ደቡብ አፍሪካና መጪው ምርጫዋ

ከአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራት ቀዳሚ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ በሚቀጥለው ሳምንት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ከባድ ፉክክር ይኖረዋል የተባለ ምርጫ ይካሄዳል።

ደቡብ አፍሪካ በ1994 ዴሞክራሲያዊ ከሆነች በኋላ የአሁኑ ምርጫ ሰባተኛው ነው። ሥራ አጥነት፣ ከፍተኛ የወንጀል መስፋፋት እና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ አገሪቱን ጭንቅ ውስጥ ከተዋት ሳለ ነው ዜጎች ድምጻቸውን የሚሰጡት።

አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ዓመታትን አስቆጥሯል። በጥቂት ነጮች የሚመራው የዘር መድልዎ ሥርዓትን (አፓርታይድ) ታግሎ ከጣለ ጀምሮ ኤኤንሲ በደቡብ አፍሪካ ጉልህ ስፍራ ይዞ እስከ ዛሬ በሥልጣን ላይ ቆይቷል።

ፓርቲው የመጀመሪያውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በ1994 አሸንፎ እስካሁን ሥልጣን ላይ ይገኛል። በአሁኑ ምርጫም ፓርቲው የሚያገኘው ድምጽ ዝቅ ሊል እንደሚችል የዳሰሳ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህም ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምረት እንዲፈጥር ሊያስገድደው ይችላል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ለኤኤንሲ ድጋፍ ማጣት ምክንያት ሆኗል። ያለፉትን 30 ዓመታት እንደ ማሳያ ብንወስድ ደቡብ አፍሪካውያን ሀብታም ሆነዋል። የድህነት ቁጥር ከመቀነሱ ባሻገር ሰዎች ቤት እና የሕክምና አገልግሎት የማግኘት ዕድላቸው ከፍ ብሏል።

ሆንም ግን ከአውሮፓውያኑ 2011 ወዲህ የአገሪቱ ዜጎች ገቢ ዝቅ እያለ መጥቷል። ገዢው ፓርቲ ምጣኔ ሀብቱን የያዘበትን መንገድ ዜጎች የሚተቹትም ለዚህ ነው።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን እና ዓለም አቀፍ የሸቀጦች መወደድም ደቡብ አፍሪካ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በአገሪቱ ገቢ እና ሀብት በእኩል ሁኔታ የተሰራጨ አለመሆኑ ሌላው ጥያቄ የሚያስነሳ ነገር ነው።

‘ጂኒ’ በተባለው መለኪያ በተሠራ ጥናት መሠረት በአገሪቱ ያለው የገቢ መጠን ደቡብ አፍሪካን በዓለም እኩልነት ካልሰፈነባቸው አገራት ቀዳሚዋ ያደርጋታል።

በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ ቤተሰቦች የሚያገኙት ገቢ ተለክቶ ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የተደረሰው። ሀብታሞቹ 20 በመቶ ደቡብ አፍሪካውያን የአገሪቱን 70 በመቶ ገቢ ተቆጣጥረዋል።

ድሃዎቹ 40 በመቶ ደቡብ አፍሪካውያን የአገሪቱን 7 በመቶ ገቢ ብቻ ነው የያዙት። የሀብት እና የገቢ እኩል አለመመጣጠን ከሥራ አጥነት ጋርም ይተሳሰራል።

የዓለም ባንክ እንዳለው በደቡብ አፍሪካ ያለው ሥራ አጥነት ከዓለም ቁጥር አንድ ነው። በወረርሽኙ ወቅት ከነበረው ሁኔታ እስካሁን አላገገመም።

ከደቡብ አፍሪካውያን አንድ ሦስተኛው ሥራ ፈልገው ማግኘት ያልቻሉ ናቸው። ምጣኔ ሀብቱ ወደ ገበያው የሚገቡ ሰዎችን ሊያስተናግድ አልቻለም።

በተለይም ወጣቶች በሥራ አጥነት እየተፈተኑ ነው። ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 34 ካሉ ደቡብ አፍሪካውያን መካከል 44 በመቶው ትምህርት፣ ሥልጣና ወይም ሥራ የላቸውም።

እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወጣቶች ይበዛሉ። በአገሪቱ ከ62 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ዕድሜያቸው ከ35 በታች ነው።

የተባበሩት መንግሥታት አምና ባወጣው ሪፖርት ሥራ አጥነትን “ሊፈነዳ የተቃረበ ቦምብ” ሲል ነው የገለጸው። ሥራ አጥነት ለወደፊት የፖለቲካ ቀውስ መንስዔ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁሟል።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ወንጀልን ለመከላከል ቃል ገብተዋል። ወንጀል የአገሪቱ ዋነኛ ራስ ምታት ከሆነ ሰነባብቷል።

ባለፉት አሥር ዓመታት ጥቃት በተወሰነ ደረጃ ቢቀንስም ዝርፊያ፣ መድፈር እና ግድያ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍተዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት በአገሪቱ በየ20 ደቂቃው አንድ ሰው ይገደል ነበር። በየቀኑ ከ130 በላይ ሴቶች ይደፈራሉ። ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ እንዳሉት፣ የሚፈጸመው ጥቃት ብዛት በሴቶች ላይ ጦርነት የተከፈተ ያህል ነው።

ፓርቲያቸው ጉዳዩን በአግባቡ አልያዘውም መባሉን ግን አስተባብለዋል። በሌላ በኩል ከደቡብ አፍሪካ አጠቃላይ ሕዝብ መካከል 3 በመቶ የሚሆነው (2 ነጥብ 4 ሚሊዮኖቹ) ስደተኞች ናቸው።

አገሪቱ ምጣኔ ሀብቷ ችግር ውስጥ ቢወድቅም የስደተኞች መዳረሻ ናት። ስደተኞች ቁጥራቸው ውስን ቢሆንም ከአገሬው ሥራ በመቀማት እና ለወንጀል መበራከት አስተዋጽኦ በማበርከት ይተቻሉ። መጤ ጠል የሆኑ ጥቃቶች ባለፉት ዓመታት ቁጥራቸው ጨምሯል።

ሂውማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፤ የውጭ አገር ዜጎች ለምርጫ ቅስቀሳ እንደ ሰበብ እየዋሉ መሆኑ የሚደርስባቸውን መጤ ጠል ጥቃት እያባባሰው ይገኛል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You