ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ግንቦት 21 ይጀምራል

– የሚዲያ ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታነት መሥራት ይኖርባቸዋል

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጀምር አስታወቀ። የሚዲያ ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታነት መሥራት እንደሚኖርባቸው ተጠቆመ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “የኢትዮጵያ ሚዲያ ለኢትዮጵያውያን ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር” በሚል መሪ ሃሳብ ከፌዴራል፣ ከክልልና ከግል የሚዲያ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ትናንት ተወያይቷል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሐመድ ድሪር እንደተናገሩት፤ የምክክሩ ሂደት አሁን በደረሰበት ደረጃ በአሥር ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ ሥራዎችን በማጠናቀቅ የአጀንዳ ግብዓት ለማሰባሰብ የመጨረሻው ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል። ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ግንቦት 21 ይጀምራል።

የምክክር ሂደቱ ከአዲስ አበባ በመጀመር ወደ ሌሎች ክልሎች የሚቀጥል ይሆናል ያሉት አምባሳደር ሙሐመድ፤ ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው መድረክ በስኬት መጠናቀቅ በሌሎች ክልሎች ለሚከናወነው ሥራ ውጤታማነት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የተባባሪ አካላት ስልጠናው በትናንትናው እለት ተከናውኗል። እንዲሁም በትግራይ ክልል ሂደቱን ለማስጀመር ከአመራሩ ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑንን ገልጸው፤ በምክክሩ ሂደት ኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት በንቃት እንዲሳተፉና ስለምክክሩ ተቀራራቢ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሚዲያው የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በዘንድሮ ጥቅምት ወር በአዳማ ከተማ በተካሄደው መድረክ የሚዲያ ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተገልጿል ያሉት ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሐመድ፤ ሚዲያዎች ከመድረኩ በኋላ ማለትም ባለፉት አምስት ወራት ለሀገራዊ ምክክሩ ትኩረት ሰጥተው የተለያዩ ዘገባዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። የምክክሩ ሂደት በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚከናወን በመሆኑ የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።

የምክክሩ ሂደት ሁሉን ያማከል፣ ግልፅ እና ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ያሉት አቶ እውነቱ፤ በተለይ የሚዲያ ተቋማት ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ለቀጣይ የምክክር ጊዜያትም በትብብርና በቅንጅት መሥራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

በመድረኩ “ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር የመገናኛ ብዙኃን ሚና” በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ወንደወሰን ሽመልስ እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ሲሆኑ፤ በጽሁፉ የሚዲያ ተቋማት በኮሚሽኑ የሥራ ሂደት ያከናወኑት ተግባራት ላይ የነበሩ ጥንካሬዎችና ድክመቶችን አብራርተዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ በ10 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን በመረጠበት ሂደት የሚዲያው ሚና የጎላ እንደነበር በጥንካሬ የተነሳ ሲሆን፤ የምክክር ሂደቱ እንደ ሀገር አዲስ በመሆኑ በቂ እውቀትና ልምድ አለመኖሩ፣ በጉዳዩ ላይ በቂ ማብራሪያና ትንታኔ የሚሰጥ ባለሙያም ውስንነት መኖሩ እና የኮሚሽኑ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ ከመገናኛ ብዙኃኑ የመረጃ ፍላጎት አኳያ ክፍተት ነበረበት የሚሉት ጉዳዮች እንደ ድክመት ተጠቅሷል።

ሚድያዎች ከኮሚሽኑ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ኮሚሽኑ በቅርቡ በአዲስ አበባና በክልሎች ለሚያደርገው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጡ በመድረኩ ጥሪ ቀርቧል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚዲያ ፎረም ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮች መቋጫ መፍትሄ የሆነው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ መገናኛ ብዙኃን የሚኖራቸው አዎንታዊ ሚና ተኪ እንደሌለው ተመልክተናል ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ የተቀመጠለት ጊዜ 10 ወራት ብቻ ቀርተውታል። ስለሆነም መገናኛ ብዙኃኑ ተናብበውና ተቀናጅተው በዚህ አስር ወር ጊዜ ውስጥ ወሳኝ ሥራ መሥራት አለባቸው ያሉት አቶ ጥበቡ፤ ከዚህ አኳያ ቀደም ሲል የተቋቋመውን ፎረም በንቃት እንዲሠራ ማድረግና አስፈላጊ ሁኔታዎችን በፍጥነት በማሟላት “ኢትዮጵያ እየመከረች ነው” የሚለውን መልዕክት የማጉላት ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙኃን እንደየባህሪያቸው የ10 ወራት ዕቅድ አውጥተው መተግበር፣ በኮሚሽኑ የፋይናንስ ድጋፍ በመታገዝም በማስታወቂያ፣ በፎቶ ኤግዚቢሽን፣ ዶክመንተሪዎች በርካታ የይዘት ሥራዎችን መሥራት፣ሥራዎችን በየወቅቱ በመገምገም ጥንካሬን ማስቀጠልና ጉድለቶችን መሙላት እና ሌሎች መሰል ሥራዎች እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።

ከሚዲያ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር የተደረገው ውይይት የመገናኛ ብዙኃንን አቅም በማቀናጀት ውጤታማ የምክክር ሂደት እንዲኖር ለማድረግ ያለመ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

Recommended For You