ከመጠላለፍ ፖለቲካችን ወደ መነጋገሪያ መድረካችን እንመለስ

የዛሬ ጹሑፌን ፈር ማስያዣ ይሆነኝ ዘንድ በአንድ ገጠመኜ ለመንደርደር ወደድኩ። ከዓመታት በፊት ተማሪ በነበርንበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ(6 ኪሎ ዋናው ግቢ) በተለያዩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የሚናጥበት ቀውጢ ወቅት ነበር።

ታዲያ የዛን ቀውጢ ሰሞን የሥነ-ተግባቦት /Com­munication Skill/ መምህራችን የነበሩት ስምዖን ገ/ መድኅን (ዶ/ር) በአንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜያችን፤ “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!” ተብሎ የተጀመረና እርሳቸውም በተማሪነት ዘመናቸው አባል የነበሩበት የዛን ጊዜው የለውጥ ጥያቄ የነጎደበትን የእርስ በርስ መጠፋፋትና የስቀለው ፖለቲካችን ባህልን ከወቅቱ የግቢያችን ነውጥ ጋር እያነጻጸሩ አስገራሚም፤ አሳዛኝም የሆነ አንድ ገጠመኛቸውን እንዲህ አወጉን።

“መሬት ላራሹ፤ ዲሞክራሲያዊ መብት ያለ ገደብ፤ የሃይማኖት እኩልነት… ወዘተ.” የሚሉ ጥያቄዎችን በማቀንቀን የሚታወቁት የዛን ጊዜው የቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በልደት አዳራሽ ተሰብስበው መፈክር በሚያሰሙበትና በማርኪሲስት ርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ በሚሟገቱበት አንድ ወቅት ላይ እንዲህ ሆነ።

በ6 ኪሎው የልደት አዳራሽ እጅግ በተሟሟቀ አብዮታዊ ስሜት፤ በሀገራዊ ወኔ በሚካሄድ ስብሰባ ወቅት የዚህ ስብሰባ ተሳታፊ የሆነ አንድ ተማሪ አስተያየት ለመስጠት ፈልጎ እጁን ያወጣል፤ ተማሪው ይፈቀድለትና ወደ መድረክ ይወጣል፤ አስተያየቱንም እንዲህ ሲል ይጀምራል፤

“… ወገኖቼ እያነሳናቸው ያሉት የለውጥ፤ የፍትሕ ያለ ገደብ እና የዲሞክራሲ መብት ይከበር ጥያቄዎቻችን ተገቢ ናቸው፤ ይሁን እንጂ ነገሥታት/መንግሥታት የሚሾሙትም ሆነ የሚወርዱት በአምላክ ፈቃድ ነውና ምናልባት ሳናውቀው ከፈጣሪ ስንጣላ እንዳንገኝ…” ሲል፣ የስብሰባው ተሳታፊ ተማሪዎች ንግግሩን አላስጨረሱትም በአንድ ድምፅ ሆነው፤

“ይሰቀል! ስቀለው! ስቀለው!” በሚል መብረቃዊ ጩኸትና መፈክር አዳራሹ ተናወጠ፤ ያ ምስኪን ተማሪም በጓደኞቹ እየተገፈታተረ ከመድረኩ እንዲወርድ ሆነ።” በማለት መምህራችን ዶ/ር ስምዖን የዛን ጊዜ የአብዮት ዘመን ትዝታቸውን በቁጭትና በሀዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ነበር ያወጉን።

በዛን ዘመን የሶሻሊስት አራማጆች ዘንድ፤ “Reli­gion is an Opium/ሃይማኖት ሕዝብን የማደንዘዣ ዕፅ ነው!” የሚለውን ፀረ-ሃይማኖት የሆነ አስተምህሮአቸውን ያስታውሷል። ይህን የዶ/ር ስምዖንን ትዝታን እንደያዝን ዛሬም ድረስ ‘ከስቀለው፤ ከመጠፋፋት ፖለቲካ’ ባህል መላቀቅ ስለምን ተሳነን በሚለው ሃሳብ ላይ አብረን ጥቂት እንቆዝም እስቲ።

ለሺህ ዘመናት የዘለቀ የሃይማኖት አስተምህሮ ውስጥ ያለፍን፤ ገናና ሥልጣኔ፣ የገዘፈ ታሪክና የዳበረ ባህል አለን የምንል ማህበረሰቦች ምን ብንሆን ነው – የሃይማኖት አባትን ያህል ሰው በገመድ አንቀን ለመግደል የደፈርነው?! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባትና መንፈሳዊ መሪ የነበሩትን የሰማዕቱን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የጭካኔ አገዳደልን ያስታውሷል።

በተመሳሳይም የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ፕሬዚዳንት የነበሩት ቄስ ጉዲና ቱምሳም የኦነግ አባልና ደጋፊ ነዎት በሚል ነበር በጭካኔ በጥይት ተደብድበው የተገደሉት። የአሁኑ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አባትና መንፈሳዊ መሪ የሆኑት ካርዲናል ብፁዕ ብርሃነ ኢየሱስ እና ፓትርያርክ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም በለውጥ/በአብዮት ስም ነበር ለሰባት ዓመታት በወኅኒ በግፍ ተግዘው እንዲማቅቁ የተደረጉት።

“የአፍሪካ አባት” በሚል ጥቁሩ ዓለም የሚያደንቃቸው የአዛውንቱ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴና የ60ዎቹ ኢትዮጵያውያን ሚኒስትሮች፣ ሹማምንትና አርበኞች የጅምላ ጭፍጨፋንም ልብ ይሏል። ይህን ከኢትዮጵያ አልፎ መላውን ዓለም በድንጋጤ ጭው ያደረገውን በለውጥ ስም የተወሰደ አብዮታዊ ርምጃን/የጅምላ ጭፍጨፋን አስመልክቶ በወቅቱም፤ እንደ ቢቢሲ ያሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን፤ “What Happened to the Bloodless

Ethiopian Revolution?!” ሲሉ ድንጋጤ የታከለበትን ዜናን አከታትለው ነበር።

ፖለቲካችንን ክፉኛ የተጣባው ይሄ የይሰቀልና የመጠፋፋት ባህል ዛሬም አብሮን ዘልቋል። ይሄ ደግሞ አንድም የባህላችን፣ ሁለተኛም የማህበራዊ ስሪታችን ውጤት ሊሆን ይችላል። በየስነቃል ስንኞቻችን የምንመለከተውም ይሄንን የመገፋፋት፤ የመበቃቀልና የመጠፋፋት ተረክ ሲሆን፤ ዛሬም ይሄንኑ ብሂል ይዘው በቤትም፣ በአደባባይም፣ በአውደ ምህረትም የሚያስተጋቡ ስለመኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

ለአብነትም፡-

እነርሱ ላም ሲያርዱ፣ እኛም ጥጃ እንረድ፣

ቢሆንም ባይሆንም፣ እጃችን ደም ይልመድ።

*****

ደመናው ሲደምን ይወረዛል ገደል፣

ይዘገያል እንጂ መች ይረሳል በደል።

****

ላዩ ጨረቃ፤ ታቹ ጨረቃ፣

“ደምላሽ” አለችው እናቱም አውቃ።

የሚሉ ቂምን ያረገዙ፤ የበቀልና ጦር ስሜት ቀስቃሽ ሥነ-ቃሎች ያሉን ኩሩ ሕዝብ ነን። በገደምዳሜውም ቢሆን ከዕርቀ-ሰላም ይልቅ ለበቀልና ለእርስ በርስ እልቂት/ መጠፋፋት የቀረብን/የመረጥን ማኅበረሰብ ነን የሚለውን የመከራከሪያ ሃሳብ ሊክድ የሚደፍር ካለ… እንደው ሌላው ሁሉ ቢቀር ባሳለፍነው ሁለት ዓመት የብዙ ወገኖቻችንን ሕይወት በከንቱ የቀጠፈውን የእርስ በርስ ጦርነት/እልቂት ማስታወስ ብቻ በቂ ይሆናል።

ያለፈውን የቅርብ ታሪካችንን ዘመን ስንፈትሽም፤ “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!” በሚል መፈክር የተጀመረው የ66ቱ ለውጥ/አብዮት አፍታም ሳይቆይ፤ “አብዮት የገዛ ልጆቿን እንኳን ሳይቀር ትበላለች!” ወደሚል አስፈሪ ፅልመት ተቀይሮ- “ያለ ምንም ደም!” በሚል የሰላምና የዕርቅን መንገድ የመረጠ የመሰለው አብዮት፤ “የማይታረቅ የመደብ ቅራኔ ውስጥ ነን፤ እናም ወይ እኛ ወይ እነርሱ ካልጠፉ በስተቀር…” ወደሚል ጠላትነት/ ባላጣነት ነበር የተቀየረው።

በአብዮቱ ግራና ቀኝ የተሰለፉት ኃይላት ተቀራርቦ ለመነጋገርና ለዕርቀ-ሰላም አማራጭ በሩን ጥርቅም አድርገው ሲዘጉ- በኢትዮጵያ ምድር የሞት መላእክት የጥፋት ሰይፋቸውን መዘው በአራቱ ማእዘን ቆሙ። እናም የሆነው ሁሉ ሆነ። ውጤቱም በመስቀል አደባባይ ባለው የቀይ የሽብር ሰማዕታት ቤተ-መዘክር ለታሪክ ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ ሀገሬ ታጠቂ በገመድ፤

የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፣

ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ።

የሚለው የኢትዮጵያውያን እናቶች እንጉርጉሮ መነሻውም ይኸው ዕርቅንና ሰላምን የገፋው የይሰቀል የፖለቲካ ታሪካችን መራር ሐቅ አካል ነው።

ግን… ግን… ደግሞ፤

በአንፃሩ በዚህ ሁሉ ውስጥ እንደ ማህበረሰብ እንዴት አብረን ቆየን ብለን ብንጠይቅ፤ “ይቅር ለእግዚአብሔርና ዕርቅ ደም ያደርቅ!” የሚል በተግባር የሚገለጽ ሥነ- ቃል ያለን ሕዝብ መሆናችንንም መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም። ለአብነትም፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት የጋሞ አባቶች እንደ ባህላቸው ሣር በጥሰው ሄደው ጫፍ ላይ የደረሰን የእልቂት ድግስን በዕርቀ-ሰላም እንዲፈታ ያደረጉበትን ክስተት ማስታወስ ይገባናል።

እንዲህ ዓይነቱ የዕርቀ-ሰላም ባህል ከሰሜን ኢትዮጵያ ጫፍ እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተንሰራፋ ነው። አሁን ላለንበት የሰላም እጦትና የይሰቀል ፖለቲካዊ ባህላችን ለፈጠረው ቀውሶቻችን መፍትሔ ለመሻት እነዚህን ሀገራዊ እሴቶቻችንን በቅጡ መፈተሽ ያለብን ይመስለኛል።

ከዚህ ባሻገርም፣ በደሎቻችንን ልንሽር፣ ችግሮቻችንን ልንሻገር የምንችልበትን ምክክር ማድረግ ይኖርብናል። ለዚህም የተመቻቸ መድረክ በመኖሩ ያንን በአግባቡ መጠቀም፤ ለዚህ የሚሆኑ ማህበራዊ እሴቶቻችንን ለመቀራረቢያ ኃይልነት ማዋል፤ በይቅርታ ትቶ ነገን የተሻለ አብሮነትን ለመፍጠር ወደሚያስችለን መድረክ እንሰባሰብ። ከመጠላለፍ፣ ከመበቃቀል፣ ከመገዳደል መንገዳችን ወጥተን፤ ወደ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ አብሮነትና ሰላም ጎጇችን እንክተም። አበቃሁ!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You