የገበያ ትስስርን እና የልምድ ልውውጥን ለማሳካት ያለመው ኤግዚቢሽን

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ በየጊዜው የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ኤግዚቢሽኖችንና ባዛሮች እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያም ስድስተኛውን ‹‹አግሮፉድና ፕላስትፕሪንት ፓክ ኢትዮጵያ 2024›› የንግድ ኤግዚቢሽንን በሚሊኒየም አዳራሽ አስተናግዳለች። ኤግዚቢሽኑ በግብርና፣ በምግብ፣ በመጠጥ፣ በፕላስቲኮች፣ በሕትመት እና በማሸጊያ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ዕውቅና ያላቸው ኩባንያዎች የተሳተፉበት ነው፡፡

ለሦስት ቀናት በቆየው አውደ ርዕይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ12 ሀገራት የተወጣጡ (ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ኢጣሊያ፣ ኬንያ፣ ታይዋን፣ ታይላንድ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና እንግሊዝ) ኩባንያዎች) 122 ተሳታፊዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን አቅርበዋል። አውደ ርዕዩ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩ ጉባኤዎችና የንግድ ልውውጦች ለመፍጠር ያስቻለም እንደነበር ተጠቁሟል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ እንደተናገሩት፤ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ምቹ አማራጮች አላት፡፡ በመንግሥት በኩል የግብርና የኢንዱስትሪ ምርቶች ምርታና ምርታማነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በምግብና በመጠጥ ማቀናበሪያና ማሽግ ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፡፡

አውደ ርዕዩ በግብርና ምርቶች፣ በምግብና መጠጥ፣ በፕላስቲኮች ሕትመትና ማሸጊያ ኢንዱስትሪዎች ረገድ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና አገልግሎቶች የቀረቡበት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ፤ ይህም ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለፈጠራ ሥራዎች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ማስተዋወቅና ያልነበሩ ግብዓቶችንም ሥራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ እንደሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት እርስ በእርስ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ አውደ ርዕዩ በሀገር ውስጥ ያሉ አምራቾች የሚያቀርቧቸውን ምርቶችና አገልግሎቶች ለማስተዋወቅ የሚያስችል ነው፡፡ በተለይ የንግድ እድሎችን ለማስፋት እና በኢንዱስትሪው ውስጥ ስላሉ አዳዲስ ለውጦች ግንዛቤ ለመጨበጥ ይረዳል። በተጨማሪም አዳዲስ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲመጣ በማድረግ ምርትና ምታማነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

በአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ከሆኑ ድርጅቶች አንዱ ‹‹ጣና ድሪሊንግ ኤንድ ኢንዱስትሪ›› ኩባንያ ነው፡፡ አቶ ሳሙኤል ፍቅረ ‹‹በጣና ድሬሊንግ ኤንድ ኢንዱስትሪ›› ኩባንያ የሽያጭና ማርኬቲንግ ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ማኑፋክቸሪንግ እና ከከርሰ ምድር ውሃን የማውጣት ሥራ ይሰራል፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ከተሰማራ 15 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪም ጥራቱን የጠበቀ ጥሬ እቃን ከውጭ በማስመጣት የፕላስቲክ ፓይፖችን ያመርታል፡፡ የፕላስቲክ ፓይፖች የማይዝጉ ከመሆናቸው የተነሳ ብረትን በመተካት ለመጠቀም ስለሚያስችሉ ጥራታቸውን የጠበቁ ፓይፖችን በማምረት ህብረተሰቡ በዘላቂነት እንዲጠቀሙበት እያደረገ ይገኛል፡፡

እነዚህ የፕላስቲክ ፓይፖችን ቢያንስ 50 ዓመታት ያህል አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል የሚለው አቶ ሳሙኤል፤ ድርጅቱ ከ20 ሚሊ ሊትር ጀምሮ እስከ 400 ዲያሜትር ድረስ ያሉ ፓይፖች እንደሚመረት ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁም ፒፒሲዎችን በማምረት ለኮንስትራክሽን እና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ እና ከኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች ጋር አብረው እየሠሩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ጥራታቸው ተፈትሾ የተረጋገጥ፣ ጥራታቸው የተጠበቁ እና ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ ምርቶች እያመረተ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ከከርሰ ምድር ውሃን ከተለያዩ ቦታዎች ለማውጣት እስከ 600ሜትር ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶችን ቁፋሮ በማካሄድ ውሃን ከከርሰ ምድር ያወጣል፡፡

ምርቶች የገበያ ተደራሽነታቸው የሰፋና ብዙ ፈላጊ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በሚፈለገው ልክ ለማምረት በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ከውጭ የሚመጣው የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት እያገጠመ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

‹‹ድርጅቱ ከውጭ የሚመጣ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲተኩ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በሀገር ውስጥ ጥራት ያለው ከውጭ ከሚገባው የሚበልጥ ምርት ማምረት እየተቻለ፤ ከውጭ ለምን ይገባል በሚል ከፕላስቲክ ኤጀንሲዎች ጋር እየተነጋገር ሥራዎች እየሰራ ነው›› የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ ‹‹ከውጭ የሚመጡት ምርቶች ጥራታቸው ያልጠበቁ ስለመሆናቸው በድርጅቱ ስታንደርዱን በጠበቀ ላብራቶሪ ሆነ በተስማሚነትና ምዘና ኤጀንሲ ተመርምረው ሲፈተሹ ጥራታቸው ያልጠበቁና ከደረጃ በታች መሆናቸው ተደርሶባቸው ውድቅ እየተደረጉ ነው›› ይላሉ፡፡ ይህ ሀገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ ከውጭ ማምጣት የገንዘብ እና የጊዜ ብክነት የሚዳርግ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ምርቶቹ ዓለም አቀፍ ጥራት ደረጃው በጠበቀ መልኩ ስለሚመረቱ ከውጭ ከሚመጡት ጋር ሲነጻጸሩ በዋጋቸው ከፍተኛና ብልጫ ያለው ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ የተሰሩበት ማቴሪያል አንዱ ዓይነት ሆነው የጥሬ እቃ አቅርቦቱ ከውጭ የሚመጣ መሆኑ ዋጋ ከፍ እንዲልና ከውጭ የሚገባ ደግሞ በዚያው ልክ ዋጋው ዝቅ እንዲል አድርጎታል ይላሉ፡፡

በምርቶቹ የተፈጠረው የገበያ ትስስር ጥሩ ቢሆንም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ሲባል ህብረተሰቡ ቅድሚያ ለውጭው ምርት የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሶ፤ የውጭ ምርቶቹን ገዝቶ የተጠቀሙ ደግሞ ከሀገር ውስጥ ምን ያህል ልዩነት እንዳለው ስለሚረዱ ከሁሉም በላይ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የሚመርጡበት ሁኔታ መኖሩን ያመላክታል፡፡ ከውጭ የሚመጣው ምርት አንዴ ከተገዛ ለመመለስም አስቸጋሪ እንደሚሆን አንስተው፤ የሀገር ውስጥ አምራች ለሚያመርታቸው ምርቶች ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ የሚሰራ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ድርጅቱ አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ አውደ ርዕዮች ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፤ በስድስተኛው አግሮፉድና ፕላስትፕሪንት ፓክ አውደ ርዕይ ላይ ለአራተኛ ጊዜ እየተሳተፈ መሆኑን ያነሱት አቶ ሳሙኤል፤ የጥሬ እቃ አቅራቢዎች ጋር የተደረጉ ግንኙነቶችና የቢዝነስ እና ቢዝነስ ትስስር በማድረጋቸው የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው እድል እንዳመቻቸላቸው አመላክተዋል፡፡

አውደ ርዕዩ የገበያ ትስስርም ሆነ ተደራሽነትን ለማስፋት ያግዛል ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ እንደዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ አውደ ርዕዮች ሲዘጋጁ በደንብ ቅስቀሳ ተደርጎላቸው ብዙ ሰዎች እንዲሳተፉበት ሆነ እንዲጎበኙ ማድረግን ይጠይቃል ሲል አስታወቀዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል፤ ድርጅቱ ወደፊት አሁን ከሚያመርታቸው ምርቶች የተሻለ የማምረት አቅም እንዲኖረው በማድረግ ተጨማሪም ተፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት በሂደት ላይ መሆናቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን እነዚህ ምርቶች ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሁኔታዎች በማጥናት ምቹ ሁኔታ ለመፈጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠሩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

‹‹ኤች ዋይ ፊሊንግ›› የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ሌላው የአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ኩባንያ ነው። የኩባንያው የምስራቅ አፍሪካ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ መንገሻ አስፋ እንደሚሉት፤ ኩባንያው ከቻይና ሀገር ማሽነሪዎችን በማስመጣት ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ጠርሙሶችን ያመረታል፡፡ ለስላሳ፣ ለጁስ፣ ውሃ፣ ለወተት አረቄ እና የመሳሰሉት ፈሳሽ ነክ ለሆኑ መያዣ የሚሆኑ ምርቶች ለማምረት የሚችሉ ማሽነሪዎች ያቀርባል፡፡ ማሽነሪዎቹ ቻይና ሀገር የሚሰሩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ጨምሮ ለምስራቅ አፍሪካ ለማሽነሪዎቹ ሙሉ ቴክኒካል አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡

ኩባንያው በሀገር ውስጥ ካሉ ከፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ብዙ ደንበኞችን ማፍራት የቻለ መሆኑን የሚገልጹት አቶ መንገሻ፤ በባለፈው ዓመት በአውደ ርዕዩ ተሳትፈው አቅም ካላቸው ፋብሪካዎች ጋር ኮንትራት የተፈራረሙበትና ሊፈራረሙ ያቀዱ ብዙ ደንበኞች ማፍራት ችለዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት ተሞክሮ በመውሰድ በዘንድሮውም አውደ ርዕይ መሳተፍ ከቻሉባቸው ምክንያቶች መካከል ዋናዎቹ የተለያዩ ደንበኞችን በማፍራት ግብይት ለማስፋፋት እና ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ይህ አውደ ርዕይ በርካታ ደንበኞች ለማፍራት የሚያስችልና የገበያ ተደራሽነትን የሚያሰፋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉት እቃዎችን አብዛኛው ጥሬ እቃ ከሀገር ውስጥ እንደሚወሰድ ነው አቶ መንገሻ የገለጹት፡፡ ‹‹ቀደም ሲል ውጭ ሀገር ተመርተው አልቆላቸው የሚመጡ ምርቶች መኖራቸው ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ጥሬ እቃው ብቻ ከውጭ በማስመጣት ምርቶቹን ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ እየተደረገ ይገኛል›› ይላሉ፡፡ ይህም መደረጉ ሁለት ነገሮችን ማስገኘት ያስቻለ ሲሆን የመጀመሪያው ያለቀ ነገር ከውጭ ሲመጣ የውጭ ምንዛሪ ፍጆታን ይጨምራል፤ ውጭውም በዚያኑ ያህል ያድጋል፤ ሁለተኛው ቴክኖሎጂ ሀገር ውስጥ ስለመጣ ጥሬ እቃ ሀገር ውስጥ ቢኖረን ሙሉ ለሙሉ ምርቱን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹Mingjia Packaging Machinery Tech­nology ›› የተሰኘው የቻይና ኩባንያም የአውደ ርዕዩ ሌላው ተሳታፊ ነበር፡፡ የኩባንያው መስራች ሚስተር ኬቨን ጊን ኩባንያው በአውደ ርዕዩ እንደ ወተት፣ ጁስ ፣ እና የመሳሳሉ የለስላሳ መጠጦች የማሸጊያ ማሽን ይዞ መቅረቡን ይናገራሉ፡፡

ሚስተር ኬቨን ጊን እንደሚሉት፤ ኩባንያው የለስላሳ መጠጦችን ጥራታቸው በጠበቁ አልሙኒየም፣ ፕላስቲክ እና መሰል ማቴሪያሎች በተለያየ ዓይነትና ዲዛይን ለማሸግ የሚያስችል ማሽን እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡ ማሽኑ የለሰላሳ መጠጦች ከ125 ሚሊ ሊትር ጀምሮ እስከ 1000 ሚሊ ሊትር ድረስ የሚያሽግ ሲሆን፤ በሰዓት ከ3ሺ እስከ5ሺ የሚደርሱ ምርቶች ማሸግ ያስችላል፡፡

ሚስተር ኬቨን ጊን ኩባንያው በስድስተኛው አግሮፉድና ፕላስትፕሪንት ፓክ አውደ ርዕይ ላይ ሲሳተፍ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው፤ የለስላሳ መጠጦችን ማሽጊያ ማሽን ለአፍሪካ ለማስተዋወቅና ደንበኞችን የማፍራት ዓላማን ሰንቆ በአውደ ርዕዩ መሳተፉን ተናግረዋል፡ ፡ አውደ ርዕዩም ከብዙ ፋብሪካዎች ጋር ትስስር በመፍጠር እና የገበያ ተደራሽነታቸው ለማስፋት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የ‹‹ወተር ፊት ጄነራል ትሬዲንግ›› የሽያጭ ባለሙያ ወጣት ሚኪያስ መንግሥቱ ድርጅቱ ከውሃ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሥራዎችን እንደሚሰራ ይናገራል፡፡ ኤች ዲፒ ፓይፓ የተሰኘ ለውሃ መስመር አገልግሎት የሚውል ከ20ሚሊ ሊትር እስከ 450 ሚሊ ምርት የሚይዝ ምርት ያመርታል፡፡ ድርጅቱ የማምረት አቅሙን ከዚህም በላይ ለማሳደግ ፕሮጀክት ተነድፎ እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስረዳል፡፡

ምርቶቹን ለማምረት የሚውሉት ጥሬ እቃዎች ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ መሆኑን የሚገልጸው ሚኪያስ፤ ጥሬ እቃውን ከምንም ጋር ሳይቀላቀል ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚመረት ይገልጻል፡፡

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ጥራታቸው የጠበቁ ሆነው ከውጭ የሚመጣው በመተካት እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ፤ እንደገናም ምርቶቹን ወደ ውጭ ኤክስፖርትም ለማድረግ አቅዶ ጥረቶች እያደረገ ሂደቶቹን መጀመሩን ይናገራል፡፡

ድርጅቱ ሀገር ውስጥ ፍላጎት መሙላት የሚያስችል አቅም እንዳለው የጠቀሰው ሚኪያስ፤ አሁን ላይ የፕላስቲክ ምርቶች ጥራታቸው እንደተጠበቀው ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የብረት ምርቶች በፕላስቲክ እየተተኩ መሆናቸውን ይገልጻል። ህብረተሰቡም ግንዛቤ እያገኘ ምርቶችም ተቀባይነት እያገኙ በደንበኞች ዘንድ ተፈላጊ እየሆኑ መምጣታቸውን ያስረዳል፡፡

አውደ ርዕዩም የመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉ መሆኑን ጠቅሶ፤ ምርቶችን በማስተዋዋቅ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ ከሌሎች አምራች ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እና ደንበኞችን ለማፍራት የሚያስችላቸው መሆኑን አመላክቷል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You