ኢትዮጵያ ውስጥ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ለፋሽን ዘርፍ መልካም እድሎችን ይዞ መጥቷል።በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከፓርኮቹ ውጪ ሆነው የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ባህላዊና ዘመናዊ የጨርቃጨርቅ አልባሳት የሚያመርቱ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች እያቀረቡ ያሉበት እንዲሁም የፋሽን ትርኢቶች እየተበራከቱ የመጡበት ሁኔታ የሚያስገነዝበውም ይህንኑ ነው።
ዜጎች በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተውም በግልም ከሚሰማሩባቸው ዘርፎች መካከል ለፋሽን ዘርፍ ከፍተኛ ቅርበት ያለው የጋርመንት ኢንዱስትሪ ነው። የጋርመንት ኢንዱስትሪው እየተስፋፋ ከመሆኑም በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሀገሪቱ የፋሽን ትርኢቶች በስፋት መታየት ጀምረዋል። በፋሽን ኢንዱስትሪ ላይ ስልጠና የሚሰጡ እንዲሁም የሚያስተምሩ ተቋማት ቁጥርም እየጨመረ መሆኑ ይገለጻል።
ኑሯቸውን በጣሊያን ያደረጉት ‹‹ዳማሪዮስ ፋሽን እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት›› በሚል በአዲስ አበባ የፋሽንና ቴክኖሎጂ ተቋም የመሰረቱት ወይዘሮ ሰናይት ማሪዮም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የፋሽን ኢንዱስትሪ እያደገ መሆኑን መስክረዋል። መንግሥት ለጋርመንት ኢንዱስትሪው የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ በርካታ የጋርመንት ፋብሪካዎች ወደ ሀገሪቱ እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ የተወለዱት ወይዘሮ ሰናይት ማሪዮ በፋሽን ዲዛይን ሙያቸው ይታወቃሉ።በአፍሪካ ደረጃ በደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ግብፅ፤ እንዲሁም በኒውዮርክ፣ ፓሪስ፣ ሚላን በነበሩ የዓለም አቀፍ መድረኮች በፋሽን ስራዎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የፋሽን ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል የሚሉት ወይዘሮ ሰናይት፣ ያለንበት ዘመን የብራንዶች እና የኢ-ኮሜርስ ዘመን ነው ። በየጊዜው እያደገ ያለውን ይህን ኢንዱስትሪ ለማጠናከር ጥራት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ያስፈልጋል ሲሉም ያስገነዝባሉ።
በከተማ ብቻ ሳይሆን ስለፋሽን ምንም እውቀት በሌለባቸው የገጠር አካባቢዎች እንዲሁም ሀብቱ ባለባቸው አካባቢዎች በርካታ የፋሽን ትርኢቶች ማዘጋጀታቸውን ወይዘሮ ሰናይት ያስታውሳሉ። ይህንም ሲያስረዱ የጉራጌ ብሔረሰብን ባህል ለአብነት ጠቅሰዋል። የብሔረሰቡን ባህል በፋሽን ለማስተዋወቅ የሚቻልበትን ፋሽን ሾው አዘጋጅተው እንደነበርም ገልጸዋል።
ማህበረሰቡ በስፋት የእንሰት ውጤቶችን እንደሚመገብ ጠቅሰው፤ ከእንሰት ተዋፅዖ አንዱ በሆነው በቃጫ ደግሞ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ አልባሳትን መስራት እንደሚቻል ገልጸዋል። በዚህ እንሰት ከምግብነትም አልፎ ለአካባቢው ኢኮኖሚ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰው፣ በአካባቢያችን ያሉንን ሀብቶች በመጠቀም እንዴት ወደ እድገት መምጣት እንደሚቻል በማሳየት፤ ለወጣቶች በስራ ፈጣሪነት እንዲነቃቁ መድረኮችን መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
እሳቸው በሚያዘጋጇቸው የፋሽን ትርዒቶች ጀማሪ ዲዛይነሮችን እና ልምድ ያላቸውን አብረው እንዲሰሩ እና ልምድ እንዲቀስሙ አድርገዋል። በዚህም ብዙ ሞዴሎችን እና ዲዛይነሮችን በማፍራት በዘርፉ ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለረጅም ዓመታት በጣሊያን ሀገር አድርገው የቆዩት ወይዘሮ ሰናይት፣ አሁን ደግሞ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የፋሽን ትምህርት ቤት አዲስ አበባ ከተማ በ1600 ካሬ ሜትር ቦታ በመመሥረት ላይ ናቸው።
ወይዘሮ ሰናይት፤ በኢትዮጵያ ለታዳጊ ንድፍ ባለሙያዎች(ዲዛይነሮች) መድረኮችን የሚያቀርቡ በርካታ ዓለም አቀፍ የፋሽን ሳምንታት እንዳሉም ይጠቅሳሉ፤ ‹‹ኢንስቲትዩቱ ተማሪዎቻችን እነዚህን መድረኮች ላይ እንዲሳተፉ ይሰራል›› ይላሉ፤ ይህም በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢትዮጵያውያን የፋሽን ባለሙያዎች ብሩህ ተስፋ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጋርመንት ፋብሪካዎች የሚቀጠር በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚፈለገውን ያህል እንዳልነበረ ጠቅሰው፣ በሀገሪቱ ውስጥ የፋሽን ኢንዱስትሪ ማሰልጠኛዎች ብዙም እንዳልነበሩም ይገልጻሉ።በፋሽን ዲዛይን ልዩ ኮርሶችን የሚሰጡ ፕሮፌሽናል ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ጥቂት በመሆኑ በሰለጠኑ ዲዛይነሮች አቅርቦት ላይ ያለውን ትልቅ ክፍተት ለመሙላት የእሳቸው ተቋም የጎላ ድርሻ እንዳለው አስታውቀዋል።
የፋሽን ትምህርት ቤቶችን መክፈትና በዘርፉም ስልጠናን መስጠት የቀጣዩን ትውልድ ተሰጥኦ ማሳደግ ያስፈልጋል የሚሉት ዲዛይነሯ፣ በፋሽን ዲዛይን፣ ንግድ እና ቴክኖሎጂ መደበኛ ትምህርት ለመስጠት ያተኮሩ ተቋማት እና ውጥኖች የአገራችንን ፋሽን ደረጃዎች ዓለም አቀፋዊ መመዘኛዎችን ለማሟላት ወሳኝ ናቸው ብለዋል። በተቋማቸው የተማረ የሰው ሃይል የፋሽን ኢንዱስትሪውን ዘላቂነት እና ቀጣይ ፈጠራን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አስታውቀዋል።
እሳቸው ከመንግሥት ተቋማት በተጨማሪ ሰዎች በተግባር እየሰሩ መማር የሚችሉባቸው የግል ትምህርት ቤቶች መቋቋም እንዳለባቸው በማመን ጥናት አድርገውም ተቋም ወደ መክፈት ስራ ማግባታቸውን ይናገራሉ።በጥናቱ በርካታ ትምህርት ቤቶችም በቦታ ጥበት ይቸገሩ እንደነበር ያመላክታሉ።ይህን ሁሉ በመገንዘብ ነው ራሱን የቻለ ፋሽን እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለማቋቋም ወደ ተግባር እንደገቡ ያስረዳሉ።
ትምህርት ቤቱ ከሌሎች የፋሽን ትምህርት ቤቶች ልዩ የሚያደርጉት ሁኔታዎችም አሉት። ከእነዚህም መካከል አንዱ ስልጠናውን በሚገባ ላጠናቀቁ ተማሪዎች በፋሽኑ ስመ ጥር ወደ ሆኑ ሀገራት በመላክ ታዋቂ በሆኑ የፋሽን ስቱዲዮ እና ተቋማት ውስጥ የተግባር ልምድ እና ልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትን እድል ተመቻችቷል።
ተቋሙ በአጫጭር ስልጠናዎች ሥራውን በመጀመር ዲፕሎማ እና ዲግሪ ድረስ በአጭር ጊዜ ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።ከመስከረም ወር በኋላም አዲስ ፈቃድ በማውጣት እስከ ዩኒቨርሲቲ ለማሳደግ መታሰቡንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ታዋቂ ከሆኑ የፋሽን ዲዛይነሮች ጋር በመተባበር ተማሪዎች ስራዎችን የሚያሳዩበት አመታዊ የፋሽን ሾው ከማዘጋጀት እና የገበያ ትስስር ከመፍጠርም ባለፈ ስራ አጥነትን ለማስወገድ አሰሪዎችን እና ተመራቂዎችን የሚገናኙበት እድል ይፈጥራል።
ኢትዮጵያ ፋሽን እና የፈጠራ ስራ ዘርፍን በማበረታታት ወደ አለም አቀፍ ላኪነት በመቀየር ሁሉን አቀፍ የእድገት ተምሳሌት ሆና ማገልገል ትችላለች ሲሉ ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ በ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው፣ መሠረታዊ ከሆነ ልብስ ለክቶ፣ ቆርጦ፣ ከመስፋት ጀምሮ እስከቅንጡ የፋሽን አስተዳደሮች፣ የጌጣጌጦች ዲዛይን፣ የኮምፒውተር ኮዲንግ እና ፕሮግራሚንግ፣ ግራፊክ ዲዛይን ስራዎች የሚሰጡበት መሆኑን ጠቁመዋል። ተቋሙም የፋሽንን ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ጋርመንት ወደ መክፈት በኢንዱስትሪ ደረጃ ጨርቃጨርቅ ወደ ማምረት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 /2016 ዓ.ም