በክልሉ በመኸር እርሻ ከ98ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብሎች ለመሸፈን ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፡- በክልሉ በመጪው የመኸር እርሻ ከ98 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ ዋና ዋና ሰብሎች ለመሸፈን ዝግጅት መደረጉን የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በበልግ እርሻ ሥራው በአጠቃላይ ከ112 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በልዩ ልዩ ሰብሎች መሸፈኑንም ቢሮው ገልጿል፡፡

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ባንጉ በቀለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በመኸር እርሻ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከወዲሁ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊው በክልሉ አብዛኛዎቹ ወረዳዎች የመኸር እርሻ ሥራ የሚከናወንባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ ምርታማነትን የሚጨምሩ ፓኬጆችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በመጪው የመኸር እርሻ በክልሉ 98 ሺህ 641 ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች ለመሸፈን እና 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በበልግ እርሻውም በአጠቃላይ 112 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በልዩ ልዩ ሰብሎች እንዲሸፈን መደረጉንና 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክተዋል፡፡

በክልሉ በተለይ ጩኮ፡ ጭሬ፡ ዳሌ፡ አሮሬሳ፡ ቦና ዙሪያ፡ ቦርቻ፡ ሀዋሳ ዙሪያን ጨምሮ 13 ወረዳዎች የበልግ እርሻ ሥራ በስፋት የሚከናወንባቸው እንደሆኑም ነው የጠቆሙት አቶ ባንጉ፡፡

በበልግ ወቅት በአጠቃላይ ለማልማት ከታቀደው 112 ሺህ ሄክታር መሬት 68 ሺህ 229 ሄክታሩ በበቆሎ እና ቦሎቄ ሰብል የተሸፈነ መሆኑን ገልጸው፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በኩታ ገጠም እንዲለማ እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የእንሰት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመው፤ በተለይ ምርት መስጠት በሚችል መሬት ላይ የተተከለ የባሕር ዛፍ ተክል እንዲነቀል በማድረግ በእንሰት ችግኝ የመተካት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ 13 ሺህ 610 ሄክታሩ ደግሞ በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡

እንሰትን በስፋት ለማልማት በተያዘው ዕቅድ መሠረትም በ40 ሺህ 824 ሄክታር መሬት ላይ የእንሰት ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 43 ሺህ ሄክታር መሬት በእንሰት ችግኝ ተሸፍኗል ብለዋል፡፡

ቅድስት ገዛኸኝ

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You