የአዲስ ዘመን ጌጦች አንባቢያኑ ናቸው፡፡ ከአራቱም ማዕዘናት ሲጎርፉ የነበሩት የጥያቄ፤ የሃሳብና የመዝናኛ ብዕሮች ከድሮ እስከ ዘንድሮ እንደተሰደሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚሁ የአንባቢያን ብዕሮች መካከል ለዛሬ ጥቂቶቹን እንድናስታውሳቸው መርጠናል፡፡ ፖለቲካው የወለደው ፈገግታ “ደስ ብሎኛል”፤ የብዙዎች ትዝታ ከፋንታ ኦሬንጅ ብርቱካን ጋር…በዛ ብለው የሚገኙት የጥያቄ ማህደሮች ደግሞ፤ ወደ ጳውሎስ ኞኞ አምድ ይወስዱናል፡፡ ለፈገግታ የሚሆንም አልጠፋም፤ ከሱም አንዱን ተመልክተን ፈገግ እንበል፡፡
ደስ ብሎኛል
ከጳጉሜ 4 ቀን 1979 እስከ መስከረም 4 ቀን 1980 በአብዮት አደባባይ አብረን ውለን ስለ ኢሕዲሪ ምሥረታና ስለ 13ኛው የአብዮት በዓል አከባበር የተሰማኝን ደስታ ከዚያ ሁሉ ጋዜጠኛ አንዱ እንኳን አጋጥሞኝ ጥቂት ሳልተነፍስ ወደ መኖሪያ ክልሌ መመለሴ ቅር ቢለኝም፤ ደስታዬ በሆዴ ታምቆ እንዳይቀር ለጓደኞቼና ለአካባቢው ኅብረተሰብ ሁኔታውን ገልጫለሁ። ይሁን እንጂ በዚሁ ብቻ ልረካ ባለመቻሌ ይህችን አጭር ማስታወሻ ልኬአለሁ።
በመሠረቱ አብዮታችን አንድ እርምጃ ወደፊት በሄደ ቁጥር ደስታ ይሰማኛል። ደስታ በተሰማኝ ቁጥር ደግሞ ትዝ የሚለኝ አንድ ነገር አለ። ይኸውም በ1967 ዓ.ም መስከረም 2 ቀን የዘውድ አገዛዝ ሥርዓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ መነሳቱ በተበሰረበት ወቅት በነበረኝ የሥርዓቱ ጥላቻና ከደስታዬ ብዛት የተነሳ ከአሁኑ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝ በማለት ደጋግሜ የተናገርኩበት ነበር። አሁን ሳስበው ግን አባባሌ በጣም ስህተት እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ምክንያቱም ያን ጊዜ ሞቼ ቢሆን ኖሮ ይህንን ሁሉ ደስታ ማን ሊያይልኝ ኖሯል?
በኢሕዲሪ ምሥረታ ጉባዔ ላይ በተመልካችነት ተሳትፌ አብዮታችን የደረሰበትን ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ለማየት በመብቃቴ ደስ ብሎኛል።
ጌታቸው ሀብቴ ባንቲ (ከቀወት)
(አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 1980ዓ.ም)
አንድ ጥያቄ አለኝ
ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
*ሰላም ለርሶ ይሁን። ለጥያቄዎቼ አጥጋቢ መልስ እንደሚሰጡኝ አምናለሁ። እንዲያው በመድኃኒ ዓለም ይዠዎታለሁ ረዘመ ብለው ጽሑፌን እንዳይሰርዙት።
ቁመቴ ረጅም ነው። እንዲያውም አንድ ሜትር ከ74 ሳንቲ ሜትር እሆናለሁ። ስለዚህ ከጓደኞቼም ሆነ ከሌላ ሰው ከ-ዘ፣ የወሎ ፈረስ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ የሚለው የቅጽል ስም አንገፍግፎኛል። አዘጋጁንም የምጠይቅዎት በሀገራችን በኢትዮጵያ ቁመተ ረጅም ሴቶች የሉ ይሆን? እኔ ባለሁበት ከተማ ግን ከኔ በቀር ለመድኃኒትም አይገኝም። ምን ይበጀኝ ይመስልዎታል? በዚህ ግምት ባልም የሚገኝ አይመስለኝም። ባንድ በኩል የወደደኝ አይጠላኝም ባይ ነኝ።
…
ወይዘሪት የሮም ወርቅ ተፈሪ (ድሬዳዋ)
– በመድኃኒዓለም ስም ስለያዙኝ አንድም አልሠረዝኩትም። መድኃኒዓለምን በጣም እፈራለሁና ነው። ወደርሶ ጉዳይ እንመለስ። በድሬዳዋ ለመድኃኒትም ረጅም ሴት ከሌለ ለመድኃኒትነቱ እርሶ ይበቃሉ። እርግጥ መጠንዎ ለሴት ቁመት ይረዝማል እንጂ አያሠጋዎትም።
“ሽንጧ የሚመስለው ዛፍ የራቀው ሐረግ” የሚባለው ግጥም ለእንደርሶ አይነቱ ነው።
በርዝማኔዎ የሴቶችን የርዝማኔ ሪኮርድ አልሰበሩም። 1889ዓ.ም በጀርመን ሀገር ቤንኬንዶርፍ በተባለ ከተማ የተወለደችው ጀርመናዊቷ ማሪኔ ወዴ የቁመቷ ርዝመት ሦስት ሜትር ይደርስ ነበር። ባለ ሪኮርዷ እሷ ናት። እርሶ የሷ ግማሽ ኖት አይስጉ። ታኮ ጫማ አያድርጉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 1958ዓ.ም
*የፍቅር በሽታ ይዞኝ መሞቴ ነውና እባክህን ስለወንድ ልጅ አምላክ መድኃኒት ያለው እንደሆን ንገረኝ።
-ከበደ አበራ
-መድኃኒት የለውምና ትንሽ ጊዜ ማቅ።
*ኤሌክትሪክ ሲይዘን ደማችንን ይመጠናል። ደሙ የት ይሔዳል?
ዘውዱ አራጋው(ከሞጆ)
-አይመጥም። ደሙም የትም አይሔድም።
*ከፍቅር መጽሐፍ ውስጥ የሚደነቀው የትኛው ነው?
– አህመድ አብዱላሂ(ከሂርና)
-እኔ የፍቅር መጽሐፍ ማንበብ ስለማልወድ አላውቀውም።
*ሱሪ ተንተርሰው ሲተኙ ሕልም ያሳያል ይባላልና እውነት ነው?
-እኔስ ሞክሬው አላውቅም፤እስቲ አንተው ሞክረው።
( አዲስ ዘመን ታህሳስ 3 ቀን 1965ዓ.ም)
*እንቁራሪቶች ከሞቱና ከበሰበሱ በኋላ ዝናብ ሲዘንብባቸው ይነሳሉ ይባላል። እውነት ነው?
-ዳርጌ ደሳለኝ(ከደብረዘይት)
-ውሸት ነው
*ከልጅነቴ ጀምሮ ጋብቻን እጠላለሁ። ለወደፊቱም ፍላጎት የለኝም። ምን አስተያየት አለህ?
– ሐቻሞ ካበቶ(ከናዝሬት)
-ተገላግልሃል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 1961ዓ.ም)
ለፈገግታ
አንድ ወጣት ዘመዱ የሆኑትን መነኩሴ ሲያማክር “እባክዎ አባ በመልክ በጠባይ፤ በሙያ በሀብትና በትምህርት ምንም ጉድለት የሌላትን ልጃገረድ ያፈላልጉልኝና ሚስት ላግባ” ቢላቸው “እንዲህ ዓይነቷ ሴት የምትገኝ ብትሆን ኖሮ እኔም አልመነኩስም ነበር” አሉት ይባላል።
-ኤፍሬም ወንድሙ
ብዙ ሺህ የሚሆኑ የፋንታ
የፋንታ ብርቱካን መጠጦች
ፋንታ ብርቱካን በነፃ ለማግኘት 2 ልዩ ምልክት የያዙ ቆርኪዎች አጠራቅሙ(ስዕሉን ተመልከቱ) ሁለት ልዩ ምልክት የያዙ ቆርኪዎች ካላችሁ ማለት፤ ሁለቱም የጠርሙሱን ቅርጽ የሚያሳዩ ሲሆን 3 “ትንሹን” ፋንታ ብርቱካን ታገኙበታላችሁ ወይንም የጠርሙስ ቅርጽ የሚያሳይና “ትልቁ” የሚለው ቃል የተጻፈበት ሁለት ቆርኪዎች ቢኖራችሁ፤ 3 ትልቁን ፋንታ ብርቱካን ስለምታገኙበት አቅራቢያችሁ ከሚገኘው የኮካ ኮላ ኩባንያ ወይንም መደብር ወስዳችሁ ሦስት ጠርሙስ ፋንታ ብርቱካን በነፃ ይሰጧችኋል። ከዛሬ ጀምራችሁ ልዩ ምልክት የያዙ የፋንታ ብርቱካን ቆርኪዎች አጠራቅሙ። የፋንታ ብርቱካን ጠርሙስ ቆርኪዎች ሁሉ ልዩ ምልክት ስለሚኖራቸው የበለጠ ዕድል ይሰጣችኋል። በፋንታ ብርቱካን ተደሰቱ። ብዙ ቢጠጡ ዕጣውን ለማግኘት ትልቁ ዕድል የርስዎ ነው።
ፋንታ ብርቱካን በጣም ያስደስታል ….
በጠማኝ፤ በጠማኝ፤ በጠማኝ ያሰኛል
(አዲስ ዘመን መስከረም 5 ቀን 1960ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም