የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠሩ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ እድሎችን ለማስተዋወቅ ያለመ የኢትዮ- ፓኪስታን የቢዝነስ ፎረም ትናንት ተካሂዷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጭና ለሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

በፖሊሲው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ዓለም አቀፍ ንግድ ለማፋጠን፣ የቱሪስት ፍሰት ለመጨመር፣ ፋይናንስ ለማሳደግ እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል ያሉት አምባሳደር ብርቱካን፤ ኢትዮጵያ በዓለም ከፍተኛና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እንዲፈጠር እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል፡፡

አምባሳደር ብርቱካን፤ በኢትዮጵያ ሰፊና እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ፎረሙ የኢትዮ-ፓኪስታን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ አምባሳደር ብርቱካን ገለጻ፤ በኢትዮጵያ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና እንዲሁም በኢንዱስትሪ ኢንቨስት ለማድረግ ካሉ እድሎች በተጨማሪ በተለያዩ የኃይል አማራጮች ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከፍተኛና አዋጭ ዓለም አቀፍ ንግድ ሥርዓት ያላት ሀገር ናት፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ በረራ ከጀመረ በኋላ ፓኪስታንን ከአፍሪካ ብሎም ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን በመጥቀስ፤ ወደፊትም አዲስ ለሚጀመረው ኢንቨስትመንት ምቹ የገበያ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ ከመኖሩም በላይ ውጤታማ የንግድ ሥርዓት እንዳላት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላትና ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ፓኪስታን መልካም ተሞክሮ ባካበተችባቸው የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ፋርማሲዩቲካልና ሌሎች ዘርፎች በጋራ መሥራት ትፈልጋለች ብለዋል።

የፓኪስታን የንግድ ልማት ባለስልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሞሐመድ ዙቤር ሞቲዋላ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ማድረጓ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከረዥም ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ፓኪስታን ካራቺ በረራ መጀመሩ ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማጠናከር ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ በመሆኑም ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ ትሠራለች፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You