በደብረ ብርሃን 167 ፋብሪካዎች በግንባታ ሂደት ላይ ናቸው

አዲስ አበባ፡- በደብረ ብርሃን ከተማ 167 የተለያዩ ፋብሪካዎች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የከተማዋ የኢንቨስትመንት ስበት ማዕከልነት በመቀጠሉ አሁንም በርካታ ባለሀብቶች ፋብሪካቸውን ለመገንባት ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛል፡፡

በዘንድሮው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተጀመሩ ኢንዱስትሪዎችን ግንባታ አጠናቆ ወደ ምርት ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 20 ፋብሪካዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በተጨማሪ ሌሎች 18 ፋብሪካዎች ለማምረት የሚያስችላቸውን ማሽኖች በማስገባታቸው በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ያመርታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

ምክትል ከንቲባው እንደተናገሩት፤ በከተማዋ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት አሁንም በርካታ ባለሀብቶች ጥያቄ እያቀረቡ ፕሮጀክታቸው እየተፈተሸ ይገኛል። አልሚዎቹ መሬት የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አስፈላጊው ሥራ ይከናወናል ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል። በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ 60 በላይ ለሚሆኑ ባለሀብቶች 52 ሄክታር መሬት ማስተላለፍ መቻሉን አስታውቀዋል።

በተያያዘ በዘጠኝ ወሩ ወደ ግንባታ መግባት ያለባቸው ባለሀብቶች ወደ ግንባታ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ከንቲባው፤ በተለያዩ ምክንያች ወደ ግንባታ መግባት ያልቻሉት ላይ ደግሞ ማስጠንቀቂያ የመስጠትና ርምጃ የመውሰድ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

ወደ ሥራ ባልገቡ 40 ፋብሪካዎች ላይ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ጠቁመው፤ ለ22 ፋብሪካ ኃላፊዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንና 12ቱ ደግሞ ማልማት ባለመቻላቸው መሬታቸው ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን አስረድተዋል።

በአካባቢው የሚያጋጥመው የጸጥታው ችግር መስተጓጎል ቢፈጥርም የከተማዋ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በከተማዋ አንጻራዊ የሚባል ሰላም በመኖሩ ከኢንቨስትመንቱ ተጨማሪ በርካታ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው እንዳመላከቱት፤ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ በሁሉም አካባቢዎች ውይይት እየተደረገ ነው።

የታየውን አንጻራዊ ሰላም በማስቀጠል የኢንዱስትሪ ፍሰቱን ለማሳደግና የከተማዋን ነዋሪ የቤት አቅርቦት ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም ወደ ከተማዋ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አቶ በድሉ ውብሸት ተናግረዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You