ጠፍቶ የከረመ ሰው፤ እንዝርት ጠፍታብን ዝም እንዳልን ዝም ብለን ነበር፡፡ ታዲያ ልብ አላልናት ይሆናል እንጂ እንዝርቷማ እየሾረች ፈትሉን ስትፈትልና ድውሩን እያደዋወረች ሸማውን ስታበጃጅ ባተሌ ነበረች፡፡ ከወዲያና ወዲህ እያለች፤ አንዱን ከአንዱ ደግሞ ከሌላው ስትፈታና ስታጋምድ መኖሯን ስናውቅ የሸማውን እጹብነት፤ በጸዓዳ ቀለማቱ ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡
መልካምነት መልክ የሰጣትን ይህችን የጥበብ ሀመልማል፤ ሙዚቃም ሆነ የሙዚቃ አፍቃሪው ለአፍታም የሚዘነጋት አይደለችም፡፡ የትናንትናውም የዛሬውም ያስታውሳታልና ከሙዚቃው ዓለም የውሃ ሽታ ሆና ስትቀር “ቻቺ ታደሰ ስለምን ሙዚቃ አቆመች…” እያለ ሲያሳስበውና ምክንያቱንም ከራሱ ሰማይ ላይ ሲያዘንብ የነበረ ብዙ ነበር።ጠፍተሻል ላልናት ሁሉ፤ እርሷም ከሰሞኑ እጅ መንሻ የሚሆን ሌላ የሙዚቃ እንጎቻ ይዛልን ተከስታለች፡፡
ከረዥም ዓመታት የሙዚቃ ዝምታና ዕረፍት ውስጥ ወጥታ የመጣች ቢመስልም ዳሩ ግን እንዲህ አልነበረም፡፡ ሙዚቃዊ ድምጽና ምስሏ፤ ከሚዲያና ከሕዝብ ጆሮ እርቆ ቢሰነብትም እሷ ግን ለሀገሯ ግዙፍ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነበረች፡፡
በጥቂቷ የብዕር መወጣቻችን በብዛት የምንውተ ረተረው የሕይወት ፍርግርጎቿንና የዝና እርካቦቿን በመርገጥ ቢሆንም አዲሱ ሥራዋም የእነዚሁ አካል ነውና በዚሁ ውስጥ ለማለፍም ግድ ይለናል፡፡ ዛሬ እንድናነሳትም ምክንያት የሆነን ይሄው ነውና ጠቅሰን ብቻ ብናልፈው የትዝብት ዓይኖቹን ይወረወሩብናል፡፡ እናም ከኋላ እየጠቀስን ከፊትም እያጣቀስን የብዕር ዱካችንን ሳናጠፋ በሙሉ የቻቺ ታደሰ መንደር ውስጥ በጥቂት በጥቂቱ ጎምለል እንላለን፡፡
የሕይወት ታሪኳን ብቻ በማተት ከመደርደር አሁናዊ የስሜት ቋጥኝ ላይ ቁጭ በማለት ከእርሷም መስማቱ ይበጃልና፤ እዚህ ላይ የሠፈሩት አብዛኛዎቹ የሀቅ ፍሬዎችን የዘገነው ከራሷው ሰፌድ ላይ ነው፡፡ ከሦስት ሳምንታት በፊት፤ የአዲሱን የሙዚቃ ሥራዋን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫም ጭምር ሰጥታበት ነበር፡፡ በዚያው ዕለትም ሙዚቃውን ለአድማጭ ተመልካቹ በትስስር ገጽዋ ጭምር አድርሳለች፡፡
ቻቺ ታደሰ ዳግም ከድፍን አሥርት ዓመታት ኋላ ድንገት አሁን ብቅ ብላ “ደርሷል ሰዓቱ” ስትለን፤ ያላወቅን እኛም ብንኖር፤ የትኛው ሰዓት? ኧረ ለመሆኑ ቀጠሮስ ነበረን እንዴ? ማለታችን የማይቀር ነው፡፡ ነገሩ ግን ወዲህ ነው…መላው ዓለም፤ ከአንድ የዘመን ቋጥኝ ላይ ቁጭ ብሎ ተንኮሉን ለማሴር የተቀጣጠረበት ሰዓት ያለ ይመስላል። የሰው ልጅ ፈጣሪውን የጎሪጥ ማየት ጀምሯል። ምድር በግንባር ቴስታው፤ ሰማይን ለመግጨት ይዘለው ተያይዟል። ጎራዴውን ከየሰገባው እየመዘዘ ወንድም የወንድሙን አንገት ይሰይፋል፡፡
አንደኛው በጥጋብ፤ ሌላኛው በረሀብ ቸነፈር ቅንጡን እየተመታ፤ ግራ ከቀኙ ተደበላልቋል፡፡ በማዕልት ጨረቃ በምሽት ፀሐይ መታየት ጀምረዋልና…ጊዜው የስምንተኛው ሺህ ነውና፤ ሠርዶው ማለትም ይህ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ፤ ሙዚቃው ሁሉ እነቅሽ እነቃ! ዳንሴ ዳንሴ፤ እስክስ በወገቤ ወረድ በጉልበቴ ካልሆነ፤ እያሞቀ አቧራውን ካላስጨሰና እያርገፈገፈ በላብ ካላጠመቀ… ሙዚቃ ምኑን ሙዚቃ ሆነ የሚለው በዝቶ አደባባይ ቢወጣም፤ እሷ ግን መረር ኮምጠጥ ብላ “ደርሷል ሰዓቱ” ስትል፤ የሚያቀዘቅዘውን ውሃ ቸልሳለችና እንግዲህ እየተንዘፈዘፉም ቢሆን ከራስ ጋር ለመምከር ማሰብ ነው፡፡
ሙዚቃው ዓለም አቀፍ የሰላም ጥሪንም ያካተተ ሁለ ገብነት ያለው ሥራ ነው፡፡ የዚህ ሙዚቃ ግጥምና ዜማ የተሠራው፤ በራሷ ቻቺና በወንድሟ ደረጀ ታደሰ ነው፡፡ ሩፋኤል ወ/ማርያም ደግሞ የሙዚቃ ቅንብሩን በማዋሀድ ተጠቦበታል፡፡ የማስተሪንግ ሥራው የተሠራው በታዋቂው የውጭ ሙዚቃ ጠበብቱ፤ ኬሊያን ሲሆን “ካሪቢያን“ የተሰኙት የሙዚቃ ባንዶችም በተለያየ መልኩ በሙዚቃው ሥራ ተሳትፈውበታል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሥራ ዓላማውን ተመርኩዞ፤ በገንዘብም ሆነ በዝግጅት ደረጃው በነጠላ ዜማ የሚታሰብ አለመሆኑን ተናግራም ነበር፡፡
ሰላም ርቆን፤ መጠላላት ከቦን፤ ዘረኝነት ታቅፎን፤ ጨለማው ወርሶናልና ካቀረቀርንበት ፈጣሪ፤ አንጋጠን ምህረቱን የምንማጸንበት ጊዜው ደርሷል ስትል የሀገሯን የቀሚስ ጫፍ ይዛም ትማጸንበታለች፡፡ ሙዚቃዎቿን ገዘፍ ባለ መልዕክት ማንጎቱ እንደሆን ቀድሞም የምትታወቅበትና የምትወደድበትም ጭምር ነው፡፡
ቻቺ ታደሰ በተለይም ባለፉት ጊዜት አይረሴ ዐሻራዎቿን ማሳረፍ የቻለች ድምጻዊት ናት፡፡ በፊልሙም ቢሆን ብቅ ጥልቅ ስትል ቆይታለች፡፡ ለድፍን 30 ዓመታት ያህል በሙዚቃው ውስጥ ስትቆይ፤ ስሟ በመልካም እንጂ በመጥፎ ያልተነሳባት፤ ስመጥር ሙዚቀኛ ናት፡፡ በ1991ዓ.ም የመጀመሪያ አልበሟን ለአድማጭ ጆሮ በማድረስ፤ እስከዛሬ ድረስም አምስት አልበሞችን ለማበርከት ችላለች። በነጠላ ዜማ ደረጃም ደርሷል ሰዓቱ ሦስተኛው መሆኑ ነው። ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ፤ ከሙዚቃ ሥራ ገለል ያለች ቢመስልም፤ ስለ ሀገሯ ግን ሁሌም በእንቅስቃሴ ላይ ናት፡፡ በበጎ አድራጎት ሥራዋ ብዙኃኑ ያውቃታል፡፡ የሰላም አምባሳደርም ጭምር ናት፡፡ ኑሮዋ በብዛት ከአሜሪካ ሀገር እንደመሆኑ፤ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር፤ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስለ ሀገሯ ትዳክራለች፡፡
ቻቺ የሰላም አርበኛ፤ የበጎነት ተምሳሌት ናት፡፡ ሁሌም ከንግግሯ ጅምር፤ እስከ ፍጻሜው ደጋግማ ስለ ሀገሯን ሕዝቧ ስታነሳ፤ ኢትዮጵያዊነትን የምታበራ ሻማ ስለመሆኗ በጉልህ ይታይባታል፡፡ ከእድሜ ቆርሶ ለሀገር፤ ከፍቅር ወርሶ ለወገን የሚል አይነት የሕይወት ፍልስፍና ያላትም ትመስላልች፡፡
ኧረ ለመሆኑ ይህን ሁሉ ጊዜ፤ ከመድረክም ሆነ ከሙዚቃ ሥራ ጥፍት ብላ የሰነበተችው፤ ከወዴት ኖሯል? በሄደችበትና በገባች በወጣችበት ሁሉ “ቻቺ ግን ምነው ጠፋሽ?” እያሉ ወዳጅ አድናቂዎቿ ሁሉ ድንገት ባገኟት ቁጥር፤ አጥብቀው እንደሚጠይቋት እሷም ብትሆን አልሸሸገችውም፡፡ ከጆሮና ዓይን ተሰውራ ለመቆየቷ፤ የምታነሳውን ምክንያት ምናልባትም በሁለት ጠቅለል ልናደርገው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ፤ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን እየቀረጸች፤ ማህበራዊ ኃላፊነቷን ለመወጣት የምታካሄዳቸው የበጎ አድራጎትና መሰል ተግባራት፤ ማፈናፈኛ አሳጥቶ ከአዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎች ጋር እንዳትገናኝ አድርጓታል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፤ በውጭ ሀገር ያሉትን ቤተሰቦቿን ፍለጋ፤ አብዛኛውን ጊዜ ወደዚያው በመሆኗም ጭምር ነው፡፡ ምናልባትም ከቻቺ ታደሰ ፊት ቀረብ ስንል… ለባሏ ባል፤ ለልጇ እናት ሆና የመኖር ትልቅ የሕይወት መርህ እንዳላት፤ ብዙም ሳንርቅ በጥቂት ቆይታ ብቻ እንረዳለን፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት፤ የመጀመሪያ ልጇን በሞት ተነጥቃ የነበረ ስለመሆኑ እናስታውስ ይሆናል፡፡ ለእርሷም ቢሆን ከባዱ ጊዜ እንደነበረ፤ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ከደግነቷና ከሩህሩህነቷ በሌላኛው ጫፍ፤ ውስጣዊ የመንፈስ ጥንካሬን አድሏታል፡፡ ሁሌም በፈጣሪዋ ያላት እምነት የማይጎድል በመሆኑ፤ “እርሱ ሰጠ እርሱ ነሳ” በማለት፤ ያን ጊዜ በጽናት አልፋዋለች፡፡ መፈጠሯ፤ ለትልቅ ዓላማና በምክንያት እንደሆነ ሁሌም ታስባለችና፤ የኔው ኃላፊነት ነው በማለት የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም በርከት ከማለታቸውም፤ ማንነቷ የተሠራባቸው ንጠረ አካላት ናቸው፡፡ በሕይወቷ፤ ነካክታ የምታልፋቸው ነገሮች የሉም።
ቻቺና የባህር ማዶ ሕይወት እንዲሁ በዋዛ ፈዛዛው፤ በመቦዘን መንገድ ውስጥ አልተገጣጠሙም። እዚህ ሀገሯ ውስጥ ለምታካሂዳቸው እንቅስቃሴዎች፤ መሠረታቸውን ጥላ የምታበሳስለው ከዚያው በመሆን ነው። በሙዚቃውም፤ በበጎ አድራጎቱም፤ ከትላልቅ የውጭ ሀገር ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፤ ወደ ኢትዮጵያ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ታደርጋለች፡፡ ፈተናው ብዙ ቢሆንም፤ በመልካም ተቀብለው አስተናግደው መልካሙን በስኬት ስለማከናወኗ እራሷ ታወሳለች፡፡ እንዲያውም ከዚህ ቀደም፤ ከአንድ ጋዜጣ ጋር ባደረገችው ቆይታ ከ“ሲድ ፋውንዴሽን” ስለደረሳት መልዕክት ቃል በቃል እንዲህ ነበር ያለችው፤ “ኢ-ሜይል ሲልኩልኝ፤ በኢትዮጵያ የታወቀችና በዓለም የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያስተዋወቀች፤ ሂዩማኒቴሪያል አክቲቪስት፤ በማለት ነው ታይትል የሰጡኝ…” ብላ ነበር፡፡ በርግጥም ቻቺ ታደሰ፤ ለሀገሯ ትልቁን አበባ ለማስቀመጥ የቻለችው፤ በሙዚቃው ላይ ብቻ እንዳልሆነ፤ እነርሱም ተረድተውታል፡፡
በእንቅስቃሴዎቿ ውስጥ በውጭው ዓለምም ያላትን ተቀባይነት የሚያሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የባህል ሙዚቃም ይዛ፤ ከታዋቂ የውጭ አቀንቃኞች ጋር በአንድ መድረክ ላይ የታየችባቸው አጋጣሚዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡
አርቲስቷ በዚህ ሰዓት፤ እንቅስቃሴዋ ብዙ ነው። በዩኒሴፍ፤ በእርዳታና በበጎ አድርጎት ተግባር ውስጥ ትንቀሳቀሳለች፡፡ በኢትዮጵያ የሰላም ሚንስቴር፣ ሴቶችና ሕፃናት፣ በቱሪዝምና አካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርት ቤቶች ምገባ፤ በኤች አይ ቪ ኤድስ እና በሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን፤ ጉልበትና ጊዜ እንዲሁም ገንዘቧን ሳትሰስት፤ መልከ ኢትዮጵያዊ መልኳን ከመጠበቅ አልታከተችም፡፡
ማህበረሰባዊ ሀገር ወዳድነቷን ተከትሎ፤ የኢትዮጵያን ባህልና እሴቶች በውጭ የማስተዋወቅ ሥራም ትከውናለች። አንድ ሆና ስለሀገሯ እልፍ የምትሠራ፤ ትጉህ ኢትዮጵያዊት አርቲስት ናት፡፡ ለዚህም በጎነቷ የአፍሪካ ህብረት እውቅናን ሰጥቷል፡፡
ከእነዚህ ሁሉ የሕይወት ዛፍና የኑሮ ቅርንጫፎች ጋር ቻቺ ታደሰ፤ አንዲት አርቲስትና የጥበብ ሰው ብቻ ናት ብለን የምናልፋት አይደለችም፡፡ እንደ እርሷ ያሉ አንጋፋ አርቲስቶች፤ በሕዝቡም ሆነ በመንግሥት ዘንድ ያላቸው ተደማጭነት ከፍ ያለ ስለሆነ ተጽእኖ ፈጣሪነታቸውም እንደዚያው ላቅ ያለ ነው፡፡ ታዲያ፤ ይህንን ነገር ለማህበራዊና ሀገራዊ ፋይዳ ለመጠቀም የሚነሡ ጥቂቶች ብቻ ናቸውና መክሊትን በወግ አግባቡ መጠቀም ካሉ አይቀር እንዲህ ነው፡፡
ምናልባትም በጥበብ ሥራዎቿ ከሰጠችን ባልተናነሰ ወይም በበለጠ፤ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቿ ዜጎቿን ለመርዳት ችላለች፡፡ ሀገርና ሕዝቧን የምትወደውን ያህል፤ እሷንም ከልብ የሚወዳት የሀገር ልጅ፤ በየሄደችበት ሁሉ ብዙ ስለመሆኑ በደስታና በኩራት በልበሙሉነት ትናገራለች፡፡ ብዙኃኑ እንደሚወዳት ብቻም ሳይሆን፤ ለምን እንደሚወዳትም ጭምር ታውቀዋለች… ምክንያቱም ሁሌም ቢሆን በሥራዎቿ ውስጥ፤ ሀገር… ሕዝብ…ባህል…የሚሉትን ጉዳዮች ለአፍታም ቢሆን ስለማትዘነጋቸው ነው። ሙዚቃዎቿ፤ ከመደሰትና ከማዝናናት ባለፈ፤ መልዕክት አዘል የፍሬ ዛፍ መስለው በመታየታቸውም ነው፡፡ እዚሁ ጋር፤ “ቻቺ ታደሰ ከሙዚቃ ሥራ የራቀችው፤ ሃይማኖቷን ስለቀየረች ነው…” የሚለው የአንዳንዶች ግምት፤ ፍጹም ውሸትና ስህተት ስለመሆኑ፤ ይህም በወሬ ወሬ ሳይሆን፤ ቻቺ በአንደበቷ ተናግራዋለች፡፡
በመሰለኝና በይሆናል ብቻ የወሬ ቱቦ መክፈት፤ ብዙ ግለሰቦችና ሚዲያዎች ሳይቀሩ እንዲህ ተያይዘው የሚወድቁበት ገደል ይሆናል፡፡ ጠርጥሮ መብላት፤ አብጠርጥሮ መናገር የሚያስፈልገውም ለዚህ ነውና በበዙ የዝነኞች ግላዊ ጉዳይ ላይ፤ ከባለቤቱ ቀድመን ባንገኝ መልካም ነው፡፡
ከአዲሱ የሙዚቃ ሥራዋ እንዳንርቅ፤ ከዚህ ሁሉ መጥፋት በኋላ፤ “ደርሷል ሰዓቱ” ለማለት፤ ስለምንስ ፈለገሽ? በማለት ከአንደበቷ ፍሬ እንልቀም፤ “ዓለም እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ በየሚዲያውና በተለያዩ አጋጣሚዎች እኛም ይህን እንመለከታለን፡፡ ያለውን ጦርነት፣ ችግር፣ መጠላላት…እያስተዋልን ነው ወይ የሚለው ጉዳይ ውስጤን ስለረበሸኝ፤ ከከበበን ጨለማ እንዴት ነው የምንወጣው ብዬ አሰብኩ፡፡ ከሙዚቃ ሥራዬ በስተጀርባ፤ በሀገሬ ላይ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሬ ከተመለከትኳቸው ነገሮችም አንጻር ደርሷል ሰዓቱ የሚል ነገር ተሰማኝ፡፡ ይህ በዚህ ሰዓት የምንመለከተው፤ የኢትዮጵያ መልክ አይደለም፡፡
ጭንቀት ውስጥ ነች፡፡ መደናበሩ ይቅር፤ ሁሉም ነገር ይብቃ፡፡ ዳግም የምንዋደድበት ሰዓቱ ደርሷል፡፡ ሰላም፣ ፍቅር፣ ተስፋ ለሁሉም የሰው ልጆች ከላይ ይሰጠን ዘንድ፤ የምንጮህበት ጊዜ አሁን በመሆኑ፤ እኔም እንነቃ ዘንድ ደርሷል ሰዓቱ ስል ይህን ሥራ ይዤ መጥቻለሁ።” በማለት ደግሞ መለስ አድርጋ፤ “ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይመጣል፤ ለሀገርና ለሕዝባችን ትተን ማለፍ የምንፈልገውስ ምንድነው?” ትለናለች፡፡ እሷ እንደሆነች፤ በሙዚቃና በሌሎችም ሥራዎቿ፤ የሀገሯን ሠርዶ በመንቀል የታላቅነትን ሸማ የማልበስ ትጋት ላይ ናት፡፡ ኢትዮጵያን አልፎም ዓለምን የመሥራት የሰላም ጥሪ አንግባ በቆራጥነት ቆማለች።
ሙዚቃና ቻቺ፤ ከብዙ ናፍቆት መልስ፤ “ደርሷል ሰዓቱ” ተባብለው እንዲህ ዛሬ ላይ ተገናኙ፡፡ እና ነገስ? ከሙዚቃው ጋራ ሸንተረር፤ ከዋርካው ስር እንጠብቃት ይሆን? ጥያቄው ለእርሷም ጭምር የቀረበ ነበረና “የተሰጠን ዛሬን ነውና የነገን አላውቅም፡፡ ዳግም በሌላ ሥራ እንገናኝ አሊያም አንገናኝ፤ እርግጠኛ አይደለሁም፤ ምናልባት ነገ የምናየው ይሆናል” የሚል ነበር ምላሹ፡፡ ቀጠል አድርጋ ግን፤ “የቀጣዩ ዋነኛ ትኩረቴና ትልቁ ዓላማዬ ግን፤ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ፊታቸውን ወደ ሀገራቸው እንዲመልሱ ማድረግ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማለት ለኔ፤ ሀገሬ ብቻ አይደለችም፡፡ እትብቴን የተቆረጥኩባት ኢትዮጵያ ከኔም፤ ከሁላችንም በፊት የነበረች ናት፡፡ ላገለግላት ተነስቼ፤ ያገለገልኳትና የማገለግላት ውድ እናቴ ነች፡፡ ባሳለፍኩት ዘመን የተረዳሁት ነገር ቢኖር፤ እኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ልጅ ነኝ፡፡ …እኛ ኢትዮጵያውያን ስንት የውጭ ጠላት ስናሸንፍ ኖረን፤ እንዴትስ እርስ በርሳችን እናንሳለን? ይህ የኢትዮጵያ መልክ አይደለም፡፡ በዓለም ሁሉ ስሟ የሚነሳው ከአሸናፊነት፣ ከሰላም፣ ከፍቅርና ከእንግዳ ተቀባይነት ጋር ነውና በዚህ ሁኔታ መታየት የለባትም፡፡ ከረዥም ጊዜ እንቅልፍ እንደ ባነነ አውሬ፤ ደነበረች እንጂ መች ነቃች ሀገሬ፤ እንዳለው ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን፤ እኔም መደናበሩ ይብቃን ብያለሁ።” ነበር ያለችው፡፡
ቻቺ የምትለው ሌላ አንድ ነገር አላት፤ “ለሀገሬና ለሕዝቤ የሚጠቅም ሥራ ካልሠራሁ…ወጣቱን የሚያስተምርና የሚለውጥ፤ ጥሩ ሥራ ካልሠራሁ፤ በቃ ፉርሽ ነኝ!” በዚህ ወኔ፤ ከተራራው ጋር እየተጋፈጠች፤ ከቁልቁለቱ ጋር እየተንደረደረች፤ ውሃውን ከምንጩ ስር ለመቅዳት ትታገላለች፡፡ ባተሌዋ በሌላ የጥበብ እንዝርት እየሾረችም፤ ድውሩን ደውራ ሸማና ቀሚሱን ለሀገሯ አልብሳ፤ ጌጧም ለመሆን ትታተራለችና፤ መልካሙን ሁሉ ከእድሜና ጤና ጋር ያድልልን!!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም