ለብዙዎች የተስፋ ብርሃን የሆነው ‹‹አዲስ ብርሃን››

ዓለም የተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በየቀኑ እየተመለከተች ባለችበት በዚህ ዘመን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መከራዋና ሰቆቃዋም እየበዛ ነው። በየቦታው የሚፈጠሩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ነዋሪዎቿን ለስቃይና መከራ መዳረጋቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ ችግሮች ደግሞ በርካታ ማኅበራዊ ቀውሶችን ፈጥረዋል።

‹‹ቅንነት ሞተ፣ መተዛዘን ጠፋ …›› የሚሉ ድምጾች ደጋግመው ይደመጣሉ። በተለይም የኢትዮጵያውያን መገለጫ ተደርገው የሚቆጠሩት ባህርያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩና እየተዳከሙ እንደሄዱ የሚናገሩ ወገኖች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። የድህነት መንሰራፋትም ሌላው ራስ ምታት ነው።

ድህነትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለተንሰራፋባቸው ማኅበረሰቦች፣ የበጎ አድራጎት ተግባራት የማኅበራዊ ፈውስ ሁነኛ መገለጫዎችና መሳሪያዎች ሆነው ያገለግላሉ። የበጎ አድራጎት ተግባራት ገንዘብን፣ ፍቅርን፣ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ እውቀትንና ሌሎች ሀብቶችን ከራስ ቀንሶ ለሌሎች በማካፈል የሌሎችን ችግር ለማቃለል፤ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን ለማጠንከር እንዲሁም መተሳሰብና መከባበር የሰፈነበትን ማኅበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ አወንታዊ ሚና አላቸው።

መረዳዳት የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነና የእርስ በእርስ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን አጠንክሮ የኖረ ተግባር ነው። መረዳዳት ባይኖር ኖሮ አሁናዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አሁን ከሚታየው የተለየ ይሆን ነበር። ይህ የመረዳዳትና የመተጋገዝ በብዙ መንገዶች ይከወናል። በተናጠልና በጥቂት ግለሰቦች ስብስብ ከሚከናወኑ የመረዳዳት ተግባራት በተጨማሪ፣ መደበኛና ሕጋዊ አሰራሮችን ተከትሎ የበጎ አድራጎት ተቋማትን የማቋቋምና የመሥራት ተግባርም በስፋት የሚታወቅ አሰራር ነው። በኢትዮጵያ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ምግባረ ሰናይ ዓላማዎችን አንግበው የተቋቋሙና የሚንቀሳቀሱ በርካታ የበጎ አድራጎት ተቋማት አሉ።

የበጎ አድራጎት ተቋማቱ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሕክምና እንዲያገኙ፣ መጠለያና ምግብ የሚያስፈልጋቸውም መጠለያና ምግብ እንዲያገኙ፣ የትምህርት ቁሳቁስ የተቸገሩ ቁሳቁሱን አግኝተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ ፣ አሳዳጊ ያጡ ሕፃናት፣ ጧሪ ያጡ አባቶችና እናቶችን በመደገፍ ፣ወዘተ.. እየሰሩ ይገኛሉ።

እነዚህ ተቋማት ለእነዚህ የተቸገሩ ወገኖች በሚያደርጉት ድጋፍ ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው አስችለዋል፤ እያስቻሉም ይገኛሉ። ሞራልና ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ማኅበረሰብና ሀገር ለመገንባት ቀላል የማይባል ሚና ይጫወታሉ።

ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፎችን በማድረግ እነዚህ ወገኖች ከችግሮቻቸው ተላቅቀው በማኅበረሰብና ሀገር ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማድረግ ዓላማን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ‹‹አዲስ ብርሃን›› የበጎ አድራጎት ማኅበርም ከእነዚህ ምግባረ ሰናይ ተቋማት መካከል ይጠቀሳል።

የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም አዳሙ እንደሚያስረዳው፤ ‹‹አዲስ ብርሃን›› የበጎ አድራጎት ማኅበር ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በቁጥር 4460 በተሰጠው ፈቃድ የተመሰረተው በ2012 ዓ.ም ሲሆን፣ ዓላማውም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና አረጋውያን ድጋፍ ማድረግ ነው። ‹‹የተጎዱና ኑሯቸውን በየጎዳናው ላይ ያደረጉ ሕፃናት እንዲሁም ሥራ አጥ ወጣቶችን በብዛት መመልከት የተለመደ ሆኗል። እኛም ይህን ችግር ለማቃለል የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለብን በማመን ማኅበሩን አቋቋምን›› በማለት ስለማኅበሩ አመሰራረት ያወሳል።

‹‹አዲስ ብርሃን›› የበጎ አድራጎት ማኅበር በርካታ ተግባራትን የሚያከናውን ሲሆን፤ ለሕፃናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን ከሚያደርጋቸው ቀጥተኛ ድጋፎች (የምግብ፣ አልባሳት…) በተጨማሪ የትምህርትና የሥራ እድሎችን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ማኅበሩ ከአባላት የተሰባሰቡ ድጋፎችን በመያዝ ድጋፍ የሚፈልጉ ግለሰቦች ወደሚኖሩባቸው ስፍራዎች በመሄድ ድጋፎችን ያስረክባል።

‹‹ድጋፍ የምንሰጠው በየቤቱ በመንቀሳቀስ ነው። ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ዝርዝር ከክፍለ ከተሞች ይላክልናል። ለካንሰርና ሌሎች ህሙማንን ድጋፎችን እንሰጣለን። ከፖሊስ ጋር በመተባበር ወድቀው የተገኙ ሕፃናት ደጋፍ እንዲሰጣቸው እናደርጋለን። ደም እንለግሳለን፤ እገዛ ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር እገዛ እናደርጋለን›› በማለት ሰብሳቢው ስለማኅበሩ የድጋፍ ተግባራት ይገልፃል።

‹‹አዲስ ብርሃን›› የበጎ አድራጎት ማኅበር በኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ ወቅት በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራትን እንዳከናወነ የማኅበሩ ሰብሳቢ ያብራራል። ‹‹በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ብዙ ድጋፎችን አድርገናል ሲል ያብራራል።

በወቅቱ የአትክልት ተራ ወደ ጃንሜዳ ተዛውሮ ስለነበር 150 በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ፣ ሰው ተራርቆ እንዲገበያይ አድርገናል። በኤግዚቢሽን ማዕከል በነበረው የማዕድ ማሰባሰብ ተግባር ላይም በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት ተሳትፈናል። ለዚህ ሥራችንም ከአዲስ አበባ ከንቲባ ቢሮ የእውቅናና የምስጋና ሰርተፊኬት ተሰጥቶናል። በለገሃር አካባቢም የፅዳት ሥራዎችን ሰርተናል›› በማለት ማኅበሩ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ስላከናወናቸው የበጎ ፈቃድ ተግባራት ያስታውሳል።

ማኅበሩ ለወጣቶች የትምህርትና የሥራ እድሎችን ለመፍጠር የሚያግዙ ተግባራትንም ያከናውናል። በአንበሳ አውቶብስ ድርጅት የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው በመኪና ማጠቢያዎች፣ ነዳጅ ማደያዎችና ቲኬት መቁረጫ ስፍራዎች ላይ እንዲሁም በምድር ባቡር ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ወጣቶች የዚህ ተግባር ማሳያዎች ናቸው። ከ300 በላይ ወጣቶች በተለያዩ ኮሌጆች ውስጥ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በመኪና ማሽከርከርና በሌሎች ሙያዎች የትምህርት እድል እንዲያገኙም አድርጓል።

ማኅበሩ በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በማኅበረሰብና በአካባቢ ልማት የሚያከናውናቸው ተግባራትም የኅብረተሰቡን ኑሮ በማሻሻል የተሻለች ሀገር እውን የማድረግ ዓላማውን ለማሳካት ያግዛሉ ብሎ ያምናል። ‹‹ጠንካራ ማኅበረሰብ ዘላቂ ለውጥን የመፍጠር አቅም አለው›› ብሎ የሚያምነው ማኅበሩ፣ የኅብረተሰብን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ለማፋጠን ያግዛሉ ብሎ ባሰባቸው ተግባራት ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። በተለያዩ ዘርፎች ላይ ከተሰማሩ ግብረ-ሰናይ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን በመፈራረም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካላት ድጋፎችን ለመስጠት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን ያደርጋል።

ማኅበሩ ታኅሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም አምስት ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉንም አቶ ኃይለማርያም ይናገራል። ፕሮጀክቱ ‹‹ሶሻል ላውንድሮ ሰርቪስ›› (The Social Laundromat Services Project) ይባላል። ይህ ፕሮጀክት በተለይ ሥራ አጥ ወጣቶችንና እናቶችን ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ አለው።

ፈጣን የልብስ እጥበት አገልግሎት በመስጠት ተግባር ላይ ያተኮረውና በሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት፣ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ ችግር ፈቺ ፕሮጀክት መሆኑን አቶ ኃይለማርያም ጠቁሟል። ‹‹አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በብዙ ስፍራዎች፣ በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ፣ የልብስ ማጠቢያና ማስጫ ችግር እንዳለ ይታወቃል። የማኅበሩ ፕሮጀክት ለዚህ ችግር አማራጭ መፍትሔ መሆን ይችላል።›› ሲልም አብራርቷል።

‹‹ፕሮጀክቱ ልብስን በ40 ደቂቃ አጥቦ የማስረከብ ሥራ ነው። በዚህም ሥራ አጥ ወጣቶችና እናቶች የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ለፕሮጀክቱ መሳካት ድጋፍ ሊያደርጉ ከሚችሉ የውጭ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል›› በማለት ስለፕሮጀክቱ ያስረዳል።

‹‹አዲስ ብርሃን›› የበጎ አድራጎት ማኅበር ሥራዎቹን ሲያከናውን የሚያጋጥሙት ችግሮች እንዳሉ የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ይገልፃል። ‹‹ዋናው ችግር የድጋፍ እጥረት ነው። ድጋፍ የሚፈልጉ ብዙ የበጎ አድራጎት ተቋማት በመኖራቸው ድጋፍ ማግኘት አዳጋች ሆኖብናል። ይህ የድጋፍ እጥረት የቤት ኪራይ ክፍያ ወጪን ጭምር ለመሸፈን ፈተና ይሆናል። ሌላው ችግር የበጎ ፈቃደኞች እጥረት ነው። የበጎ አድራጎት ሥራዎችን የምናከናውነው በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ነው። የበጎ ፈቃደኞች እጥረት በሥራዎቻችን ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል›› ይላል።

70 አባላትን ይዞ የተቋቋመው ‹‹አዲስ ብርሃን›› የበጎ አድራጎት ማኅበር፣ ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና 200 በጎ ፈቃደኛ አባላት አሉት። ማኅበሩ እስካሁን ድረስ ባከናወናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት ከአንድ ሺ 200 በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል። እነዚህ ዜጎች ማኅበሩ ባደረጋቸው ቀጥተኛ ድጋፎችና በፈጠራቸው የሥራና የትምህርት እድሎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ማኅበሩ ከውጭ የሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሌለው እና የበጎ አድራጎት ተግባራቱን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኘው ከአባላት መዋጮና ከሀገር ውስጥ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ተቋማት መሆኑን ጠቅሶ፣ የድጋፍ እጥረቱ ሥራውን ይበልጥ በማስፋት ከዚህ የበለጠ ቁጥር ያላቸውን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ትልቅ መሰናክል እንደሆነበት የማኅበሩ ሰብሳቢ ይገልፃል።

እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለፃ፣ ማኅበሩ ከመደበኛ የድጋፍ፣ የትምህርትና የሥራ እድል ፈጠራ ተግባራቱ በተጨማሪ ‹‹ሶሻል ላውንድሮ ሰርቪስ›› ፕሮጀክትን ተግባራዊ ማድረግ ዋናው እቅዱ ነው። ማኅበሩ ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ድጋፎችን ለማግኘት ጥረት እያደረገ ይገኛል። የፕሮጀክቱ ትግበራ እስካሁን ያልተጀመረው በገንዘብ እጥረት ምክንያት ነው።

‹‹አዲስ ብርሃን›› የበጎ አድራጎት ማኅበር ከአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ የሚገልጸው አቶ ኃይለማርያም፣ የመንግሥት ተቋማት የማኅበሩን ሥራዎች ለመደገፍ የሚያስችሉ ድጋፍ ደብዳቤዎችን እንደሚሰጧቸው ይናገራል። ማኅበሩ ከሌሎች ተቋማትም የቁሳቁስ፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን፣ የበጀትና ሌሎች ድጋፎችን ቢያገኝ ሥራዎቹን በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን እንደሚያግዘው ያስረዳል።

‹‹አዲስ ብርሃን›› የበጎ አድራጎት ማኅበር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሏቸው ማህበረሰብ ተኮር ተግባራትን ሲያከናውን በመቆየቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ከበርካታ ባለድርሻ አካላት የዕውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀቶች ተበርክተውለታል።

በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ የተሰማሩ ተቋማት ለተቋቋሙበት እውነተኛ ዓላማ በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ኃይለማርያም ይናገራል፡ ‹‹የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሥራዎቻቸውን ሲያከናውኑ የሚያጋጥሟቸው ብዙ ችግሮች (የቢሮ፣ የገንዘብ…) ይኖራሉ። አንዳንድ ተቋማት ከመንግሥት ድጋፍ ተደርጎላቸው ይሰራሉ። ድጋፍ የሚደረግላቸውና ማበረታቻ የሚሰጣቸው ለተቋቋሙበት እውነተኛ ዓላማ በትጋት እንዲሰሩ ነው። ስለሆነም ዓላማቸውንና የሚደረግላቸውን ድጋፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት በትክክል መሥራት ይኖርባቸዋል›› በማለት ይመክራል።

አንተነህ ቸሬ

 

Recommended For You