ኢንስቲትዩቱ ለጎርፍ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ አሳሰበ

አዲስ አበባ፡- ካለፉት ወራት ጀምሮ በተለያዩ ተፋሰሶች ላይ ከፍተኛ የእርጥበት መጠን በመስተዋሉ በጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢፕድ በሰጠው መረጃ እንዳሳወቀው፤ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች አደጋ እንዳይደርስ ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅትና የጥንቃቄ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል።

በሚቀጥሉት ዘጠኝ ቀናት በመካከለኛው እና ታችኛው ተከዜ፣ አባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ግቤ፣ የላይኛውና የመካከለኛው አዋሽ፣ የስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው ዋቤ ሸበሌ እና የገናሌዳዋ ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኝ ተመላክቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተስፋፋ ዝናብ ስለሚኖር እርጥበታማው የአየር ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው መረጃው ጠቁሟል፡፡

ኢንስቲትዩቱ እንዳመላከተው፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚጠበቀው ከፍተኛ እርጥበት በተለይም ረባዳማ በሆኑ ቦታዎች ላይ በሚገኙ የሰብል ማሳዎች ላይ የእርጥበት መብዛት እና ውሃ በሰብሎች ላይ እንዳይተኛ የመከላከል ሥራዎች ያስፈልጋሉ፡፡

የውሃ ማንጣፈፍ ሥራዎችን መሥራት እንዲሁም የጎርፍ መቀልበሻ በማዘጋጀት የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አመላክቷል።

እርጥበቱ ተፋሰሶች የተሻለ የውሃ መጠን እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር አዎንታዊ ሚና የሚኖረው ሲሆን፤ በተጨማሪም ለመስኖም ሆነ ለኃይል ማመንጫነት የሚያገለግሉ የግድቦችን የውሃ መጠን እንደሚያሻሽል ተገልጿል፡፡

በቀጣይ ዘጠኝ ቀናት የሚገኘው እርጥበት በአርብቶ አደርና በከፊል የአርብቶ አደር አካባቢዎች የዕፅዋት ልምላሜን፣ የእንስሳት ግጦሽ ሳርንና የመጠጥ የውሃ አቅርቦትን ከማሻሻል አንጻር ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቅሷል።

በመረጃው መሰረት፤ በቀጣይ ዘጠኝ ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት አስቀድመው ለተዘሩ የበልግ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎችና ለጓሮ አትክልቶች የውሃ ፍላጎትን ከማሟላት አንጻር በጎ ሚና ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም አስቀድመው ለሚዘሩ የመኸር ሰብሎች የማሳ ዝግጅት ለማከናወንና ዘር ለመዝራት አዎንታዊ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።

እርጥበቱ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የረጅም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራትና ለቋሚ ተክሎች እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለተተከሉ የዛፍ ችግኞች እድገት የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተብራርቷል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You