መቼም ሀገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ለመወጣት መፍትሄው በእጃችን ስለመሆኑ ማንም የሚጠፋው ያለ አይመሰለኝም። በዚህ ዘመን ‹‹አንተም ተው፤ አንተም ተው ብሎ›› የሚያስታርቅ ሽማግሌ ጠፍትቷል። አስታራቂ ሽማግሌ በታጣበት፤ አስታረቂ ጠፍቶ አራጋቢ አቀጣጣይ በበዛበት በዚህ ወቅት እርስ በእራሳቸችን ከመመካከር እና ከመታረቅ የተሻለ አማራጭ የለም።
የአንድ ሀገር ሕዝቦች ለጋራ እድገት፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት፣ በጥቅሉም ለሁለንተናዊ ደህንነት በጋራ የመቆማቸውን ያህል፤ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምክንያት የማይግባቡባቸው ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ትልቁ አማራጭ ስክነት የተሞላበት ምክክር ማድረግ አማራጭ የለውም። በየጊዜው ለሚፈጠሩ ያለመግባባቶች ደግሞ ሕዝቦች በዋናነት የመፍትሄ አካል ሊሆኑ ይገባቸዋል።
ማንነት ምንነት የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት እንኳን ቆሞ የሚነጋገሩበት ሀገር ማስፈለጉ አያጠያይቅምና በሕዝቦች መካከል ያሉ አለመግባባቶችን መክረው ወደ መፍትሄ መድረስ የሕዝቦች ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። በሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶቻቸው ወደ ልዩነት፤ ልዩነቶችን ወደ ግጭትና የእርስ በእርስ ጦርነት ማምረታቸውን ከታሪክ መዛግብት ከመመልከታችንም በላይ የእኛም ሀገር አውነታ ሊሆን እየተቃረበ ነው። ይሄ አለመግባባት ወደ ልዩነት፣ ልዩነቱም ወደ ግጭትና ጦርነት በማምራት ሀገራችን በድህነትና ኋላ ቀርነት ውስጥ እንዳትዳክር ፤ አንድነት የወለደው ጥንካሬዋ ጠፍቶ ተበታትነን እንዳንቀር አስታራቂ ሳንሻ እኛው እንታረቅ እላለሁ።
ኢትዮጵያም እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ በአንድ ቆመው ወራሪን አሳፍረው ነጻነትና ሉዓላዊነታቸውን አጽንተዋል። እውቀቶቻቸውን ደምረውም በዓለም ሥልጣኔ (በባህል፣ በሥነጥበብና ሥነ ሕንጻ፣ በሥነጽሑፍና ሥነፈለክ፣ …) ውስጥ የሚጠቀስ ተግባርን ፈጽመዋል፤ ይሄንኑ የሚናገር ዐሻራንም አኑረዋል።
ከሚያጣላቸው ነገር በላይ የሚያዋደዳቸው ከሚያለየያቸው የውሸት ትርክት በላይ በአንድ የሚያጋምድ ፅኑ የሥልጣኔና የታሪክ ገመድን በማጤን ምርቱን ከግርዱ ለይቶ ወደ እውነት መጠጋት ለሁላችንም የሚበጅ መሆኑ አያጠራጥርም።
በተለያዩ ምክንያቶች ምናልባትም ከብዝሃ ማንነት ጋር የሚፈጠር የፍላጎትም ሆነ የአስተሳሰብ ልዩነትን በልኩ አጣጥሞ መጓዝ ሲያቅት በተለያዩ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ቅራኔዎች አሉ። እነዚህ ቅራኔዎች ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭትን ብሎም ጦርነትን እንድናስተናግድ ማደረጋቸውን ተመልክተናል። በግጭቶቹም የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት ከፍለናል፤ እንደሀገርም ተጎድተናል።
በየጊዜው የሚነሱ አለመግባባቶች፣ ልዩነትና ቅራኔዎች ደግሞ ወደ ግጭትና ጦርነት የማምራታቸው ምክንያት፣ በችግሮቹ ዙሪያ ቁጭ ብለን መነጋገርና መፍታት ባለመቻላችን ነው። ዛሬም በዚህ መልኩ ለችግሮቻችን መነጋገርና መመካከርን ባለማስቀደማችን፤ ችግሮችን በጠብ መንጃ መፍታት ይቻላል የሚል እሳቤን ይዘን ዘልቀናል። ለዚህም እንደ ሀገርም፣ እንደ ሕዝብም ከጦርነት አዙሪት መውጣት ተስኖናል። ስለዚህ ቆም ብለን ግራ ቀኝ ማየት ይገባናል። ብልጥ ከሰው ሞኝ ከራሱ ስህተት ይማራል ይሉት ነገር ደርሶብን በራሳችን ስህተት እንኳን ለመማር ጊዜ እየፈጀን ነው። ስለዚህም ቆም ብለን ጉዟችንን መመርመር ይገባናል። ጦርነትና ግጭት ከኪሳራ ውጭ ያስገኘልን ፋይዳ እንደሌለ ልንረዳ ይገባል።
ሀገራችን ለዘመናት እየዳከረችበት ካለ ችግር እንድትወጣ፤ ከትናንት እስከ ዛሬም ዋጋ እያስከፈለን ያለ ጉዳይ ቀርቶ በአዲስ ይተካ ዘንድ ትልቁ አማራጭ እርቅ ብቻ ነው። ለዚህም መደላደል ተፈጥሯል። መደላደሉም ኢትዮጵያውያን በልዩነቶቻቸውና ችግሮቻቸው ላይ ቁጭ ብለው እንዲመክሩ፣ ችግሮቻቸውን ፈትተው፣ ልዩነቶቻቸውንም አቻችለውና አጥብበው እንዲጓዙ የሚያስችላቸውን አውድ ለመፍጠር እንዲቻል ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ታቀዶ የተገባበት ጉዳይ ሆኗል።
ዘመናትን የተሻገሩ እንደ ሀገር የተከማቹ እና አሁንም ድረስ የሚታዩ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እና ለሕዝቦች አብሮነት ማጠናከር ሀገራዊ ምክክርን እንዲያመቻች የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ፤ ኮሚሽነሮች ተመድበውለት እና አደረጃጀት ተፈጥሮለት
ወደ ሥራ ገብቷል። በዚህም የቅድመ ዝግጅት ተግባራቱን አጠናቅቆ፤ በዝግጅት ጊዜ ተግባሩም አጀንዳ መረጣ ለማካሄድ ውይይት የሚያካሂድበት መእራፍ ላይ ደርሷል።
ኮሚሽኑም በምክክር ሂደቱ ያግዙኛል፣ ተልዕኮዬን እንዳሳካ አቅም ይሆኑኛል ያላቸውን ባለድርሻዎች አብረውት እንዲሰሩ በሚችለው ሁሉ እየጣረ ነው። ቀርቦ ያማክራል፤ ሃሳብ ይሰበስባል፤ አቅም ይገነባል፤ በሕግና አሠራሮች ላይ ያወያያል፤ ሁሉም ዜጋና ተቋም ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ችግሮች መፈታት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ደጋግሞ ሲያሳ ስብም አድምጠናል።
በዚህ በኩል በየደረጃው ያለው ሕዝብ፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የፖለቲካ እና የተለያዩ ሲቪክ ድርጅቶች፣… ሁሉም በየፈርጃቸው ከፍ ያለ ኃላፊነት መወጣትም አለባቸው። ለምሳሌ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ በማድረግ በኩል ከፍ ያለ ኃላፊነት አለባቸው። በዚህም ዜጎች ግንዛቤ ኖሯቸው በምክክሩ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል መረጃ የመስጠት፣ የማስገንዘብ እና የመነጋገር ባህልን ለማጎልበት የሚያስችሉ ዘገባዎችንና ፕሮግራሞችን መሥራት ይኖርባቸዋል።
በዚህ ረገድ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም፤ አሁንም ግን ከኮሚሽኑ ከፍ ያለ ተግባርና ኃላፊነት፣ ከጉዳዩም ክብደት አኳያ ሲታይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ኮሚሽኑ ተግባሩን ለማጠናቀቅ የሚቀረው ጊዜ የአስር ወራት እድሜ ከመሆኑ አኳያ፤ ከመገናኛ ብዙሃኑም ሆነ ከመላው ሕዝብና ተቋም ከፍ ያለ የቤት ሥራ ይጠበቃል። ይሄን ማድረግ የሚቻለውም ሀገራዊ ምክክሩ ከችግሮቻችን መውጫ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
አስታራቂ በማይኖርበት ‹‹ኑ እንነጋገር ፤ ወደ መግባባት እንሂድ ›› የሚለውን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሃሳብ በአንድ ተቀብሎ ችግሮችን ጠረጴዛ ላይ በማስቀመጥ ለመፍታት መጣር አማራጭ የሌለው መሆኑን ልንረዳ ይገባናል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የከተማ አስተዳደርና ክልላዊ የምክክር ምዕራፉን በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሯል። ለሠባት ቀናት በሚቆየው በዚህ የምክክር ምዕራፍ በቀዳሚነት ለምክክሩ የሚቀርቡ ተሳታፊዎች በምክክርና በውይይት የአጀንዳ ሃሳቦችን እንደሚያመጡ ይጠበቃል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የሚነሱ ማንኛውንም አጀንዳዎች ለማስተናገድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል። በምክክሩ ላይ የሚገኙት ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ አሰባስበውና አደራጅተው የመፍትሔ ሃሳቦችንም በዚሁ ምዕራፍ ያቀርባሉ ተብሏል።
ታዲያ ይህ ተስፋ ሰጪ ጅምር ይሳካ ዘንድ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባዋል። ሰዎች በብሄር፤ በኃይማኖረትና በቀዬ ሳይወሰኑ የተሻለ ሃሳብ ያለው ሁሉ ያለውን በማዋጣት እስከመጨረሻው ድረስ በምክክሩ ሊዘልቅ ይገባል። ይህ ሲሆን የግጭት ምዕራፍ ይዘጋል፤ የትብብር፣ የአንድነታችን የአብሮነት ምዕራፍ ያብባል። ኢትዮጵያ እንደጥንቱ ገናና ትሆናለች።
ለብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም