ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በርካታ ዘመናዊ ስቴድየሞች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኘውና የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው እየተጠናቀቀ ካለው ብሔራዊ ስቴድየም አንስቶ በባህርዳር፣ ሐዋሳ፣መቐለና ሌሎች ክልሎች እየተገነቡ የሚገኙ ዘመናዊ ስቴድየሞች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግንባታቸውን አጠናቀው በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) እውቅና በማግኘት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እስከ ማስተናገድ ደርሰዋል፡፡
ሀገራችንም በስፖርቱ ዘርፍ የተለየ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ የምትገኘው ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ ነው። በዚህም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የአገራችን ክልሎች ከትንንሽ ጥርጊያ ሜዳዎች እስከ ትልልቅ ስቴድየሞች፣ ጅምናዚየሞች፣ የመዋኛ ገንዳዎችና ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ስምንተኛው የስፖርት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው ከ2003ዓ.ም በፊት በተለያየ ደረጃ የሚገኘው የአገሪቷ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ብዛት 26ሺ281 የነበረ ሲሆን፤ ከ2003ዓ.ም እስከ 2007ዓ.ም ባለው የዕቅድ ዓመት 20ሺ497 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለመገንባት ቢታቀድም 19ሺ807ያህሉ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ትልልቅ ስቴዲየሞች ተገንብተዋል። በዚህም መሰረት የእቅዱ አፈጻጸም 96 ነጥብ 6 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።
የኦሊምፒክና የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችን መርህ መነሻ በማድረግ ህብረተሰቡን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በስፋት በማሳተፍ እና ተጠቃሚነቱን በማጎልበት የበርካታ ባህልና ትውፊቶች ባለቤት የሆኑ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በአንድ መድረክ ተገናኝተው የባህል እና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ታስቦ 1990 ዓ.ም የተቀረፀው አገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ብቻም ሳይሆን አገራችን ለገነባቻቸው ዘመናዊ ስቴድየሞች መነሻ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ክልሎች የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ለማስተናገድ እንዲያስችላቸው የተለያዩ መካከለኛ ደረጃ ላይ ሊመደቡ የሚችሉ ስቴድየሞችን እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ገንብተዋል፣ እየገነቡም ናቸው፡፡ ከብሔር ብሔረሰቦች ቀን ጋር ተመሳሳይነት ያለው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችም በአገራችን ለሚገነቡ ግዙፍ ስቴድየሞች ዋነኛ ምክንያት ነው። ይህም አገራችን በምትከተለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን በማጠናከር በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ መተሳሰብ እና መቀራረብ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ታምኖ በታል።
የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች የሆኑት የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችና የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለአገሪቱ ትልልቅ መሠረተ ልማቶችን አስገኝተዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ኢትዮጵያ የአፍሪካን ሁለተኛውን ትልቅ የእግር ኳስ ዋንጫ የ2020 አፍሪካን ኔሽን ቻምፒዮን ሺፕ (ቻን) አዘጋጅነት እድል እንድታገኝ እነዚህ ስቴድየሞች ካፍን ማሳመን ችለዋል። ዋነኛው የአፍሪካ ዋንጫም ቢሆን በቅርብ ዓመታት ወደ አገራችን እንደሚመጣ ማሳያዎች ናቸው። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በየሁለት ዓመቱ የሚካሄዱትን መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ እያሳዩ ያለው ፉክክር ወደ መጋጋል ደረጃ ለመምጣቱ አንዱ ማሳያም የስቴድየሞች ግንባታ ነው፣ ክልሎች ውድድሮችን ለማዘጋጀትና መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ ለመገኘት የሚያደርጉት ሽር ጉድ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች ቀንም ከመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ባልተናነሰ መልኩ ለስቴድየሞች ግንባታ ዋነኛ መነሻ ነው። በነዚህ ስቴድየሞች ግንባታ ሂደትም በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ከመፈጠሩ ባሻገር በግንታው ዘርፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሊንቀሳቀስ ችሏል። በዚህም የአገራችን ተቋራጮችን አቅም ከማሳደጉ በተጨማሪ በዘርፉ ትልቅ የእውቀት ሽግግር ሊደረግ ችሏል። በብሔር ብሔረሰቦች ቀን አማካኝነት ግንባታቸው ከተጀመሩ ስቴድየሞች መካከል በጋምቤላ ፣አፋር ፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የሚገነቡት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ለመሆኑ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ያፈሯቸው እነዚህ ስቴድየሞች አሁን ላይ በምን ደረጃ ይገኛሉ? ግንባታቸውስ መቼ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባሉ? የሚሉ ጥያቄዎች በስፖርት ቤተሰቡ ይነሳል። ዛሬ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሚከበርበት እለት እነዚህ ስቴድየሞች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለመዳሰስ ወደድን።
የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የነዚህን ስቴድ የሞች፣ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ማሰልጠኛ ማዕከላት ግንባታ የደረሱበትን ደረጃ እንዲሁም በስራ ላይ የሚገኘውን እንቅስቃሴ ምልከታ ለማድረግ እና መረጃ ለመሰብሰብ ሁለት ቡድኖችን በቅርቡ ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ልኳል፡፡ በተገኙት መረጃዎች መሰረትም እነዚህ አራት ስቴድየሞች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ጋምቤላ ብሔራዊ ስቴድየም
በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እየተገነባ የሚገኘው ጋምቤላ ብሔራዊ ስቴድየም የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ምክንያት በማድረግ ነበር ግንባታው የተጀመረው፡፡ የዚህ ስቴድየም ግንባታ የካቲት 12/2007 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በሁለት ዓመታት ውስጥ ተገንብቶ 2009 ዓ.ም ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ታስቦ ነበር፡፡ አምስት ነጥብ ዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ስቴድየም በመቀመጫ ከሰላሳ አምስት እስከ አርባ ሺ ሰው የመያዝ አቅም አለው፡፡ ስቴድየሙ በአፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽን ተቋራጭነት እና በኤም ኤች ኢንጂነሪንግ አማካሪነት የሚገነባ ሲሆን ባለቤትነቱ የጋምቤላ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ነው፡፡ ለስቴድየሙ ግንባታ የተመደበው በጀት ስድስት መቶ አርባ ስምንት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሰባ ስድስት ሺ አምስት መቶ ዘጠና ብር ሲሆን ግንባታው በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ይከናወናል፡፡
በነዚህ ምዕራፎችም የስቴድየሙ የስትራክቸር ስራን ጨምሮ የመሮጫ ትራክ (መም)፣ የወንበር ገጠማ፣ የሦስት በአንድ ሜዳ (የቅርጫት፣ቮሊ ቦል፣እጅ ኳስ ሜዳዎች)፣ የመብራት፣የጣራ፣ የመዋኛ ገንዳ ስራዎች ይገነባሉ፡፡ በዚህ ክልል አምስት ብሔረሰቦች የሚገኙ በመሆናቸው የስቴድየሙ መግቢያ በሮች አምስት ተደርገው የሚገነቡ ሲሆን ሲጠናቀቅም በየስማቸው የሚሰየም ይሆናል፡፡ የስቴድየሙ ግንባታ አሁን ላይ አራባ ዘጠኝ በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን ግንባታው በተፈለገው ፍጥነት እየተጓዘ እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በክልሉ ባህላዊ ቁስ ዲዛይን ተደርጎ እየተገነባ ከሚገኘው ስቴድየም ጎን ለጎን የተለያዩ ስፖርቶች ማሰልጠኛ ማዕከል በክልሉ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ይህን ማዕከል ለመገንባት ከአስራ ሁለት ሔክታር በበለጠ መሬት ላይ በሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ነበር፡፡ ለዚህ ካርታ ተሰርቶ የነበረ ቢሆንም ምክንያቱ ሳይታወቅ ቦታው ተነጥቆ ለባለሀብት መሰጠቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በምትኩ ሌላ ተለዋጭ ቦታ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ድረስ ምንም እንዳልተፈጠረና በአጠቃላይ የማዕከሉም የስቴድየም ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶት እየተገነባ እንዳልሆነ ታውቋል፡፡
አሕመድ ነስር መታሰቢያ ስቴድየም
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እየተገነባ የሚገኘው አሕመድ ነስር መታሰቢያ ስቴድየም በአስራ አራት ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡ የዚህ ስቴድየም ግንባታ የካቲት 23/2006 .ም የተጀመረ ሲሆን ጥቅምት 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡ ሰላሳ ሺ ተመልካቾችን በወንበር የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የሚገነባው የዚህ ስቴድየም ግንባታ ወጪው በመንንግስት የሚሸፈን ሲሆን በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ ይገነባል፡፡ ለሦስቱ የተለያዩ ምዕራፍ ግንባታዎች ሦስት የተለያዩ በጀቶች ፀድቀው በስራ ላይ ውለዋል፡፡ ለመጀመሪያው ምዕራፍ ስልሳ ሰባት ሚሊዮን ብር ፣ ለሁለተኛው መቶ ሰባ ሁለት ሚሊዮን ብርና ለሦስተኛው ሁለት መቶ ሃያ ሦስት ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ እካሁንም በአጠቃላይ ሦስት መቶ አርባ ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡
በዚህም ሃምሳ በመቶ ግንባታው ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ ስቴድየሙ ስምንት በሮች እንዲኖሩት ተደርጎ የሚገነባ ሲሆን ሜድሮክ ኮንስትራክሽን በተቋራጭነት፤ ኤም ኤች ኢንጂነሪንግ በአማካሪነት ይገነቡታል፡፡ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስቴድየሙ ባለቤት ሲሆን ለግንባታው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ቢገኝም በአሁኑ ጊዜ በተፈለገው ፍጥነት ግንባታው እየሄደ እንደማይገኝ ታውቋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በክልሉ የሚገኘው ወንበራ ወረዳ ላይ በአስራ ሁለት ሔክታር መሬት ላይ የወጣት ማዕከል ለመገንባት ዲዛይኑ ተጠናቆ በስፖርት ምክር ቤት ላይ ቀርቦ መጽደቁ ታውቋል፡፡ ይህ ማዕከል የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮኗ አትሌት አልማዝ አያና የትውልድ ቦታ ላይ የአትሌት መንደር ለመገንባት ያለመ ሲሆን ያለፈው 2010ዓ.ም ላይ የመሰረት ድንጋይ ይቀመጣል ተብሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ማዕከል ግንባታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ አልተቻለም፡፡
የሐረር አባድር ስቴድየም
በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሚገነባው የሐረር አባድር ስቴድየም ሚያዝያ 2008 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረ ሲሆን ስትራክቸራል ስራው ጥቅምት 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግንባታውን በታሰበበት ጊዜ ለማጠናቀቅ በ2010 ዓ.ም ሦስት መቶ ስልሳ ሚሊዮን ብር ተመድቦ ግንባታው እንዲፋጠን ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ግንባታው እንደተቋረጠ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ስቴድየሙ የስትራክቸራል ስራው የግንባታ አፈፃፀም ስልሳ አምስት በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን ፋይናንሽያል አፈፃጸሙ ሰላሳ ሦስት በመቶ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ስቴድየሙ ሙሉ በሙሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን እስካሁን ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ከአባድር ሁለገብ ስቴድየም በተጨማሪ በቀጣይ በስቴድየሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ የስልጠና ማዕከል ለመገንባት ታቅዷል፡፡ ይህም ግንባታ በሰማንያ ሁለት ሺ ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ይሆናል፡፡ ግንባታው በአፍሮ ፂዮን ኮንስትራክሽን አማካኝነት የሚከናወን ሲሆን የግንባታውን ጥራት ሸገዝ አማካሪ ድርጅት ይቆጣጠራል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በሐረር ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ጅምናዚየም ተገንብቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ምን ያህል በጀት እንደወጣበት ማወቅ እንዳልተቻለ ከፌዴራል ስፖር ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክልሉ ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ እየተገነባለት ይገኛል፡፡
ሰመራ ስቴድየም
በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እየተገነባ የሚገኘው የሰመራ ስቴድየም ሐምሌ 18/2009 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በሦስት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ሐምሌ 18/2012 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ሰላሳ ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ይህ ስቴድየም በአስራ ሰባት ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ግንባታውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ተይዞለታል። አሁን ላይ የስቴድየሙ ስትራክቸራል ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአጠቃላይ የስቴድየሙ ግንባታ አርባ አራት በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ግንባታው እንደመጀመረ ከሌሎቹ ስቴድየሞች አኳያ በተሻለ ፍጥነት እየተጓዘ እንደሚገኝ መታዘብ ይቻላል። ግንባታውን አፍሮ ፂዮን ኮንስትራክሽን ውል ወስዶ እየሰራ ሲሆን ኤም ኤች ኢንጂነሪንግ የግንባታውን ጥራት ይቆጣጠራል።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2011
ቦጋለ አበበ