
መላ የክርስትና እምነት ተከታዮች ላለፉት ሁለት ወራት ለሚጠጉ ጊዜያት በዐብይ ፆም ውስጥ ቆይተዋል:: በዚሁ ወቅትም ጸልየዋል፤ መፅውተዋል:: ራሳቸውን ለፈጣሪያቸው ለማስገዛት ከማናቸውም ሥጋቸውን ሊያዳብሩ ከሚችሉ ምግቦች በመታቀብ፣ ከክፉ ተግባራት ሁሉ በመራቅ ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል:: ፈተናዎችን ለማሸነፍ ታትረዋል:: ካላቸው ቀንሰው የተቸገሩ ወገኖቻቸውን ለመርዳት ታላቅ መንፈሳዊ ተግባር አከናውነዋል::
ይህ ትልቅ ራስን የመግዛት፣ ሌሎችን የማሰብ፣ ለፈተናዎች ያለመበገር ተግባር ከፆሙ በኋላም በተለያዩ መስኮችም መቀጠል ይኖርበታል:: ይህ ልምምዳቸው የሕይወታቸው መርሕ ይሆን ዘንድም መትጋት ይጠበቅባቸዋል::
በፆሙ ወቅታቸው ስለሰላም ጸልየዋል:: ፈጣሪያቸው ሀገራቸውን ሰላም እንዲያደርግላቸው እንዲጠብቅላቸው ተማጽነዋል፤ የታመሙትን እንዲፈውስ፣ መውጣት መግባታቸውን እንዲያሳምር፣ የዘሩት እንዲያፈራ፣ የጀመሩት በስኬት እንዲጠናቀቅ ወዘተ ተማጽነዋል::
ይህ ሁሉ ሰብዓዊነት እንዲጸና፣ አንዱ ለአንዱ እንዲያስብ፣ መረዳዳት እንዲጎለብት፣ ተግቶ በመሥራት ራስን ሕዝብንና ሀገርን ማሳደግ ስር እንዲሰድ በእጅጉ ያስፈልጋል::
ኢትዮጵያውያን ብዙ ፈተናዎችን ተሻግረው ነው ሀገራቸውን ጠብቀው፣ ተፋቅረው አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት:: አሁንም ብዙ ፈተናዎች አሉባቸው፤ በቀጣይም ብዙ ፈተናዎች አይገጥሟቸውም ተብሎም አይታሰብም:: ቆም ብለው ሊያስቧቸው፣ አሻግረው ሊመለከቷቸው የሚገቡ ብዙ ሀገራዊ ሥራዎች ይጠብቋቸዋል::
ድህነትን አሽቀንጥረው ለመጣል፣ እርስ በርስ የሚያጋጩዋቸውን ጉዳዮች በጋራ ለመፍታት በጽናት መሥራት ይኖርባቸዋል:: ከሀገራቸው አሻግረው መመልከትም ይጠበቅባቸዋል::
ጊዜው ዓለም አቀፍ ውድድር የጦፈበት ነው:: በእዚህ ውድድር በመሳተፍ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የሀገር ውስጥ ሥራዎቻቸውን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ይኖርባቸዋል:: ለዚህም ከመቼውም ጊዜ በላይ ራሳቸውን ዝግጁ ሊያደርጉ፣ ጠንክረው ሊሠሩ ብዙ ሆነው እንደ አንድ ሊሠሩ ይገባቸዋል::
አብረው መሆናቸውን የሚፈልጉ ሀገራዊም ማኅበረሰባዊም ግላዊም አጀንዳዎች አሉባቸው:: ከራሳቸውም አልፈው ሀገራቸውንና ሕዝቡን እያሰቡ መሥራት በሚያስፈልጋቸው ወቅት ላይ መሆናቸውን መረዳት አለባቸው::
በአንዳንድ አካባቢዎች በግጭት የተነሳ ሕዝብ እየተፈተነ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል:: ለፈተና ባለመበገር ታሪካቸው እነዚህን ፈተናዎች አሁንም ለመሻገር በግልም በጋራም መሥራት ይኖርባቸዋል::
ቀደምት ጀግኖች በዓድዋ በቅርቡ ደግሞ የአሁኑ ትውልድ በዓባይ ግድብ ስማቸው በዓለም የገነነ እንደመሆኑ፣ ለእነዚህ ፈተናዎች የመጨረሻ መፍትሔ ለማስቀመጥ ከእነሱ በላይ ማንም እንደሌለ ተረድተው መትጋት ይኖርባቸዋል::
ይህን ለማድረግ ደግሞ በወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን:: ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲናፍቁት የኖሩት ሀገራዊ መግባባት የመፍጠሪያው ወቅት ላይ እንገኛለን:: ለእዚህ ደግሞ ለግጭቶቻችን፣ ለአለመግባባቶቻችን ሁሉ መሠረታዊ ምክንያት ናቸው የተባሉ አጀንዳዎች በብሔራዊ ምክክር እየተለዩ ይገኛሉ::
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለዚህ ምዕራፍ የደረሰው በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ነው:: ከአብዛኞቹ ክልሎች አጀንዳዎች ተሰብስበዋል:: ይህን አጀንዳ መሰብሰባቸውን ሲያጠናቅቁ ደግሞ በሀገር ደረጃ ቁጭ ብለው ይመክራሉ:: ከዚያም መግባባት ባለባቸው ይግባባሉ፤ መግባባት ላልቻሉባቸው ደግሞ መፍትሔ ያኖራሉ:: ይህም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፍጻሜ ያገኛል::
ለምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰቡ ሥራ በአብዛኛው ውጤታማ እንደሆነ ሁሉ ቀጣዩ ምዕራፍም የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ በእጅጉ ይፈልጋል:: ውጤታማ እንዲሆን ኢትዮጵያውያን እስከ አሁን አስተዋፅዖ እንዳደረጉ ሁሉ በቀጣይም አስተዋፅዖዋቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል::
ከጾም ወቅት ልምምዳችን ጥንካሬን፣ መተሳሰብን፣ መቻቻልን ተምረናል:: ይህን በልማቱም ሰላም በማስፈኑም መጠቀም ይኖርብናል::
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም