ለአንድ ሀገር ሁሉን አቀፍ ነጻነትና ሉዓላዊነት እውን መሆን በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ፣ ማህበራዊ ሁነት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂያዊ ክስተት፣… እየተባሉ ሊዘረዘሩም ይችላሉ። ከእነዚህ ሁሉ በተለየ መልኩ የሚገለጽ አንድ ጉዳይ ግን አለ። ይሄም የሀገር መከላከያ ኃይል።
ይሄ ተቋምና ኃይል ደግሞ ለአንድ ሀገር ከፍ ያለ የነጻነት ገጽ፤ የሉዓላዊነት መልክ ያለው አበርክቶ እንደ ሌሎች መስኮች የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም ዘርፉ ኢኮኖሚንም፣ ቴክኖሎጂንም፣ የሰው ኃይልንም የሚፈልግ ብቻ ሳይሆን፤ ስለ ሀገር ክብር፣ ሉዓላዊነትና ነጻነት ሲባል የሕይወት መስዋዕትነትንም የሚጠይቅ ነው።
ዛሬ ላይ ሀገራት “ኃያል” የመባላቸው ምስጢርም፣ ያላቸው የኢኮኖሚ ከፍታ፤ የቴክኖሎጂ እምርታ ብቻ አይደለም። በዚሁ ልክ የተገነባ የመከላከያ እና የደህንነት አቅማቸውም ጭምር ከፊት ተሰልፎ የሚገለጽ እንጂ። እነ አሜሪካ ኃያል ቢባሉ፤ እነ ቻይና አስፈሪ ሆነው ቢወጡ፤ እነ ሩሲያ ፈርጣማነታቸው ተደጋግሞ ቢገለጥ፤… ሁሉም ከኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ አቅማቸው ባሻገር የሚታይ የመከላከያ አቅም በመገንባታቸው ነው።
ይሄ የመከላከያ እና ደህንነት አቅማቸው ታዲያ በስም ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ይልቁንም ከፍ ያለ የሰው ኃይልን ያቀፈ፤ በቴክኖሎጂ የተደራጀና ራሱም የቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ የሚገለጥ ነው። በተመሳሳይ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ አቅምን የሚፈልግ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም ያለው ሆኖ የተገነባ፤ እየተገነባም ያለ ነው።
ለዚህም ነው ሀገራት ነጻነት እና ሉዓላዊነታቸው ከትናንት እስከ ዛሬ ጸንቶ የመዝለቁ ምስጢር፤ የነገ ዋስትናም ሊኖረው የመቻሉ እውነትን ሊያረጋግጡ ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ የመከላከያና ደህንነት አቅምና አቋማቸው ተደርጎ የሚወሰደው። ለዚህም ነው ሀገራት የመከላከያ እና ደህንነት ተቋሞቻቸውን በማዘመን፣ በማደራጀትና በማላቅ ተግባር ላይ ተጠምደው መታየታቸው።
ኢትዮጵያም እንደ ሀገር፤ ያውም ከፍ ያለ የነጻነትና ሉዓላዊነት ታሪክ እንዳላት፣ ያልተቆራረጠ ሥርዓተ መንግሥት አጽንታ እንደኖረች ታላቅ ሀገር፤ ይሄንን ታሪክና ታላቅነቷን የሚመጥን የመከላከያ እና የደህንነት ኃይል እውን ለማድረግ እየተጋች ትገኛለች። በዚህ ረገድ፣ ከጥንት እስከ ዛሬ ለነጻነትና ሉዓላዊነቷ ሲሉ የተዋደቁላት፤ ስለ ክብሯ የሞቱላት አያሌ ጀግኖችን ያፈራች ሀገር በመሆኗም ነው በዘመናት ጉዞዋ ውስጥ ነጻና ሉዓላዊት ሆና የመዝለቅ ታሪኳን ሳታደበዝዝ የኖረችው።
ይሄን ታሪኳን የበለጠ ለማጽናት ሲባልም፣ ከ116 ዓመት የተሻገረ የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል ዘመናዊ እና የተደራጀ የማድረግ ተግባር ተከናውኗል። በዚህም እንደየዘመኑ እና ሥርዓቱ መከላከያው አደረጃጀቱ እየተቃኘ ዛሬ ላይ ደርሷል። ዛሬ ደግሞ የመከላከያው ሌላ ገጽ፤ ሌላ ቁመና፣ ሌላ አቅምና አቋም ይፈልጋል።
ይሄን ታሳቢ በማድረግም እንደ ሀገር በተለይም ከለውጡ ማግስት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል። የአደረጃጀትና የተቋም ሪፎርምም ተፈጥሯል። ዘመኑን በሚመጥን መልኩም የምድር፣ የአየር፣ የባሕር እና የሳይበር አውዶች ተፈጥረውለትም ተዋቅሯል። ይሄን አወቃቀር ለመተግበር የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም እንዲፈጠር፤ የባህር መዳረሻም እንዲኖር ተሠርቷል፤ እየተሠራም ይገኛል።
በተለይ ከለውጡ ማግስት የተካሄደውን ተቋማዊ ሪፎርም ተከትሎ፣ ዘርፉን በሰው ኃይል የማደራጀት፣ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በማድረግ፣ የሰው ኃይሉንም በሥልጠና በማብቃት እና ሌሎችም መከላከያና ደህንነቱን ከፍ ብሎ እንዲገለጥና ዘመኑን የሚመጥን ቁመና እንዲኖረው የሚያስችሉ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛል።
ይሄው ተግባር ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ ከሰሞኑ የታዩ ሁነቶችም መከላከያውን ዘመኑን የሚመጥን አቋምና ቁመና እንዲላበስ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ አቅም እንዲኖረው ብቻ ሳይሆን፤ የዘርፉ ቴክኖሎጂዎችን በራሱ አቅም እንዲያደራጅ፤ የሰው ኃይሉም ብቁ እና ጤናማ ሆኖ እንዲሰለፍ የሚያደርጉ የሥልጠና እና የጤና ማዕከላት ግንባታ ተግባራት መከናወናቸውን የሚያረጋግጡ ናቸው።
በአንድ ሀገር ያለ የመከላከያ እና ደህንነት ኃይል ደግሞ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ከፈጠረ፤ ቴክኖሎጂን የሚያውቅ፣ የሚያፈልቅና የሚጠቀም እንዲሁም ብቁና ጤናማ በሆነ የሰው ኃይል ከተደራጀ፤ ዘመኑን የሚመስሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መታጠቅና መጠቀም ከቻለ፤… ለሀገር ነጻነትና ሉዓላዊነት መጠበቅ የሚኖረው ሚና ከፍ ያለ ነው። ይሄን መሰል ተቋምና ኃይል መገንባት መቻልም እንደ መንግሥት የሀገርን የተሟላ ነጻነትና ሉዓላዊነት የማፅናት ከፍ ያለ መሻት መገለጫዎች ናቸው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2016 ዓ.ም