ታዳጊ ሀገራት በታዳሽ ኃይል ልማት ትብብር ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋል

አዲስ አበባ:- በማደግ ላይ ያሉ በተለይም የአፍሪካ ሀገራት በታዳሽ ኃይል የጋራ የልማት ትብብሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውንም ማሳደግ እንደሚኖርባቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ለሁለት ቀናት በመዲናዋ ሲካሄድ የነበረው ሁለተኛው የደቡብ ደቡብ ትብብር ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ እንደተናገሩት፤ ታዳሽ ኃይል ኢኮኖሚን በፍጥነት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ እምቅ ሀብቱን ወደ ልማት ተጠቃሚነት መቀየር ይገባል።

በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ያለው እምቅ ሀብት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት አልፎ ለሌሎች ሀገራትም የሚተርፍ ነው፤ ለዚህም ከተለያዩ ሀገራት ጋር ተባብሮ መሥራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

አብዛኛው የተፈጥሮ ሀብት ያለው አፍሪካ ውስጥ ይሁን እንጂ በሀብቱ ተጠቀሚ ለመሆን አለመቻሉን የጠቆሙት አማካሪው፤ ግማሹ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ በገጠር የሚገኘው ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡

የዋናው የአሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር በማይደርስባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን በሙከራ ደረጃ በ11 የተለያዩ አካባቢዎች ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል፡፡

ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ 200 የሚደርሱ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።

አማራጭ የኃይል አቅርቦት ልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ኅብረተሰቡን ከኋላ ቀር አሠራሮች በማላቀቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል። በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን ተጽእኖ ለመቀነስ የሚረዳ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ታዳሽ ኃይል አስፈላጊና በፍጥነት ለምቶ ጥቅም ላይ መዋል ያለበት መሆኑን ተናግረው፤ የታዳሽ ኃይል ልማት በተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ድህነትን ለመቀነስ፣ በጤና፣ በኢነርጂ፣ በትምህርትና በመሳሰሉት ዘርፎች የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፉን ማልማት አስፈላጊ ነው፤ ለትግበራውም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።

ጉባኤው በታዳሽ ኃይል በሚሠሩ ሥራዎች ልምድ ለመለዋወጥ፣ ተሞክሮ ለመቀመር፣ ትብብርን ለማጠናከር ጠቃሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

በጉባኤው የተሳተፉት የሲልኮ ተቋም መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ህንዳው ሃሪሽ ሁንዴ በበኩላቸው፤ ትብብሩ ለታዳጊ ሀገራት ከፍ ያለ ጥቅም ያለው እና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ራሳችን ማልማት እንችላለን ትብብሩም ይህንን እውን ማድረግ አለበት፤ ከውይይት ባሻገር ውጤት ማምጣት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ፕሪሳይስ የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ አሰፋ በበኩላቸው፤ ታዳሽ ኃይል የኢኮኖሚ ልማት ለማምጣት፣ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡ ኤሌክትሪክን በመጠቀም የተሠራው ሥራ የሰውን ልጅ የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻል መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ ከ600 ሚሊዮን በላይ በዓለም ደግሞ ከ800 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ጠቁመው፤ ታዳጊ ሀገራት በታዳሽ ኃይል ልማት በትብብር ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የደቡብ ደቡብ ትብብር በማድረግ ላይ ያሉ ሀገራት የሚያደርጉት ትብብር ማዕቀፍ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You