‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› የሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲስፋፉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠረ ይገኛል። ንቅናቄው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ተደራሽነታቸው እየሰፋ መምጣቱ ይነገራል። ንቅናቄ በተለያዩ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚሊኒየም አዳራሽ የከፈቱት ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።
በኤክስፖ የማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ210 በላይ ኩባንያዎች ምርታቸውን አቅርበው ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተከናውኗል። በ74 የገበያ ትስስር መፈጠሩንና ሰባት የውጭ ሀገራት የኢትዮጵያን ምርት ለመግዛት መስማማታቸውን ገልጸዋል።
ኤክስፖ ላይ የተሳተፉ አምራቾችም ኤክስፖው በፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ምርቶቻቸውን እንዲያስፋፉ ምቹ ሁኔታዎች እንደተፈጠረላቸው ይገልጻሉ። አቶ አክመል ሽኩር ‹‹የአውሳን››ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሊቀመንበር ናቸው። ‹‹አውሳን›› ዓለም ገና ወለቴ አካባቢ ባለ ኢንዱስትሪ ዞን የተመሠረተ ጨርቃጨርቃና አልባሳትን የማምረት ሥራ ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው። 30 ሠራተኞች ይዞ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፤ አሁን ላይ ከ300 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት አቶ አክመል ይናገራሉ።
ድርጅቱ ከሕፃናት ጀምሮ እስከ አዋቂ እድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች የሚሆኑ አልባሳት የሚያመርት ሲሆን፤ ሱሪዎች ፣ ሸሚዞች ፣ጃኬቶችን እና የመሳሰሉ የተለያዩ አልባሳትን ያመርታል። በተለይም ደግሞ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የደንብ ልብሶች (ዩኒፎርሞችን) ያመርታል። ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎችን የደንብ ልብስ (ዩኒፎርሞችን) አምርቶ ማቅረቡንም አስታውሰዋል።
ያመረተቻቸውን የደንብ ልብሶች ተማሪዎች ለብሰው ሲያዩአቸው በእጅጉ እንደሚደሰቱ ነው አቶ አክመል የሚገልጹት። በአሁኑ ጊዜ ሀገር ውስጥ ተመርተው የሚለበሱ ልብሶች እየተበራከቱ በመሆናቸው በዚያው ልክ ደግሞ ለባሾችም እየበዙ መምጣት የሀገር ውስጥ አምራቾችን የሚያበረታቱ በመሆናቸው ያለውን የገበያ እንቅስቃሴ የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹ስራውን ስንጀምር አብዛኛው ሰው የሀገር ውስጥ ምርቶች ጥራትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ናቸው በሚል አይጠየቅም ነበር፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የኅብረተሰቡም አመለካከት እየተቀየረ በመምጣቱና እኛም ደግሞ እያደረ በጥራት ላይ ማሻሻያዎች በማድረጋችን አሁን ላይ የእኛን ምርቶች የሚመለከቱት ሰዎች፤ እነዚህ አልባሳት እውን ሀገር ውስጥ የተመረቱ ናቸው የሚል ጥያቄን እንዲያነሱ አድርጓል›› ይላሉ።
ድርጅቱ ከስፌት ጀምሮ በጥራት እየተሻሻለ መምጣቱ፤ የሰውን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ጥራታቸውን የጠበቁ አልባሳት እያመረተ ነው የሚሉት አቶ አክመል፤ የምናመርተው አልባሳት ከውጭ ከሚገቡት የበለጠ ጥራት ያላቸው በመሆናቸው ብዙ ሰው እየለበሳቸው እየተጠቀመባቸው ይገኛል ሲሉም ያስረዳሉ።
አቶ አክመል ለአልባሳት የሚሆኑ የጥሬ እቃ አቅርቦት ከሀገር ውስጥና ከውጭ እንደሚያስገቡ ይገልጻሉ። ከውጭ የሚገቡ ጥሬ እቃዎች ለማምጣት ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈተና እየሆነባቸው መሆኑን አንስተው፤ ችግሮቹ የሚቀረፍ ከሆነ የተሻለ ምርቶች ማምረት እንደሚችሉ ያስረዳሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ላይ ያለው የፋብሪካው የማምረት አቅም እንደሚመረተው የጨርቅ አይነት የሚወሰን ቢሆንም በቀን በአማካይ ከ3ሺ እስከ 5ሺ አልባሳት ይመረታል። ምርቶቹን መርካቶ ለሚገኙ አከፋፋዮች ያስረክባሉ። እንዲሁም ምርቱን ለሚፈልጉ ተቋማት ያስረክባሉ።
እነዚህም ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባሻገር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲቻል ያሉ ሂደቶችን በማጠናቀቅ በቅርቡ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል። የሀገር ውስጥ አልባሳት በዋጋ ደረጃ ቢሆን የኅብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ባማከለ መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአከፋፋዮች የሚያስረክቡ መሆኑን ነው አቶ አክመል ያስረዱት፤
የጨርቃጨርቅ ሥራ ዘርፉ በአብዛኛው የሰው ኃይል የሚይዝ መሆኑና በዘርፉ የሚሰማሩ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሥራ የመልቀቅ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቅሶ፤ በእነዚህ ሰዎችን ለመተካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ላይ ተሳታፊ መሆናችን ብዙ ሰዎች እንድንገናኝና የገበያ ትስስር እንድንፈጥር ረድቶናል። የመጀመሪያው ምርታችንን ተመልክተው እንደዚህ አይነት አልበሳት ሀገር ውስጥ መመረታቸውን ማወቃቸው በራሱ ትልቅ ግብዓት ነው። ሁለተኛው የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል እድልን የፈጠረ ነው። በተጨማሪም ለእኛም ከሌሎች ጨርቅ አምራቾች ጋር ስምምነት ለመፍጠር የሚያስችል እድል ፈጥሮልናል›› ይላሉ።
ሌላኛው የኤክስፖ ተሳታፊ የንብ ከረሜላ ፋብሪካ የማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ፋሲል ናደው ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ፋብሪካው የሚገኘው ቡራዩ ታጠቅ አካባቢ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ነው። የንብ ከረሜላ ፋብሪካ ከ50 ዓመት በላይ ያስቆጠረ አንጋፋ ድርጅት ነው። በመጀመሪያ ላይ በከረሜላ ምርቶቹ ነበር የሚታወቀው። አሁን ላይ ወደ ቸኮሌት ምርት ገብቶ የተለያዩ ቸኮሌቶችን እያመረተ ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።
ለቸኮሌት ምርት የሚውሉ ጥሬ ግብዓቶችን በብዛት የሚያስመጡት ከምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች ከጋና እና አይቬሪኮስት ሲሆን፤ የሚመጣው የግብዓት አይነት የኮካዋ ፍሬ ነው። የኮካዋ ፍሬ በፋብሪካ ውስጥ በተለያየ ሥርዓት ተቀነባብሮ የሚጣፍጥ ሆኖ ለገበያ ያቀርባል።
በአሁኑ ሰዓት ምርቶቹ በሱፐር ማርኬቶች፣ በሆቴሎች፣ በሱቆች ስለሚገኙ በጣም በርካታ ደንበኞች ምርቶቻችን ይጠቀማሉ የሚሉት አቶ ፋሲል፤ ‹‹ምርቶቹ በገበያው በደንብ የሚታወቁ ከመሆናቸው በላይ ሀገር ውስጥ የትኛው ቦታ ላይ ቸኮሌት ሲባል የንብ ቸኮሌት ታዋቂና ተመራጭ ነው›› ይላሉ። ንብ ቸኮሌት ያገኘውን ይህን የታዋቂነትና ተመራጭ በደንብ ሰርጾ ገብቶ ‹ብራንድ እንዲሆን› ለማድረግ አሁንም የማስተዋወቅ ሥራዎች እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹የንብ ቸኮሌት በሀገር ውስጥ ታዋቂም ከመሆኑም በላይ በዋጋው ቢሆን ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለገበያ እየቀረበ ነው፤ ቸኮሌቱ የራሳችን የሆነ ጣዕምና ጥራት አለው››የሚሉት ፋሲል፤ ደንበኞችም ይህን በሚገባ ስለሚያውቁ ምርቶቻቸውን እንደሚወዱት ይናገራሉ። አሁን ላይ በሀገሪቱ የቸኮሌት ገበያ ተቆጣጠሪ ቢኖርም ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት የሚያስችል ሥራዎች እየሰሩ መሆኑን ይገልጻል። ለዚህ የሃምሳ ዓመታት ልምድ በመጠቀም የሚያስፈልገው የማምረት አቅም እና ጥራት በመጨመር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
አቶ ፋሲል ‹‹በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የገበያ ትስስር በመፍጠር በርካታ ደንበኞች ምርቶቻችንን እየገዙ እየተጠቀሙ ነው፤ ደንበኞች ምርቱን ከተጠቀሙ በኋላ የሚሰጡት አስተያየት ደስተኛ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው›› ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ከድርጅቱ ሱቆችም ሆነ ኪዮስኮች፣ ሱፐር ማርኬቶች እና ሃይፐር ማርኬቶች ንብ ከረሜላና ቸኮሌቶቻችንን ይወስዳሉ። ድርጅቱ ኬክ ግብዓቶችንም ስለሚያመርት፤ ለሆቴሎች፣ ለካፌዎች ብስኩትና ብስኩት መሰል ነገሮች ለሚያመርቱ እንዲሁም ኮርንፊሌክስ እና አይስክሬም ለማምረት በግብዓትነት የሚጠቀሙ ድርጅቶች ደንበኞቹ ናቸው። አሁን ላይ ያለው የገበያ ፍላጎት ሰፊ ስለሆነ የማምረት አቅምን በመጨመር ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ድርጅቱ በቋሚ ሠራተኞች ከ400 በላይ ያሉት ሲሆኑ፤ ለበርካታ ሠራተኞች የሥራ እድል የፈጠረ ነው። ድርጅቱ የቤተሰብ ድርጅት ሲሆን የመጀመሪያ ትውልድ ከረሜላውን ሲሰራ ሁለተኛው ትውልድ ደግሞ ወደ ቸኮሌት አድርሶታል። ወደፊት ብዙ ሥራዎችን እየሰራ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚሄድ ይሆናል ሲሉ አስታውቀዋል።
ድርጅቱ ዋነኛ ተግዳሮት የሆነበት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲሆን፤ ይህን መሻገር ከተቻለ የተሻለ ሥራን መስራት የሚችል መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይም ከመንግሥትም ብዙ ድጋፎች እያገኙ መሆኑንም አንስተዋል።
በቀጣይ በሀገር ውስጥ የሚመረተው የቸኮሌት ምርት ለውጭ ገበያ የመላክ በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ዓመት መጨረሻ ቢያንስ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የመላክ እቅድ ይዘው ለዚህ በዝግጅቱ ሂደት እንደሚገኙ አመላክተዋል።
ሌላው የኤክስፖው ተሳታፊ የሆነው ኤርጌንዶ ንግድና ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን፤ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን ተሰማ በበኩላቸው ኤርጌንዶ ከተመሰረተ ከ24 ዓመት በላይ ማስቆጠሩን ይገልጻሉ። በመጀመሪያ ላይ ሥራ ሲጀመር በሀገሪቱ ብራንድ ሆነውን ኤርጌንዶ ጫማ ሲያመርት እንደነበር አስታወሰዋል። ረጅም ጊዜ በጫማ ሥራ ላይ ከቆየ በኋላ አሁን ላይ ለተለያዩ ጂሞች፣ ለሕፃናት መዋያዎች፣ ለሕፃናት መጫወቻ እና ለተለያዩ ግብዓት የሆነ ነገሮችን እያመረተ ይገኛል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ግብዓቶችንም ሆነ ማቴሪያሎች የሚመረቱ እዚሁ ሀገር ውስጥ ነው። ኤክስፖ ከሚያደርጉ ድርጅቶች ጋር የተወሰኑ ምርቶች በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ እየሰራ ይገኛል። ድርጅቱ በተለያዩ ጊዜ የተለያዩ አይነት ምርቶችን እየጨመረ ይገኛል። በተጨማሪም አሁን ላይ በአዲስ ምርት ለከብት እርባታ የሚውሉ እና ከብቶች የሚተኙበት ምንጣፎች ማምረት ጀምሯል። በሁሉም ዘርፎች ላይ የምንችለውን ለመስራት ጥረት እያደረግን ነው።
በተለይ ለሕፃናት እየገጣጠሙ የሚጫወቱበት እና በየመሥሪያ ቤቶች እየተቋቋሙ ላሉ የሕፃናት ማቆያዎች ውስጥ ምንጣፍ የሚውሉ ምርቶች በማምረት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ተደርገዋል ይላሉ።
ድርጅቱ ለግብዓት የሚውሉ ጥሬ እቃዎችን የሚያመርት ሲሆን፤ ለሚመረተው ግብዓት የሚውሉ የተወሰኑ የምንዛሪ እጥረቶች እንዳሉ ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ በተቻለ መጠን ማምረት በሚቻለው አቅም እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው፤አሁን ላይ ፋብሪካ መስራት ከሚችለው 20 እና 30 በመቶ ያህሉን ብቻ እየሠራ መሆኑን አቶ ሳምሶን ያስረዳሉ።
ድርጅቱ የሀገር ውስጥ ምርቶችን እንደማምረቱ አሁን ላይ ያለው የገበያ ትስስር የተሻለ ነው ያሉት አቶ ሳምሶን፤ ‹‹በተለይ ኤክስፖ ላይ መሳተፍ ከጀመርን ጀምሮ የተለያዩ ድርጅቶች የመገናኘት እድል የተፈጠረ መሆኑን ይበልጥ የገበያ ትስስርን መፍጠር ችለናል። ቀደም ሲል ከውጭ የሚያስገባቸው ግብዓቶች ከኛ እየገዙ ያሉ የጫማ ፋብሪካዎች እንዳሉ ሆኖ ኤክስፖ ላይም ጥሬ እቃዎቻችንን ፈልገው የሚገዙ ፋብሪካዎች አሉ›› ይላሉ።
ኤክስፖ የተሻለ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ያደረገና የተሻለ እድሎች የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የማምረት ሥራው የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ምርቶቻቸውን የገዙትም ሆነ አሁን ላይ ምርቶቻችን ለመግዛት የሚፈልጉ አካላት ስለምርቶች የሚሰጡት አስተያየት ምርቶቹ ጥራት ያላቸው እና ለረጅም ጊዜ እንደተገለገሉባቸው ይጠቅሳሉ። ኤክስፖርት የሚያደርጉት ሳይቀር የተወሰነ ግብዓቶች ከእነርሱ እየወሰዱ እየተኩ ኤክስፖርት እንደሚያደርጉ አመላክተዋል።
‹‹በጥራት ደረጃ ምንም የማይወጣለት ጥራት ያለው ምርቶች ነው የምናመርተው›› የሚሉት አቶ ሳምሶን፤እንዲያው ጥራት የሌላቸው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ስላሉ ኅብረተሰቡ እነዚህ የሀገር ውስጥ ምርቶች እየመሰሉት አስተያየት ሲሰጥ ይስተዋላል። ነገር ግን ኤርጌንዶን ብራንድ አይቶ የገዛ ደግሞ ምርቱ ጥራት ያለው ለረጅም ጊዜ የተገለገለበት መሆኑን ይመሰክራል፤ ከዚህ በሻገር ኤርጌንዶ የሚለውን ስም ብዙዎች እንደ ቤተሰብ አድርጎ ያዩታል ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ አሁን ላይ ምርቶቹን ወስደው የሚሸጡ አከፋፋዮች ያሉ ሲሆን፤ ወደፊት የራሱን መሸጫ ሱቆች ከፍቶ ምርቶች ለመሸጥ አቅዶ እየሰራ ነው። ድርጅቱ ባለው አቅም የማምረት አቅሙ ውስን ሆኖ እንኳን 150 እስከ 200 የሚደርሱ ሠራተኞች በስሩ ይገኛሉ። አቅሙን አጠናክሮ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ ከ500 በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ይፈጥራል።
እስካሁን ይህ እንዳይሆን ያደረገው የምንዛሪ እጥረት እና የገበያ ክፍተት ሰው ከሀገር ውስጥ ምርት ይልቅ ለውጭ ምርቶች የነበረው ፍላጎት ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። ‹‹አሁን ግን የሰው አመለካከት እየተቀየር የእኛን ምርት መርጠው ይመጣሉ። በጥራት ሆነ በዋጋ ደረጃ የኛ የተሻለ መሆኑና የውጭውን ገዝተው የሀገር ውስጥ ሲያነጻጽሩት ዋጋችንም እጅግ ተመጣጣኝ በመሆኑ ብዙዎቹ ይገረማሉ። አሁን ላይ ግን በጣም የተሻሉ ነገሮች አሉ›› ብለዋል።
ኤክስፖው የገበያ ትስስር ከማስገኘቱ ባሻገር ምርቶቹን የተጠቀሙት ሰዎች ድርጅቱን እንደ ቤተሰብ እንዲያዩ ያደረገ ነበር ያሉት አቶ ሳምሶን፤ ወደፊት የሚመረቱ ምርቶችን አይነት በመጨመር በሕፃናትና አረንጓዴ አሻራ ዙሪያ የሚሰሩ ሥራዎች መኖራቸው ጠቅሰው፤ የበለጠ ሥራዎች እንዲያስፋፉ እድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁመዋል። ከተወሰኑ ድርጅቶች ጋር ባደረጉት የገበያ ትስስር ብዙ የገበያ እድሎች ገበያ ያገኙበት መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይ ወደ ኤክስፖርት ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ሳምሶን፤ ምርቶቹን በደንብ በማምረት የሀገር ውስጥ ገበያ በቂ ሁኔታ ተደራሽ በማድረግ ለኤክስፖርት ዝግጅት መደረጉን ይገልጻሉ ።‹‹አሁን ላይ ሁኔታዎች እየተስተካከሉ እየመጡ ስለሆነ ወደፊት የተሻለ እድሎች እያገኘን እንመጣለን። በተለይ መንግሥት የሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲገዙ እያበረታታ መሆኑ በጣም አጋዥ ስለሚሆን በቀጣይም በክልሎች ተደራሽነት እያሰፋን እንመጣለን›› ብለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም