የተማሪዎች የሳይንስ ፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ

ሰላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? በርትታችሁ እያጠናችሁ ነው አይደል? ጎበዞች። ልጆችዬ 9ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ ከግንቦት 16 ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ተካሂዷል። በአውደ ርዕዩ በተማሪዎችና መምህራን የተሰሩ የፈጠራ ሥራዎች ለዕይታ ቀርቧል። ልጆችዬ ዛሬ በፈጠራ ሥራ በጣም ጎበዝ የሆኑ ልጆችን በማነጋገር እናንተም ብዙ ልምድ ትቀስማላችሁ ብለን በማሰብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ኤርሚያስ ኪዳኔ እና ናትናኤል ሀብቴ የሚማሩት “ፊታውራሪ አባይነህ መተኪያው ትምህርት ቤት” ነው። ተማሪዎቹ በአውደ ርዕዩ ላይ ሦስት የፈጠራ ሥራዎችን ይዘው ቀርበዋል። አንደኛ የፈጠራ ሥራቸው እነርሱ ‹‹ፋየር ፋይቲንግ ሮቦት›› የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ይህ የፈጠራ ሥራ በከተማችን የሚገኙ የእሳት አደጋ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎችን ሥራ የሚቀንስ እንደሆነ ይናገራሉ። ሮቦት እሳት በሚነሳ ሰዓት እና እሳት ባለበት አካባቢ በመሄድ ውሃ በመርጨት እሳቱን ያጠፋል።

የኤርሚያስ እና ናትናኤል ሌላኛው የፈጠራ ሥራ ‹‹ኢመርጀንሲ ኮል›› ይሰኛል። ይህ የፈጠራ ሥራን በቤት ውስጥ የእሳት አደጋ በሚነሳበት ወቅት ወደቤቱ ባለቤት እና ወደ እሳት አደጋ የሚደውል ነው። ሦስተኛ ፈጠራቸው ኤሌክትሪካል ዊልቸር ነው። ታማሚዎች አቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞችን ከዊልቸርነት በተጨማሪ እንደ አልጋ የሚጠቅም መሆኑን የፈጠራ ባለሙያዎቹ ኤርሚያስ እና ናትናኤል ይገልጻሉ።

ተማሪዎቹ አያይዘው እንደገለጹት፣ በዚህ አውደ ርዕይ በመሳተፋቸው የበለጠ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው እና ሌሎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ ልጆች ብዙ ለመማር ችለዋል።

መስማት ለተሳናቸው በቀላሉ የሚማሩበትን ፊደል የሠራችው ኤልዳ ሀጎስ ትባላለች። ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን የመስማት እክል ለሌለባቸው ተማሪዎች በቀላሉ የምልክት ቋንቋን ለመማር የሚረዳ እና መስማት ከተሳናቸው ጋር ለመግባባት የሚያግዝ ነው ስትል ትገልጻለች።

በዝክረ ቴዎፍሎስ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ኤልዳ ስለ ፈጠራ ሥራዋ ስታስረዳ ለምሳሌ ይህንን የእንግሊዝኛ L ፊደልን ስንነካ በምልክት ቋንቋው L ምን እንደሚመስል አምፖል በርቶ ምልክቱን ያሳያል። የፈጠራ ሥራዋ በተለይም ለመዋዕለ ሕፃናት ተማሪዎች በሚገባ ይጠቅማል ስትል በራስ መተማመን ትናገራለች። ኤልዳ ከዚህ ቀደም በፈጠራ ሥራዎች ላይ ተወዳድራ ዋንጫ፣ ላፕ ቶፕ እና 15 ሺ ብር ተሸልማለች። እንዲህ ዓይነቱ አውደ ርዕይ ላይ መሳተፏም ብዙ ትምህርት እንዳገኘችበት እና በቀጣይ ምን መሥራት እንዳለባት ትምህርት አግኝታበታለች።

ሳሙኤል መክብብ በብራይት አካዳሚ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። እርሱም እንደሌሎች ተማሪዎች በአውድ ርዕዩ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ችሏል። እርሱ የሠራው የፈጠራ ሥራ ለአሽከርካሪዎች የሚጠቅም እንደሆነ የሚናገረው ተማሪ ሳሙኤል አሽከርካሪዎች በብዛት በድካም ወይም በድባቴ ምክንያት እያሽከረከሩ እንቅልፋቸው በመምጣቱ በአግባቡ ማሽከርከር ይሳናቸዋል። በተጨማሪም ለአደጋ ይጋለጣሉ። ይህን ችግር ለመቅረፍ አሽከርካሪዎች እንቅልፋቸው እንደመጣ እና እንዳልመጣ በመለየት እንቅልፋቸው ከመጣ መኪናቸው እንትቆም በማድረግ፣ ጩኸት እንድታሰማ በማድረግና እና ኢሜል በመላክ አደጋ እንዳይከሰት የሚረዳ መሆኑን ያስረዳል።

ተማሪ ሳሙኤል በአውደ ርዕዩ ላይ በመሳተፍ የራሱን የፈጠራ ሥራ ይዞ ከመቅረብ በተጨማሪ ብዙ ልምዶች እንዳገኘም ነግሮናል። ሌሎች ተማሪዎችም ችግር ፈቺ እና በቀላል ወጪ ሊሠሩ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲሠሩ ይመክራል።

በአጠቃላይ በአውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፋ ልጆች በተለይም የፈጠራ ሥራ ኖሯቸው ቤታቸው ለተቀመጡ ልጆች መልዕክት አላቸው። መልዕክቱ ምንም መሰላችሁ ልጆች ? <<ምንም የሚያስፈራ ነገር የለም። ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ የፈጠራ ሥራ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ከማሸነፍ በተጨማሪ ብዙ ልምድ ትቀስማላችሁ>> የሚል ነው።

ልጆችዬ መቼም ከነዚህ ጎበዝ ልጆች ብዙ እንደተማራችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። እነርሱ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን የሚሠሩት ባላቸው የትርፍ ሰዓት ነው። እናንተም ትርፍ ሰዓታችሁን በአግባቡ እየተጠቀማችሁበት እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆችዬ በዚሁ እናብቃ። ሳምንት በቸር ያገናኝን። ለእናንተም መልካም የእረፍት ቀን እና የትምህርት ሳምንት እንዲሆንላችሁ ተመኘን።

እየሩስ ተስፋዬ

 

አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You