ከሦስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ እና ከዲፒ ወርልድ ጋር የበርበራ ወደብን የወደቡን 19 በመቶ ድርሻ በመያዝ እንደምታለማ ሲገለጽ ነበር። በኋላም ኢትዮጵያ ከሶማሊ ላንድ ጋር በወደብ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ደርሳ የመግባቢያ ሰነድ ስትፈራረም ጉዳዩ ለዓለም መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
በርካታ ሀገራት በጂቡቲና በሶማሊያ የጦር ሠፈር ገንብተው እንዳሻቸው ሲንቀሳቀሱ ከጅቡቲ የወደብ ኪራይ ባለፈ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር በር ያስፈልገኛል ብላ ስትነሳ ከግብጽና አንዳንድ አካላት ጉዳዩ ቀጣናውን ለትርምስ የሚዳርግ ነው ተብሎ የሀሰት ክስ እንደተሰነዘረባት ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለምን ይሄን ያክል እንደጥፋት ተቆጠረ? ለሚለው በርካታ ማብራሪያ የሚፈልግ ቢሆንም ኢትዮጵያ በተለያዩ የባሕር ላይ ወንበዴዎችና በተፈጥሮ አደጋዎች በሚታመሰው ቀይ ባህር ላይ አስተማማኝ የባህር በር አማራጭ ያስፈልገኛል ብላ መነሳቷ አግባብ መሆኑን የሚስማሙ በርካቶች ናቸው። ጉዳዩ ወቅታዊና የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በወሳኝ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚረዳና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ጥያቄ መሆኑን ደግሞ የተለያዩ ምሁራን ይስማሙበታል።
በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ሙሐመድ ጀማል (ዶ/ር) የባሕር መውጫና ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄና ታሪካዊ ዳራዎችን እንዲሁም በቀጣይ መከናወን ስላለባቸው መሠረታዊ ጉዳዩች አንስተዋል።
ዶክተር ሙሐመድ እንደሚገልጹት፤ ጥንታውያን የዓለም ሕዝቦች ኢትዮጵያን የሚያውቋት በውሃማ አካሎቿ ነው ፤ የዓባይ መፍለቂያ ናት፡፡ በቀይ ባሕር አጠገብ የምትገኝ ገናና ሀገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የተካሄዱ ብዙዎቹ የሺህ ዘመናት ጦርነቶች ይሄንን በፈጣሪ የተሰጣትን ጸጋ ለመንጠቅ የተካሄዱ ጦርነቶች ናቸው፡፡
በታሪካዊ ጠላቶች ጫና፣ በየዘመናቱ በነበሩ መሪዎች ድካምና በሀገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭቶች የተነሣ ኢትዮጵያ ሁለቱን የውኃ ሀብቶቿን በሁለት መንገድ ተነጥቃ መቆየቷን ያነሳሉ፡፡
በዚህም ከባሕር ውኃ ቀስ በቀስ እንድትርቅ ተደርጋ በመጨረሻም የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ወደብ አልባ ሀገር ሆናለች። ያውም የባሕሩን ውኃ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት እየታዘበች፡፡ ጨዋማ ያልሆነውን ውኃ ደግሞ በበቂ ሁኔታ እንዳታለማ ተደርጋለች ይላሉ።
ወንዞቿን ለማልማት የተነሡ መሪዎች ሁሉ ጫና ሲደረግባቸው፤ ገንዘብ ሲከለከሉና ጦርነት ሲዘመትባቸው መኖራቸውና ለዚህም ዓባይ አንዱ ማሳያ መሆኑን ያነሳሉ። ኢትዮጵያ ከ12 በላይ ወንዞችን ለአካባቢውና ከአካባቢው ለራቁ ሀገራት እያበረከተችና ጎረቤቶቿ ሁሉ ከኢትዮጵያ ንጹሕ ውኃ ቢያገኙም በወንዞቿ ላይ የምታከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች እንደሚሆኑ ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ መነጋገር ከተቻለ በኢትዮጵያ የባሕር መውጫ ላይ መነጋገር ለምን አይቻልም? ለምን ነውር ይሆናል? ሲሉ ዶክተር ሙሐመድ ይጠይቃሉ። ኢትዮጵያ እነዚህን በታሪክ አጋጣሚ የተነጠቁ ጸጋዎቿን የማስመለስ መብት አላት፡፡ በተለይም የነቃ፣ የተደራጀ፣ ወደፊት የሚያይና ተጽዕኖዎችን ለመቀበል የማይፈልግ ትውልድ ሲፈጠር የተነጠቁትን ዕድሎቹን እንደገና ማስመለሱ አይቀሬ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
ጨዋማ ያልሆነውን ውኃ የማልማት መብቱን በእጁ አስገብቶ ዓባይን እንደገደበ ሁሉ ጨዋማ ውኃውን የማግኘት መብቱንም መጠየቅ አለበት ይላሉ።
ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት ለመጠየቅ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ መነሻዎች እንዳሏት በማንሳት፤ ለሺህ ዓመታት ከአራት በላይ ወደቦች የነበሯት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛውን የሕዝብ ቁጥር የያዘች፣ ትልቁን ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስ ሀገር መሆኗን ያስረዳሉ።
የባሕር በር ከሌላቸው 44 የዓለም ሀገራት መካከል ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ኢትዮጵያ መሆንዋን ጠቁመው፤ በአፍሪካ ከሚገኙ 17 የባሕር በር አልባ ሀገራት መካከል ደግሞ ሲሶው ሕዝብ የሚኖረው በኢትዮጵያ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለውን የሕዝብ ብዛቷን፣ ኢኮኖሚ እና የቆዳ ስፋቷን የሚመጥን አስተማማኝ የባሕር በር ያስፈልጋታል። በዓለም ላይ እጅግ ብዙ ሕዝብ ያላት የባሕር በር አልባ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይሄ ፍትሐዊ ሊባል፣ ሊሆን አይችልም ይላሉ።
ዶክተር ሙሐመድ እንደሚያመላክቱት፤ ከኢትዮጵያ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ወደ ስድስት ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የባሕር ዳርቻ ይገኛል፡፡ ይሄ ሰፊ የሆነ የባሕር ዳርቻ በሦስት የጎረቤት ሀገሮች ብቻ የተያዘ ነው።
የባሕር በር ጉዳይ አሁን ለምን ዋና አጀንዳዋ ሆነ? ለሚለው ደግሞ አሁን ያለው መንግሥት አንዱ ተልዕኮ በዘመናት የተፈጠሩ መዛነፎችን ማረምና ሀገሪቱ ያጣቻቸውን መብቶቿን ማስከበር ነው። ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች 3ኛውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ እየገነባች ነው፡፡ ይህ ትልቅ ኢኮኖሚ የባሕር በር ያስፈልገዋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የምትጠቀመው አንድ የጂቡቲን ወደብ ብቻ ነው፡፡ ሰፊው ሕዝቧ የኢኮኖሚው ማንቀሳቀሻ የሚሆን የባሕር መውጫ ካላገኘ በዘመናት ሂደት ለአካባቢው አለመረጋጋት ምክንያት ይሆናል የሚል ስጋት እንዳለም አመላክተው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገትና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት አማራጭ የባሕር መውጫ እንዲኖራት የሚያስገድድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
እንደ ተመራማሪው ከሆነ፤ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ያለመረጋጋት፣ ግጭትና ያልጸና የመንግሥት ሥርዓት እየገጠመው ነው፡፡ አካባቢው ገንዘብና ጉልበት ያለው ሁሉ የሚራኮትበት በመሆኑ መጻኢውን ሁኔታ ለመተንበይ አስቸጋሪ አድርጎታል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ መጪውን ጊዜዋን ለምናልባት ትታና ባይተዋር ሆና መኖር አይቻላትም፡፡ ስለዚህም በዚህ ጂኦፖለቲካዊ አለመረጋጋት ከባድ ተጽዕኖ የማይደርስበት አማራጭ ያስፈልጋታል።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ፣ በቀይ ባሕርና በሕንድ ውቅያኖስ እየተከሠቱ በሚገኙ የጸጥታና የደኅንነት ፈተናዎች የተነሣ የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ አደጋ እየተጋረጠበት ይገኛል፡፡ በመሆኑም ደኅንነቱና አስተማማኝነቱ የተጠበቀ የባሕር እንቅስቃሴ ማድረግ የግድ ይለናል፡፡ ለዚህ ደግሞ አማራጭ የባሕር በር ያስፈልጋል፤ ይላሉ።
ኢትዮጵያ በኤርትራ፣ በጂቡቲ፣ በሱዳንና በሶማልያ በኩል የሚገኙ የባሕር መውጫ አማራጮችን የመጠቅም ዕድሎች አሏት፡፡ እነዚህን ዕድሎች ዘላቂ፣ አስተማማኝ፣ በሌሎች ጫና ውስጥ የማይወድቁና የሀገሪቱን ዕድገት የማይገቱ እንዲሆኑ ማድረግ የግድ መሆኑንም ዶክተር ሙሐመድ ያነሳሉ።
ጉዳዩን የሕዝብ፣ የጎረቤት ሀገሮችና የዓለም አቀፍ አካላት መወያያ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግና ሰላማዊ መንገዶችን እስከሚወስዱበት የመጨረሻው ጫፍ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተመራማሪው ሃሳብ ሰጥተዋል።
ከአካባቢ ሀገሮች ጋር የሰጥቶ መቀበልና የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ ውይይት ማድረግ፣ የዓለም አቀፍ ሕጎችንና ልምዶችን መሠረት ማድረግ፣ የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ሂደትን መከተል አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ሁሉንም የባሕር መውጫ አማራጮችን ለውይይት በማቅረብ ዘላቂ፣ አስተማማኝ የባሕር መውጫ የምታገኝበትን ትግል ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑንም ዶክተር ሙሐመስ ያስነዝባሉ።
በኢኮኖሚያዊ አቅም የተደገፈ ፍላጎትን ለማሳካት ቤልጂየምና ኔዘርላንድ እንዲሁም ሰሜን አሜሪካና ሌሎች ሀገራት እንዳደረጉት መሬት እስከመለዋወጥ የሚደርስ ስምምነት በመመስረት የባሕር በር ማግኘት የሚቻልበት አማራጭ መኖሩን አመላክተዋል::
በፍትሕና በርትዕ አካሄድ ላይ የተመሰረተ ግብ በመያዝ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በፌዴሬሽንና በኮንፌዴሬሽን መዋሃድ ድረስ የሚዘልቅ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተመራማሪው ይናገራሉ።
ከቀጣናው ሀገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረጉ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ሠፊ ሕዝብ ያላትና ከባህር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘውን ሀገር የወደብ ባለቤት የምትሆንባቸው አማራጮችን ማጠናከር እንደሚገባ ያስታውቃሉ።
በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር) በበበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ባደረገ አካሄድ የባሕር መውጫ ባለቤት የምትሆንበትን አማራጮች ማስፋት እንደሚገባት ነው የሚገልጹት።
ጉዳዩን የሕዝብ አጀንዳ ማድረግና ለተፈጻሚነቱም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ ምሁራንን ለአንድ አላማ ማስተባበር ይጠይቃል የሚሉት ዶክተር በዛብህ፤ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በትብብር ላይ የተመሠረተ የጋራ ጥቅምን በማስቀደም የሚከናወን የባሕር በር ተጠቃሚነት ወሳኝነት አለው ይላሉ።
የኢትዮጵያን ሰላማዊ አካሄድ በቅጡ ማስረዳትና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ አስምረው፤ በሀገር ውስጥ ደግሞ ሕዝቡ ጉዳዩን በልኩ ተገንዝቦ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ውስጥ ዋና ጉዳይ አድርጎት እንዲሰራበት ሰፊ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ነው የሚያስረዱት።
በትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በጸጥታ ተቋማትና በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ጉዳዩ ሕዝባዊ መልኩ እንዲጠናከር የሚረዱ በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ የግንዛቤ ሥራዎችን ማከናወን ተገቢ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
ዩኒቨርሲቲው በባሕር በር ሃሳብ ላይ ጥናትና የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ማኅበረሰቡ ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ እንዲቀጥል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በተመሳሳይ ሌሎች ተቋማትም አጀንዳው እስከ ቀበሌ እንዲወርድና የሕዝብ አቅም እንዲሆን መሥራት እንደሚገባቸው ያመላክታሉ።
በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ከባሕር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድና በውይይት ከምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት ጋር በመሥራት አላማዋን ማሳካት አስቦ መንቀሳቀስ እንደምትችል በተግባር ማስረዳትና ለውጤታማነቱም መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ያመላከቱት።
የባሕር በር ጉዳይ አሁንም ወሳኝ አጀንዳ መሆን እንዳለበት ይታወቃል፤ መገናኛ ብዙሃን፣ ምሁራና የተለያዩ የህብረተሰብ አካላት ጉዳዩ ተገቢውን ውጤት እስኪያስገኝ ድረስ ይበልጥ መሥራት ይገባቸዋል ሲሉ ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ።
ኢትዮጵያ ስለ ባህር በር ብትጠይቅና ብታነሳ ሕጋዊ መሠረት አላት፤ ታሪክም ያግዘናል፡፡ በመሆኑም በዚህ ሀገራዊ አጀንዳ ዙሪያ በሰፊው ምክክር ማድረግ የሚያስፈልግበት ትክክለኛ ወቅት ነው። ዲያስፖራውም ሆነ በሀገር ውስጥ ያለው ዜጋ የባህር በር ጉዳይን ከጎረቤት ሀገራት ባለፈ የአፍሪካና የዓለም አጀንዳ በማድረግ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠየቅ እና የሀገሩን ጥቅም ማስጠበቅ ይገባዋል ይላሉ።
ምሁራኑ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ዳራ ያለው መሆኑን በማንሳት፤ ተፈጻሚነቱን በጋራ ጥቅም ላይ በተመሰረተ መልኩ በሰላማዊ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ቅርብ ርቀት ላይ እያለች ከባህሩ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በመገለል ልትቆይ እንደማይገባ በመጠቆም፤ ጉዳዩን የሕዝብ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳ በማድረግ በተደራጀ አግባብ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚጠይቅና በሁሉም አቅጣጫ የሚገኙ የባህር በር መውጫ አማራጮችን ማማተር እንደሚያስፈልግ የተስማሙበት ጉዳይ ነው።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም