ከወርቅ በላይ የደመቁት ወጣት ከዋክብት

በናጄሪያ አቡኩታ እየተካሄደ የሚገኘው የአፍሪካ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል። ከእድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ ችግር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በወሰደው ጠንካራ ርምጃ በተለያዩ ርቀቶች ሃያ ስምንት አትሌቶች ብቻ በውድድሩ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ይህ ርምጃ ፌዴሬሽኑ “ጊዜያዊ ውጤት ይቅርብኝ” ብሎ ከእድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ፈር ለማስያዝ ቅድሚያ በመስጠቱ በስፖርት ቤተሰቡ ተደንቆለታል።

እንዳለፉት ዓመታት ቢሆን ኢትዮጵያ ከውድድሩ የመጀመሪያ ቀን አንስቶ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ትችል ነበር። በእድሜ ተገቢነት ላይ የተወሰደው አበረታች ርምጃ የተለመዱ ውጤቶችን ኢትዮጵያ እንድታጣ ቢያደርግም በተገቢው እድሜ የተገኙ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ እንጂ አንገት የሚያስደፉ አይደሉም። ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በአጭር ጊዜ ዝግጅት በውድድሩ የመጀመሪያ ቀን ወርቁ ቢቀርባቸውም በተለያዩ ርቀቶች ሁለት የብርና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ ችለዋል።

ወጣት ኢትዮጵያውያን ከእድሜም ከብቃትም አንፃር ተስፋ ባሳዩበት የ3ሺህ ሜትር ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያውን ለማጥለቅ ተፋልመዋል። በዚህም ትርሃስ ገብረሕይወት ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ስታሸንፍ፣ ውድነሽ አለሙ አራተኛና ቤተልሔም ጥላሁን ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል። በተመሳሳይ በ1500 ሜትር ሴት ከ18 ዓመት በታች ፍፃሜ ድንቅ ፉክክር ያደረገችው ኤልሳቤጥ አማረ የብር ሜዳልያ ስታጠልቅ፣ ደስታ ታደሰ የነሃስ ማዳልያ ማግኘት ችላለች።

በ1500 ሜትር ወንድ ከ18 ዓመት በታች ፍፃሜ በውድድሩ መሀል ከወደቀበት ተነስቶ ሜዳሊያ ለማጥለቅ እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረገው ወጣቱ አትሌት ሳሙኤል ገብረሃዋርያ በመጨረሻም የነሐስ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ ማስመዝገብ ችሏል። ትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ተወልዶ ያደገውና ከሽሬ ታዳጊ ፕሮጀክት የተገኘ ወጣት አትሌት የመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ክለብን በመወከል ድሬዳዋ ላይ በወጣቶች እና ታዳጊዎች ቻምፒዮና በ1500ሜ 2ኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ነው በአህጉር አቀፉ ቻምፒዮና ሀገሩን መወከል የቻለው። በውድድሩ በቴክኒካዊ ችግር (ተጠልፎ፣ የቦታ አያያዝ) ችግር ባይገጥመው የተሻለ ውጤት ሊያስመዘግብ የሚችልበት አቅም እንዳለው ማሳየት ችሏል።

በቻምፒዮናው ሁለተኛ ቀን ውሎም ኢትዮጵያውያን በ3ሺህ ሜትር ሴቶች ከ18 ዓመት በታች ውድድር በደስታ ታደለ እና ብርነሽ ደሴ አማካኝነት የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተመዝግቧል።

በቻምፒዮናው ሦስተኛ ቀን ውሎ ትናንት ረፋድ ላይ በ400 ሜትር ሴቶች ከ18 ዓመት በታች ፍፃሜ ባንቻለም ቢክስ ሦስተኛ ሆና በማጠናቀቅ በአጭር ርቀት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችላለች።

ቻምፒዮናው ትናንት ከሰዓት በኋላና ምሽት ላይም ሲቀጥል ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ርቀቶች የፍፃሜ ፍልሚያዎችን አድርገዋል። ዛሬም በርካታ ሜዳሊያዎች ያስመዘግቡባቸዋል ተብለው በሚጠበቁ የተለያዩ የፍፃሜ ፉክክሮች ተሳታፊ ናቸው። ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ቻምፒዮናም ነገ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ የምትጠብቅባቸው በርካታ የፍፃሜ ፍልሚያዎች ይኖራሉ።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You