የ12ኛው የበጎ ሰው ሽልማት እጩዎች ጥቆማ እስከ ሰኔ 14 ይከናወናል

አዲስ አበባ፦ የ12ኛው የበጎ ሰው ሽልማት እጩዎች ጥቆማ ከግንቦት 14 እስከ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚከናወን የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት አስታወቀ።

የዘንድሮውን የበጎ ሰው ሽልማት አስመልክቶ ትናንት መግለጫ በተሰጠበት ወቅት የቦርዱ ተወካይ አንዷለም አባተ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የበጎ ሰው ሽልማት እጩዎች ጥቆማ ለአንድ ወር ይካሄዳል።

ላለፉት 11 ዓመታት ለሀገራቸው መልካም ሥራ ለሚሠሩ፣ ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በብቃት ለሚወጡና የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ለውጥ አምጪ ተግባር ለፈጸሙ አካላት እውቅና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ በዘንድሮው ዓመትም በተለያዩ 10 ዘርፎች እውቅና ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ሽልማቱ በመምህርነት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ኪነ-ጥበብ፣ ቅርስ ባህልና ቱሪዝም፣ ሚዲያና ጋዜጠኝነት፣ በጎ አድራጎት፣ ንግድ ኢንዱስትሪና ሥራ ፈጠራ፣በመንግሥታዊ ተቋማት ኃላፊነት፣ ማህበራዊ ጥናት፣ለሀገራቸው እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የኪነጥበብ ዘርፍ በውስጡ የተለያዩ ሙያዎችን ያካተተ ስለሆነ በየዓመቱ የተለያዩ ሙያዎች እንደሚመረጡ የተጠቀሰ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት በኪነጥበብ ዘርፍ ስልጠና በመስጠት ተተኪዎችን ለማፍራት ትልቅ ሀገራዊ አበርክቶ ላላቸው ተቋማት ሽልማቱ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በግልና በመንግሥት ስር በቲያትር፣ በስዕል፣ ሙዚቃና መሰል የኪነጥበብ ዘርፎች ተተኪዎችን ለማፍራት እየሠሩ ላሉ ተቋማት መጠቆም እንደሚቻል ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት የበጎ ሰው ሽልማት ዓላማና ትውልድን ለመቅረጽ ያለውን ጥቅም በመገንዘብ ሕዝቡና የተለያዩ ድርጅቶች ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረበው ቦርዱ፤ ሥራው በዘላቂነት እንዲቀጥል ተሳትፎና ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

እጩዎችን በስልክ ቁጥር 0977232323፣ በቫይበር፣ በቴሌግራም፣ በዋትስ- አፕ፣ በኢ-ሜይል begosewprize@gmail.com እንዲሁም በፖስታ ሳጥን ቁጥር 150035 መጠቆም እንደሚቻል የተገለጸ ሲሆን፤ ጠቋሚዎች የእጩዎችን ሥራና አበርክቶ በዝርዝር እንዲገልጹና የሚገኙበትን አድራሻ በአግባቡ እንዲያካትቱ የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት ቦርድ አሳስቧል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You