የባከነው የአባቶች እውቀት

ታክሲ ውስጥ ወይም በሆነ መገልገያ ቦታ ውስጥ አጋጥሟችሁ ሊሆን ይችላል። በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች በትንሽ ትልቁ ይገረማሉ። በሆነ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ መስጠት ይወዳሉ። አድማጩ ወጣት ከሆነ በይሉኝታ ይሰማቸዋል እንጂ በውስጡ ‹‹አይ የሽማግሌ ነገር!›› እያለ እንደተንዛዙበት አድርጎ ይቆጥረዋል፤ በትህትና ለመማር ብለው የሚያዳምጡት እንዳሉ ሆነው ማለቴ ነው። ምክንያቱም ወጣቱ በብዙ ነገር የተወጠረ ነው፤ ቀልቡ በአጫጭር ነገሮች የተላመደ ነው። አዛውንቱ ደግሞ የውስጣቸውን የሚተነፍሱበት ዕድል ብዙም ስለሌለ ባገኙት አጋጣሚ ለመናገር ይጓጓሉ። ከዓመታት በፊት ያስተዋልኩት አንድ ገጠመኝ መነሻ ላድርግ።

በአንድ መድረክ ላይ አንድ የዕድሜ ባለጸጋ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋበዙ። በአዳራሹ የሚበዙት ወጣቶች ናቸው። ወጣቶች ናቸው ማለት እንግዲህ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ቀደም ሲል እንዳልኩት አጫጭር ነገሮች የሚወድ ነው። የተጋበዙት አዛውንት ንግግራቸው በጣም ዘለግ አለ። በእያንዳንዱ ወጣት ልብ ውስጥ ‹‹አይጨርሱም እንዴ!›› የሚል ምኞት ይነበባል። ስልኩን ይነካካል፣ ያፋሽካል፣ ከጎን ያወራል፣ እየወጣ ይሄዳል፤ አዛውንቱ የቀደምት ትዝታቸውን እያወሩ ይህን ትውልድም በነገር ወረፍ ያደርጋሉ።

አዛውንቱ ማሳረጊያ የሚመስል ዓረፍተ ነገር ሲናገሩ አዳራሹ በጭብጨባ ይናጣል፤ የሚያጨበጭቡት በተናገሩት ነገር ተደስተው ሳይሆን ‹‹እፎይ ሊጨርሱ ነው›› በሚል ደስታ ነው፤ እግረ መንገድም ይበቃዎታል የሚል መልዕክት መሆኑ ነው። አዛውንቱ የሞቀው ጭብጨባ ቀዝቀዝ ሲል ጠብቀው እንደገና አዲስ ታሪክ ይጀምራሉ፤ ታዳሚውም እንደ አዲስ ተስፋ መቁረጥ ይጀምራል። በጭብጨባና በፉጨት አያስቆማቸው ነገር አዛውንት ናቸው፤ በዚህ በኩል ታዳሚው ይመሰገናል። እንዲህ እንዲህ እያለ በብዙ መሰላቸት ሲያልቅ አዳራሹ በጭብጨባ ተናወጠ። ጭብጨባው በአዛውንቱ ንግግር ሳይሆን በመጨረሳቸው (በደስታ) መሆኑን ብዙ ሰው ስላወቀ አፉን ይዞ የሚስቅም ብዙ ነበር።

ይሄ ነገር ‹‹ለምን ተፈጠረ?›› ብለን ካስተዋልን በሁለት ምክንያት ይሆናል። አንድ በታዳሚው፣ ሁለት ራሳቸው በአዛውንቱ። ታዳሚው ለምን እንዲህ አይነት እውቀት ሰለቸው? አዛውንቱስ የዕድሜ ዘመን ገጠመኛቸው ሁሉ በአንድ መድረክ ያልቅ ይመስል ለምን ነገር ያስረዝማሉ?

መድረክ ላይ አንድ ችግር አለ፤ ጥልቅና ትንታኔ ያላቸው ነገሮች አይወደዱም። የተለመደው አጠር አጠር ያለ የሚያስቅ ነገር ነው። ከዚያ አለፍ ሲልም መንግሥትን ወይም የሆነን አካል የሚሳደብና የሚያስጨበጭብ ነገር ነው። ለነገሩ አሁን አሁን በመድረክ ብቻ ሳይሆን በዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃንም የተለመደው ይሄው ሆኗል። እንዲያውም እኮ መድረክ ሲዘጋጅ ታዳሚን ለማብዛት የሚጠቀሱት ሰዎች አስቂኝ ንግግር ያላቸውን ነው። ጥልቅ ትንታኔ ያላቸው ነገሮች እየጠላን ነው።

በዚህ ምክንያት አዘጋጆቹም ሆኑ አቅራቢዎቹ የመድረኩን ዓውድ መለየት አለባቸው። የመድረክ ታዳሚ ሁሉ አጫጭርና አስቂኝ ነገሮች ነው የሚወድ ማለት አይደለም። ለምሳሌ፤ መድረኩ የጥናትና ምርምር መድረክ ከሆነ ታዳሚው የዚያ ዘርፍ ሰው ስለሚሆን አይሰለቸውም። አንዳንድ ጊዜ ግን የተደበላለቀ ነገር ይፈጠራል። ይሄ ማለት ቀለል ያለ መድረክ ላይም የምርምር ሥራ ሊቀርብ ይችላል ማለት ነው።እንዲያውም አንድ ሌላ ገጠመኝ ትዝ አለኝ።

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ፍትሕ መጽሔት ወደ ገበያ ልትገባ በብሔራዊ ቴአትር የተዘጋጀ የምርቃት (ማስተዋወቂያ) የተዘጋጀ መድረክ ነበር። በአዳራሹ መቆሚያ መቀመጫ እስከሚጠፋ ሰው ሞልቷል፤ አብዛኛው ወጣት ነው። ዝግጅቱን አስመልክቶ አዝናኝም አስተማሪም አጫጭር ነገሮች ቀረቡ። ፍትሕ መጽሔት ከዚህ በፊት ፍትህ ጋዜጣ ነበረች። እናም ፍትሕ ጋዜጣን የሚዳስስ ጽሑፍ ሊያቀርብ ብርሃኑ ደቦጭ ተጋበዘ። ገና ሲጀምረው የፍትሕን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ጋዜጦች እያጣቀሰ ጥልቅ ትንታኔ ማቅረብ ጀመረ። በትንታኔው ተመስጬ በጉጉት እያዳመጥኩ ሳለሁ ግን ሊቀጥል አልቻለም።

የ‹‹ይበቃሃል›› መልዕክት ያለው ጭብጨባ አስተጋባ። ብርሃኑ ወረቀቱን ጠቅልሎ ወረደ። በግሌ በጣም አፈርኩ፤ በጣም ተናደድኩ! ይህኔ እንቶፈንቶ አሉቧልታና ቀልድ ቢያወራ ኖሮ ጭብጨባው የአድናቆት ይሆን ነበር። አሁን ላይ ሳስበው ግን እኔም በከፊል ሳልሳሳት አልቀርም። እኔ የሚዲያ ሰው ስለሆንኩ (ለዚያውም የህትመት ሚዲያ) በሀገራችን የነበረው የህትመት ሚዲያ ታሪክ ሲነገር ተመስጬ ላዳምጥ እችላለሁ። ከሌላ ዘርፍ የመጣ ሰው ግን በእኔ ልክ ሊመሰጥበት አይችልም። እነርሱ የመጡት ፖስተር ላይ የተለጠፉ አንዳንድ ዝነኛ ሰዎችን አይተው ነው።

አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ለምን ወደ መድረክ እንደሚሄዱ ሁሉ አይታወቅም። ጉዳዩ ስለምን እንደሆነ በግልጽ ተነግሮ እያወቁት ይሄዳሉ። አዳራሹ ውስጥ ሆነው ግን አይከታተሉትም፤ እንዲያውም ሌላም ሰው እንዳይከታተል ነው የሚረብሹት።

ወደ ዕድሜ ባለጸጎች እንመለስ። ከእነዚህ አባቶች የምናገኘው እውቀት የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ነው፤ ያ ማለት ተናጋሪው የአይን እማኝ ናቸው ማለት ነው። ያዩትን የኖሩትን ነው የሚነግሩን፤ ዳሩ ግን እንዲህ አይነቶቹን አንሰማም፤ ቆይ ግን እውነት አንወድም ማለት ነው?

በእርጅና ዕድሜ ላይ ያሉ ሰዎችም በባህሪያቸው ነገር ያስረዝማሉ፤ ምክንያቱ ግን ግልጽ ነው። የሚናገሩበት ዕድል ስለሌላቸው ነው። አንተ ወጣቱ በየገባህበትና በየሄድክበት ታወራዋለህ (ወጣት ነህና ብዙ ቦታ ትዞራለህ)፤ አዛውንቱ ግን ብዙ ቦታ አይሄዱም፤ ሲሄዱ ኖረው አሁን ቁጭ ብለው የሚናገሩበት ነበር (ሰሚ ቢገኝ)።

እንዲያውም ልብ ብለን ከሆነ መድረክ ላይ ሲወጡ ብቻ አይደለም ነገር የሚያስረዝሙት። ቀደም ሲል እንዳልኩት የሆነ ነገር ሲያዩ ወይም ሲሰሙ ዝም አይሉም፤ ይናገራሉ። ባያዩና ባይሰሙ ራሱ ዝም ብለው ይናገራሉ። ይመክራሉ፣ ይቆጣሉ፣ ይገስጻሉ።

መድረክ ላይ ሲወጡ ነገር የሚያስረዝሙበት ምክንያት ይሄው ነው፤ የሚናገሩበት ዕድል ስላልነበራቸው ውስጣቸው ያለውን ለመናገር ነው። በነገራችን ላይ አዛውንቶች የአዳራሽ መድረክ ብቻ አይደለም ያጡት፤ መንደር ውስጥ ራሱ የሚያወሩበት ዕድል የለም። ምናልባት የእነርሱ ዕድሜ እኩያ የሆኑ ካላገኙ ወጣቶች ከእነርሱ ጋር አያወሩም። እነርሱ ደግሞ መምከርና መገሰጽ የሚፈልጉት ወጣቱን ነበር እንጂ አዛውንት ከአዛውንትማ ታሪካቸውና ገጠመኛቸው ይመሳሰላል።

እነርሱም እንዲህ የሚያወሩበትና የሚሰማቸው ሲያጡ ውስጣቸው የተጠራቀመውን ብሶት ሁሉ መናገር ይፈልጋሉ።

ምናልባት ግን መድረክ ላይ እንደዚያ በረጅሙ ካልተናገሩ ብሎ መፍረድም ይከብዳል። ምክንያቱም መድረክ ማለት የተወሰነ ሰዓት ያለበት ነው፤ ሌሎች ፕሮግራሞችም የተያዙበት ነው። ይህንን ዓውድ ደግሞ እነርሱ አይረዱም።

ከአባቶች እውቀት እንጠቀም ከተባለ ራሱን የቻለ መድረክ ማዘጋጀት፣ ያ እንኳን ባይቻል ቁጭ ብለን ብናዳምጣቸው፣ የመገናኛ ብዙኃን ዕድል ብንሰጣቸው። ደግሞ እኮ ‹‹ተንቀሳቃሽ የቤት መጽሐፍ›› እያልን እንጠራቸዋለን፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም። የአባቶች እውቀት አይባክን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ግንቦት 5 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You