ነህሚያ-የበጎነት ተምሳሌት

ወይዘሮ ራሄል አባይነህ ትባላለች።የነህሚያ ኦቲዝም ሴንተር መስራችና ዳይሬክተር ነች። የተወለደችው በአባ ጅፋሯ ጅማ ከተማ ይሁን እንጂ ያደገችው፤ የተማረችውና ተድራ ሶስት ልጆቸ ያፈራችው እዚሁ አዲሰ አበባ ነው።

በትዳሯም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወቷ ደስተኛ መሆንዋን የምትገልጸው ራሄል፣ ሁለተኛ ልጇን እንደወለደች ግን ያልጠበቀችው፤ ይሆንብኛል ብላ ፈፅሞ ያልጠረጠረችውና በጊዜው አስደንጋጭ የሆነ ነገር እንዳጋጠማት ታስታውሳለች።ይኸውም ማርዬ እያለች እያቆላመጠች የምትጠራው ሁለተኛ ልጇ ከኦቲዝም (የአዕምሮ እድገት ውስንነት) ጋር መወለዱ ነው፡፡

ልጇ ኦቲዝም እንዳለበት ያወቀችበትን አጋጣሚ አስታውሳ ‹‹እኔ ልጄ ኦቲዝም እንዳለበት ያወቅሁት ሁለት ዓመት ከስምንት ወሩ ላይ ነው፤ ይሁንና ከአንድ ዓመቱ ጀምሮ ባህሪው ከሌሎች ልጆች የተለየ መሆኑ፤ መናገርና እንደልቡ መፀዳዳት ያለመቻሉ፤ በቂ እንቅልፍ የማይተኛና ራበኝ የማይል በመሆኑ ሁልጊዜም ጥያቄ ይፈጥርብኝ ነበር።በመሆኑም ችግሩን ለመረዳት ስል የተለያዩ የህክምና ተቋማት ሄጄያለሁ፤ ግን ደግሞ አንዳቸውም ችግሩን ቶሎ ሊያገኙለት አልቻሉም›› በማለት ታብራራለች።

‹‹አንድ ቀን ግን በአረብ ቻናል ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውን ሕፃናት ስመለከት የልጄ ችግር ኦቲዝም ሊሆን እንደሚችል ጠረጠርኩኝ፤ በጉዳዩም ላይ የምግባባውን ሐኪም / ዶክተር/ አማከርኩት፤ እሱ ግን ልጄ ኦቲዝም እንደሌለበት ሆኖም የበለጠ ርግጠኛ ለመሆን በዘርፉ ያጠና ባለሙያ ጋ ላከኝ፤ ሲመረመር ግን ልጄ ኦቲዝም እንዳለበት ተረጋገጠ›› ስትል ታክላለች።ስልጇ ሁኔታ ቀድማ ብትገነዘብም በሐኪሞች ምክንያት በመዘናጋቷና ለልጇ ቶሎ ድጋፍ ባለመድረጓ ዛሬም ድረስ በቁጭት የምታነሳው እንደሆነ ታነሳለች፤ በዚህ ረገድ ብዙ ወላጆች ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ስለሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ከጊዜው ጋር የሚራመድ እውቀት ሊያጎለብቱና ከማህበረሰቡ ቀድመው ሊገኙ እንደሚገባ ትመክራለች።የጤና ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤና ዝግጅቱ ከሌላቸው ጦሱ ለወላጆች እንደሆነ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው ባይም ነች፡፡

ይህንን ተቋም ልትመሰረት የቻለችው ለልጇ የሚሆን ትምህርት ቤት በማጣቷና እንደእርሷ ብዙ እናቶች እየተቸገሩ እንደሚኖሩ በመገንዘቧ ነው።‹‹እኔም ሆንኩኝ በተመሳሳይ መልኩ ከኦቲዝም ጋር የተወለዱ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ለእነሱ የሚሆን ትምህርት ቤት በማጣት ምክንያት ማህበረሰቡ የሚሰጠውን በጎ ያልሆነ አስተያየት ተቀብለን ቤት ውስጥ እንድንቀመጥ የተገደድንበትን ሁኔታ ለመቀበል ፍቃደኛ አልነበርኩም፤ እናም ልጄና ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውን ሕፃናት ሕይወት መታደግ እንዳለብኝ በማመኔ ነው›› በማለት ትገልፃለች።

ባደጉት ሀገራት ከኦቲዝም ጋር የተወለዱና ትልልቅ ደረጃ የደረሱ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሳ፤ ይህ ሊሆን የቻለው ግን ሀገራቱ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠታቸውና እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ሊያስተናግድ የሚችል ተቋም መስርተው በቂ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው በመሆኑ ጭምር እንደሆነ ታስረዳለች።

‹‹እኛ አጠቃቀሙን አላወቅንም እንጂ በዓለም ላይ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ሰዎች በያዙት ነገር ውጤታማ ናቸው።እንደቢልጌት፤ አልበርት አንስታይን፤ ሞዛርት ያሉና ከራሳቸው አልፈው ለብዙዎች የተረፉ አነጋጋሪ ሰዎች ከኦቲዝም ጋር የተወለዱ ናቸው።እኛ ግን እነዚህን ሰዎች መጠቀም ያለመቻላችን እንደሀገር ኪሳራ ላይ ነን ብዬ አስባለሁ›› ስትልም ታብራራለች።በመሆኑም እነዚህን ልጆች ትምህርትና የተለያዩ ሕክምናዎች አግኝተው እንዲያድጉ በማድረግ ይዘው የመጡትን እውቀት ልንጠቀምበት ይገባል ስትል ትጠቁማለች።

ስለ ኦቲዝም የነበራት እውቀት እንዲህ እንደ አሁኑ አይሁን እንጂ ለቃሉ አዲስ እንዳልነበረች፤ በተለይ ሌሎች ከሷ በፊት ተመሳሳይ ድርጅት የከፈቱ ሰዎች በመገናኛ ብዙሃን ስለበሽታው በሚያደርጉት ገለፃ የተወሰነ መረጃ ማግኘቷን ትገልፃለች።ይሁንና እቤቴ ይገባል ብላ ፈፅሞ ያልጠረጠረችው ጉዳይ ስለነበር እምብዛም ትኩረት ትሰጠው እንዳልነበር ትናገራለች።

ወይዘሮ ራሄል እንኳን ማህበረሰቡ ኦቲዝምና ተያያዥ ችግሮች ያሉባቸውን ሕፃናት፤ ከፈጣሪ ቁጣ ጋር የማያያዝና እንደተለየ ፍጡር የማየት ክፉ ባህል ቢኖርበትም እሷ በኖረችበት ገርጂ አካባቢ አብዛኛው ሰው የነቃና ስለጉዳዩ ግንዛቤ ያለው በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ችግር እምብዛም እንዳላገጠማት ታስረዳለች።‹‹እኔ ዘንድ የለም ማለት ግን ሌላ ሰው ጋ የለም ማለት አይደለም፤ ልጄ ገና ሕፃን ሳለ አንዳንድ ጊዜ ቤት ሲያስቸግረኝ ይዤው ስወጣ ሰማይ ሰማይ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ጎን እያየ ስለሚሄድ ይህንን ያዩ የሰፈራችን አዛውንት ይሄ ሁኔታ የተለመደ እንዳልሆነና ጉዳት ሊያደርስበት ስለሚችል እንድጠነቀቅና ለሐኪም እንዳሳየው ይወተውቱኝ ነበር፤ እኔም ከዚያ ወዲህ ነው የልጄን ያልተለመደ ባህሪ ማጥናት የጀመርኩት›› በማለት ታብራራለች፡፡

ይሁንና ዘጠኝ ዓመቱ አካባቢ እንደተለመደው ልታዝናናው ከቤት ይዛው በወጣችበት አጋጣሚ እግሩን እያነሳ ሲጫወት ያዩት አንዲት እናት ጠጋ ብለው እንደዚህ ዓይነት ልጅ ከቤት እንደማይወጣ፣ የሰው ዓይን ጥሩ እንዳልሆነ፤ እንደ እዚህ ዓይነት ልጆች ለፈጣሪ ቅርብ ስለሆኑ ቤት መቀመጥ እንዳለባቸው በመግለፅ እንደመከሯትም ታስታውሳለች።ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ያሏቸው ሌሎች እናቶችም እንደተረገሙ፤ በሰሩት ሐጥያት ፈጣሪ ተቆጥቶባቸው እንደሆነ በማህበረሰቡ እየተነገራቸው ኑራቸውን ጠልተው ራሳቸውን እስከማጥፋት የሚደርሱበት አጋጣሚ ስለመኖሩ መስማቷንም ታስረዳለች።

እሷ እንዳለችው፤ እንደዚህ ዓይነት ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ትምህርት ቤት በማጣትና ማህበረሰቡ በሚያደርግባቸው ማግለል ምክንያት ብዙ ትዳር ይፈርሳል፤ ብዙ የተማሩና ትልቅ ቦታ መድረስ የሚችሉ ሰዎች ቤት ውስጥ ቀርተዋል።

ከዚህም አልፎ ሌሎቸ ልጆቿንም የምትጎዳበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቅሳ፣ ትልቅ ቦታ የመድረስ ህልማቸው እንደሚጨናገፍ በተጨባጭ እንደሚታይ ታመለክታለች።በዚህ ምክንያት ልጆች ያለእድሜያቸው ጎዳና ላይ የሚወጡበት ሁኔታም ይፈጠራል ስትል ጠቅሳ፣ ‹‹ዛሬ እኔና ባለቤቴ ስላለን ልጆቻችንን ተንከባክበነን አሳድገናል፤ ነገ ባንኖር ግን የሀገር ሸክም ነው የሚሆኑት›› ስትል አስገንዝባለች።በድምሩ ከኦቲዝም ጋር አብረው የተወለዱ ልጆችንን የሚያስተናግድ ሥርዓትም ሆነ ተቋም ያለመኖሩ ለሀገር ትልቅ ኪሳራም ነው ባይ ነች።

እንደ ወይዘሮ ራሄል ገለፃ፤ ነህሚያ ኦቲዝም ሴንተር ከተመሠረተ ሰኔ ወር ላይ ዘጠኝ ዓመት ይሆነዋል።ድርጅቱን የመሠረተችበት ምክንያትም ለኦቲዝም ተጠቂዎች የሚሆን የትምህርት ተቋም በአቅራቢያዋ ያለመኖሩ ሲሆን፣ ህመሙ በቤቷ በመኖሩ እሷና ባለቤቷ እንደእነሱ የተቸገሩ ወላጆችን ያቅማቸውን ያህል ለማገዝ በማለም ነው።

በተለይም እናቶች ከተደበቁበት ወጥተው ልጆቻቸውን ሙሉ እምነት ይዘው የሚያስቀምጡበት ቦታ መፍጠርና የራሳቸውን ሥራ የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው።ልጆችም ከታፈነና ከተጨናነቀ ቤት ወጥተው ሰፊ ለምለም መስክ ባለበት ጊቢ ውስጥ የሚዝናኑበትና የሚቦርቁበትን ሥፍራ ለመፍጠርም ያለመ ነው።

ለዚህ ዓላማ መሳካት ያስችላት ዘንድም ወደ ቤተክርስቲያን በቀጥታ በመሄድ የሚያቋትን አገልጋዮችና ምዕመናን እንዲያግዟትና ድጋፍ እንዲያደርጉላት ተማፀነች።እነሱም አለሳፈሯትም፤ የአቅማቸውን ለገሷትና ቤቷን ተከራየች፤ አንዳንድ የሚያስፈልጋትን መሠረታዊ ቁሳቁስ አሟልታ ኦቲዝም ያለባቸውን ሕፃናት መንከባከብ ጀመረች።

‹‹ትልቁ ነገር ግን በማህረሰቡ ዘንድ ስለኦቲዝም ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ እድሉን ማግኘታችን ነው›› ስትል ገልጻ፣ የባልና ሚስቱን ጥረት ያየ አንድ ሰው ደግሞ የሚሰራው ፕሮጀክት ጊዜው ያለፈበት (ፌዛውት ያደረገበት) መሆኑን ጠቅሶ የቤቱን እቃ በሙሉ እንደሰጣቸው ትናገራለች።

‹‹ነህሚያ የእኔም የብዙዎች የፀሎት መልስ ነው፤ እግዚአብሔር ስለረዳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍቃድ አግኝተን ነው ተቋሙን ማስፋፋት የቻልነው›› የምትለው ወይዘሮ ራሄል፤ ተቋማቸው ልጆቹን ከተረከበ በኋላ የተለያዩ ደረጃዎች ያሏቸውን ተግባር ተኮር ስልጠናዎችን በመስጠት ከማህበረሰቡ ጋር በቀላሉ መግባባት እንዲችሉ፤ ለመደበኛ ትምህርት ቤት የማብቃት ሥራ እንደሚሠራ ገልጻለች።የልጆቹ በተቋሙ ውስጥ የሚኖራቸው የቆይታ ጊዜ እንዳሉበት የኦቲዝም መጠን የሚለያይ መሆኑን ገልፃ፤ በአሁኑ ወቅት ተቋማቸው 80 ተማሪዎች እንዳሉት ትጠቁማለች። በተጨማሪም 30 ከኦቲዝም ጋር የተወለዱ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት መላክ መቻሉን ትገልፃለች።

እንደ ወይዘሮ ራሄል ማብራሪያ ፤ የኦቲዝም ማዕከሉ ቋሚ የገቢ ምንጭ ባይኖረውም በየጊዜው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ያዘጋጃል፤ ባንኮችን፣ ኢንሹራንሶችና አትራፊ ኩባንያዎች ድጋፍ እንዲያደርጉለትም ቅስቀሳ ያደርጋል።አሁን ላይ በተለይ መንግሥታዊ ተቋማት የማዕከሉን በጎ ሥራ በገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል።ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ልማት ባንኩ ተጠቃሽ ነው።ባንኩ ከአራት ወር በፊት ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማዕከሉ የሰጠ ሲሆን፣ ይህም ማዕከሉ ለጀመረው ሥራ መስፋፋትና መጠናከር ያግዛል፡፡

‹‹አሁን ላይ ማዕከላችን ያለበት ጊቢ ካሉት ተማሪዎች አንፃር ጠባብ የሚባል ነው፤ ከ53 በላይ ሠራተኞች ቢኖሩንም ሁሉንም ልጆች በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል አቅም ስለሌለን በሳምንት ሁለት ጊዜ ከፍለን 40 ልጆችን በመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት በመቀጠልም ባሉት ቀናት ቀሪዎቹን 40 ተማሪዎች እያሰለጠንን ነው ያለነው›› በማለት ታብራራለች።ባንኩ ማዕከሉ ያጋጠመውን ችግር በመረዳት ከሰሞኑ ደግሞ ተጨማሪ ሶስት ሚሊዮን ብር እንዳባረከተላቸው ነው የማዕከሉ ዳይሬክተር የጠቆመችው።ንግድ ባንክና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን የመሳሰሉ መንግሥታዊ ተቋማትም ከማዕከሉ ጎን በመቆም አለኝታ እንደሆናቸውም ጠቅሳለች፡፡

ወይዘሮ ራሔል እንደምትለው፤ መጀመሪያ ላይ የእናቶችን ድካምና እንግልት ለመቀነስ ማዕከሉን በየአካባቢው የማስፋፋት እቅድ ነበራት።ሆኖም ካለው ሀገራዊ ሁኔታ አንፃር ይህንን ማሳካት በቀላሉ የማይቻል መሆኑን በሂደት ተገነዘበች።በኋላም አስር ዓመት ላይ አዳሪ ትምህርት ቤት ለመክፈት አልማ መሥራቷን ቀጠለች።ይህ ትልሟ በተለይ በኩላሊት፣ በኤች.አይ.ቪ ኤድስ፣ በኮቪድ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት እጇ ላይ ያሉ በመሆናቸው ደረጃውን የጠበቀና በአግባቡ በሞግዚት ታግዘው እንዲያድጉ የሚያግዝ ነው።ግን ደግሞ ይህንንም ማሳካት የተራራ ያህል ከባድ ሆነባት፤ ይልቁንም አሁንም ድረስ የግለሰብ ቤት ተከራይታ ነው እየሰረች ያለችው።በመሆኑም ይህንን ችግሯን የተረዳ የመንግሥት አካል ቦታ ይሰጠኛል የሚል እምነት እንዳደረባትም ገልጻለች።

‹‹ይህ መሆን ከቻለ ብዙ ሕፃናትና እናቶቻቸውን እናሳርፋለን፤ በነገራችን ላይ ነህሚያ ለሕፃናቱ ብቻ ሳይሆን ለእናቶች የሥራ እድል ይፈጥራል፤ እናቶችን እናሰለጥናለን፤ እናማክራለን፤ በጣም የተጎዱና ራሳቸውን ለማጥፋት የሞከሩ እናቶች አሁን በማዕከሉ ያሉ በመሆኑ የእነሱንም ሕይወት የመታደግ ሥራ ይሠራሉ›› ስትል የወደፊት እቅዷን አጋርታናለች።

ይህ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር በኦቲዝም ዙሪያ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት በመኖሩ ይህንንም ችግር በመፍታት ረገድ ነህሚያ ወሳኝ ሚና ለመጫወት አስቧል።እነዚህ ሁሉ እቅዶቹን ማሳካት የሚችለው ግን አሁንም የመልካም ሰዎችና ተቋማት በጎ እጆች ሲዘረጉላቸው ብቻ እንደሆነ ነው ያስገነዘበችው።

በአሁኑ ወቅት ኦቲዝም ብዙ ቤት እየገባ ነው፤ በመሆኑም ልክ እንደእኔ ኦቲዝም ሩቅ አድርጋችሁ አታስቡት፤ መዘናጋትም የለብንም፤ የእኔ ልጅ ኦቲዝም እንዳለበት በታወቀበት ጊዜ ከ15 ሺ አንድ ልጅ ላይ ነው ይገኝ የነበረው።አሁን ላይ ግን ከ36 ልጅ በአንዱ ላይ እየተገኘ ነው።ይሄ አሃዝ አስደንጋጭ ነው።ስትል አስገንዝባለች።‹‹ ኦቲዝም በቀላሉ የምናየው አይደለም።በመሆኑም ሁሉም ሰው በቻለው መጠን ኦቲዝም ልጆችን መርዳት፣ በየቦታው ማዕከላት እንዲከፈትላቸው የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት፤ እንዲህ ዓይነት ልጅ ያላትን እናት በማግለልና ጫና በማሳደር ሌላ ሥራ ላለመሆን መጣር፤ ይልቁንም ጥንካሬዋን እየነገሩ ማበረታታት ይገባዋል ስትል ወይዘሮ ራሔል ለማህበረሰቡ መልእክቷን አስተላልፋለች፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You