የዲጂታል ቴክኖሎጂ ቱሩፋቶች፣ ስጋቶችና መውጫዎች

አሁን ባለንበት ‹‹ዘመነ ዲጂታላይዜሽን›› የበለጸጉ ሀገራት ዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ከፍተኛ ሀብት እያከማቹበት ይገኛሉ። ዲጂታል ዘርፍ ከፍተኛ ሀብት እየተንቀሳቀሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከዚህ ሀብት አለመጠቀምና ከዲጂላይዜሽን እሳቤ ውጭ መሆን የማይታሰብና ከዓለም ወደኋላ ለመቅረት በራስ እንደ መፍረድም ሊቆጠር ይችላል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ የሚባሉት ሀገራት ደግሞ ይህን የዲጂታላይዜሽን ዓለም በመቀላቀል ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ዲጂታላይዜሽንን መተግበር ብቻም ሳይሆን በዘርፉ በፍጥነት መጓዝ የሚያስችላቸውን አካሄድ መከተል ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያም ዲጂታላይዜሽንን ለመቀላቀል ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ቀረጻ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች። ባለፈው ወር የዲጂታል ኢትዮጵያን አስፈላጊነት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) እንደተናገሩት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ እንዲኖርና በሁሉም ተቋማት ተሰናስሎ እንዲመራ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት በዘርፉ እንደ ሀገር ከተቆየበት ችግር ለመወጣት ወጣ ያለ አስተሳሰብና አሰራር በመከተል ዲጂታል ኢኮኖሚን ተግባራዊ ማድረግ በማስፈለጉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ አሁን ያለው የዲጂታል ዘመን ዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባትን ይጠይቃል። ከዓለም አሥር ሀብታም ኩባንያዎች ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ የያዙት በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የሚሰሩ ናቸው። ከዚህ የሚበልጡት ደግሞ ሰባተኛ፣ ስምንተኛ፣ ዘጠነኛና አስረኛ ደረጃ የያዙትም ተራ ኩባንያዎች አይደሉም። ለምሳሌ እንደ ቴስላ፣ ቪዛ ካርድ እና ትልቁ የሳውድ አረቢያ የነዳጅ ኩባንያን ጨምሮ ከስድስቱ በታች ባሉ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች ያከማቹት ሀብት ተደምሮ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የያዙት ሁለቱ ኩባንያዎች ያከማቹትን ሀብት አያህልም። ይህ የሚያሳየው አብዛኛው ሀብት ያለው በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ መሆኑን ነው።

ለዚህም መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባትን የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ(አይሲቲ) ዘርፍ አንድ ምሰሶ አድርጎ ወስዶ ዲጂታል 2025 ስትራቴጂም ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ዲጂታል ኢኮኖሚ አካታች ከባቢን መፍጠርን ይጠይቃል። በመሆኑም በዚህ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የግሉ ዘርፍ በዘርፉ እንዲሳተፍ፣ መነሻ የፈጠራ ሃሳቦች /ስታርት አፖችን/ እንዲስፋፉ ማድረግ ያስፈልጋል።

ባለፈው ሳምንትም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በሳይንስ ሙዚየም ባዘጋጀው ‹‹ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ 2024›› የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሥራ የእስካሁኑ ሂደት ፈተናዎች እና ቀጣይ እቅዶች ላይ የመከረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ካውንስልን በበላይነት የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተገኝተዋል። ‹‹ቴክኖሎጂ ለሀገር ልማት የሚያመጣው ቱሩፋት እና የዲጂታል ኢኮኖሚን በዲጂታል ቴክኖሎጂ » በሚል ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሃሳብ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። በሁሉም ዘርፎች ላይ የቴክኖሎጂ አስፈላጊነት እጅግ ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል። ከዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር እጅግ የተሳሰሩ የቴክኖሎጂ አማራጮች እንዳሉ ሆነው አጠቃላይ ሀገራዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ይህም የቴክኖሎጂ ጥገኛ የሆኑ ብዙ ኢኮኖሚዎች እንዲኖሩ አድርጓል። በዲጂታል ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ወጣቶች ራሳቸውን እያሳደጉ የሥራ እድል እንዲፈጥሩ አስችሏል።

‹‹ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ማሳደግ የመንግሥትን አገልግሎት ለማሳለጥ፣ ማህበራዊ ተሳትፎ እና የሥራ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና አለው›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለታዳጊ ሀገሮች ኢኮኖሚን ለመገንባትና ከድህነት ለመውጣት ትልቅ ኢኮኖሚ አመንጪ በመሆን ሊያገለግል እንደሚችል አመልክተዋል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ትልቁ ፈተና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ግልጸኝነት የጎደለው፣ ተደራሽ ያልሆነና ብዙ ችግሮች ያሉበት እንደ መሆኑ፣ ታዳጊ ሀገራት ቴክኖሎጂን እንደ ትልቅ መሳሪያ የሚጠቀሙት አገልግሎታቸውን ለማቀላጠፍ ሲሉ ነው ብለዋል።

መንግሥት የሚሰራቸው ሪፎርሞች በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሊሆኑ ይገባል። ይህም ለማህበራዊ ተሳትፎና ለሥራ እድል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ‹‹በሳይንስ ሙዚየም እንደጎበኘነው በኤግዚቢሽኑ የቀረቡት ኩባንያዎች በሁለትና ሦስት ዓመት ጊዜ በቀላሉ ከሶስት ሺ እስከ 5ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ ሲናገሩ ሰምተናል›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ዘርፋ በርካታ ወጣቶችን የሚያሳተፍ ስለመሆኑ ማየት ያስችላል። በተጨማሪም ማህበራዊ አገልግሎቶችን ያሳልጣል፤ ተደራሽነትም ያረጋግጣል፤ ከዚህ ባሻገርም የሥራ እድልን ይፈጥራል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ካሏት አስቻይ ሁኔታዎች መካከል አንደኛው በርካታ የሕዝብ ብዛት ያላትና ከዚህ ሕዝብም አብዛኛው ወጣት መሆኑ ነው ። ወጣቱ ደግሞ ለቴክኖሎጂ ያለው መሰጠት እጅግ ከፍተኛ ነው። ሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከአምስቱ (ከግብርና፣ ከማኑፋክቸሪንግ፣ ከቱሪዝም እና ከማዕድን) ዘርፎች ቀጥሎ ኢንፎርሜሽን፣ ኮሙዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) አንዱ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ነው። ይህ በመሆኑ ኢኮኖሚን በማመንጨት የመንግሥት አገልግሎትን በማዘመን፣ ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠር ያስችላል።

ሦስተኛው የመሠረተ ልማት እድገት ሲሆን መሠረተ ልማት በዳታ ተደራሽነትም ሆነ ከሌሎች አንጻር ሲታይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። አሁን መንግሥት በቴሌኮም አገልግሎት በኩል የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ በሰጠው እድል መሠረት እንደ ሳፍሪኮም ዓይነት ኦፕሬተሮች ወደ ሀገር ገብተው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ተጨማሪ ኦፕሬተሮች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ለማድረግም እየተሰራ ነው።

ከመሠረተ ልማት አኳያም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የማልማት ሥራውን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘርፉ ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል። ከእዚህ አንጻር ሲታይ ዲጂታል ኢትዮጵያን በማሳደግና የኢኮኖሚ ምንጭ በማድረግ፣ የአገልግሎቶችን ማቀላጠፍ እንደሚቻል አስታውቀዋል። ፡

መንግሥት ዲጂታል ኢትዮጵያ የ2025 ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም በ2025 በአጠቃላይ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዲጂታል ቴክኖሎጂን እያሳደገች ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ሀገሪቱን በዲጂታል ሽግግር በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱም በመድረኩ ተጠቅሷል። ስለካውንስሉ አስፈላጊነት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ እንዳሉት፤ ኮውንስሉ የተቋቋመበት ዓላማ መንግሥት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የማሳደግ፣ የማልማት፣ የመጣውን እድል የመጠቀም ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ሲደረግ ቆይቷል። ኮውንስሉ በተለይ አይሲቲ ዘርፍ ውስጥ የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ተቋማትን ኃላፊነትና ተግባር የሚተካ አይደለም። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እነዚህን ለማስተባባር እየሰራ ነው። መንግሥት የከዚህ በፊት አካሄዶችን ለየት ባለ መልኩ ለማየት እንዲያስችል ኮውንስሉ በዋናነት እንዲቋቋም ማስፈልጉን አመላክተዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ኮውንስሉ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች ለመመለስ ያስችላል። የመጀመሪያው ቅንጅታዊ አሠራርን ማሳለጥ ነው፤ በግልና በመንግሥት ዘርፍ መካከል እንዲሁም የመንግሥት ተቋማት እርስ በርስ እንዲናበቡ በማስቻል ቅንጅታዊ አሰራሩን የበለጠ ማስፋትና ሀገሪቱ ከዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ተጠቃሚ የምትሆንበትን ሁኔታ ለማሳደግ የሚያስችል ዲጂታል አሠራርን ለማጎልበት ነው።

ሁለተኛው የዲጂታል ትራንስፎሜሽን ሥራን ማፋጠን ያስፈለገበት ምክንያት በራስ ለማልማት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍና የሚያሳልጥ ሥራን ለመሥራት ነው። በግሉ ሆነ በመንግሥት ዘርፉ የሚሰሩ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ሌሎች ሥራዎችም ለሀገር የሚጠቅሙ ናቸው ወይ፣ የትኛው መቅደም አለበት፣ በቀጣይ እንዴት ማደግ ይችላሉ በሚሉት ላይ አትኩሮ ይሰራል።

ሦስተኛው ወጪ ቆጣቢ አሠራሮችን መከተል ነው። ኮውንስሉ ከመቋቋሙ በፊት ሥራው በግብረ ኃይል የሚመራ ስለነበር ግብረ ኃይሉ ባደረገው ጥናት ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የመንግሥት ግዥ ብክነት መታየቱና ብዙ ክፍተቶች እንዳሉበት ተመላክቷል። ወጪ ቆጣቢ ሲባል የሚገነቡ ሲስተሞችን በፍጥነት በመለየት መገንባት ነው። በሌላ በኩል ያሉትን ሲሰተሞች ጥቅም ላይ ማዋል ሲሆን፤ የማያስፈልጉትን ማስወጣትንም ያመለክታል። ለአብነት ዳታ ቤዝን ብንመለከት በመንግሥት ተቋማትና በግል ዘርፉ በጣም በርካታ ዳታ ቤዞች ተገንበተዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ እነዚህን ወደ ጥቅም የማሸጋገር ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን እድገት ውስጥ የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ የብዙ ሀገሮች ተሞክሮ እንደሚያመለክት አስታውቀዋል።

እስካሁን መንግሥት ሲከተለው በቆየው ስትራቴጂ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ኢንቪስት እንዲያደርግ የተጀመሩ ሥራዎች እንደነበሩ አስታውሰው፣ አሁን ባለው ዲጂታላይዜሽን ሥራ ደግሞ የግሉ ዘርፍ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የመሪነት ሚና መጫወት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ይህ ሲባል፤ የመንግሥት ደጋፍ አያስፈልግም ማለት እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ የግሉ ዘርፍ መንግሥት እንዲደግፈው ብቻ ሳይሆን የመንግሥት አገልግሎቶችን በማዘመን፣ አጠቃላይ የዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሥራ መኖር እንዳለበት ይገልጻሉ። የግሉ ዘርፍ በዲጂታላይዜሽንና ትራንስፎርሜሽን ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በመንግሥት በኩል የዲጂታል ዘርፉ ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ብቻ ሳይሆን ገቢንም የሚያመንጭ ነው የሚል እይታ እንዳለ ገልጸው ፤ በዚህ ምክንያት የግሉ ዘርፍ በካውንስሉ ውስጥ እንዲሳተፍ በማድረግ ከመንግሥት ጋር በጥምረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

‹‹ይህም የዲጂታል ዘርፉ ለውጥ እያመጣ ስለመሆኑ ማሳያ ነው። በኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ለውጥ እያሳየ ነው። በኛ ሀገር ደግሞ ስናይ በርካታ በግላቸው የሚንቀሳቀሱ እና ሶፍትዌሮችን የሚያለሙ ተቋማት እየተፈጠሩ ነው›› ሲሉም ያብራራሉ። በዚህ ውስጥ የመንግሥትንም ሆነ የግል ተቋማትን የጋራ ጥምረት ለማሳደግም ሆነ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን በጋራ ሰርቶ ለመፍታት እንደሚያስችል ይገልጻሉ። በግሉና በመንግሥት ትስስር ላይ በሁለቱም በኩል ትልቅ ለውጥ እንዳለ ጠቅሰው፤ ይህን በመጠቀም ዲጂታል ቴክኖሎጂን ማሳለጥ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለኢኮኖሚ እድገቱ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንደመሆኑ ሁሉ የሚያስከትላቸው ተግዳሮቶችም እንዳሉት ይታወቃል። የዚህ አንዱ ምክንያት የቅንጅት ክፍተት መሆኑን ጠቅሰው፣ የግል ዘርፉ እርስበርስ፣ የመንግሥት ተቋማት ከግሉ ዘርፍ ጋር ባለው መስተጋብር ክፍተቶች እንደሚታዩ ተናግረዋል። ይህ ችግር በመፍታት በጎ ፉክክሮችና ትብብሮች እንዲጎሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ሁለተኛው ችግር በቂ መሠረተ ልማት አለመኖር መሆኑን አመልክተዋል። በመሠረተ ልማት በኩል ለውጦችና መሻሻሎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ መሠረተ ልማት የመጠበቅ ክፍተቶች እንዳሉም አመላክተዋል፤ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ክፍፍልም እንደቀላል ክፍተት የሚታይ ስላልሆነ ክፍተቶች መፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል።

ሦስተኛው ቁልፍ ችግር የሳይበር ደህንነት ችግር መሆኑንም አስታውቀዋል። ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያመጣውን ቴክኖሎጂ መጠቀም ስንጀምር ለተለያዩ ጥቃቶች የመጋለጥ እድል እየጨመረ ይመጣል ሲሉ ጠቅሰው፣ ለእዚህም ንቃተ ህሊና በማስፋት ረገድ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You