‹‹ኢትዮጵያ እንደምን ሠለጠነች?››

የታሪክ መታጠፊያዎች በግለሰቦች የሚጀመሩ ናቸው:: ዘመን ተሻጋሪ ቅርሶች ሺህ ዘመናትን የሚመሰክሩት በግለሰቦች ታስበው፣ በብዙዎች ተፈጽመው ነው:: እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች የአንዲት ሀገር የሥልጣኔ መለያ ይሆናሉ ማለት ነው:: ለምሳሌ፤ የአክሱም ዘመነ መንግሥት እያልን እንጠራለን፤ የአክሱም ዘመን የሥልጣኔ ምልክት ነው:: ምክንያቱም የአክሱም ሐውልት ቆሞ እየመሰከረ ነው:: የላሊበላ አንድ ወጥ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት እና የፋሲል ግንብ የዘመናት ምስክሮች ናቸው:: በዓለም አቀፉ የሚዲያ ተቋም ቢቢሲ የሀገሮች ታሪክ ላይ ኢትዮጵያ በእነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ትጠቀሳለች::

በእንዲህ አይነት ሥልጣኔዎች የምትታወቀው ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ዘመን በኋላ የፖለቲካ ውጥረቶች የበዙባት ሆናለች:: ይባስ ብሎ ደግሞ ከ1966 ዓ.ም በኋላ በተፈጠረው አብዮት የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተባብሰው በዓይን የሚታዩ ነገሮች እንዳይኖሩ አድርጓል:: በዓይን የሚታዩ ማራኪ ነገሮች ከመሥራት ይልቅ የፖለቲካ ግርግሮችና የውስጥ ጦርነቶች የበለጠ ቦታ ያዙ:: በዚህም ምክንያት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የራሱን ሀገር የሚራገም ሆነ:: ባለፈበት ቦታ ሁሉ ንፁህ አካባቢ ስለማያገኝ ‹‹አይ! ኢትዮጵያ!›› እያለ ሀገሩን ያማርራል:: ልክ የሌላ ሀገር ዜጋ የሆነ ይመስል አካባቢው አምሮና ተውቦ ማየት የሚፈልገው ሌሎች በሚሠሩት ነው::

ይህ ችግር ላለፉት ብዙ ዓመታት ሲንከባለል ቆይቷል:: አሁን ግን ባለራዕይ፣ አርቆ አስተዋይ እና ሥልጣኔ የገባቸው መሪዎችን አግኝቷል:: በውጭ ሀገር ያዩትን ሥልጣኔ ‹‹እገሌ ሀገር የሠለጠነችው እንዲህ ነው…›› እያሉ ተረት ከመናገር ይልቅ ራስን እንዴት ማሠልጠን እንደሚቻል እያሳዩን ነው:: ቀጣዩ ትውልድ ‹‹ኢትዮጵያ እንደምን ሠለጠነች?›› ብሎ የሚጠይቅ ይሆናል::

የአራት ኪሎና አካባቢዋ የኮሪደር ልማት ከተጀመረ ገና ሦስት ወር እንኳን አልሞላውም:: አሁን በዚያ አካባቢ የሚያልፉ ሰዎች ‹‹ሌላ ሀገር ያለሁ መሰለኝ!›› ሲባባሉ የሰማሁት በጆሮዬ ነው:: እነዚህ ሰዎች በቴሌቭዥንና በፊልም የሚያዩትን ወይም አውሮፓና አሜሪካ ሄደው የመጡ ሰዎች ሲያወሩ የሰሙትን ወይም ራሳቸው ሄደው ያዩትን የሠለጠነ ሀገር ማራኪ ነገር ማየት ቻሉ ማለት ነው:: ሌሎች አካባቢዎችንም እንደዚህ ማድረግ እንደሚቻል ሰርቶ ማሳያ (ሞዴል) አገኙ ማለት ነው:: ኢትዮጵያን የሠለጠኑ ናቸው እንደሚባሉት አውሮፓና አሜሪካ ማድረግ እንደሚቻል አረጋገጡ ማለት ነው::

አንድ ግን ግርም የሚለኝ ነገር አለ:: መንግሥትን እንቃወማለን የሚሉ አካላት አሥር ጊዜ ምሳሌ የሚጠቅሱት የሠለጠኑ ሀገራትን የአካባቢ አያያዝ ነው:: የአውሮፓና አሜሪካ ሀገራትን እየጠቀሱ ንጽህናቸውን ይናገራሉ:: አዲስ አበባን ‹‹የገማች ናት፣ የቆሸሸች ናት፣ በዚህ መንግሥት እየተመራች….›› ይላሉ:: እንዲህ ሲሠራ ግን አያመሰግኑም:: ጭራሽ ይባስ ብሎ መሠራቱን የሚቃወሙም አሉ:: እነዚህ አካላት ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ ከሀገር ዳር ድንበርና ከውጭ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ቢሰጡ ጥሩ ነበር፤ ሀገር ውስጥ የሚሠራ፣ ጥቅም ብቻ እንጂ ምንም ጉዳት የሌለውን ነገር ከተቃወሙ የምርም የመቃወም ሱስ ብቻ ነው:: ደግነቱ መንግሥት እንዲህ አይነቶችን ባለመስማት አዲስ አበባን የሥልጥንና ተምሳሌት እያደረጋት ነው::

ከዚህ በኋላ ‹‹ኢትዮጵያ እንደምን ሠለጠነች?›› የሚል ትርክት ይፈጠራል:: ከምን አይነት ኋላቀር አኗኗር ወደ እንዲህ አይነት የሠለጠነ አኗኗር እንደተቀየረች ታሪክ ይናገራል:: ‹‹እነሆ በዚያን ጊዜ እገሌ የሚባል መሪ ነበር፣ እገሌ የምትባል የአዲስ አበባ ከንቲባ ነበረች…›› እየተባለ ይነገራል:: በእነዚህ የሠለጠኑ መሪዎች አፍላቂነትና አስፈፃሚነት ይህ ትውልድ የዚህ ሥልጡን ዐሻራ ባለቤት ይሆናል ማለት ነው::

ይህ እውን ይሆን ዘንድ ግን ሁሉም ተባባሪ ሊሆን ይገባል:: ሀገር የሚገነባው በጥቂቶች አሳቢነት ቢሆንም የሚሳካው ግን የሁሉም ትብብር ሲኖርበት ነው:: ለዚህ ደግሞ እገዛዎች ብዙ አይነት ናቸው:: ለምሳሌ፤ ጽዱ ኢትዮጵያ ለመፍጠር ባለፉት ሳምንታት የገንዘብ መዋጮ ዘመቻ ነበር:: በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ በ100 ብር እንኳን ዐሻራን ማስመቀጥ ይቻላል ማለት ነው:: ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ እንደመሳተፍ ታሪካዊ ዕድል የለም::

ሌላው እና ዋናው እገዛ ግን የሃሳብ ሞራል መስጠት ነው:: ማድነቅን ልማድ ማድረግ ነው:: ሥራዎች እስከሚጠናቀቁ ድረስ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ:: መንገዶች ይዘጋጋሉ፣ አቧራ እና ጭቃ በጣም ሊያስቸግር ይችላል፤ ብዙ ቦታ መንገዶች ስለሚዘጉ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች በእግር መሄድ ያጋጥማል፣ በመንገዶች መዘጋት ምክንያት ትራንስፖርት ላይኖር ይችላል… የመሳሰሉት ችግሮች ያጋጥማሉ:: እነዚህ ችግሮች ሲያጋጥሙ ከማማረር ይልቅ በአርቆ አስተዋይነት የነገውን ማሰብ ብልህነት ይሆናል:: ለምሳሌ፤ አራት ኪሎ ከዛሬ ሁለት ወር በፊት እና ዛሬ ሌላ ሀገር እና ሌላ ሀገር እንደማለት ነው:: ከዛሬ ሁለት ወር በፊት አካባቢው ሁሉ ተቆፍሮ ተቆፍሮ መሻገሪያ እስከሚያስቸግር ድረስ ችግር ነበር፣ በአካባቢው ውሃ እና መብራት እየተቋረጠ ለቀናት ችግሮች ነበሩ:: የዛሬዋ አራት ኪሎ ግን የራስን ሀገር በቅናት እና በስስት ለማየት የምታስገድድ ናት:: ዝናብ ሲዘንብ መንገደኛ የሚተላለፈው ቆሞ ወረፋ እየተጠባበቀ ነበር:: መቆሙ ብቻ አልነበረም ችግሩ፤ በአስፋልት ላይ የሚያልፍ መኪና ውሃ ረጭቶበት ይሄዳል፤ ምክንያቱም አስፋልቱ ውሃ የሚያጠራቅም ነበር:: አሁን ግን የእግረኛ መንገዱ ከመኪና ወርዶ በእግር ለመሄድ የሚያስመኝ ነው:: አሁን ግን የሚተላለፉ ሰዎች እንኳን ወረፋ ሊጠባበቁ ላይተያዩ ሁሉ ይችላሉ:: አስፋልቱ እንኳን ውሃ ሊያጠራቅም ዝናብ መዝነቡ የሚታየው ከሰማይ ሲወርድ ብቻ ነው:: ሁለት ወር እነዚያን ችግሮች የተቋቋመ የአራት ኪሎና አካባቢዋ ነዋሪ አሁን ሌሎች አካባቢዎችን የሚያስቀና ሆነ ማለት ነው::

አራት ኪሎና አካባቢዋ ውብ መሆኗ አዲስ አበባ ውብ ሆነች ማለት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፤ መልሱ ግን አራት ኪሎና ፒያሳ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢዎችም እየተሠሩ ነው:: በሂደት ሁሉም ይሠራሉ ማለት ነው:: አዲስ አበባ ሥልጡን እና ውብ ሆነች ማለት ኢትዮጵያ ሠለጠነች ማለት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ በጣም ተገቢ ጥያቄ ነው:: ሁለት ነገር ግን ልብ እንበል:: አንደኛ፤ የዓለም መሪዎችና ዲፕሎማት ኢትዮጵያን የሚያውቋት መጀመሪያ በአዲስ አበባ ነው:: የሠለጠኑ የዓለም ሀገራትን በዋናነት የምናውቃቸው በዋና ከተሞቻቸው ነው:: የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ስለሆነችና የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖሪያ ስለሆነች ዋናዋ ኢትዮጵያ ናት ማለት ነው::

ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት ግን፤ ሁሉንም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደ አዲስ አበባ ለማድረግ አርዓያ ይሆናል ማለት ነው:: ስለዚህ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሆነ እያሉ ከማማረር ሌሎች አካባቢዎችም እንደ አዲስ አበባ እንዲሆኑ መረባረብ ያስፈልጋል ማለት ነው:: ይህ ትውልድ ይህን ሥራ ከሠራ ‹‹ኢትዮጵያ እንደምን ሰለጠነች?›› የሚል ትርክት አካል ይሆናል::

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You