ድምጽ አልባው ድማሚት

በሁለት በኩል እንደተሳለ ሰይፍ ነው። የማዳንም የመግደልም አቅም አለው። ለበጎ ተግባር ካዋሉት ምድራዊ በረከቱ ብዙ ነው። ለእኩይ ዓላማ ካዋሉት ግን ድምጽ ሳያሰማ እንደ ድማሚት እየፈነዳ ትውልዱን ሊያመክን ይችላል።

እሱ ልክ እንደ ጅምላ ጨራሽ መሆን ይችላል። በአግባቡ ካልተጠቀሙት ወግ፣ ባህል፣ እሴት፣ ታሪክና እምነት ሳይል መልካም ልማድን በማስቀረት ሀገርን ያርዛል።የማህበራዊ ሚዲያ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ዓለም ከመዘመኗ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ማደግን ተከትሎ ብቅ ያለ ቴክኖሎጂ ነው።እንደ ተጠቃሚው ይወሰናል እንጂ በረከትም እርግማንም አለው ለማለት ያስችላል።

መላው ዓለምን አንድ በማድረግ የተለያዩ ሸክሞችን ከማቅለሉ በተጨማሪ መረጃ፣እውቀት፣ ልምድ፣ክህሎት ለመለዋወጥ እንዲሁም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር የማዕዘን ድንጋይ ሆኗል። በአግባቡ ካልተጠቀሙት ግን ጉዳቱም በዚሁ ልክ ‹‹ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ›› ሳያስብል አይቀርም።በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መረን የሳተ ይመስላል።

የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ትክክል ባልሆነ መንገድ በመተግበራቸው በዓለማችን በርካታ ሀገራት የዜጎቻቸውን መልካም ስብዕና አጥተዋል።ካጠቃቀማቸው የተነሳ ለጭንቀት፣ ለድብርት፣ ተስፋ ለመቁረጥ እንዲሁም ውስብ ስሜት ውስጥ ገብተዋል።በዚህ ምክንያት ሀገራት የተለያዩ መቆጣጠሪያ መንገድ ሲያበጁና ዜጎቻቸው እንዳይጠቀሙ ሲያግዱ ጭምር ይስተዋላል።

በሀገራችንም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ማንነታችንን ከባህል፣መልካም እሴትና ከእምነት የሚያራቁትና በስነ-ልቦና የጠነከረ ትውልድ እንዳይፈጠር የሚያደርግ እየሆነ ነው። ይህ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ተባብሶ ቀጥሏል። ስንቶቻችን ነን ማህበራዊ እሴቶቻችን ለሰላማችን ብሎም ለሀገራችን የወደፊት ህልውና ዘብ እንደሆኑ የምንረዳው።

የሰላም ትርጉሙ ከአካላዊ ጥቃት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሚደርሱ ስነ- ልቦናዊ ጫና መቋቋም እንዲሁም አዕምሯዊ ደህንነት ማረጋገጥ ጭምር ነው።በየማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለጠፉ አብዛኞቹ መረጃዎች ግን የሰዎችን የመኖር መብት የሚጋፉ፣ ስነ-ልቦናን የሚያላሽቁ፣የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚጥሉ ከሆኑ ውለው አድረዋል።አሁን ላይ በግልጽ እንደሚስተዋለው ከማህበረሰቡ አኗኗር ዘዬ ያፈነገጡ የውሸት ታሪኮች እየተፈበረኩ ይቀርባሉ።

የዚህ ዋነኛ ተዋናዮች ደግሞ አእምሯቸውን በጥቅም ያሰከሩ የማህበራዊ ትስስር ገጽ አርበኞች ናቸው። አርበኞቹ ጊዜያዊ ዝና ያናወዛቸው በመሆናቸው እኩይ ግብራቸው የተገነባ ማህበረሰብ እያፈረሱ መሆኑን፣ ‹‹በሰው ቁስል እሾህ ስደድበት›› እንዲሉ በሰዎች ቁስል እንደሚቀልዱ እንዲሁም እስከ ወዲያኛው ነውጥ እያዋለዱ እንደሆነ አያስተውሉትም ለማለት አያስደፍርም።

የማህበራዊ ትስስር ገጽን ለእኩይ ዓላማ ያዋሉ አካላትን ስንኮንን ለበጎ ዓላማ አውለው መልካም ፍሬ ያፈሩ ወገኖች እንዳሉ በመዘንጋት አይደለም።በዕኩይ ተግባራቸው አጀብ አሰኝተው እጅ በአፍ ያስጫኑ የመሰላቸው የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞቹ ለሀገሪቱ ማህበራዊ ቀውስ አንድ ጠጠር እያስቀመጡ ነው። የሚገርመው ያሰቡትን ሁሉ መናገራቸው ብቻ አይደለም ጆሮን ጭው የሚያደርጉ የራሳቸው ታሪክ መፍጠራቸው እንጂ።

በዓለም ላይ በሁሉም አይነት በሚባል ደረጃ ህጎች ይወጣሉ። ይሁን እንጂ የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተግባብቶ እንዲኖር ያስቻለው ሞራሊቲ(መልካም እሴቶች) ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በተለይ በባህል፣ በቋንቋና በታሪክ ከፍተኛ የጋራ እሴት እና 99 በመቶ አማኝ አላት በምትባል ሀገር ላይ ስርዓት አልበኝነት ማንገስ ተገቢ ነው ወይ? የሚለውን ለአንባቢው መተው ሳይሻል አይቀርም።

ከሕገ መንግሥት አንጻርም ቢሆን የሰው ልጅ በሰላም በመኖር ያለምንም የደህንነት ስጋት የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን መፈጸም አለበት የሚለውን ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን መንጠቅ ይሆናል። ከሀገር ግንባታ ጋር በተያዘም በሥነ ልቦና የዋዠቀና በአስተሳሰቡ ችግር ያለበት ዜጋ እንዲፈራ የሚያስገድድ ነው።

ይህ አይነቱ እኩይ ተግባር የትውልዱን አስተሳሰብ በማቀንጨር ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዳይፈራ ከማድረጉም በላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እየሆነ መጥቷል ለማለት ያስደፍራል።

ሌሎች ደግሞ የሀገሪቷን ሰላም የናጡና የሕዝቡን ወገብ ያጎበጡ ክፉ አንደበታቸውን ላልተገባ ዓላማ በማዋል የስድብ ዘውድ የጫኑ ናቸው።ከግብር አባታቸው በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ማህበራዊ ሚዲያውን እየጋለቡ ዘመን ተሻጋሪ መርዛቸውን እየረጩ ነው።

እነሱ በስድብ ከብረዋል፣ የአዕምሮ ጡንታቸው አቀጭጨው ኪሳቸውን አደልበዋል። ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሃይማኖታዊ ተቋማትና መሪዎች እስከ ታላላቅ ሀገራዊ ተቋማት ድረስ መልካም ስሞችን አጉድፈዋል። ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች ለኢትዮጵያውያን ማንም የማይነካባቸው የግል እሴት ቢሆንም ውሎ ባደረ ቁጥር ግን እየቀሙት፣እየነጠቁት ይገኛሉ።አዲሱን ትውልድ በራሳቸው ልክ ቀደው እየሰፉ እጸ በለስ እንጂ እጸ ሕይወትን እንዳይበላ ነፍገውታል።

የእነዚህ ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት እንደ አሸን መፍላት የተመልካቹ አልያም ጊዜ ሰጥቶ የሚሰማው አካል ያልተናነሰ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በመገንዘብ ከማህበረሰቡ እሴት ያፈነገጡ መረጃዎችን መቃወም ተገቢ ነው።

በቅርብ ጊዜ ጉዳዩን ትኩረት በመስጠት በመንግሥት የተጀመረው እንቅስቃሴ የተወሰነ እፎይታ የሚፈጥር ይመስላል። በተለይም መሰል ችግሮችን ለመቀነስ ከየሀገራቱ መንግሥታት ጋር ከስምምነት መድረስ ተገቢና አስፈላጊ ይሆናል።ይህ ጅምር ተጠናክሮ መቀጠል ቢችል መልካም ውጤት ለማግኘት መነሻ እንደሚሆን መገመቱ አያዳግትም።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You