በአርባ ምንጭ ከተማ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፦ በአርባ ምንጭ ከተማ 39 የጋራና የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቅነህ አብርሃም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ አርባ ምንጭ ጽዱና ውብ ከተማ ናት። ይህንን ለማስቀጠል በርካታ ሥራዎች በከተማ አስተዳደሩ እየተሠሩ ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በአርባ ምንጭ ከተማ ጽዱ ለማድረግ በአረንጓዴ መናፈሻዎች፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶችና በገበያ ቦታዎች የሕዝብ እና የጋራ መፀዳጃ ቤቶች እየተገነቡ ነው ያሉት አቶ ወርቅነህ፤ በዚህም 39 የጋራና የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የግንባታው አጠቃላይ አፈጻጸም ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን የገለጹት አቶ ወርቅነህ፤ የመጸዳጃ ቤቶቹን ግንባታ እስከ ሐምሌ 2016 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

17 የሕዝብ እና 21 የጋራ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ወርቅነህ፤ በመቀጠልም ከዚህ በፊት በከተማው ተገንብተው በአግባቡ አገልግሎት የማይሰጡ የነበሩ ስድስት የጋራ እና አራት የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች እድሳት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ በፊት አሥር የሕዝብና የጋራ ዘመናዊ መፀዳጃና ሻወር ቤቶች ተገንብተው ለወጪ ቆጣቢ ቤቶች ነዋሪዎች እና ለተደራጁ ማህበራት መሰጠቱንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እየሠሯቸው ካሉት ሥራዎች መካከል አንዱ ጽዱ ቢሮን፣ ጽዱ ከተማን እና ጽዱ ሀገርን መፍጠር ነው፡፡ ከጽህፈት ቤታቸው የጀመሩት ይህ እንቅስቃሴ ከአዲስ አበባ አልፎ ወደ ተለያዩ የክልል ከተሞች እያደገ ሀገር አቀፍ ሆኗል፡፡

“ሰው አካባቢው ጽዱ ከሆነ መልካም ነገር የማሰብ ኃይል ያገኛል” የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በይፋ ያስጀመሩት የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለሆነችው አዲስ አበባ አዲስ የንጽህና ባህል እንደሚያስጀምር ይታመናል፡፡

ንቅናቄው ዜጎች አካባቢያቸውን በንጽህና እንዲጠብቁ ከማድረግ ጎን ለጎን ክብራቸውን ጠብቀው እንዲፀዳዱ የንጹህ መጸዳጃ ቤቶችን ተደራሽነት ለማስፋት ያለመ ነው።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You