማለት ይሄን ነን ብለን ለሌሎች መልዕክት የምናስተላለፍበት ነው፡፡ አንድ ሰው በንጽህናው ማንነቱ እንደሚፈረጅ የከተማ ንጽህናው እንደዚሁ መታወቂያችን ነው፡፡ ስለሆነም ከጋራችን ለጋራችን በሆነ ጽዳት መር እሳቤ ላይ በ ‹‹ያገባኛል›› በመሳተፍ ሂደቱን ማቀላጠፍ ከሁላችን ይጠበቃል፡፡ ‹‹‹ጽዱ ከተማ ኑሮ በጤና››› ቸር ሰንብቱ፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You