ሴቶችን ለመደገፍ የተፈጠረችዋ ማርያ

ወይዘሮ ማርያ ሙኒር የሕግ ባለሙያ ናቸው። ረዥም ዓመታት በዳኝነት አገልግለዋል። ጠበቃም ነበሩ፤ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ሲቋቋም ማህበሩን ከመሰረቱት ሴት የሕግ ባለሙያዎች አንዷ ሲሆኑ፤ በማኅበሩ ነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት ይሰጡ ነበር። የማኅበሩ የቦርድ አባል የነበሩት ወይዘሮ ማርያ በወቅቱ የማኅበሩ የሕግ ቢሮዎች እንዲከፈቱም ተንቀሳቅሰዋል። የሕግ ምክር አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማኅበሩ ይሄዱ የነበሩ ሴቶችና ሕፃናት ማረፊያን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች ያጋጥሟቸው ስለነበር ጥቃት የደረሰባቸውና የምክር አገልግሎት የሚሰጣቸው ሴቶችና ሕፃናት ያርፉበት ዘንድ ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የቀድሞውን ጾታዊ ጥቃት ተከላካይ ማኅበር የአሁኑን የሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር እ.ኤ.አ. 2006 አቋቁመዋል።

ወይዘሮ ማርያ ሙኒር ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ መርካቶ አንዋር መስጊድ አካባቢ ነው። ለቤተሰቦቻቸው አራተኛ ልጅ ይሁኑ እንጂ ቤተሰባቸው ሰፊ እንደሆነም ይናገራሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸው ካቴድራል ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ደግሞ በቀድሞው የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ማጠናቀቃቸውን ይናገራሉ።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተከታተሉበት ካቴድራል ትምህርት ቤት በጣም ፈጣን በትምህርታቸው ጎበዝ እንዲሁም ትምህርት ቤቱ ውስጥ ባሉ ተሳትፎን በሚጠይቁ ተግባራት ሁሉ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነበሩ። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩበት ካቴድራል ትምህርት ቤት ልጆች በራሳቸው እንዲተማመኑ ወደፊት መሪ የመሆን ህልምን ከችሎታ ጋር እንዲያዳብሩ ከፍ ያለ ሥራን ይሰራ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለወይዘሮ ማርያ በብዙ መልኩ የተቀመጠ ስለነበር፤ ሰባትና ስምንተኛ ክፍል ሲሆኑ የተቀሩትን ተማሪዎች ሥነ ሥርዓት መቆጣጠር የግቢውን ሥነ ሥርዓት ማስከበር ብቻ በጠቅላላው የተማሪዎቹን የትምህርት ቤቱን ሥነ ሥርዓት ለማስከበር ኃላፊነት ወስደው ከጓደኞቻቸው ጋር ተንቀሳቅሰዋል።

“………ካቴድራል ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ስደርስ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ትምህርት ቤቱ በመረጠኝ መሠረት የግቢውን ሥነ ሥርዓት መቆጣጠር ተማሪዎችን፤ ከሰልፍ ላይ ጀምሮ ወደ ክፍል ውስጥ ሲገቡ ለምሳና ለእረፍት ሲወጡ ያሉትን ተግባራት በአግባቡ ይፈጽሙ ዘንድ የማስተማር፤ አለፍ ሲልም የመቅጣት ሥራን እሰራ ነበር” ይላሉ።

ትምህርት ቤቱ ይህንን ኃላፊነት ለተማሪዎች ሲሰጥ ዝም ብሎ አይደለም። ይልቁንም በቅንነትና በታማኝነት አገለግላለሁ ብለው ቃለ መሃላ ፈጽመው ባጅ ተሰጥቷቸው ሥርዓት ባለውና ኃላፊነት በሚሰማቸው መንገድ የሚያገለግሉበትን መንገድ ሁሉ ያመቻች ነበር። ይህ ደግሞ ለተመረጡት ተማሪዎች ትልቅ ደስታን የሚፈጥር ሥራውንም በከፍተኛ ተነሳሽነት እንዲሰሩት የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር ትምህርት ቤቱ የሚፈልገውን መሪዎችን የማውጣት ሂደት እንዲለማመዱት የሚያደርግም እንደነበር ወይዘሮ ማርያ ይናገራሉ።

በሌላ በኩልም ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ቅዳሜና እሁድን ተጠቅመው በትምህርት ቤቱ ዙሪያ የሚገኙ አቅመ ደካሞችን እንዲያግዙ፤ ቤታቸውን እንዲያጸዱ፤ ገላቸውን እንዲያጥቧቸው ጥፍራቸውን እንዲቆርጧቸው በጠቅላላው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ አድርገው በረከት እንዲያገኙ ይደረግ እንደነበር ይናገራሉ።

ወደ ስምንተኛ ክፍል ሲሸጋገሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ሕፃናትን በሚረዱ ድርጅቶች ጋር ሄደው የጽዳትና ሌሎች ሥራዎችን በበጎ ፍቃደኝነት እንዲሰሩ ትምህርት ቤታቸው ይልካቸው እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮ ማርያ፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ መረዳዳትን ሰው መውደድን እንዲለምዱ ከማድረጉም በላይ ቅዳሜና እሁዳችንን ባልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ እንደጠቀማቸው ያስረዳሉ።

“…….ትምህርት ቤቱ ያመቻቸው ይህ ሥራ ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን ሕይወት ምን ትመስላለች? ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ? ምን ምን ዓይነት ችግሮችንስ ይጋፈጣሉ? የሚለውን ነገር በደንብ እንድረዳ አድርጎናል። ያም ብቻ አይደለም፤ አሁን ላለሁበት ወይም ለምሰራው ሥራ ጥሩ መሠረት ጥሎልኛል” ይላሉ።

ወይዘሮ ማርያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ይሂዱ እንጂ፤ ካቴድራል ያስተማራቸውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አላቋረጡም ነበር። በዚህም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ከወንድና ሴት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ሰፈራቸው ውስጥ ወዳለው “አባድር ትምህርት ቤት” በመሄድ እናቶችን በተለያየ ምክንያት የትምህርት እድል ማግኘት ያልቻሉ ሴቶችን በማታው ክፍለ ጊዜ ያስተምሩም ነበር።

“…….ትምህርት ያልተማሩና ማንበብ መጻፍ የማይችሉ፣ በተለያየ ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ የእናቶቻችን ጓደኞችና ከዛም በእድሜ አነስ ላሉ ሴቶች ትምህርት እናስተምራለን። ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ ትርፍ ጊዜያችንን ቁምነገር ባለው ሥራ ላይ እንድናውል አድርጎናል” ይላሉ።

ይህ የእነ ወይዘሮ ማርያ የትምህርት ብርሃን ደግሞ ብዙዎችን ከመጥቀሙም በላይ በእድሜ ወጣት የሆኑ በዛው ትምህርታቸውን ቀጥለው በጣም ትልልቅ ቦታ ላይ ደርሰውም እንዳዩ ይናገራሉ።

ምንም የባከነ የወጣትነት ጊዜ የሌላቸው ወይዘሮ ማርያ፤ 12ተኛ ክፍል ሊደርሱ አካባቢ የወጣት ወንዶችና ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወሴክማ) መዋል ጀመሩ። በዚህም እጅ ሥራ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን መማር ቻሉ፤ ይህ በራሱ ሌላ የሕይወት መስመርን ፈጠረላቸው ፤ በተለይም ወጣቶቹ ከተለያየ ቦታ የተሰባሰቡ መሆናቸው የልምድ ልውውጡ ብቻ ብዙ ነገሩ አስተማሪ እንደነበር ይናገራሉ።

በ1977 ዓ.ም በሀገራቸው የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎም እነ ወይዘሮ ማሪያና ጓደኞቻቸው ዝም አላሉም፤ “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በማለት፤ በጋራ በመቀናጀት ከፍተኛ ዝግጀት በማድረግ በአዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ትልቅ የሙዚቃ ዝግጅት በማድረግ ብዙ ገንዘብ ሰብስበው ወደ ወሎ በመጓዝ ርዳታ ስለማድረጋቸው ያብራራሉ።

“……ከአንደኛ ደረጃ ጀምሬ በተማርኩበት ወቅት በጨዋታና በቀልድ ያሳለፍኩት የወጣትነት ጊዜ አልነበረኝም፤ ያሳለፍኩት በሁሉም ነገር ላይ እየገባሁ ነው፤ ይህ ደግሞ ሕይወቴን ሙሉ ለማከናውናቸው ነገሮች ከፍ ያለ ጥንካሬን ከመስጠቱም በላይ አሁን እየሰራሁት ወዳለሁት ሥራ አመጣኝ” ይላሉ።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወይዘሮ ማርያ ወደ ትዳር አመሩ። ይህም የሆነው በቤተሰብ አልያም በሌሎች ግፊት ሳይሆን በራሳቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት ነበር።

“……. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ ያመራሁት ወደ ትዳር ነው፤ ማንም አስገድዶኝ አልያም በቤተሰብ ምንም መጥቶልኝ ሳይሆን በራሴ ፍላጎት የሆነ ከመሆኑም በላይ ወድጄና ፈቅጄ ያፈቀርኩትን ሰው አገባሁት፤ ነገር ግን ቤተሰቦቼ ፍጹም አልደገፉኝም ነበር ፤ በወቅቱ ባለቤቴም የባህር ኃይል ባልደረባ ነበር “ ይላሉ።

“…….ቤተሰቦቼ በጣም ጎበዞች ናቸው፤ በተለይም አባቴ ጎበዝ ነው፤ ለሥነ ሥርዓትና ለሃይማኖት ትልቅ ዋጋ የሚሰጡም ነበሩ፤ በዚህ የተነሳም ጋብቻውን አልወደዱትም፤ እኔ ደግሞ ማግባት በጣም ፍላጎቴ ስለነበር ትዳር መስርቼ ከቤቴ ወጣሁ። ከቤተሰብም ተጣላሁ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

የድሮው 12ተኛ ክፍል ትልቅ ዋጋ የነበረው በመሆኑ ወይዘሮ ማርያ ከ12ተኛ ክፍል ትዳር ይመስርቱ እንጂ የቤት እመቤት አልነበሩም፤ የትምህርት ደረጃቸው በፈቀደላቸው ልክ ማህበራዊ ጉዳይ የሚባል መሥሪያ ቤት ሥራ ተቀጠሩ። ሥራቸውን እየሰሩም የመጀመሪያ ልጃቸውን ነፍሰጡር ሆኑ።

ምንም እንኳን ቤተሰባቸው ያልደገፉት ትዳር ቢሆንም እናትና አባታቸው መጥተው ባያዩዋቸውም ከአንዳንድ ቤተሰባቸው እንዲሁም ከባለቤታቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የእርግዝና ጊዜያቸውን በጥሩ ሁኔታ አሳልፈው የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸውን ወለዱ።

ባለቤታቸው በጣም ጥሩ ባል ከመሆናቸው የተነሳ በትዳርና በልጅ ምክንያት ከትምህርትሽ መስተጓጎል የለብሽም ያቋረጥሽውን ትምህርት ቀጥይ ማለታቸው አልቀረም። ወይዘሮ ማርያ አሁንም ከቤተሰብ ባይገናኙም ሁለተኛ ልጃቸውን ነፍሰጡር ሆኑ። የእርግዝና ጊዜያቸው እየገፋ ባለበት ወቅት ግን ያላሰቡት ዱብዳ ወደቀባቸው። ባለቤታቸው ጠዋት ሥራ ብለው ተሰናብተዋቸው እንደወጡ ሳይመለሱ ቀሩ። ሁኔታው እጅግ ግራ አጋባቸው፤ የሚሄዱበት አጡ። የሚያውቋቸውን ሁሉ ቢጠይቁም አጥጋቢ ምላሽን አላገኙም። ምናልባት ከወቅቱ ፖለቲካ ጋር ተያይዞ ታስረው ይሆናል በማለት በአዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ውጪም በየማረሚያ ቤቱ ፈለጉ አስፈለጉ ነገር ግን ውጤት አልመጣም። ጓደኞቻቸውም ሆነ እሳቸውን አየን የሚል ጠፋ።

በዚህም በጣም ተስፋ ቆርጠው ባሉበት ወቅት አንድ ሰው ቁርጡን ነገራቸው የወይዘሮ ማርያ ባለቤትና ጓደኞቻቸው እንደተገደሉ መርዶውን ሰሙ። ይህ ለሳቸው በጣም ከባድ ነበር ፤ ሁኔታውን በጣም ከባድ ያደረገው ደግሞ ሀዘናቸውን ጮኸው አልቅሰው ማስወጣት ቀብረው ቁርጣቸውን ማወቅ አለመቻላቸው ነበር።

“…….መርዶውን የነገረኝ ሰው በፍጹም ማልቀስ እንደማልችል አስጠንቅቆኛል፤ ምክንያቱም ጉዳዩ ሚስጢር በመሆኑ እኔ ካለቀስኩ እሱም የጓደኞቹ ጽዋ እንደሚደርሰው ስለተነገረው ነበር” ይላሉ።

በመሆኑም የሚወዷቸውን የሚያፈቅሯቸውን ከቤተሰብ የተለያዩባቸውን ባለቤታቸውን እንደዘበት አጥተው መቀመጥ እጣ ፋንታቸው ሆነ። ወይዘሮ ማርያ ቀናቸው ደርሶ በሰላም ተገላገሉ። ከዛም የሁለት ወንዶች ልጆች እናት ሆኑ። ግን ደግሞ ወደፊት ብዙ ነገር እንደሚጠብቃቸው ማሰባቸው አልቀረም።

“……በጣም የሚገርመው ነገር በወቅቱ በጣም ጠንካራና እልኸኛ ሆንኩኝ ፤ እንደዚህ ሆኜም ወደ ቤተሰቤ ተመልሼ አልሄድም ይልቁንም እራሴን አበርትቼ የሆነ ነገር ይዤ ነው የምቀላቀለው ብዬ ቆረጥኩ፤ በትንሽ ደመወዝ ልጆቼን እያሳደኩ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሕግ ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ። ” ይላሉ።

በወቅቱ ወይዘሮ ማርያ ብቻቸውን ልጆች እያሳደጉ እንደገና ደግሞ ከፍሎ መማር በጣም መከራ ቢሆንባቸውም የወደፊቱን ብሩህ ቀን በማየት እጅ መስጠትን በፍጹም አልፈለጉም። የቅርብ ጓደኞቻቸውም እያገዟቸው እርሳቸውም ጠንክረው እየሰሩ የጀመሩትን ትምህርት በጥሩ ሁኔታ በማጠናቀቅ ዲፕሎማ አገኙ።

ትምህርታቸውን በሚገባ ካጠናቀቁና ዲፕሎማቸውን ከያዙ በኋላም የሚሰሩበት ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ከሚሰሩበት ክፍል ወደ አሰሪና ሠራተኛ ዳኝነት ክፍል ተዘዋውረው እንዲሰሩ እድሉን አመቻቸላቸው። በዚህ ሥራቸውም ላይ ከቆዩ በኋላ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኞች ሲሾሙ እዛ እንዲሰሩ ተዘዋወሩ። በዚህም የተለያየ ችሎቶች ውስጥ የመሥራት እድልን አገኙ።

በዚህ የኑሮ ትግል ውስጥ ልጆቻቸውን በሚገባ አሳደጉ አስተማሩ፤ ልጆቻቸው ግን እናታቸው ለእነሱ ዋጋ እየከፈሉ ጥሩ ትምህርት ቤት እያስተማሩ ምንም እንዳይጎልባቸው የቻሉትን ብቻ ሳይሆን የማይችሉትን ሁሉ እያደረጉ። እርሳቸው በትምህርታቸው መግፋት አለመቻላቸው ቁጭት አሳድሮባቸዋል፤ በወቅቱ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕግ ትምህርትን በማታ ክፍለ ጊዜ ጀምሮ ነበርና የመጀመሪያ ልጃቸው ለእሳቸውም ሳይናገር የትምህርት ማስረጃቸውን ሰብስቦ በመያዝ ወደ ዩኒቨርሲቲው በመሄድ እናቴን መዝግቡልኝ ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ ሁሉም በመደነቅ ከመዘገቧቸው በኋላ ለፊርማ መጠራታቸውን ይናገራሉ።

ወይዘሮ ማርያ በልጃቸው በተደረገላቸው ነገር እጅግ ከመደሰታቸውም በላይ የመማር ፍላጎታቸው ተጨናግፎ አለመቅረቱ እድለኛ እንደሆኑ እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸውም ይናገራሉ።

“…….አሁን ሥራዬም ጥሩ ነው ደመወዜም እያደገ ነው፤ ልጆቼም አድገዋል። ትምህርት ቤት ለመክፈል የምችልበት ቁመና ላይ ነበርኩ፤ እኔም ተማርኩ በጣም ደስተኛ ሆንኩ ትምህርቴን አጠናቅቄ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ሳገኝ ከአንዱ ልጄ ጋር አብሬ ተመረቅኩ። ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

ወይዘሮ ማርያ አንድ ቦታ ደርሼ ካልሆነ በቀር ቤተሰቤ ላይ ሸክም ለመሆን አልታረቅም ባሉት መሠረት፤ ልክ ትምህርታቸው ሲያጠናቅቁ አንድ የቅርብ የሆነ ዘመዳቸው በረመዳን ጾም ላይ አባታቸው ጋር በመሄድ መታረቅ አለባችሁ አላቸው። ምንም እንኳን አባታቸው በጣም የሚወዷት ልጃቸው ከቤት ወጥታ መቅረቷ ቢያስቆጫቸውም፤ ነይ ብሎ መጥራቱ ደግሞ ለሌሎቹም ልጆች መጥፎ አርዓያ መስጠት ነው በሚል አምቀው ነበር የያዙት፤ ነገር ግን ሰውየው ገፍቶ ሲሄድባቸው ሁኔታውን መግፋት አልፈለጉም። ወይዘሮ ማርያ ድግስ ተደግሶ ከቤተሰቦቻቸው ለመታረቅ ቻሉ።

ወይዘሮ ማርያ ከዛም በኋላ ትዳር መስርተው ተጨማሪ ልጆች መውለድን አልፈለጉም፤ ነገር ግን ዋጋ ከፍለው ያሳደጓቸው ልጆች ዛሬ አንዱ ከኢትዮጵያ ውጭ ሲሆን፤ አንዱ ሀገር ውስጥ ነው። ሁለቱም ትዳር መስርተው ሶስት ሶስት ልጆች በመውለድ ወይዘሮ ማርያ የስድስት ልጆች አያት እንዲሆኑም አድርገዋቸዋል። በዚህም በጣም ደስተኛ እንደሆኑ ፊታቸው ላይ በሚነበብ መልኩ ይናገራሉ።

ወይዘሮ ማርያ በጉብዝናቸው ዳኛ እስከመሆን ደረጃ ደረሱ፤ በዚህ የዳኝነት ሥራቸው ላይ እያሉ ግን የሚያዩት ክፍተት በተለይም በሴቶች ላይ የሚደርሱ በደሎች የፍርድ ሂደት መጓተቶች፣ ምቾት አልሰጥ አላቸው። ስለዚህ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ማሰብ ጀመሩ።

“……ተበዳይ ሴቶች ምንም እንኳን ወደፍትህ አካል ቢሄዱም የሚደርሱባቸው ችግሮች ተደራራቢና የፍትህ ሂደቱን እንዳይቀጥሉ የሚያደርጉ ናቸው። ብዙዎቹ ከፍተኛ የሆነ የአቅም ማነስ ስላለባቸው ጠበቃ አቁመው መከራከር አይችሉም። በጸብም በበደል ከቤት ከወጡ በኋላ የሚያርፉበት አይኖራቸውም። ፍርድ ቤት ቆመው ስለደረሰባቸው ነገር እንኳን ለዳኛ ማስረዳት ይከብዳቸዋል። ይህንን ሳይ በቃ በሙያዬ ለተበዳይ ሴቶች የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ ብዬ አሰብኩ እና ከጓደኞቼ ጋርም ተማከሩ። ›› ይላሉ።

የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር መቋቋም

ከላይ ያነሳኋቸውና በሴቶች ላይ የሚፈጠሩ በደሎች የእነሱም የደረሰባቸውን በደል ለማስረዳት አለመቻል፤ ከዛ በኋላ ከልጆቻቸው ጋር ወይም ለብቻቸው ለመኖር በጣም መቸገር ማህበሩን ለማቋቋም ምክንያት ሆናቸው።

“…….እኛ ባየነውና በተረዳነው መሠረት ወንዶቹ በዳዮች ቢሆኑም ገንዘብ አላቸው ጥፋታቸውን ለማስተባበል ጠበቃ ይቀጥራሉ። ሌላም ሌላም ነገር ያደርጋሉ፤ ቢያንስ አስፈራርተው አልያም ገንዘብ ከፍለው የሀሰት ምስክር ማግኘት የሚችሉ ናቸው። ሴቶቹ ደግሞ በተገላቢጦሽ ምንም አቅም የላቸውም ይህ እንግዲህ እኔንም ጓደኞቼንም ያሳስበን ስለነበር ማህበሩን እውን እንድናደርገው ተጨማሪ አቅም ፈጠረልን” ይላሉ።

በማህበሩም ለተጎጂ ሴቶች ነፃ የሕግ ምክር አገልግሎትና ፍርድ ቤቶች ላይ ቀርቦ በነፃ የመከራከር ሥራ መሥራት ጀመሩ። ኋላም ወይዘሮ ማርያ ከዳኝነት ሥራቸው ወጥተው ጠበቃ ሆኑ፤ ይህም ቢሆን ግን ለሴቶች የሚሰጠው አገልግሎት አልተቋረጠም ነበር።

ይህንን አገልግሎት እየሰጡ ባሉበት ሁኔታ ሌላ ችግር አስተዋሉ። ሴቶቹ የሕግ ምክርና ድጋፍ ያገኛሉ፤ ፍርድ ቤትም ገብተው ይከራከሩላቸዋል። ነገር ግን ማደሪያ፣ ልብስ፣ ምግብ ደግሞ ማግኘት ችግር ሆነ በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

“……ሴቶች ፍርድ ቤት እናገኛቸዋለን፤ በተለያየ ሰውም ወደ እኛ ማህበር ይመጣሉ፤ የሕግ አገልግሎቱን ይፈልጉታል። ነገር ግን የወጣነው ልጆች ይዘን ነው። የት እንውደቅ? ምን እንብላ? ይላሉ። የምንችለውን ከኪሳችን እያዋጣን እንሰጣለን፤ ነገር ግን ያ በቂ ሆኖ ችግራቸውን ሊፈታ እንደማይችል ደግሞ እናውቃለን። ታዲያ ምን ይሁን? ምን ይደረግ የሚለው ሌላ አስጨናቂ ነገር ሆነ” ይላሉ።

በዚህ መካከል ግን ድሬዳዋ ላይ አንዲት ልጅ ተደፍራ ሞተች የሚል ዜና በየመገናኛ ብዙሃኑ ተሰራጨ። በዚህ ጊዜ ደግሞ አብዛኛው ሰው የእናንተ ማህበር ምን እየሰራ ነው? የሚል ጥያቄውን አነሳ የሚሉት ወይዘሮ ማርያ፤ ችግሩን ለመፍታትም የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር እንዳለ ሆኖ ሌሎች በጾታ ላይ ከሚሰሩ ማህበራትና ድርጅቶች ጋር በጋራ በመቀናጀት ዘመቻ ተደረገ በማለት ይናገራሉ።

እነ ወይዘሮ ማርያ ከመሰሎቻቸው ጋር ያካሄዱት ዘመቻ 6 ወራት የቆየ ነበር፤ በዚህም በጥቃት ላይ ህብረተሰቡ ግንዛቤው ያድግ ዘንድ ሥራዎች ተሰሩ። በትምህርት ቤቶች፣ በእድርና በተለያዩ አካባቢዎች ሁሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራው ተደረገ። በመጨረሻም ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ በትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ጥያቄዎች ለፓርላማና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ እንደቀረቡ ያስታውሳሉ።

በዚህም መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶት የተለያዩ ሕጎች ወጡ፤ የወንጀል ሕጉም ተሻሻለ። ነገር ግን በዚህ ስድስት ወር ዘመቻ ብቻ ሥራው ማብቃት የለበትም ጥቃቱ እንዳለ ነው በማለት እንቅስቃሴውን ካደረጉት ሴቶች መካከል ወይዘሮ ማርያን ጨምሮ የተወሰኑት ወደኋላ ቀርተው በቃ ለተበደሉ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ማረፊያ የሚሆን ማዕከል ማቋቋም አለብን ብለው ወሰኑ።

እዚህ ውሳኔያቸው ላይ ስላደረሳቸው ምክንያት ሲናገሩም “……. አንዲት ሴት ተበደልኩ ብላ ፖሊስ ጋር ትመጣለች ፖሊስም ሥራውን ይጀምራል፤ ነገር ግን ጉዳዩ አልቆ ዓቃቤ ሕግ ጋር ሲደርስና ሴቶቹ ለምስክርነት ሲፈለጉ ቋሚ አድራሻ ስለማይኖራቸው አይገኙም። በዚህ መካከል ምስክር ስላልቀረበ በሚል ፋይሉ ይዘጋና ወንጀለኛው በነፃ ይለቀቃል። ይህ ደግሞ በጣም ከባድ ችግር ነው፤ በመሆኑም እኔና መሰሎቼ ይህንን ችግር የሚፈታ በደል የደረሰባቸው ሴቶች ቢያንስ ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክርነታቸውን ሰጥተው ወንጀለኛው ተገቢውን ቅጣት እስኪያገኝ ማረፊያ ይኑራቸው በማለት ነው ሃሳቡን የጀመርነው” ይላሉ።

ምስረታ የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር

ለእዚህ ማህበር ምስረታ በወቅቱ የነበሩ ባለሙያዎች ሁሉም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያበረክቱም ወይዘሮ ማርያ ጊዜውና አቅሙ ስለነበራቸው የምስረታውን ሰፊ ሥራ የሠሩት እርሳቸው ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜም የራሳቸውንም የሚያውቋቸውንም ሰዎች አስቸግረው ገንዘብ በማግኘት ቤት ተከራይተው ለስድስት ሴቶች መጠለያን ሰጡ።

ከዛ በኋላም ለበርካታ ሴቶችና ሕፃናት መጠጊያ እየሆኑ የብዙዎችን ችግር እየተካፈሉ በዳዮች ተገቢውን ቅጣታቸውን እንዲያገኙ እያደረጉ። ሴቶቹም ከወጡ በኋላ ምን ሆኜ እኖራለሁ እንዳይሉ በተለያየ መልኩ እያገዙ 18 የስኬት ዓመታትን መጓዛቸውን ወይዘሮ ማርያ ይናገራሉ።

“……. ለስድስት ተበዳይ ሴቶች ማረፊያ በመስጠት የጀመረው ማዕከል፤ ዛሬ ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ አዳማ ፣ሀዋሳ፣ ደሴ፣ ደብረብርሃን፣ ወልደያና ቆቦ ላይ ቅርንጫፎቹን በመክፈት በቀን ለበርካታ ሴቶች አገልግሎት እየሰጠ ነው” ይላሉ።

ተበዳይ ሴቶች ወደ ማዕከሉ ከተለያዩ ቦታዎች ይመጣሉ የሚሉት ወይዘሮ ማርያ፤ አሁን ላይ ፖሊስ እንደዚህ ዓይነት ክሶችን ሲጀምር ዳር እስከሚያደርሰው ድረስ በሕግ ባለሙያ ሴቶች አማካይነትም ሆነ በራሱ መንገድ ሴትየዋን ወደ ማዕከሉ ያመጣታል ፤ ማረፊያ ታገኛለች የፍትህ ሂደቷን ተከታትላ ውጤት እያገኘች ነው ይላሉ።

ማዕከሉ ሴቶች በተበደሉበት በደል የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግም ባሻገር በቀጣይ ሕይወታቸው በራስ መተማመን እንዲኖራቸው፣ የሕክምናና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። ከሥነ ልቦና ጉዳታቸው እንዲያገግሙ ይታገዛሉ፤ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ደግሞ ማንበብ መጻፍ እንዲችሉ የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል ይላሉ።

በማቆያው የሚገቡ ሴቶች በብዙ መልኩ እንዲታደሱና እንዲታነጹ ከገቡበት የሥነ ልቦና ቀውስ እንዲያገግሙ ብዙ ሥራ ስለሚሰራባቸው እነሱ ያገኙትን እድል ሌሎች እንዲያገኙ በማሰብ፤ በቃ እኛ ደግሞ ለቀጣዮቹ ቦታ እንልቀቅ በማለት በራሳቸው ፍቃድ የሚሰሩትን አስበው የሚወጡም ብዙ ስለመሆናቸው ያብራራሉ።

ማዕከሉም ሙያውን ከማስተማሩ ባሻገር መቋቋሚያ ሰጥቶ የሶስት ወር የቤት ኪራይ ከፍሎ ከመሸኘቱም በላይ ‹‹ወደ ሀገሬ እገባለሁ›› የሚሉ ሲኖሩ ደግሞ፤ ወደምትሔድበት አካባቢ ያለው ሁኔታ ታይቶ መሥራት መኖር የሚያስችላት ነገር መኖሩ ተረጋግጦ የምታርፍባቸው ሰዎች እነማን ናቸው የሚለው ተለይቶ ትራንስፖርት ተከፍሎ ከባለሙያ ጋር አንዳንዴም ብቻቸው ይላካሉ ይላሉ።

በተማሩት ሙያ እስከ አራት ኮከብ ሆቴሎች በሕፃናት ማሳደጊያ ቦታዎች የገቡ ብዙ ሴቶች ያሉ ሲሆን፤ የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ደግሞ 10 ሴቶችን ከነልጆቻቸው በመውሰድ ሥራ እንደሰጣቸው ይናገራሉ። በዚህ ሁኔታ ኑሯቸውን እንደ አዲስ የጀመሩ ብዙ ስለመሆናቸው ነው ወይዘሮ ማርያ የሚያብራሩት።

ሌላውና በብዙ እየደገፋቸው ያለው እናት ባንክ ሲሆን፤ አሁን እንኳን በቅርብ 10 ልጆችን በመቅጠር ትልቅ ትብብር እያደረገላቸው ስለመሆኑ ወይዘሮ ማርያ ይናገራሉ። ከዛ በተረፈ ግን ሴቶቹ በማዕከሉ በሚኖራቸው ቆይታ የቀሰሙትን እውቀት በመያዝ እንዲሁም በመተባበርና በመረዳዳት አብረው የሚሰሩ አብረው የሚኖሩ በጋራ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ ብዙ ናቸው የሚሉት ወይዘሮ ማርያ፤ ከዚህ ሁሉ ባለፈ ደግሞ እንደ ማህበር ተደራጅተው የሕፃናት ማቆያ እንዲሁም የዶሮ እርባታ ሥራን ለመጀመር የሚንቀሳቀሱም መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ደስ የሚያሰኛቸው

ወይዘሮ ማርያ ‹‹እኔ ከምንም ነገር በላይ በሕይወቴ ደስ የሚያሰኘኝ ተጎድታ ብዙ በደል ደርሶባት በዛውም ላይ ደግሞ የጤና ችግሩ እርግዝናው አልያም ሕፃን ልጅ ይዛ በብዙ መከፋት ውስጥ የነበረች ሴት እኛ ጋር መጥታ ማረፊያ ስታገኝ፤ ታክማ ስትድን፤ ከሥነ ልቦና ሰብራቷ ስትላቀቅ የበደላት ሰው ፍርድ ሲያገኝ ማየትን የመሰለ የለም። ›› ይላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በቅርብ ቤተሰብ ተደፍረው አልያም ሌላ ጉዳት ደርሶባቸው እነርሱ ጋር የሚመጡና የክስ ሂደታቸው አልቆ እነሱም አገግመው መሄጃ የማይኖራቸውን ልጆች እድሉን ሰጥተው አስተምረው ውጤታማ ሲሆኑ ትልቅ ደስታ እንደሚሰማቸው እና ‹‹ እንኳንም ወደዚህ ሥራ ገባሁ›› እንደሚያስብላቸው ይናገራሉ።

መልዕክት

አሁን ላይ በጾታዊ ጥቃት በኩል ያለው ግንዛቤ ከፍ እያለ መጥቷል፤ በፊት ዝም በሉ የቤተሰብ ጉድ አታውጡ እየተባለ የሚባለው አሁን የለም። ይህ ደግሞ ጥቃቱ የበዛ አስመስሎታል። ያም ሆነ ይህ ግን አሁንም ከንግግር ያለፈ ሥራን የሚጠይቅ ዘርፍ ነው። የእውነት ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገም ታች ተወርዶ ከትምህርት ቤት ጀምሮ መሥራት አማራጭ የሌለው መፍትሔም ነው ይላሉ።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You