መተግበሪያዎችን በመነሻ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በመነሻ ሃሳብ ፈጣሪዎችን /ስታርትአፖችን/ ለማበረታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ ይገኛሉ:: በቅርቡም በኢንፎርሜሽን፣ ኮሙዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (በአይሲቲ) ዘርፍ የቢዝነስ ሃሳብ ያላቸውን እነዚህን የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች ለማበረታታት እና ለመደገፍ የሚያስችል የኢኖቬሽን ማዕከል ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል:: ማዕከሉ የሚፈለገውን መስፈርት አሞልተው የተገኙ የመነሻ ሃሳብ ፈጣሪዎች የፈጠራ ሃሳባቸውን ይዘው ወደ ማዕከሉ ገብተው ሃሳቡን እያጎለበቱ ይገኛሉ::

ወጣት ቢሊሱማ ጌታቸው እና ጓደኞቹ ከእነዚህ የመነሻ ሃሳብ ያላቸው ሥራ ፈጣሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ:: ‹‹እንጫወት ጌምስ›› የተሰኘ ለተማሪዎች የሚሆን የመመሪያ ዘዴ /ሲስተም/ የያዘ መተግበሪያ ሰርተዋል:: መተግበሪያው የተማሪዎች መማሪያ ጌሞችን የያዘ የፈጠራ ሥራ ነው:: እነ ቢሊሱማ ‹‹እንጫወት ጌምስ›› የተሰኘ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል የጌም ዴቨሎፕመንት ተቋም መስረተው የፈጠራ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ::

ይህ የእነቢሊሱማ የፈጠራ ውጤት የሆነው ‹‹እንጫወት ጌምስ›› የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በሚመጥን መልኩ ለመማሪያነት እንዲያገለግል ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ቢሊሱማ ይናገራል:: ‹‹እንጫወት ጌምስ›› ጨዋታን ባማከለ መልኩ የተሰራ የመማሪያ ዘዴ /ሲስተም/ ሲሆን፣ ሥራው ከተጀመረ አምስት ዓመታትን አስቆጥራል፤ በተግባር ላይ ማዋል ከተጀመረ ግን ሁለት ዓመቱ መሆኑን ጠቁሟል::

የፈጠራ ሃሳቡ እሱንና በተለያዩ ሙያዎች ላይ የሚገኙ ጓደኞቹን ወደ አንድ ሃሳብ በማምጣት ይህን ፈጠራ ሃሳብ እንዲያመነጩ እንዳደረጋቸው ወጣት ቢሊሱማ ይናገራል:: ወጣት ቢሊሱማ ከጓደኞቹ ጋር ተመሳሳይ ፍላጎት አለው:: ሁሉም ጌሞች ላይ የመሥራት ውስጣዊ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሶ፣ ይህም ጌሞችን መፍጠር ላይ እንዲያተኩሩ እንዳደረጋቸው ያስረዳል:: አሁን ኢትዮጵያውያን ልጆች በውጭ ሀገራት የሚሰሩ ጌሞችን እየተጫወቱ የሚያድጉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለምን ሀገር በቀል ጌሞችን አንፈጥርም ብለው እንደተነሳሱ ያብራራል::

‹‹እንጫወት ጌምስ›› በርካታ የጌም ዓይነቶችን ያዘጋጃል:: ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ‹ጉዞ ግዕዝ› የሚባል የመማሪያ ዘዴ /ሲስተም/ ነው:: ይህም የመማሪያ ዘዴው የግዕዝ ቁጥሮችን በጌም መልኩ ይዟል::

‹‹በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቻችን የግዕዝ ቁጥሮችን ስለማናውቃቸው መለየት ያቅተናል፤ ማንበብ አንችልም›› የሚለው ቢሊሱማ፤ ኢትዮጵያዊ የሆኑትን እነዚህን የግዕዝ ቁጥሮች ሰዎች እንዲያወቁና ቁጥሮች አእምሯቸው ውስጥ ተቀረጸው እንዲቀሩ ለማድረግ ‹ጉዞ ግዕዝ› የተሰኘውን የመማሪያ ጌም መፈጠር መቻላቸውንም አስታውቋል::

‹‹ጌሙ የግዕዝ ቁጥሮችን የያዘ በመሆኑ ሰዎች በጨዋታ መልክ እየተዝናኑ እንዲማሩ ያስችላል:: ከመዝናናትና ከመማር ባሻገርም ሀገር በቀል እውቀትን በመጠበቅ፤ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ይረዳል:: ትውልዱ የምዕራባዊያን ባህልና ትምህርት ብቻ እየተከተለ ስለሆነ ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ ጊዜውን በጠበቀ መልኩ በሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ በመቅረጽ ማስተማር የምንችልበትን ዘዴ መፍጠር ይጠይቃል ››ይላል::

ዛሬ የቀድሞውን ዓይነት የማስተማር ዘዴ መከተል ጊዜው አይፈቅድም የሚለው ቢሊሱማ፤ ጊዜው በሚፈቅደው ልክ በፍጥነት በመጓዝ ጊዜውን የሚዋጁ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ባሕልን በጠበቀ መልኩ በሀገራችን ያሉ የተለያዩ ቋንቋዎች በመጠቀም ማስተማር እንደሚያስፈልግ ይገልጻል::

እንደ ግዕዝ ዓይነት ትምህርቶች በጨዋታ መልኩ መዘጋጀታቸው ሰዎች ትኩረት ሰጥተው በጥልቀት እንዲገነዘቡ የሚያስችላቸው መሆኑን ጠቁሞ፤ በጨዋታ መልኩ ሳይሆን እንዲሁ ብናስተማራቸው ብዙዎች ትኩረት ሰጥተው ትምህርቱን እንደማይከታተሉት ገልጿል:: ውጤታማ መሆን እንደማይቻልም በጥናት ጭምር መረጋገጡን ቢሊሱማ ያመላክታል::

በጨዋታ /ጌም/ መልኩ የሚሰጠው ትምህርት በቃል ከሚሸምድደው የተለየ መሆኑን ይገልጻል:: በጌም ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት በቀላሉና በትክክል በሰዎች እእምሮ ውስጥ ተቀርጾ እንዲቀርና የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ የሚያግዝ ነው ሲል ያስረዳል::

እነቢሊሱማ ወደ የኢኖቬሽን ማዕከል ከገቡ በኋላ በተሰጡ ስልጠናዎች ተሳትፈው ‹‹ሊቁ›› የተሰኘ መመሪያ ዘዴንም መሥራት ችለዋል:: ይህ የመማሪያ ዘዴ /ሲስተም/ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ላሉ የግብርና ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት የሚያስችል ነው::

‹‹ሊቁ›› በግብርና ላይ ለውጦች ለማምጣት ያስችላል:: ይህ የመማሪያ ዘዴ ከጂ.አይ.ዜድ እና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሶ፣ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ ልዩና በሀገራችንም ቀዳሚ የዲጂታል መተግበሪያ ነው ሲል ያብራራል::

እንደ እሱ ማብራሪያ፤ ዲጂታል መተግበሪያው በጨዋታ መልክ የቀረበ የአፈር ጥበቃ ሥራን በዘለቄታ ለመሥራት የሚረዳ ነው:: የግብርና ባለሙያዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተጫወቱ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያስችላል:: ለባለሙያዎቹ መተግበሪያው በታብሌቶች ላይ እንዲጫን ተደርጎ የሚያስተምር መሆኑን ጠቅሶ፤ በጨዋታ ቁም ነገር ለማስተማር ያስችላል ሲል ያስረዳል::

እንደ ቢሉሲማ ማብራሪያ፤ መተግበሪያው በጎ መንደር የተሰኘ ቦታ እንዳይጠፋ ለማድረግ ተጫዋቾች በሚያደርጉት ጥረት የአፈር ጥበቃ ግንዛቤን ያዳብራል:: መተግበሪያውን ያለምንም ክፍያ ከጎግል ፕሌይስቶር ላይ ማውረድ የሚቻል ሲሆን፤ የጌሙ ተጠቃሚዎች ጨዋታውን ባሸነፉ ቁጥር ግንዛቤ እና ችሎታን የሚጨምሩ የዲጂታል ሽልማቶችን ማግኘትም ይቻላል::

መተግበሪያው ለአፈር ጥበቃ የሚረዱ የተለያዩ መንገዶችን እንደ ዛፍ መትከል ፣ እርከን መሥራት እና የመሳሰሉትን ተግባራት በጨዋታው በመተግበር በቂ ግንዛቤን ይሰጣል:: በተጨማሪም በጨዋታው በጎ መንደር የተሰኘው ምናባዊ ስፍራ የሚጠፋ ሲሆን፣ ተገቢው እንክብካቤ ባደረጉ ቁጥር ይህንን ምናባዊ ስፍራ መታደግ የሚችልም ይሆናል:: በጨዋታው ከሚገኙ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ደግሞ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ጀግንነትን መጎናጸፍ ነው ሲል አብራርቷል::

በዚህም ጨዋታ የሚያገኟቸውን የግንዛቤ እና የክህሎት ሽልማቶች በመጠቀም ባሸነፉ ቁጥር በስተመጨረሻ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ጀግና የሚል ስያሜን እንደሚያገኙም አስታወቋል::

‹‹ ጌሞች አብዛኛውን ጊዜ በነፃ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ እንጫወት ጌምስም እንዲሁ የጌም አገልግሎቶችን በነፃ የሚሰጥ ሆኖ የራሱን ገቢ የሚያገኝበት ቢዝነስ ሞዴል ያለው በመሆኑም በእዚያ መንገድ ገቢ ማግኘት ያስችላል:: በተጨማሪም ሽልማት ባላቸው ጌሞቹም እንዲሁ ገቢን ያስገኛል›› ሲል አብራርቷል::

ቢሊሱማ በአሁኑ ወቅት ለመነሻ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች የሚሰጠው ትኩረት መጨመሩን ጠቅሶ፣ በተለያየ መልኩ ድጋፍ እና ማበረታት እንደሚደረግላቸው አስታውቋል፤ በተለይ በኢኖቬሽን ማዕከሉ በተመቻቸላቸው እድል በቢዝነስ ፣ በሶፍትዌር እና በፋይናንስ ረገድ ባገኙት ስልጠና ብዙ መጠቀም መቻላቸውንም አመልክቷል::

ወጣቶች ጊዜያቸውን ባልተገባ ተግባር ላይ በከንቱ ከሚያሳልፉ የተለያየ እውቀት ሊያገኙ የሚችሉባቸውን የማህበራዊ ሚዲያ እና የቴሌግራም ቻናሎች ላይ በመግባት ስልጠናዎች በመወሰድ ራሳቸውን ማብቃት እንደሚችሉ ጠቁሞ፣ ይህ ዘመን ለወጣቶችና ለተማሪዎች ትልቅ እድል የተፈጠረበት መሆኑን ጠቁሟል::

ጀማሪ የፈጠራ ሃሳብ ፈጠራዎች /ስታርት አፖች/ ወደ ፈጠራ ሥራ ሲገቡ በቢሮክራሲ ማነቆዎች ሳቢያ ለትንሽ ጊዜ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቁሞ፣ ችግሩ ቀጣይነት ያለው እንዳልሆነም አስገንዝቧል:: በቡድን ሆነው ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት ቢያደርጉ ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ያስገነዝባል::

ወጣት ቢሊሱማ፤ ‹‹የመነሻ ፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች የፈጠራ ሥራውን ከሰሩ በኋላ ወደ ቢዝነስ ሳይገቡ በየትኛው መንገድ ስልጠና መውስድ አለባቸው:: ምክንያቱም ስልጠናውን ሲወሰዱ የሚከሰሩት ጊዜያቸውን ብቻ ነው፤ የሚያገኙት ጥቅም ይበልጣል፤ ስልጠናው አንድ ርምጃ ወደፊት ለመጓዝ ያስችላቸዋል›› ሲል ያብራራል::

የመነሻ ሃሳብ ፈጣሪዎቹ ለገበያው አዲስ ምርት ይዘው እንደሚቀርቡ ጠቅሶ፣ ስልጠናው ምርቱን ወደገበያ አቅርበው ወደኋላ መመለስ እንዳይጋጥማቸው በተለመደ መልኩ ሳይሆን በተሻለ መንገድ ቢዝነሱንም አውቀው ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመሥራት ያስችላቸዋል ሲል ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል::

ሌላኛዎቹ የመነሻ ሃሳብ የፈጠራ ባለሙያዎች ወጣት አቤል አባቡ እና ጓደኞቹ ናቸው:: ‹‹ኤግዛም ታይም›› የተሰኘ የተማሪዎች መለማመጃ መተግበሪያ ሰርተዋል:: ‹‹ኤግዛም ታይም›› ለተማሪዎች የጥናት አጋዥ የሆነ ሞባይል መተግበሪያ ነው:: ከስምንተኛ ክፍል እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ይገለግላል::

ቀደም ሲል የተለያዩ አጋዥ መጻሕፍትንና የፈተና ወረቀቶች(ሽቶች) ሲጠቀሙ ብዙ ችግሮች ያጋጠማቸው እንደነበር የሚያስታውሰው አቤል፤ ይህ መተግበሪያም እነዚህን ሁሉ ችግሮች መቅረፍ እንደሚያስችል ይናገራል:: መተግበሪያው ሥራ ከጀመረ ሁለት ዓመት ያህል ማስቆጠሩን አመላክቷል::

‹‹ይህን ሥራ ለመሥራት መጀመሪያ ላይ የመጽሐፍ ችግሩን ለመቅረፍ በማሰብ መነሳሳታቸውን የሚገልጸው አቤል፤ የዩኒቪርሲቲ ተማሪ ሆነው መጽሐፍ ለማግኘት ሲያጋጥሟቸው ከነበረው ችግር ተነስተው፤ እነዚህን ችግሮች እንዴት መቅረፍ ይቻላል ብለው በማሰብ ያገኙት መፍትሔ መተግበሪያውን እንዲሰሩ እንዳስቻላቸው ይገልጻል::

በተለይ ቀደም ያሉ ጊዜያት ያሉ የፈተና ወረቀቶች(ሽቶችን) ለማግኘት በእጅጉ ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ:: ብዙ ተማሪዎች ገቢ ስለሌላቸው መጽሐፍ ለመግዛት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሶ፤ ‹‹ችግሩን መፍታት ስንጀምር የሰራነው መተግበሪያ ጥያቄን ብቻ ነበር የሚያለማምደው፡፤ ከዚያ በኋላ ተማሪው በማጥናት በኩል የሚገጥሙትን ችግሮች በመለየት ሁሉንም በአንዴ ጊዜ የሚፈታ መፍትሔ ማግኘት ችለናል›› ይላል::

አቤል እንደሚለው፤ መተግበሪያው የስድስተኛ፣ የስምንተኛ እና የአሥራ ሁለተኛ ክፍል የማጠቃለያ ትምህርቶችን የአምስት ዓመት ጥያቄዎች መለማመድ ያስችላል:: ከ2015 በፊት የነበሩትን የአምስት ዓመት ጥያቄዎች በሙሉ ይዟል:: ለእያንዳንዱ ትምህርትም አጫጭር ማስታወሻዎችን( ሾርት ኖቶች) በማስቀመጥ ተማሪዎች እንዲያጠኑ፤ እንዲጠይቁ ያስችላል፤ እያንዳንዱን ትምህርት የሚያስረዱ ቪዲዮዎችም አሉት:: ተማሪዎቹ በቪዲዮቹ ይለማመዳሉ ፤ ጥያቄዎችን ይሰራሉ:: እነዚህን ሁሉ በአንድ የያዘ የሞባይል መተግበሪያ ነው::

መተግበሪያውን በፕሌይስቶር ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከ30ሺ በላይ ሰዎች አውርደውታል:: ከሁለት ሺ በላይ ተማሪዎች ከፍለው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ:: ተማሪዎች መተግበሪያውን ለመጠቀም ፕሌይስቶር ላይ ‹‹ኤግዛም ታይም›› ብለው አውርደው ተመዝግበው መጠቀም ይችላሉ፤ በመጀመሪያ በነፃ የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ከትንሽ ጊዜያት ቆይቷ በኋላ ክፍያ እንዲከፍሉ ይደረጋል::

ክፍያዎቹ የሦስት ወር ፣ የስድስት ወር እና የአንድ ዓመት በሚል የተከፋፈሉ ናቸው:: በሦስት ወር 200 ብር በመክፈል ሙሉ መተግበሪያውን መጠቀም የሚቻል ሲሆን፤ በስድስት ወር 300 ብር እንዲሁም በዓመት ደግሞ አምስት መቶ ብር በመክፈል የመተግበሪያውን ፓኬጅ በሙሉ መጠቀም ይችላሉ ሲል አቤል ይገልጻል::

‹‹አንድ ተማሪ መጽሐፍ ሲገዛ ለአንድ መጽሐፍ በትንሹ ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ብር ያወጣል›› ያለው አቤል፣ ‹‹በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች መጽሐፍ ሲገዛ ግን ከአንድ ሺ ብር በላይ ወጪ ሊያወጣ የሚችልበት አጋጣሚ አለ›› ሲልም ያብራራል:: ክፍያው ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሶ፣ አንድ ተማሪ መተግበሪያውን ሲጠቀም በአንድ ዓመት ውስጥ ቢያንስ አምስት መቶ ብር እንዲከፍል የተደረገ መሆኑን አሳውቋል::

ወጣት አቤል፤ መተግበሪያ ላይ ያሉት ጥያቄዎች ከእነአሠራራቸው እና ከነምልሶቻቸው መቅረባቸውንም አመልክቷል:: ተማሪዎቹ ጥያቄዎቹን ሲሰሩ ፈተና እየተፈተኑ እንደሆነ አድርገው መለማመድ ይችላሉ፤ ከፈለጉ ደግሞ እየተለማመዱ እዚያው መልስ እየመለሱ መለማመድ ይችላሉ ማለት ነው ሲል አብራርቷል::

መተግበሪያው የስድስተኛ ክፍል፣ የስምንተኛ ክፍል እና የአሥራ ሁለተኛ ክፍልን ታሳቢ በማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሶ፣ በቀጣይ ደግሞ መውጫ ፈተና (ኤግዚት አግዛም) ለመፈተን የሚያግዙ አጋዦችን በመተግበሪያው እንደሚጫኑ ጠቁሟል::

በሌላ በኩል የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመጀመር የሚያስችሉ መለማመጃዎች እየሠሩ መሆናቸውንም ጠቅሶ፣ የመንጃ ፈቃድ ለማውጣት የሚያስችሉ አጋዥ መለማመጃዎችንም እንዲሁ እያዘጋጁ እንደሆነ ገልጸዋል:: በቀጣይም መተግበሪያዎቹ የሚሰጡትን አገልግሎት ወደ ጎረቤት ሀገራት ለማስፋት ታቅዶ እየተሠራ ነው ሲል አመልክቷል::

ተወዳድረው ከተመረጡ በኋላ ወደ ኢኖቬሽን ማዕከሉ በመግባት የተለያዩ ስልጠናዎች ማግኘታቸው ጠቅሶ፤ በዚህም የተለያዩ ድጋፎች እንደተደረገላቸው ይገልጻል:: ይህም የሚጓዙበትን መንገድ እንደጠረገላቸውም ይናገራል:: በተለይ የመነሻ ሃሳብ ያላቸው የፈጠራ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ይዘው ወደ ማዕከሉ ቢመጡ ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲል አቤል ጠቁሟል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You