“አሁን በአገሪቱ እየታየ ያለው ሁኔታ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡ ብዙ መልካም መልካም ነገሮች እያየን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህም ከዚያም የምናያቸው ግጭቶችና የሰላም እጦት ችግሮች ይህንን ደስታችንንና ተስፋችን እንዳናጣጥም አድርገውናል፡፡ የሰላም ጉዳይ ሁሉም ሊያስብበትና መፍትሔ ሊፈልግለት ይገባል” የሚሉት 13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር ከጅግጅጋ የመጡት ወይዘሮ መፍቱሃ ሀሰን ናቸው፡፡
በበዓሉ አከባበር ወቅት ተገኝተን ያነጋገር ናቸው ወይዘሮ መፍቱሃ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መገኛና የኢትዮጵያ ተምሳሌት በሆነችው በውቧ አዲስ አበባ አዘጋጅነት መከበሩ የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ለየት እንደሚያደርገው ጠቁመው “ይህንን የመሰለ በብዝሃነት የደመቀ ውብ ኢትዮጵያዊነታችን ከምንም በላይ ልንወደው ይገባል” ይላሉ፡፡ “በእውነቱ ይህንን አብሮነታችን ለማጥፋት የሚደክሙ ሰዎች የሁላችንም ጠላት ናቸው፤ የአገርንና የህዝብን ሰላም የሚጠሉ ራሳቸውንም የሚጠሉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በድርጊታቸው የሚጎዱት ሌላውን ብቻ አይደለም እነርሱን ራሳቸውን ጭምር ነው” ፡፡ ስለሆነም ለራሳቸው ሲሉ ከዚህ እኩይ ምግባራቸው መታቀብ ይገባቸዋል በማለት ከሰላም በተቃራኒ መሄድ ትርፉ ለማንም የማይጠቅም ኪሳራ ብቻ መሆኑን ይመክራሉ፡፡
ከነቀምት ከተማ የመጡት አቶ ዋቆ ግርማ በበኩላቸው፤ “በዓሉን ስናከብር ስለ ሰላማችን እያሰብን መሆን ይገባዋል” ይላሉ፡፡ ምክንያቱም እርሳቸው እንደሚሉት ማንም ቢሆን መብቱና ማንነቱ ተከብሮለት ሊኖር የሚችለው አገር ሰላም ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ህብረተሰብ ራሱን ለግጭት ከሚያጋልጡ ነገሮች ማራቅና ሆን ብለው ሰላምን ለማደፍረስ ከሚሰሩ ሴረኞች መጠበቅ ይገባዋል፡፡ በአንጻሩ መከባበርን፣ መተባበርንና ወንድማዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ደግሞ በንቃት መሳተፍና ቀዳሚ ተሰላፊ መሆን ይኖርበታል፡፡
“አገር ማለት የጋራ መኖሪያ ቤት ናት፤ ስለሆነም አገር ሰላም ካልሆነች ራሱ ወይም ቤተሰቡ ብቻ ሰላም ስለሆነ ብቻ በሰላም መኖር አይቻልም” የሚሉት አቶ ዋቆ በሰላም ጉዳይ አንዱ አንዱን አያገባኝም ሳይል ሁሉም ተባብሮ መስራት የሚገባው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጽጌረዳ አሰፋ በበኩላቸው “የሰላም ጉዳይ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም” በማለት አስተያታቸውን ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ረገድ ራሱ ህብረተሰቡ እርስ በእርስ ተባብሮ ሰላሙን ጠብቆ የመኖር ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የሚያመላክቱት ወይዘሮ ጽጌረዳ “በሰላም ጉዳይ መንግስትም ጠንከር ያለ አቋም ሊይዝ ይገባል፤ ሆን ብለው ሰላምን ለማደፍረስ በሚሰሩ አካላት ላይ ከመደራደር ባለፈ ህጋዊ መንገድን ተከትሎ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ይላሉ፡፡
“ሰላም የማይፈልጉ አካላት ለራሳቸውም ለሃገርም ጠንቅ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በክፉ ድርጊታቸው ችግር የሚያደርሱት በሌላው ላይ ብቻ የሚመስላቸው የቂል አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ናቸው፤ ራሳቸው ጭምር ተጎጂ መሆናቸውን ስለማይገነዘቡት ከጥፋት ተግባራቸው ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ስለሆነም ጉዳቱን ከማድረሳቸው በፊት ቁጥጥር ሊደረግባቸውና ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሊደረግ ይገባል” ይላሉ ወይዘሮ ጽጌረዳ፡፡
ከአፋር ሰመራ ከተማ የመጡት ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ የ65 ዓመት አዛውንቱ አቶ አፍኪኤ ኡመር ደግሞ “ሁላችንም ሰላምን ልንወዳት ይገባል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ አምሮብን በአንድነትና በፍቅር የምንኖረው ሰላም ሲኖር ነው” የሚል አባታዊ ምክር አዘል አስተያየተቸውን ይለግሳሉ፡፡ አሁን በአገሪቱ የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥን ለማስቀጠልም ከሁሉም በላይ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት አዛውንቱ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም በያለበት የሰላም ዘብ ሊሆን ይገባል፤ ለዚህም እጅ ለእጅ ተያዞ በፍቅር ወደፊት መጓዝ ይገባል ይላሉ፡፡ “የሰላም እንቅፋቶችንም እንዳሉት “የእኩይ ሃሳባቸው ተባባሪ ባለመሆን ምኞታቸው እንዳይሳካ ማድረግ ይቻላል” በማለት በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ አባባል አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 1/2011
ይበል ካሳ