‹‹ዘላቂው የሰላም መንገድ… ምክክር!››

ጦርነት የሰው ልጅ የዘመናት ታሪክ ሲሆን፤ ውድመትን፣ መከራን እና ኪሳራን እየተወ የሚኖር አሳዛኝ እውነታ ነው። በአንድ ሀገር የሚኖሩ ብሔር እና ብሄረሰቦች እርስ በርስ ሲጋጩ ደግሞ መዘዙ አስከፊ ነው። በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ ተዋጊዎቹን ብቻ ሳይሆን ንጹሐን ዜጎችን፣ መሠረተ ልማቶችንና አካባቢን ጭምር የሚጎዳ ነው። የጦርነት ጠባሳ ጥልቅ እና መራር ነው።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደር የለሽ ውድመት እና ስቃይ ያስከተለ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊ ከሆኑ ክስተቶች አንዱ ነው። ጦርነቱ ታላላቅ የዓለም ኃያላን መንግሥታት እና አጋሮቻቸውን ያሳተፈ፤ ከ70 እስከ 85 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ነው።

እ.ኤ.አ. በ1945 ዩናይትድ ስቴትስ በሄሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ ያደረሰቻቸው የቦምብ ጥቃቶች የጦርነትን አውዳሚነት ማሳያ ምልክት ነው። እነዚህ የአቶሚክ ቦምቦች በተጣሉበት ቅጽበት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጃፓናውያን ሲገድሉ፤ በሕይወት በተረፉ ሰዎች ላይ የረጅም ጊዜ የጤና እክል አስከትሏል። በፍንዳታዎቹም ከተሞቹ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል፣ በተረፉት ላይ ያደረሰው የሥነ ልቦና ጉዳት ለትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል።

የቅርብ ጊዜ ታሪክ አካል በሆነው የኢራቅ ጦርነት እ.ኤ.አ. በ 2003 በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው ጥምር ጦር ኢራቅን ወረረ፤ በአካባቢውም ሰፊ ትርምስ፣ እና አለመረጋጋት አስከተለ። ግጭቱ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ኢራቃውያን ሞት ምክንያት ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል። በተጨማሪም በሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የመኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በመሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ሊመዘን የሚችል አይደለም። ለቤተሰብ መበታተን እንዲሁም ለማህበረሰብ ሁከት እና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። በጦርነቱ የነዳጅ ዘይት ብክነት እና የወደሙ መሠረተ ልማቶች ብክለት ተደማምረው የኢራቅን ሕዝብ ስቃይ ክፉኛ ሲያባብሱት አይተናል።

በሶሪያ የተከሰተው እና አሁንም ያላባራው የእርስ በርስ ግጭት የጦርነትን አውዳሚነት ሌላው ማሳያ ነው። እ.ኤ.አ. በ2011 የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ሶሪያ ፋታ በሌለው ጦርነት ውስጥ ናት። በአየር ላይ በተፈፀሙ የቦምብ ጥቃቶች ለሚሊዮኖች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። እንደ አሌፖ እና ሆምስ ያሉ ከተሞች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። በአንድ ወቅት የበለፀጉ የከተማ ማዕከላት ወደ ውድመት እና ተስፋ መቁረጥ ተለውጠዋል። ሆስፒታሎችን እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደረገው ኢላማ ሠብዓዊ ቀውሱን በማባባስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሶሪያውያን ርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል።

በኬሚካል ጦር መሣሪያ እና ቦምቦችን በመጠቀም የተካሄደው ጦርነት በንፁሃን ዜጎች ፣ ሴቶች እና ህጻናት ላይ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ስቃይ በማድረስ በሰው ልጆች ሕሊና ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሏል።

ከእነዚህ ልዩ ምሳሌዎች ባሻገር፣ ጦርነት በማኅበረሰቦች ላይ ያለው ሰፊ ተፅዕኖ ሊገለጽ አይችልም። እንደ መንገድ፣ ድልድይ እና የኃይል ማመንጫዎች ያሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን መውደም፤ የኢኮኖሚ ልማትን የሚያደናቅፍ እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለማግኘት እንቅፋት የሚሆን ነው።

አንድ ሀገር ከግጭት በኋላ ለማገገም እና ራሷን መልሳ ለመገንባት በምታደርገው ጉዞ ላይ ከፍተኛ የጉልበት እና የገንዘብ ወጪን የሚጠይቅ ነው። ከዚህም በላይ በጦርነት የሚደርሰው የሥነ ልቦና ጉዳት ለብዙ ዜጎች በቀላሉ የማይፈወስ ጥልቅ የስሜት ጠባሳን የሚጥል ነው። በዓለማችን ውስጥ በጦርነትና በግጭት ውስጥ እያደጉ ያሉ ልጆች ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ ናቸው። ለትምህርት ማጣት፣ ለቤተሰብ አባላት እጦት እና ለጥቃት መጋለጣቸው በደህንነታቸው ላይ ዘላቂ ተጽእኖ ሊያመጣ ይችላል።

በጦርነት ምክንያት የሚደርሰው ውድመት በአካላዊ መሠረተ ልማት እና በሰው ሕይወት ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ባህላዊ ቅርሶች እና ታሪካዊ ምልክቶችም ያወድማል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ጦርነቶች የባህል ቦታዎች ላይ ሆን ተብሎ እንዲነጣጠሩ እና እንዲወድሙ በማድረግ የወደፊቱን ትውልድ ውርስ ያጠፋሉ።

ጦርነት በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ በቸልታ ማለፍ አይቻልም። የኬሚካል ጦር መሣሪያዎች አጠቃቀም፣ የደን ጭፍጨፋ፣ የዘይት መፍሰስ እና በየቦታው የተቀበሩ ቦንቦች ፍንዳታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የሥነ-ምህዳር ጉዳት ያስከትላል። ጉዳቱም ግጭቱ ካበቃ በኋላ ለአስርተ ዓመታት ሊቆይ ይችላል። ይህ የአካባቢ መራቆት በአካባቢው ሕዝብ ላይ የጤና ጠንቅ መሆን ብቻ ሳይሆን ከጦርነቱ በኋላ እንደገና ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እና ኢኮኖሚያዊ ማገገምን ያደናቅፋል።

የአውዳሚ ጦርነት ተጽእኖ የሀገራትን ድንበር የሚሻገር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እርስ በርስ በተሳሰረ ዓለም ውስጥ የትጥቅ ግጭቶች ለጎረቤት ሀገሮችና ክልሎች ብዙ መዘዝ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ጥቃትን የሚሸሹ የስደተኞች መጉረፍ ሠብዓዊ ቀውሶችን ይፈጥራል። የሀብት መጨናነቅ እና የጎረቤት ሀገራትን ርዳታ የመስጠት አቅም ይፈትሻል። በተጨማሪም ግጭቶች ወደ ሰፊ ክልላዊ አለመረጋጋት ሊሸጋገሩ ይችላሉ፣ ይህም ወደ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ያመራል።

የሀገራችን የቅርብ ጊዜ ትውስታ የሆነው የሰሜኑ ጦርነት ለበርካቶች ሞት፤ የርሃብ እና የስደት ምክንያት፤ ለጾታዊ ጥቃት፤ ለህጻናት የሥነልቦና ቀውስ፤ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ውድቀት እና ለመሳሰሉት አሉታዊ ተጽእኖ ምክንያት ሆኗል።

የዓለማችን ታሪክ እንደሚያሳየው የትኛውም ጦርነት መጨረሻው በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር እንደሆነ ያመላክታል። ስለሆነም ብዙ ውድመቶች ከመከሰታቸው በፊት ይህንን አማራጭ ለምን መከተል እንደማይቻል ግልጽ ባይሆንም ሀገራትና ፖለቲከኞች ከታሪክ በመማር የትኛውንም ትግል በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ ይገባቸዋል። አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚያስፈልግ የቀደመውን የሰው ልጅ ታሪክ ማስታወስ ያስፈልጋል።

ከታሪካችን ተምረን ተጨማሪ ጥፋትን ለመከላከል ያለመታከት መሥራታችን የግድ ነው። ሰላምን ለማስፈን፣ ዓለም አቀፍ ሕግን ለማስከበር እና የግጭት መንስኤዎችን ለመፍታት በተቀናጀ ጥረት ብቻ መጪውን ትውልድ ከጦርነት ጥፋት ለመታደግ መሥራት ይኖርብናል።

በተለያዩ ግጭቶችና ጦርነቶች ለምነን እና ተበድረን የገነባናቸውን መሠረተ ልማቶች እያሳጣን መኖር የኋሊት ጉዞ ነው። ጥያቄህ እንዲመለስ ለውጊያ ተነስ ከሚል ብሂል ወተን፤ ጦርነት በየትኛውም ዓለም የየትኛውንም ቡድን ችግር ሲፈታ አለመታየቱን አምኖ በጦርነት የተሰላቸውን እና ለጥቅሙ እቆምለታለሁ ለሚለው ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄን ማቅረብ፤ የሰላማዊ ትግል አማራጮችን በማሳየት ሀገሪቱን ከውድቀት መከላከል ይገባዋል፤ መልዕክቴ ነው። ሰላም!

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You