የችግሮቻችን መሻገሪያ ብቸኛው አማራጭ

ኢትዮጵያ የነጻነትና የአይበገሬነት ተምሳሌት የመሆኗን ያህል፤ የጦርነት፣ የርሃብ፣ እርዛት፣ የመፈናቀልና የጥላቻ ትርክትን የያዙ ታሪኮችም ባለቤት ሆናም ትገለጻለች:: አብዛኛውን የኢትዮጵያን የውስጥ ታሪክ መለስ ብሎ ላየውም የውስጥ አለመግባባት፤ ግጭትና ጦርነት የበዛበት ነው:: በጋራ ታሪኮቻችን ላይ መግባባት ካለመቻላችንም በላይ አለመግባባቶቻችን የግጭትና የጦርነት መንስኤ እስከ መሆን ደርሷል::

ይህ ደግሞ ሀገሪቱን በማያባራ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ከትቷታል፤ ለበርካታ ሰዋዊና ቁሳዊ ኪሳራም ዳርጓል:: ለሀገሪቱ ዕድገትም ፈተና ሆኗል:: በአንድ ሀገር ላይ ቆመን የጋራ ትርክት መገንባት አቅቶናል:: ባለፈው ታሪካችንም መግባባት ካለመቻላችንም በላይ መጪውንም ለመተንበይ አደጋች ሆኖብናል::

በተለይም የሀገሪቱ ፖለቲካ የሚመዘዘው ከኋላ ታሪካችን በመሆኑ፣ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል:: ቀደም ሲል የተሰሩ ጥፋቶችን እንደትምህርት በመውሰድ ለቀጣይ ጉዟችን ምቹ መደላድል መፍጠር ሲገባን፤ በማይቀየር ታሪክ ላይ ተጣብቀን ዛሬ እና ነጋችንን ስናበላሽ እንታያለን::

ከሁሉ የከፋው ደግሞ ያለፉት ታሪኮቻችን ላይ የሙጥኝ ብለን ስንነታረክ ዛሬ ጭምር አዲስ ቁስልና ጠበሳ እያስቀመጥን መጓዛችን ነው:: በእኛ ሀገር ብቻ የተፈጠረ በሚመስል መልኩ ከማይለውጥ ታሪክ ጋር ግብግብ ከገጠምን ዓመታት ተቆጠሩ:: ስለዚህም ከትናንት ታሪኮቻችንን ተምረን ነገን ብሩህ ለማድረግ ቆርጠን መነሳት ይጠበቅብናል::

ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በምክክርና በመግባባት ነው:: ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባትም እንደሀገር የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ከሁለት ዓመታት በላይ አስቆጥረናል:: በእነዚህ ጊዜያትም ምክክሩ የሚመራበትን አቅጣጫ ከመቀየስ ጀምሮ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮዎች የመቀመርና በአጀንዳ መረጣ ሂደት የሚሳተፉ ሰዎችን የመለየት ሥራዎች ተከናውነዋል::

በቀጣይም የምምክሩን አጀንዳዎች ከህብረተሰቡ የመቀበልና ምክክሩን ወደ መሬት የማውረድ ሥራዎች ይከናወናሉ:: እስካሁንም በአስር ክልሎች የተሳታፊና የተባባሪ አካላት ምርጫ አካሂዷል:: ስልጠና ሰጥቷል:: እነዚህ ስራዎች በተጠናቀቁባቸው ክልሎች ደግሞ አጀንዳ የመቅረጽ በተቀረጹት አጀንዳዎች ላይም ምክክር የማድረግ ሥራ ይከናወናል:: በሌላ በኩልም በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ ከግንቦት 21 እስከ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አጀንዳ ማሰባሰብ ይካሄዳል:: ይህ ሂደትም ለሌሎች ክልሎች መነሻ የሚሆንና የምክክር ሂደቱንም ውጤታማነት ከወዲሁ ለመተንበይ የሚያስችል ነው::

ከሰሞኑም መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይነት ምክክር የሚደረግባቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ለመወሰን የምክክር መድረክ አካሂደዋል:: የውይይቱም ዋና ዓላማ አጀንዳዎችን ለመለየትና የምክክር ሂደቱን ለመወሰን የተካሄደ ነበር:: ውይይቱ በመንግሥትና በፓርቲዎች መካከል የትብብር ባህልን ለማጠናከርና ጤናማ የፖለቲካ ፉክክርን ለመትከል የሚያስችል ነው።

መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን፣ የፖለቲካ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲደግፉ ምቹ ምህዳር እንደሚፈጥርም ታምኖበታል::ይህ በጎ ጅምር ነው:: ምክንያቱም ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል:: ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል:: አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፣ ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን፤ ውይይትና ምክክር ብቻ ነው::

ስለዚህም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል:: የስልጣኔ አንዱ መለኪያም ይኸው ነው:: በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው::

ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት:: የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው:: ጽንፍ ለጽንፍ ሆኖ ቃላት መወራወርና ይዋጣልን ማለት እንደሀገር ዋጋ አስከፍሎናል:: በዚህም መንገድ ለዘመናት ተጉዘን ያተረፍነው ድህነትን፣ ኋላቀርነትና ዕልቂትን ብቻ ነው::

ስለሆነም የታሪካችን አንዱ ክፋይ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን ጦርነትና ግጭትን ለማስወገድና የተረጋጋች፤ ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የመጣውን ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል::

በ2017 ዓ.ም በሀገራችን እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየትን ራዕዩ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የምክክር ኮሚሽኑ፤ ያለፉት የታሪክ ስብራቶችን ዘግተን በአዲስ መንፈስ ሀገራችንን እንድናሻግር ጥርጊያ መንገድ የሚቀይስ ነው::

ስለዚህም ምክክሩ የቀድሞ ችግሮቻችን፤ አሁን ያሉት ችግሮቻችን መፍቻና በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳያጋጥሙን የመፍትሔ አቅጣጫን የሚጠቁመን መድህን መሆኑን ማመን ይጠበቅብናል:: በሀገሪቱም መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመስረትም እርሾ ሆኖ እንደሚያግዝ እምነት መጣል አለብን::

ሀገራዊ ምክክሩ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ወሳኝ ሚና ይጫወታል:: ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሲችል ነው:: የምክክር ሂደቱ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ የሚጠይቅና ውጤታማነቱም በእያንዳንዳችን አበርክቶ ላይ የሚወሰን ነው::

እያንዳንዱ ዜጋ በቅድሚያ ሁሉም ነገር በንግግር እና በምክክር ይፈታል የሚል እምነት መጨበጥ ይጠበቅበታል:: ዘመናትን የተሻገሩ ጥያቄዎችም ሆኑ እነሱን ተከትለው የመጡ አለመግባባቶች በምክክር እና በውይይት እንደሚፈቱ እምነት መጨበጥ ይገባል::

የወሰንም ሆነ የማንነት ጥያቄ እንዲሁም ራስን በራስ ማስተዳደር እና የፍትሕ ጥያቄዎች በአጠቃላይ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ሊፈቱ የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም::

አሁን ያሉት አለመግባባቶች ተወግደው በፍቃደኝነት እና በመግባባት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው:: ሀገራዊ ምክክሩ ከዘመን ወደ ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታትና የመወያየትና የመነጋገር ባህልንም ለማዳበር ይረዳል:: በመወቃቀስ ላይ የሚያተኩረውንም የፖለቲካ ባህላችንንም ወደ መነጋገር፤ መተባበርና መደጋገፍ እንዲመጣ ያደርጋል::

ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል::ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል::አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፣ ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው::

ስለዚህም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል:: የስልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነው:: በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው:: ሀገራዊ ምክክሩን እንደ ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል::

እንደ ሕዝብም የታሪካችን አንዱ ክፋይ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን ጦርነትና ግጭትን ለማስወገድና የተረጋጋች፤ ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የመጣውን ዕድል መጠቀም ሀገርን የማሻገር አንዱ ተልኮ ነው::

ስለዚህም በየትኛውም ጫፍ ያለ ኢትዮጵያዊ በዚህ የምክክር ሂደት መሳተፍና የመፍትሔው አካል መሆን ሀገርን ማዳን መሆኑን ሊረዳ ይገባል::

አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን ማድረግ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ይፈጥራል:: ኢትዮጵያውያን በዘር፤ በሃይማኖት፤ በጾታና በአካባቢያዊ ርቀት ሳይገደቡ ስለሀገራቸው መጻኢ ዕድል ሊመክሩ ይገባል:: ሀገራዊ ምክክሩ ከሞላ ጎደል ሁሉም ሃሳብ አለኝ የሚል የኅብረተሰብ ክፍል ሃሳቡን ያለምንም ገደብ የሚሰጥበትና በመደማመጥ ጉዳዮች እልባት የሚያገኙበት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል::

የምክክር ኮሚሽኑም የተሰጠውን ጊዜ ሊያጠናቅቅ የቀረው 10 ወራት ብቻ ናቸው:: እነዚህ አስር ወራት ለኢትዮጵያውያን ወሳኝ ጊዜያት ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል:: ቀሪዎቹ አስር ወራት ከፍተኛ የሆነ ሥራ የሚሰራባቸው ጊዜያት ናቸው:: እስከ አሁን የነበረው ሥራ ቢያንስ በምክክሩ የሚሳተፉ ሰዎችን የመለየት ነው::

ይህ ሂደት በራሱ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ መውረድን የሚጠይቅ በመሆኑና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደፊት ማምጣት ስለነበረብን ረዘም ያለ ጊዜን ወስዷል:: ሌላው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደዚህ ምክክር ማምጣቱ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ስለቆየ ኮሚሽኑ ሰፊ ጊዜን ወስዶበታል::

ሌላው በሀገራችን ያለው የሰላም መደፍረስ ጉዳይ ሥራው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዳይሄድ እንቅፋት ሆኗል:: እስከ አሁን በትግራይ ሥራው አልተከናወነም፤ በአማራም በሚፈለገው ልክ አልተሠራም:: በመሆኑም በቀሩት ጊዜያት መሰል ችግሮችን መልክ አስይዞ በፍጥነት ሁሉም ክልሎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ምክክር የሚመጡበትን ሁኔታ ከፈጠርን አስር ወራት ቀሪውን ሥራ ለማከናወን ያንሳል የሚባል ጊዜ አይደለም::

ጊዜ ሊወስድ የሚችለው አማራ ክልል ያለው ችግር ነው:: ነገር ግን አሁን ሥራው ተጀምሯል:: ትግራይ ክልልም እንደዚሁ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤ በመሆኑም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ መልክ ማስያዝ ከተቻለ በቀሪዎቹ አስር ወራት በጣም ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላል:: በዋነኝነት ግን ችግሮቻችን በሙሉ የሚፈቱት በምክክርና በውይይት ብቻ ነው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል::

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው:: ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርአያነት ሲጠቀስ የኖረ ሕዝብ ነው:: ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው:: ከዚህም አልፎ የውጭ ሀገር ዜጎች ምንም አይነት የባዳነት ስሜት ሳይሰማቸው እንደሀገራቸው እንዲኖሩ የሚፈቅድ ድንቅ ዕሴቶች ያለው ሕዝብ ነው::

ይህ አኩሪ እሴት በየዘመኑ እየተሸረሸረ ቢመጣም፣ ጨርሶውኑ ጠፍቷል ማለት አይቻልም:: በመሆኑም ኢትዮጵያዊ እሴቶች ሙሉ ለሙሉ ተሸርሽረው ከመጥፋታቸው በፊት እንደገና መመካከር ይጠበቅብናል:: ምክንያቱም ከጥንት እስከ ዛሬ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶች ከሀገር ውስጥ ባንዳ አሸባሪዎች ጋር ተባብረው ኢትዮጵያን ለመበታተን መሄድ እስከሚችሉት ድረስ ተጉዘዋል::

ለዘመናት አብሮ የኖረው ሕዝብን በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል እርስ በእራሱ እንዳይተማመንና በሂደትም በሚኖሩ ግጭቶች ኢትዮጵያ እየተዳከመች እንድትሄድ ያለማሰለስ ሠርተዋል:: ለሀገሪቱ መድከምና በሂደትም መፈራረስ አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚሉትን ኃይል በማደራጀት፤ በማስታጠቅና በማሰልጠን ታሪካዊ ጠላትነታቸውን በገሃድ ሲያስመሰክሩ ኖረዋል:: በየቦታው ነፍጥ የሚያነሱ ቡድኖችን የልብ ልብ ሰጥተው፤ አቅፈውና ደግፈው አንዳንዶችንም ለስልጣን አብቅተው ኢትዮጵያ በጊዜ ሂደት እንድትዳከምና እንድትፈራርስ በረዥሙ አልመው ሠርተዋል::

እነዚህ አካላት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሆን ብለው ሲሠሩ የነበሩት ኋላ ታሪክን እንደ አንድ የማጋጫ ስልት መጠቀምን ነበር:: እገሌ በእገሌ ተበድሏል፤ እገሌ እገሌን ለማጥፋት ጦር ሰብቋል፤ በርካቶችን ጨርሷል በሚል ኢትዮጵያ ከመጪው ጊዜ ይልቅ በኋላ ታሪካቸው ላይ ብቻ የሙጥኝ ብለው እንዲቀሩና ቋሚ የግጭት ምንጭ ሆኖ ሲናቆሩ እንዲቀሩ ያለመታከት ሠርተዋል::

ዛሬ ግን ሀገራዊ ምክክሩን ከችግሮቻችን መሻገሪያ ብቸኛው አማራጭ አድርገን እየተጓዝን ሲሆን፤ በዚህም በታሪክ አጋጣሚ የተፈጸሙ ስህተቶችን እንደትምህርት በመውሰድ፤ በምክክር ሀገራችንን ለማጽናት ተነስተናል:: ዳግም ሀገራችንን የበለጸገችና ገናና ለማድረግ ወደ ምክክር ገብተናል:: ይህም ይሳካል::

እስማኤል አረቦ

 አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You