በማራካሽ ዳይመንድ ሊግ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል አድርገዋል

የ2024 ዳይመንድ ሊግ ውድድር ከትናንት በስቲያ አራተኛ መዳረሻ ከተማ በሆነችው በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ማራካሽ ሲካሄድ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።ከተመዘገቡት ድሎች መካከልም በ 5 ሺ ሜትር ኢትዮጵያን የወከሉት መዲና ኢሳ እና ፎይተን ተስፋይ ተከታትለው በመግባት ድንቅ ብቃት ማሳየት ችለዋል።

በቻይናዎቹ ዚመን እና ሻንጋይ ከተሞች ጅማሮውን አድርጎ ወደ ኳታሯ መዲና ዶሃ በማቅናት በተለያዩ ርቀቶች አትሌቶችን ሲያፎካክር የቆየው የዳይመንድ ሊግ መድረክ፤ በማራካሽ ሲቀጥል በትራክ (መም) እና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች በርካታ ከዋክብት አትሌቶች ድንቅ ብቃታቸውን በማሳየት ለዳይመንድ ዋንጫው እና ለመጪው የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ አቋማቸውን ፈትሸዋል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ በ800 ሜትር ሴቶች፣ 1500 ሜትር ወንዶች፣ 3 ሜትር መሰናክል ወንዶች እና 5 ሺ ሜትር ሴቶች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድንቅ ፉክክር አድርገዋል።

በ5 ሺ ሜትር ሴቶች ወጣቷ አትሌት መዲና ኢሳ በቀዳሚነት በማጠናቀቅ አሸንፋለች። ርቀቱን ለማጠናቀቅ 14፡34፡16 የሆነ ሰዓትን ፈጅቶባታል። አትሌቷ በቅርቡ ተካሂዶ በተጠናቀቀው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በርቀቱ ሀገሯን ወክላ የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወሳል።በተጨማሪም እአአ በ2022 በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር ወርቅና በ2023 የአውስትራሊያ በትረስ የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር የብር ሜዳሊያ አስመዝግባለች። ባሳየችው ተስፋ ሰጪ ብቃት በርቀቱ ወደፊት ሀገሯን ወክላ ውጤታማ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡

ፎይተን ተስፋይ 5 ሴኮንዶችን ዘግይታ 14፡34፡ 21 በመግባት ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች። በውድድሩ ኢትዮጵያን አትሌቶችን የተፎካከረችው ኬንያዊት አትሌት ኤዲናህ ጄቢቶክ በ14፡35፡64 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

ከመዲና ጋር የአሸናፊንት ቅድመ ግምት አግኝታ የነበረችው እና ጥሩ ተፎካካሪ መሆኗን ያሳየችው ሌላኛዋ ወጣት አትሌት መልክናት ውዱ አራተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሯን ፈጽማለች። አትሌቷ በመድረኩ ድል በይቀናትም ከዚህ በፊት ባደረገቻቸው ውድድሮች የግል ምርጥ ሰዓቶችን በማስመዝገብ ብቃቷን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገች ትገኛለች። በአክራው የአፍሪካ ጨዋታዎችመ የብር ሜዳሊያ ማስመዝገብ እንደቻለች ይታወሳል።ልቅና አምባው አምስተኛ፣ ጌላ ሃምቢሴ ስምንተኛ፣ ፍሬሕይወት ገሰሰ አስረኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉበት የ3 ሺ ሜትር ወንዶች መሰናክል ሌላው ፉክክርን ያስተነገደ ሲሆን ጌትነት ዋለ በሁለተኛ ደረጃ አጠናቋል። አትሌቱ በዚህ ርቀት ከፍተኛ ልምድ እና ብቃት ካላቸው አትሌቶች መካከል አንዱ ሲሆን በርካታ ውድድሮችን ማሸነፉም ይታወቃል። በምሽቱ የዳይመንድ ሊግ ውድድርም ጠንካራ ፉክክር አድርጎ 8፡09.40 በሆነ ሰዓት የሞሮኮውን አትሌት ሶፊያን ኤል-ባካሊን ተከትሎ በሁለተኝነት ጨርሷል። ሳሙኤል ፍሬው 8፡11.73 በመግባት አራተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።

ከፍተኛ ፉክክር ባስተናገደው የ800 ሜትር ሴቶች ውድድር አትሌት ሀብታም አለሙ የወድድር ዓመቱን ምርጥ ሰዓቷን አስመዘግባ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።ውድድሩን ለማጠናቀቅ 1፡57፡ 70 የሆነ ሰዓትም ፈጅቶባታል። ደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ፕሩዴንሴ ሴክጎዲሶ በ1፡57፡26 የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችላለች፡፡

በዚመን ዳይመንድ ሊግ በ 5 ሺ ሜትር ተወዳድሮ አንደኛ የወጣው አትሌት ለሜቻ ግርማ በራባት ደግሞ በ1500 ሜትር ተወዳድሮ በ3፡32፡ 86 በሆነ ሰዓት አራተኛ በመሆን አጠናቋል።በርቀቱ ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቢሳተፉም ድል ሳይቀናቸው ቀርተዋል።ለሜቻ ውጤታማ የሆነበትና እና ክብረወሰኖችን ያሻሻለበት የ3 ሺሜትር መሰናክል ውድድሮች ቢሆንም በረጅም ርቀትም ውጤታማ መሆን እንደሚችል ያሳየበት የቻይናው 5 ሺ ሜትር ውድድር ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

እአአ በ2023 የውድድር ዓመት ስኬታማ የሚባል ዓመትን እንዲያሳልፍ ካደረጉት ድሎች መካከል በፈረንሳይ ሌቪን 3 ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር እና በፓሪስ የተካሄደው የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር ሁለት ክብረወሰኖችን እንዲያሻሽል አስችለውታል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You