ቅንጅታዊ ሥራ የሚሻው የክልሉ የማዕድን ልማት

የትግራይ ክልል በርካታ የማዕድናት ሀብት ክምችት ከሚገኝባቸው ክልሎች አንዱ ነው። በክልሉ እንደ ወርቅ፣ የከበሩ ማዕድናት፣ ለኢንዱስትሪ እና ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት የመሳሰሉት በስፋት ይገኙበታል። ክልሉ በወርቅ ማዕድን ክምችቱ ይታወቃል፤ ከጥቂት ዓመታት በፊትም በወርቅ ልማቱ ይታወቅ ነበር።

የሰሜኑ ጦርነት ባለፉት ሦስት ዓመታት በማዕድን ዘርፉ ልማት ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ከጦርነቱ በኋላ የማዕድን ዘርፉ ወደ ልማቱ እንዲመለስ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ይሁን እንጂ ዘርፉን ለማልማት የሚደረገው ጥረት በሕገ ወጥነት ምክንያት እየተፈተነ እንደሚገኝ ከክልሉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ፈቃድ ሳይኖራቸው በማዕድን ማውጣት እና መሸጥ ሥራዎች የተሰማሩ ሕገ ወጦች መበራከታቸውንም መረጃው ጠቁሟል። በዚህ የተነሳ ለሀገሪቱ ብሎም ለክልሉ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተውና ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችል የታመነበት የማዕድን ዘርፍ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻለም። በክልሉ በተለይ ሕገ ወጥ የማዕድን ዝውውርና ግብይቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በዘላቂነት ችግሩን በመከላከል ውጤቶች እያስመዘገቡ እንዳልሆነ የክልሉ የመሬትና ማዕድን ቢሮ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ ግርማይ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በጦርነቱ የተነሳ በማዕድን ዘርፉ ባለፉት ሦስት ዓመታት እምብዛም አልተሰራበትም። በክልሉ ከጦርነት በኋላ በ2015 እና 2016 በጀት ዓመት የማዕድን ቢሮን መልሶ ለማደራጀትና ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ሠራተኞች ጦርነቱና አለመረጋጋቱ ከሳደረባቸው አሉታዊ ተጽእኖ ወጥተው ወደ ሥራ እንዲመለሱና ለሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያደርግ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።

በጦርነቱ በወደመው የቁሳቁስ እና የሰው ኃይል የተነሳ ዘርፉ ተዳክሞ እንደነበር ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ ከጦርነቱ በኋላ ያለውን አቅምና የሰው ኃይል በማሰባሰብ ወደ ሥራ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ የመጀመሪያው ሥራ የማዕድን ዘርፉን ወደ ሥራ ለመመለስ ከፍተኛ የማዕድናት ክምችትና ያላቸው ወረዳዎች እንዲለዩ ተደርጓል። በተለይ በተያዘው በጀት ዓመት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ማዕድናት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እና ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል በመፈጠር ኢኮኖሚውንም ማነቃቃት እንዲቻሉ ተደርጓል።

በክልሉ ኮንስትራክሽን ማዕድናት የሚገኙባቸው ዘጠኝ ወረዳዎች ተለይተዋል። ከእያንዳንዱ ወረዳ አራት ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት በአጠቃላይ 75 ለሚሆኑ ሰዎች ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ስልጠናው ወረዳዎች ሥራውን ረስተው ስለቆዩ ያላቸው አቅምና ብቃት ተገንዘበው ተነሳሽነት ኖሯቸው ወደ ሥራው ለመመለስ ዝግጁነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው። ወደ ሥራም ከተመለሱ በኋላ አቅማቸው አሟጠው እንዲጠቀሙ በማስቻል ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል እንዲፈጥሩ አስችሏል።

በመቀጠል በወርቅ ክምችት አቅም ያላቸው ወረዳዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሥራቱንም ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ። በክልሉ ሰሜን ምዕራብ ዞን በሚባል አካባቢ ያሉ 26 ወረዳዎች ከፍተኛ የወርቅ ክምችት እንዳለባቸው አመልክተው፣ እነዚህ ወረዳዎችና ዞኖች አመራሮች እና የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። ከዚህም በወረዳው ያሉ የወርቅ አምራቾች እና የሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸው፣ ወደ ሥራ እንዲመለሱም መግባባት ላይ መድረስ የተቻለበት መሆኑን አቶ ፍሰሃ ጠቅሰዋል።

የክልሉን የወርቅ ክምችት መጠን ለማወቅ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጂኦሎጂስቶች ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን የጠቆመት አቶ ፍሰሃ፤ ጥናቱ ሲጠናቀቅ የክምችቱ መጠን እንደሚታወቅም አመላክተዋል። በክልሉ ወርቅ ከአምራቾች ተረክቦ ለብሔራዊ ባንክ የሚያስገባ ሕጋዊ ኢዛና ከተባለው ድርጅት ጋር በመተባበር ወርቅ ከሚገኝባቸው የሰሜን ምዕራብ ዞን አካባቢዎች ወርቅ አምራቾች ጋር ‹‹በሕገ ወጥነት እየተመረተና እየተሸጠ ያለውን የወርቅ ምርት እንዴት ወደ ሕጋዊ ማምጣት እንችላለን›› በሚል ርእስ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎም አምራቾቹ ወደ ሥራ የገቡበት ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል።

አቶ ፍሰሃ፤ የቢሮው የመጀመሪያ ሥራ የስልጠና መድረኮችን በመፍጠር ግንዛቤዎች በማስፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት አምራቾቹ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ጥረት ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። ከስልጠና በኋላ አምራቾች ወደ ማምረት ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል። በተለይ በዘርፉ ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩ ባለሀብቶች ያለምንም እንግልት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ በመግባባት ላይ ተደርሶ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም አመላክተዋል።

በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት ፈልጎ ፈቃድ የሚጠይቅ ባለሀብት የሚጠበቅበትን አሟልቶ ከተገኘ ያለምንም እንግልትና ቅድመ ሁኔታ ወደ ሥራ እንዲሰማራ እንደሚደረግ ገልጸው፣ ይህ አሰራር ዘንድሮ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ አስተዋጽኦ ማድረጉን አቶ ፍሰሃ ጠቅሰዋል፤ ‹‹ይህ ማለት በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ሁሉም ችግሮች ተቀርፎላቸዋል ማለት አይደለም። በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ችግሮችና ክፍተቶች እንዳሉ መረዳት ተችሏል፤ በዚህም ላይ ክትትል በማድረግ የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በ2016 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፉ ለመሰማራት በርካታ ባለሀብቶች ፍላጎት አሳይተዋል፤ በርካታ ባለሀብቶችም ፍቃድ የጠየቁበት ሁኔታ ታይቷል። በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ለ90 አዳዲስ አምራቾች የማምረት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 25 አምራቾች የግራናይት ማዕድን፣ 28 አምራቾች ጠጠር፣ 16 ሲልክሳንድ፣ ስድስቱ አሸዋ ፣ 13 ወርቅ እና ሁለቱ ሳፋየር ማዕድን ለማምረት ፈቃድ ወስደዋል።

በተጨማሪም ሦስት ባለ ከፍተኛ ፈቃድ ማዕድን አምራች ኩባንያዎች በክልሉ በማዕድን ዘርፍ በመሰማራት ወርቅ ለማምረት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ከማዕድን ሚኒስቴር መውሰዳቸውን አስታውቀዋል። ለኩባንያዎቹ ሰፊ መሬት እንደተሰጣቸው ጠቅሰው፣ እስካሁን ግን ወደ ሥራ እንዳልገቡ ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ይህ ችግር በክልሉ የማዕድን ልማት ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መጥቷል። በወርቅ ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ አዳዲስ የወርቅ አምራቾች ፈቃድ በመሰጠቱ ሂደት ላይ ፈተና እየሆነ ይገኛል። በሌላ በኩል እነዚህ ኩባንያዎች መሬት በወሰዱት አካባቢ ይፈጥራሉ ተብሎ የታሰበውን የሥራ እድል መፍጠር አልተቻለም። ችግሩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በክልሉም ሆነ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ጫና ስለሚፈጠር የፌዴራል መንግሥት ድጋፍና ክትትል በማድረግ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል።

በተያዘው በጀት ዓመት ማዕድን ለማምረት ፈቃድ ከወሰዱትም ሆነ ቀደም ሲል ፈቃድ ከነበራቸው አምራቾች መካከል ወደ ሥራ የገቡ እንዳሉ ሁሉ ወደ ሥራ ያልገቡም አሉ ያሉት አቶ ፍሰሃ፤ በክልሉ በማዕድን ዘርፍ እስካሁን 578 አምራቾች የማምረት ፈቃድ መወሰዳቸውን አስታውቀዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ እያመረቱ መሆናቸው ሪፖርት የተደረገው 127ቱ ብቻ ናቸው ይላሉ። ከእነዚህም በስምንቱ ላይ ፍተሻ ተደርጎባቸዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህ አሃዝ 22 በመቶ ያህሉ ብቻ ወደ ሥራ መግባታቸውን እንደሚያሳይ አመልክተዋል። በማዕድን ዘርፉ ፍለጋና ምርመራ ለመሰማራት 346 ባለሀብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፤ 511 ደግሞ የዳሰሳ ፈቃድ መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።

በማዕድን ዘርፉ ከተሰማሩት ባለሀብቶች ውስጥ ወደ ሥራ የገቡት ጥቂት መሆናቸውን አቶ ፍሰሃ ያመላክታሉ። ለዚህም ምክንያቱ ጦርነቱ ባለሀብቱ አቅም እንዲያጣና የሰው ኃይል፣ የቁሳቁስና የፋይናንስ አቅሙ የተዳከመ እንዲሆን ማድረጉ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህን አቅማቸውን አነቃቅተው በተቻላቸው መጠን ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡት ማምረት የጀመሩበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመው፤ የአቅም ውስንነት የገጠማቸው ደግሞ ወደሥራ እንዳልተመለሱ አስረድተዋል።

‹‹ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ ለመመለስ ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን የአቅም ውስንነት አለባቸው፤ ብድር ቢመቻችላቸው የተሻለ የማምረት አቅም አላቸው፤ ይህን ሁሉ በተለያዩ ጊዜያት ያነሳሉ›› የሚሉት አቶ ፍሰሃ፤ የሚመለከተው አካል የባለሀብቱን ችግር ተረድቶ ድጋፍ ቢያደርግላቸውና ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ ቢመቻችላቸው ወደማምረት ሥራ ሊመለሱ እንደሚችሉ እሳቸውም አስታውቀዋል። ባለሀብቶቹ በፌዴራል ሆነ በክልል ደረጃ ያለባቸው ክፍተት ተጠንቶ ድጋፍ ቢደረግላቸው የተሻለ የኢኮኖሚ መነቃቃት ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በክልሉ ወርቅ በማምረት ሥራም ሆነ ግብይት ሕጋዊ ፈቃድ ያልተሰጣቸው አካላት ወርቅ አምርተው ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የሚሸጡበት ሁኔታ መኖሩን ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ። በዚህ ድርጊት ከፍተኛ ሀብት እየባከነ መሆኑን ገልጸዋል፤ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በመሥራት እነዚህ ሕገ ወጦች ሕጋዊ መስመር ተከትለው እንዲሰሩ ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በሕገ ወጥ ተግባሩ የተሰማሩትን አካላት አደራጅቶ ወደ ሕጋዊ መስመር ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ በክልሉ ከዘርፉ ገቢ የተሰበሰበበት ሁኔታ እንዳለም አስታውቀዋል። ከአገልግሎት፣ ከመሬት ኪራይ፣ ከሮያሊቲ ክፍያ በክልልና በወረዳ ደረጃ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል። ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሯል።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በአስር ወራት ውስጥ በክልል ደረጃ 10 ሚሊዮን ብር፤ በወረዳ ደረጃ ደግሞ 18 ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ 28 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፣ በክልል ዘጠኝ ሚሊዮን 831ሺ 277 ብር ፣ በወረዳ 13 ሚሊዮን 549ሺ 568 ብር ፤ በአጠቃላይ 23 ሚሊዮን 380ሺ 845 ብር ገቢ ተገኝቷል። አፈጻጸሙም የእቅዱን 83 በመቶ ነው።

በማዕድን ዘርፉ በተያዘው በጀት ዓመት 45ሺ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ፤ በአስር ወራት ውስጥ ለ41ሺ 285 ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል። ይህም የእቅዱን 95 በመቶ ያህል ማሳካት ያስቻለ ነው።

እንደ ክልል 50 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ኢዛና (ኢዛና ወርቅን ከአምራቶች ተረክቦ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ የሚያደርግ ድርጅት ነው) ለማስገባት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፤ በወርቅ አመራረት ላይ ባሉ ችግሮች የተነሳ እስካሁን ከሦስት የወርቅ አምራች ወረዳዎች የተገኘው ሪፖርት እንደሚያሳየው ሁለት ነጥብ 316 ኪሎ ግራም ወርቅ ብቻ መግባቱን አስታውቀዋል።

ወርቅን ሕጋዊነት በተከተለ መልኩ ለኢዛና የማስገባቱ ሥራ የተዳከመ እንደሆነ ይገልጻሉ። ለዚህም አንዱ ምክንያት ወርቅ በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ከፍተኛ ደረጃ አምራች ኩባንያዎች ወደ ሥራ ያለመግባታቸው መሆኑን ገልጸው፤ ፈቃድ ሳይሰጣቸው ወርቅ የሚያመርቱና የሚሸጡ አካላት መበራከት ሌላኛው የመዳከሙ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

አምራቾች ወርቅ አምርተው በሕጋዊ መንገድ ወደ ኢዛና ከማስገባት ይልቅ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የሚሸጡበት ሁኔታ፣ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የተከሰተ ችግር እንዳልሆነም አስታውቀዋል። በወርቅ ልማትና ግብይት ላይ የተቀናጀና የተናበበ ሥርዓት ስላልተፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።

ቢሮው ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የሚመለከታቸውን አካላት በማወያየትና ግንዛቤ በመፍጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል ያሉት አቶ ፍሰሃ፤ የተጠናከረ ክትትል በማድረግ ሕገ ወጥነት ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ክልሉ በማዕድን ዘርፍ የማምረት አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ የማዕድን ሀብቱን በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። የማዕድን ሀብቱን በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲለማ በማስቻል ለበርካታ ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ይሰራል ሲሉ አቶ ፍሰሃ ተናግረዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You