በዓለም ላይ ሰፊ የሥራ ዕድልን ይፈጥራሉ ከሚባሉ ዘርፎች ውስጥ ቱሪዝም በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጥናት ውጤቶች ያመላክታሉ። ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብቷ ተጠቃሽ ከሚባሉ የዓለም አገራት መካከል አንዷ ብትሆንም ባሏት የቱሪዝም ሀብት ልክ ለበርካታ ዜጎቿ የሚሆን የሥራ ዕድል መፍጠርና ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አግኝታለች ማለት አያስደፍርም።
በአገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ትኩረት ባለማግኘቱ ዘርፉ በሙያው የተመረቁ ወጣቶችን እንኳን የማስተናገድ አቅም አጥቶ ቆይቷል። ወጣቶች በየአካባቢያቸው ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ግርጌና ራስጌ ተቀምጠው ስለሥራ አጥነት ችግር ማውራታቸው በዘርፉ ሠርተው ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ግንዛቤ እንደሌላቸው ያሳያል። ይህ ያልተሠራበት ዘርፍ በተደራጀ መንገድ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ሥራ ቢገባበት ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና የውጭ ምንዛሬንም በማስገኘት የሀገርን ኢኮኖሚ ሊያሳድግ እንደሚችል ታምኖበት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያሏት የቱሪስት መዳረሻዎች በሚፈለገው ደረጃ እንዲለሙና ቱሪስቱ ሀገር ውስጥ ገብቶ እስከሚወጣ ድረስ ማንኛውንም አገልግሎት እንዲያገኝ የሚሠራ ተቋም ነው፤ ቱሪዝም ኢትዮጵያ። የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሌንሳ መኮንን ሰሞኑን ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ምክክር ዘርፉ የሥራ ዕድል ከመፍጠርና ገቢን ከማሳደግ አንፃር የሚጠበቅበትን እንዳልተወጣ በመግለጽ በቀጣይ ወጣቶችን በማደራጀት በማሰልጠንና ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ ማስገባት ወቅቱ የሚጠይቀውና ተቋማቸውም የሚያምንበት አዲስ አሠራር መሆኑን አስረድተዋል። ከክልልና ከተለያዩ ተቋማት የተሰባሰቡት ባለድረሻ አካላትም በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ምንም እንኳን ሀገራችን ከጎብኚዎች የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ የሚናቅ ነው ባይባልም ጎረቤት አገር ኬኒያ ውስን የቱሪዝም ሀብቷን በአግባቡ በመምራት ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያገኘች መሆኑንና በአንፃሩ ሀገራችን የተሻለ አቅም ይዛ ያን ያህል ያለመጠቀሟ እንደ ማሳያ ተነስቷል። ከቱሪስት በሚያገኙት ዳጎስ ያለ ገቢ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ያሳዳጉ እንደግብጽ፣ እሥራኤልና ፈረንሳይን የመሳሰሉት የዓለማችን አገራትም በዋቢነት ተጠቅሰዋል።
አሁን በተያዘው መርሀ ግብር ወጣቶች ዘርፉን ተቀላቅለው የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ቢደረግ በየ አካባቢያቸው የሚገኙ የቱሪዝም ፀጋዎችን ወደ ኢኮኖሚ የመቀየርና አገራቸውንም በቱሪዝም ከበለፀጉ አገራት ተርታ የማሰለፍ አቅም እንዳላቸው ተወስቷል። ዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳለውና መንግሥት የሥራ አጡን ቁጥር ለመቀነስ ለያዘው አቅጣጫም በተወሰነ መልክ መልስ የሚሰጥ መልካም ጅምር እንደሚሆን ሀሳብ ተሰጥቶበታል። ከየክልሉ የመጡ ባለሙያዎችም የአካባቢያቸውን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት አድርገው ሲገልፁ በቱሪስት መዳረሻዎች የሚታየው ዘልማዳዊ የአገልግሎት አሰጣጥ በርከት ያሉ የሥራ ዘርፎችን አካቶ ዘመናዊ በሆነ መልክ እንዲይዝ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኦሮሚያ ክልል ኢንተር ፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ቶሎሳ በክልሉ በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የቱሪዝም ፀጋዎች እንዳሉ በመግለጽ እስከ አሁን ግን እንደሌሎች ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ እንዳልተሰራበት ይንገራል። ቀደም ሲል እንደ ማኑፈክቸሪንግና ኮንስትራክሽን ያሉት የሥራ ዘርፎች በርካታ ወጣቶችን የተሸከሙና ገቢ የሚያስገኙ መስኮች ነበሩ የሚሉት ዳይሬክተሩ ከአራት ዓመት ወዲህ ደግሞ እምብዛም ውጤት ይታይበት ያልነበረው የማዕድን ዘርፍ ዛሬ ላይ ከሌሎች ዘርፎች በተሻለ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው ብለዋል። ከፍተኛ ገቢን እያስገኘ እንዳለ ተናግረዋል።
ይህ የሆነው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በመሰራቱና ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሠሩ በመደረጉ ነው ። አሁንም ባልተነካው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተሠርቶ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሠሩ የሚያደርግ አሠራር ቢዘረጋ ውጤት እንደሚመጣበት አያጠራጥርም ይላሉ። በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት በርካታ ሃይቆች፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ መዳረሻዎች፣ ፓርኮች ሎጆችና መዝናኛዎች ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩና በእጃችን እያሉ ያልተጠቀምንባቸው ሀብቶቻችን ናቸው ይላሉ።
በተሰጠው አቅጣጫ መሰረትም ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የቱ አካባቢ ምን ዓይነት የቱሪዝም ሀብት አለን፤ ምንያህል የሰው ሃይል ለማሰማራት ያስችላል፤ ምንምን ሥራዎችን ለማከናወን ይረዳል የሚሉትን በመለየት ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችል አቅም ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል። በክልሉ መጠነኛ ጅማሮዎች እንዳሉ የገለፁት አቶ ፍቃዱ አሁን እንደ ሀገር በአዲስ መልክ የተጀመረው እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረውና ክትትልና ድጋፍ ተደርጎለት ዳር ማድረስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
አቶ ይርጋ ጌትነት የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው በአማራ ክልል በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ቢኖሩም በዘልማድ ከሚንቀሳቀሱ ጥቂት ወጣቶች በስተቀር በሚፈለገው መጠን ወጣቶች ተደራጅተው በየጊዜው ወደ ክልላችን ለሚመጡ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኝዎች አገልግሎት በመስጠት እራሳቻውን መለወጥ የሚያስችል ዕድል ፈጥረዋል ማለት አይቻልም ይላሉ።
ቱሪዝም ለተማረውም ላልተማረውም የህብረተሰብ ክፍል የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ዘርፍ ነው የሚሉት አቶ ይርጋ በሆቴልና ቱሪዝም የተመረቁ ወጣቶች በመረጃ መስጠትና በጋይድ ቢሠሩ ሌሎች ደግሞ መጓጓዣ፣ ድንኳን፣ የምግብ ማብሰያና የመሳሰሉትን በማከራየት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አስረድተዋል። ይሁንና ወጣቶቹ ለጎብኚዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲጡ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሊፈጠርላቸው ይገባል። መንግሥት የስልጠና፣ የብድርና የቦታ አቅርቦት በማድረግ የታሰበውን አዲስ የሥራ ዘርፍ ውጤታማ ማድረግ ይቻላል ይላሉ።
በአማራ ክልል የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ኤክስፐርት አቶ ኑሩ ወለላው እንደሚሉት ደግሞ ዘመናዊ ቱሪዝም ቱሪስቶች አይተው የሚሄዱበት ብቻ ሳይሆን በመሥራትና በዓይን ተመልክተው ራሳቸውም ተሳትፈውበት የበለጠ እርካታ የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። በዘመናዊ ቱሪዝም ቱሪስቶች በሚጎበኙበት አካባቢ የሚዘጋጁ ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦች እራሳቸው እያዘጋጁ የመጠቀም ፍላጎት አላቸው።
ለምሣሌ ጠጅ እንዴት እንደሚሠራ፣ እንጀራ እንዴት እንደሚጋገር በቦታው ሆነው እራሳቸው እያዘጋጁ የመጠቀም ፍላጎታቸው እየዳበረ መጥቷል። ስለዚህ የፍላጎታቸው መጨመር በርካታ የሥራ ዕድልን ይፈጠራል። አንድ ቱሪስት የሀገራችን የቡና አፈላለ ሥርዓት ከሚነገረው ይልቅ አሠራሩን ቢያየው ይመርጣል፤ ከማየት አልፎም በሥራው ላይ ቢሳተፍ ደስ ይለዋል።
ቡናውን መቁላት፣ መውቀጥ፣ የምድጃውን እሳት እየቆሰቆሱ ማፍላት ያረካዋል። ቱሪስቱ ስፌት መስፋት፣ እንጀራ መጋገር፣ ጠጅ መጥመቅ፣ አሠራሩን እያየ መመራመር፣ ማወቅ፣ የሰውን አኗኗር አይቶ ሳይሆን ሆኖ ወይም ኖሮ ማወቅ ይፈልጋል። በዚህ ሂደት አገልግሎቱን በማስፋት የወጣቶችን ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይቻላል ።
ቱሪስቶች በሚያርፉበት አካባቢ እንደዚህ አይነት አገልግሎት ቢያገኙ የቆይታ ጊዜያቸው ይረዝማል፤ እንደ ላልይበላ፣ አክሱምና ሶፍ ኡመርን በማየት ከሚረኩት በላይ የህብረተሰቡን ባህላዊ ምግቦችና አለባበሶች እየሠሩ ለመጠቀም በሚያደርጉት ይደሰታሉ። ወጣቶች በዚህ መንገድ አገልግሎት ቢያቀርቡ ያልተጠቀምንበትንና ያልሸጥነውን የሀገራችንን ሀብት ልናስተዋውቅ የምንችልበት መልካም አጋጣሚ ይፈጠራል።
የዕደ ጥበብ ውጤቶችና የየአካባቢውን ባህላዊ ቁሶች በመሸጥም ገቢ ማግኘት ይቻላል። የ ቱሪዝም ሥራ እንደሌሎች ሥራዎች ውጤቱ አይዘገይም እዛው በእዛው ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ሥራ ነው። ቱሪስቱ አገልግሎት እስከተሰጠው ድረስ የያዘውን ብር ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጁ ነው።
በመጨረሻም ቱሪዝም ያልተጠቀምንበት ዘረፍ እንደሆነ በመግለጽ የተለያዩ አገሮች እዚህ ግባ የሚባል የቱሪስት መዳረሻ ሳይኖራቸው እያገኙ ያሉትን ጥቅም ስንመለከት እኛ ይህ ሁሉ ሀብት እያለን ያለመጠቀማችን ያስቆጫል። ስለዚህ ወጣቱ ቱሪስቶችን እየተከተለ ልብስ እየጎተተ እጅ ከሚዘረጋ ተደራጅቶ አገልግሎት በመስጠት የተሻለ ጥቅም ማግኘት የሚችልበት ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮለታል።
በሐረሪ ክልል የከተማ ምግብ ዋስትና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አለማየሁ እሸቱ ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ እርሳቸውም በክልሉ የጀጎል ግንብንና የጅብ ትርኢትን የመሳሰሉ መስዕቦች እንዳሉ ጠቅሰው የቱሪዝም ዘርፍ በሚፈለገው ደረጃ አልተሰራበትም ይላሉ። ሐረር ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ተብላ በዩኔስኮ አንደመመዝገቧ ከቱሪስት ጥቅም አግኝታለች ማለት አይቻልም ይላሉ። ለዚህም ዋናው ምክንያት በሚፈለገው መጠን ለዘርፉ ትኩረት የሰጠው አካል ባለመኖሩና የአካባቢውን ወጣቶች አደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገቡና አካባቢያቸውንም በማስተዋወቅ እራሳቸውን እንዲጠቅሙ የሚያደርግ አሠራር ባለመኖሩ ነው ይላሉ።
አሁን ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ለሐረር አካባቢ ወጣቶች ሠርቶ የመኖር ህልውና ይፈጥርላቸዋል ይላሉ። በየክልሉ ያሉ ወጣቶች በተለይም በሙያው የተመረቁ ወጣቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ዘርፉ ያለውን አቅም ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር የተፈጠረላቸውን አጋጣሚ የሚጠቀሙበት ወቅት አሁን ነው ይላሉ። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቱሪስት መዳረሻ የሚገኙ ወጣቶችን ግንዛቤ በማጨበጥ በማሰልጠንና የብድር አገልግሎት በማመ ቻቸት ለቱሪስቶች የሚሰጡትን አገልግሎት አስፍተው መሥራት እንዲችሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011
እያሱ መሰለ