ኮሚሽኑ ኢትዮጵያውያን የሀገራዊ ምክክሩን ፋይዳ በመረዳት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ

  • በአዲስ አበባ የምክክር ምዕራፍ ነገ ይጀመራል

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያን የሀገራዊ ምክክሩን ፋይዳ በመረዳት በንቃት እንዲሳተፉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡ በአዲስ አበባ የምክክር ምዕራፍ ነገ እንደሚጀመርም ተጠቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ ትናንት በሰጠው መግለጫ ላይ ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ምክክሩ የሚያመጣቸውን ሁለተናዊ ፋይዳ በመረዳት በንቃት ሊሳተፉ ይገባል፡፡ በምክክሩ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትም ይህን በመረዳት ለስኬታማነቱ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ የሚያካሂደው የምክክር ምዕራፍ ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ይህ የምክክር ምዕራፍ ከሁለት ሺ 500 በላይ ተወካዮችን ተሳታፊ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በሂደቱ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተሳታፊዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት እና የመንግሥት አካላት እና የተለያዩ የተቋማትና ማህበራት ተወካዮች የሚመካከሩበት፣የአጀንዳ ግብዓታቸውን የሚያዘጋጁበትና በሀገራዊ ጉባኤው የሚወክሏቸውን ተሳታፊዎች የሚመርጡበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ፤ ቀደም ሲል ኮሚሽኑ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በክልላዊ የምክክር ምዕራፍ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን ከየኅብተሰብ ክፍሉ አስመርጧል፡፡ የምክክር ምዕራፍ መርሀ ግብሩ ሦስት ዋና ዋና ተግባራት ይከናወኑበታል፡፡ በዚህ እርከን ላይ የሚመጡ ተሳታፊዎች በምክክርና በውይይት የአጀንዳ ሃሳቦችን በመስጠት፣ አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ የማደራጀትና የመፍትሔ ሃሳቦችን ያንሸራሽሩበታል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸውን ይመርጡበታል።

መርሀ-ግብሩ ኮሚሽኑ በከተማ አስተዳደሩ ስር ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋል የሚሏቸውን እጅግ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች የያዙ አጀንዳዎችን በሕዝባዊ ውይይት የሚሰበስብበት ምዕራፍ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሯ፤ በቀጣይነት ኮሚሽኑ ተመሳሳይ መርሀ-ግብሮችን በክልሎች እና በከተማ አስተዳደር እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነትና አለመግባባት በአካታች ሀገራዊ ምክክር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ይታወቃል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You