የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ወደ ፍኖተ ካርታ የዝግጅት ምዕራፍ ተሸጋገረ

አዲስ አበባ:- በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነዱ የተመላከቱ ስልቶች ቅደመ ተከተላቸውን ጠብቀው እንዲተገበሩ ወደሚያስችለው የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ሥራ መሸጋገሩን ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሚኒስቴሩ የብሄራዊ ሰብአዊ መብቶች ድርጊት መርሃ ግብር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አወል ሱልጣን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሰነዱ የተመላከቱ ስልቶች ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው እንዲተገበሩ ወደ ሚያስቻለው የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ስራ ተሸጋግሯል፡፡ በዚህም ባለፈው ሳምንት የተጀመረውን ተግባር በቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ፍኖተ ካርታው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የትግበራ ምዕራፍ ምን ላይ ተጀምሮ ምን ላይ እንደሚያበቃ የሚያመለክት እና በሂደቱ የሚከናወኑ ተግባራትን የሚዘረዝር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተግባራቱን የሚያከናውኑ ተቋማት፣ የትግበራ ምዕራፉ የሚጠናቀቅበት ጊዜ እና አስፈላጊ በጀትንም በአግባቡ የሚያመላክት ነውም ብለዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው በመንግሥት ተቋም ባለሙያዎች ብቻ የሚሠራ ሳይሆን ከሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮችና ከሰብአዊ መብት ድርጅቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

ተጠያቂነትን ማስፈን ፣ ቅድመ ሁኔታን ከግምት ያስገባ ምህረት፣ እውነትን ማፈላለግና ይፋ ማድረግ፣ ይቅርታ፣ የማካካሻ እና የተቋም ግንባታ ሥራዎች በሰነዱ መካተታቸውንም አመልክተዋል፡፡

ስልቶቹን የሚያስተገብሩ ገለልተኛ ተቋማት እንዲዋቀሩ በፖሊሲው መመላከቱን በማስታወስም፤ ተቋማቱ ከተቋቋሙ በኋላ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ማስተግበር የቀጣይ ትግበራ አካል ይሆናል ነው ያሉት አቶ አወል ፡፡

በገለልተኝነት የሚቋቋሙ የእውነት ማፈላለግ ኮሚሽን፣ የተቋም ግንባታ ኮሚሽን፣ ልዩ ዐቃቤ ሕግ እና ልዩ ችሎት በፖሊሲው የተመላከቱትን ስልቶች ያስተገብራሉ፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር ተቋማቱን ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች የሲቪል ማህበረሰብና የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን በማስተባበር እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ስልቶቹን ለማስተግበር የሕግ ማእቀፎች ይወጣሉ፣ ማህበረሰቡ ግንዛቤው ኖሮት በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ጎን ለጎን ይሠራሉ፡፡

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በአንድ ሀገር ውስጥ አስፈላጊ የሚሆንባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ያሉት ኃላፊው፤ በጣም አምባገነን የሆነ ሥርዓተ መንግሥት ኖሮ ያንን ሥርዓተ መንግሥት ለመቀየር በተደረገ ጊዜ ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን መርምሮ በእርቅ፣ ተጠያቂነትን በማስፈንና በሌሎችም ዘዴዎች የነበረውን ሥርዓተ መንግሥትን ወደ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የሚቀየርበት አንዱ መንገድ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ሌላው በግጭት ውስጥ ያለፈ ሀገር ውስጥ የተወለዱ ብሶቶች፣ ጉዳቶችና ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲኖሩ መርምሮ በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ስልቶች አማካኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቁስልን አብሶና ሽሮ የነበረን ግጭትና አለመግባባት አስተካክሎ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ዴሞክራሲን ለመገንባት፣ ሰብአዊ መብትና የሕግ የበላይነትን ለማክበር የሚወሰድ ርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በተለያዩ ጊዜያቶች በግጭቶች ውስጥ የነበርን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እስካሁን በነበሩ ግጭቶች የደረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመደበኛው የፍትህ ሥርዓት ውስጥ እልባት ሳይሰጣቸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲንከባለሉና እልባት ሳይሰጣቸው የቆዩ ችግሮች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎችም ሀገራት ልምድ በመነሳት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን ነድፋ ተግባር ላይ በማዋል አለመግባባቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ካልቻለች ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም በሚል እምነት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት መጀመሩንም አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከነበሩ ፖሊሲዎችና የሕግ ማዕቀፎች በተለየ መልኩ የሕዝብ ባለቤትነት የሚያስፈልግ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ከጅምሩ ሕዝብ በማሳተፍ ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ አማራጮችን የያዘ የፖሊሲ አማራጮችን የያዘ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ እንዲሰራጭ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

በሰነዱ ላይ ተመርኩዙ ማንኛውም ሰው በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አንብቦ መካተት ስለሚገባቸው ጉዳዮችም አስተያየት እንዲሰጥበት መደረጉን አውስተው፤ በአዲስ አበባ ስድስት የውይይት መድረኮች በማካሄድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የግብአት ማሰባሰብ ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ የቀጠለው ተግባርም ከ49 በላይ መድረኮች የግብአት ማሰባሰብ ሥራ የተካሄደበት እንደነበር ገልጸው፤ በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦች ላይ ሕዝቡ የሚሰማውን ሃሳብ እንዲያንጸባርቅ መደረጉንና ያለተጽእኖ እንዲካሄድ ለማድረግም ከ200 በላይ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዲሳተፉበት መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

ከክልል ውጪ በሆኑ ጉዳዮች ደግሞ ተጎጂዎችን፣ ሕፃናትና ሴቶችን ተሳታፊ ያደረጉ ከ20 በላይ መድረኮች ለየብቻቸው መካሄዳቸውንም ነው የገለጹት፡፡

መድረኮቹ ሲካሄዱ 13 አባላት ያሉት ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተደራጅቶ እንደነበር በመግለጽም፤ የፖሊሲ አማራጮቹ የተዘጋጁት፣ የምክክር መድረኩም የተመራው ገለልተኛ ከሆኑ ባለሙያዎች ማለትም ከጠበቆች፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና በየግላቸው ከሚሠሩ በጉዳዩ ላይ ረጅም ጊዜ የተመራመሩ ፣ ያጠኑ፣ ያሰለጠኑ፣ ያማከሩና ያስተማሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ቡድኑ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ረቂቅ የሽግግር ፖሊሲ ሰነዱን አስረክቧል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ረቂቅ የሽግግር ፖሊሲ ሰነዱ ላይ አራት መድረኮች ተደርገዋል፡፡ የተገኘውን ግብአት በማካተትም የመጨረሻውን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሰነድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረብ ችሏል፡፡

ምክር ቤቱም ለሀገር ሰላም መስፈን፣ ለእኩልነት፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን ያለውን አስተዋፅኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ለጉዳዩ ቅድሚያ በመስጠት በጉዳዩ ላይ መክሮ በአጭር ጊዜ ጸድቆ ወደ ተግባር አስገብቷል ብለዋል፡፡

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You