የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃን በሚመለከት ያዘጋጀውን ሀገራዊ ሪፖርት በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በዚህ መነሻ መሠረት በሀገሪቱ ያለው በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ምን ይመስላል? ማህበራዊ ሚዲያው በየቀኑ የሚረጨውን የጥላቻ ንግግር ፈር በማስያዝ በኩል ባለስልጣኑ ኃላፊነቱን እንዴት እየተወጣ ነው? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ለባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለአቶ ዮናታን ተስፋዬ አቅርበናል። መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን፡- ቀድሞ የብሮድካስት ባለሥልጣን ይባል የነበረው አሁን ስሙን ወደ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቀይሯል? ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ዮናታን፡- ቀደም ሲል ብሮድካስት ባለሥልጣን እንዲቆጣጠረ በአዋጅ የተሰጠው ብሮድካስቶችን ብቻ ነው። ማለትም ቴሌቪዥን፤ ሬዲዮና ሕትመትን ነበር። አሁን ግን በሪፎርሙ አዲስ አዋጅ ከፀደቀ በኋላ በእሱ መሠረት መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ተቋቁመዋል። በፊት ከነበረው በተጨማሪ አሁን ላይ የመጣው የበይነ መረብ ሚዲያዎችን ይቆጣጠራል። ይህ ሲባል የሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡትን እንጂ የማህበራዊ ሚዲያዎችን በሙሉ አይደለም።
የበይነ መረብ ሚዲያ እንደ ዋናዎቹ ሚዲያዎቸ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ኖሮት፤ የንግድ ፈቃድ አውጥቶ የሚዲያ ሥራ የሚሠሩትን የመቆጣጠር ኃላፊነትን ያካትታል። ለዛ ነው ስሙንም ብሮድካስት ከሚለው ወደ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የለወጠው።
አዲስ ዘመን፡- ባለሥልጣኑ የተቋቋመበት አላማ ከላይ የጠቀስናቸውን ሚዲያዎች መቆጣጠር ከሆነ ሌሎቹን የማህበራዊ ትስስር ገፆችን መቆጣጠር የምንችለው እንዴት ነው?
አቶ ዮናታን፡- ማህበራዊ ትስሰር ገፆችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕግ ክፍተት አለ። በይነ መረብ ሚዲያዎችን በምን መልኩ ነው ህጋዊ ሰውነት አግኝተው መንቀሳቀስ የሚችሉት የሚለውን መዳሰስ ያስፈልጋል። አሁን እየመጣ ያለውን በጣም ተለዋወጭ ባህሪ ያለውን ማህበራዊ ሚዲያ ከባህሪው ጋር አብሮ የሚዛመድ የማህበራዊ ሚዲያ አዋጅን፤ ወይም ደግሞ በወጡት አዋጆች ውስጥ ማለትም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅና የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ የእነሱን መሠረት በማድረግ ሌላ ማስፈፀሚያ ደንብ ወይም እራሱን የቻለ ሕግ ያስፈልገዋል።
ስለዚህ እንደ ሚዲያ እንሰራለን የሚሉ በኦላይን ሚዲያ የሚንቀሳቀሱ ህጋዊ ሰውነት ማግኘት ግዴታ ይኖርባቸዋል። አይ የለም እንደ ሚዲያ ሳይሆን አንደ ማንኛውም ዜጋ ሃሳባችንን ነው የምንገልፀው ለሚሉት ወይ በሌላ ማስፈፀሚያ ደንብ ወይም በሌላ የማህበራዊ ሚዲያ አዋጅ ሊዳኙ የሚችሉበት አግባብ መፈጠር ይኖርበታል። በሕገ- መንግሥቱ መሠረት ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት ቢከበረም ገደብ መጣል ይኖርበታል። ይህም ገደብን ተላልፎ የተገኘ ሰው ወደ ፍትህ የሚወስደበት፤ ተጠያቂነት የሚሰፍንበት ነገር ወይ በማስፈፀሚያ ደንብ ወይም ደግሞ ራሱን የቻለ የማህበራዊ ሚዲያ አዋጅ ሊወጣለት ይገባል።
አሁን ባለው ግን ከነ ክፍተቱም ቢሆን ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ የሚሰሩ አሉ። ከተለያዩ መነሻዎች ደግሞ ሳይመዘገቡ እንደዚሁ የሚንቀሳቀሱ አሉ፤ እውቅና እንሰጣቸውም። የተወሰኑት ደግሞ ከሀገር ውጭ ሆነው ከተጠያቂነት ለመራቅም ወይንም በሌላ ምክንያት የሚሰሩ አሉ። ሆኖም ሁሉም ተገቢውን ቁጥጥር ካተደረገባቸው አደጋው ከባድ ነው።
በእኛ ሥልጣን ወሰን ውስጥ ያለውን እንደ ሚዲያ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ፕሮፌሽናል ሥራ የሚሠራውን አካል እንቆጣጠራለን። ከዛ ውጭ ያለው ግን በሂደት የሚታይ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ምን ያህል የመገናኛ ብዙኃን ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ?
አቶ ዮናታን፡- ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሆኑ ከሰላሳ በላይ ናቸው። ዋናዎቹ ሚዲያዎች ደግሞ በየዓመቱ ቁጥራቸው እየጨመረ በርካታ ሆነዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት ይህ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ከወጣ ጊዜ ጀምሮና አዋጁም ከመፅደቁ በፊት ባሉ ጊዜዎች በርካታ የኤ ፍ ኤም ሬዲዮዎች፤ የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ጭምር ተከፍተዋል። ከዚህ በፊት የሃይማኖት ቲቪዎችን የብሮድካስት አዋጅ እውቅና አይሰጣቸውም ነበር። አሁን ግን በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር በብሮድካስት ስር ገብተው የሚሠሩበት ማዕቀፍ አለ። ለእነሱም አዲስ ፍቃድ መስጠት ተጀምሯል። አብዛኞቹ ሕጋዊ እውቅናም አላቸው። በቴሌቪዥን ፤ በሬዲዮ በሃይማኖት ሚዲያ አካባቢ እድገት አለ።
የሳሳ የሚመስለው ሕትመትና የኮሚንቲ ሬዲዮ አካባቢ ነው። ኮሚኒቲ ሬዲዮኖች ራሱ ሪፎርሙን ተከትሎ ወጣ ገባ ቢሉም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ብዙ ሥራ ይጠይቃል። በሕትመት አካባቢ ደግሞ ሕትመት ያሉበት ተግዳሮቶችን ታግሎ እንዲያሸንፍ መደረግ ይኖርበታል።
አሁን ያለው ማህበራዊ ሚዲያ ዘመን እንኳን ለሕትመቱ ሚዲያ ይቅርና ለብሮድካስቱም ፈታኝ እየሆነ በመጣበት ዘመን የሕትመት ዘርፉ ተግዳሮት ቢያጋጥመው የሚጠበቅ ነው። ከላይ ከጠቀስናቸው ሚዲያዎች በስተቀር በቲቪ፤ በሬዲዮና፤ በማህበራዊ ሚዲያዎች ያለው እድገት ሁለት መቶ በመቶ በላይ ነው። በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ሁሉንም የሚዲያ ዓይነት ጨምሮ 230 ሚዲያዎች አየር ላይ እየዋሉ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባለሥልጣኑ እነዚህን የመገናኛ ብዙኃን ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርገው በምን መልኩ ነው?
አቶ ዮናታን፡- በዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን የሌላውን ማህበረሰብ እሴት ያላከበሩ የጥላቻ ንግግሮች ሲተላለፉ የሚታይበት ወቅት አለ። ግጭቶች ሲኖሩ ግጭቱ አካባቢ ባሉ ሚዲያዎች በሌላኛው ማህበረሰብ ላይ የሚናገሩት ንግግር ለሀገሪቱ ዜጎች አብሮነት አጠቃላይ እንቅፋት ሲሆኑ ታይተዋል።
ይሄንን ባለን ልምድ በተለያዩ ክትትሎች በሰበሰብናቸው መረጃዎች ከሚዲያዎቹ ጋር ግልፅ የሆነ ግንኙነት ፈጥረናል። በዚህም የለም በሚባል ደረጃ ከዋናዎቹ ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግርን ለማስወገድ ተችሏል። ያ የሆነው ግን በአጠቃላይ ሀገሪቱ እያለፈችበት ካለው የሪፎርም ባህሪ አንፃር ትንሽ አስቸጋሪ ስለነበር ነው። በዚህም ምክንያት ርምጃ መውሰድ፤ መቅጣትና መዝጋትን አማራጭ ተደርጎ አልተወሰደም ነበር። በጣም የወጡ ችግሮች ማለትም ኦ ኤም ኤን እንደዘገባቸው ዓይነት ጉዳዮች፤ አስራት እንደተዘጋበት ኬዝ፤ ድምፅ ወያኔና ሌሎች እንደተዘጉበት ዓይነት ካልሆነ የከፋ ርምጃ አልተወሰደም ነበር።
አብዛኞቹ ግን የንግድም የሕዝብም በሚባሉት ሚዲያዎች ውይይት በማድረግ እንዲታረሙ ለማድረግ ተሞክሯል። አንዳንዶቹን ደግሞ በመርህና በማስረጃ ስህተታቸውን እንዲያዩ በማድረግ ረጅም ርቀት ለመሄድ ተችሏል። ከዛም ሲያልፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አሉ፤ ጊዜያዊ እግድ የተሰጣቸውና ኋላ ሲያስተካከሉ መልሶ ብርድካስት እንዲያደርጉ የተፈቀደላቸውም ይገኙበታል።
አሁን ላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ፈታኝ የሆነ ወቅት ቢሆንም ሚዲያዎች ላይ አስፈላጊ የሚባል ለውጥ መጥቷል። አሁንም በቅርበት ክትትል እየተደረገ ነው። የክትትል ሲስተሙ አሁን ላይ እንደ ድሮው የሞኒተር ባለሙያዎች እየተመለከቱ የሚውልበት ሳይሆን በትኩረት ክትትል በማድረግና፤ በ9192 የሚባል ነፃ የስልክ መስመር ዜጎች በቀጥታ ደውለው በየትኛውም ሚዲያ የሚያዩትን ጥሰቶችን በሙሉ ሪፖርት ያደርጋሉ። ይህ ሲሆንም በክትትል ከተደረሰባቸው በኋላ በማስጠንቀቂያ ከማለፍ ጀምሮ ርምጃ እስከ መውሰድ ይደርሳል።
አዲስ ዘመን፡- የማህበራዊ ሚዲያን የሚቆጣጠር መመሪያስ አለ? የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓቱስ ምን ይመስላል?
አቶ ዮናታን፡- የክትትልና ቁጥጥር አሠራራችን የሚመነጨው ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅና፤ ከማስታወቂያ አዋጅ ነው። ይህ የማህበራዊ ሚዲያን ወይም የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን የሚቆጣጠረው አዋጅ ነው። ሶስቱ በመሠረታዊነት ይመልከቱናል። ሌሎችንም ሚዲያን የሚመለከቱ አዋጆች መሠረት በማድረግ መመሪያ ተዘጋጅተዋል።
መመሪያው በአዋጁና በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው አግባብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተመዝግበው እውቅና አግኝተው ነው የሚሠራባቸው። የሚዲያ ተቋማት መመሪያውን ተላልፈው ሲገኙ ደግሞ ክትትል አድርጎ የእርምት ርምጃዎችን መውሰድ ግዴታ ነው። ተቋሙ የዲሞክራሲ ተቋም እንደመሆኑ አስተዳደሪያዊ ርምጃዎች ነው የሚወስደው። ፖሊስ አይደለንም፤ የፍትህ አካል አይደለንም መውሰድ የምንችለው አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰድ ነው።
የመጨረሻው ርምጃችን ፈቃዱን መንጠቅ ነው። ሌላ የሕግ ጉዳይ ሲኖር ወደ ፍትህ አካላት እንዲሄዱ ይደረጋል።
ቅጣት ላይ ከመድረሱ በፊት ግን መመሪያውን ለማስከበር የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ። ይህ ማለት ግዴታዎችን እንዲረዱ እና በገቡት ውል መሠረት እየሠሩ ስለመሆኑ ቁጥጥር በማድረግ በሕግና በሥርዓት እንዲሠሩ ይደረጋል።
በማህበራዊ ሚዲያው ላይ እስካሁን ድረስ ራሱን የቻለ መመሪያ የለም። ያለው ጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን የሚመለከት አዋጅ ነው። በቀጥታ ማህበራዊ ሚዲያን የሚመለከት የለም።
የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪዎች ማለትም እንደነጎግል ሜታ የመሳሰሉት ሊያደርጓቸው የሚገቡ ድንጋጌዎች አሉ። ካላደረጉ ግን እንዴት ተጠያቂ ይሆናሉ የሚለው ላይ እስካሁን የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉ። ራሱን የቻለ አዋጅ ያስፈልጋል። ይህ ማለት ድንበር ተሻጋሪ ጉዳይ በመሆኑ አቅም ያላቸውን አካላት ያካተተ፤ የፍትህ አካላት የሚሳተፉበት መሉእነት ያለው ደንብ ማስፈፀሚያ አዋጅ ያስፈልገዋል።
ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስላሉ ጥሰቶች አሁን ላይ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እያደረገ የሚገኘው ግንዛቤ ማስጫዎች ላይ መሥራት ነው። በዚህም ወደ ሰባ ስምንት የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ በመድረስ ስልጠና ሰጥተናል፤ በማህበራዊ ሚዲያ ጥሪ በማድረግ ፋክት ቼኪንግ ላይ፤ ስለ ጥላቻ ንግግር የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫዎች እየተሰጡ ይገኛሉ። ይህ ጉዳይ በስፋት ለውጥ እንዲመጣ ሲቪክ ማህበራት፤ ሚዲያዎችና ትምህርት ቤቶች በስፋት ቢሰሩበት ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሪፖርት ማውጣት ነው። ከዛ ያለፈ ሚና የለውም ባለሥልጣኑ። ሪፖርቱ ግን ማንቂያ ደውል ነው። ሌሎች አካላትም ያሉ ችግሮች እንዲያዩበት ማደረጊያ ነው። በጣም በጠራ መልኩ የተለያዩ ተቋማት ያላቸውን ኃላፊነት እንዲመለከቱ የሚያደርጉ ረፖርቶች ይወጣሉ። በአጠቃላይ እንደ መንግሥት የማህበራዊ ሚዲያ ቱርፋትን እየታየ ጥፋቱን የሚያቀጭጭ አዋጅ ሊዘጋጅለት የሚገባ መሆኑን ነው የምናምነው።
አዲስ ዘመን፡ – ስለዚህ ማህበራዊ ሚዲያው በየቀኑ የሚረጨውን የጥላቻ ንግግር ፈር በማስያዝ የሚያስችል መመሪያ የለም ማለት ነው?
አቶ ዮናታን፡- መኖር አለ። የተጠቃሚዎች በብር ወይም በእስር እንዲቀጡ የሚል መመሪያ አለ። በዚህም በዜጎች መካከል በጣም ጥላቻ ሊፈጥር የሚችል ንግግር ሲያሰራጩ የሚጠየቁበት ሁኔታ አለ። ይህ ግን በበቂ ሁኔታ ሊሆን አልቻለም ለማለት እንጂ ይህን ጥፋት ማረሚያ መመሪያ አለ።
ለምሳሌ አንቺ ጋዜጠኛ ነሽ ፤ ፕሬስ ውስጥ ነው የምትሰሪው፤ ስታጠፊ አንቺ ትቀጫለሽ፤ የሚያሰራሽም ተቋም ይቀጣል። በርካታ መስመሮችን አልፎ ለሕዝብ የጥላቻ ንግግር በማድረሱ የሚያሰራሽ ተቋም ይጠየቃል። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ግን አገልግሎት አቅራቢው ድርጅት ላይ ግዳጆች ይቀመጣሉ። ለምሳሌ ፌስቡክ ላይ የተቀመጡ ማህበረሰቡ ላይ የሥነ ልቦና ጫና የሚያደርሱ ንግግሮችን ማስወገድ ካልቻለ ግን ያንን ሊያስገድድ የሚችል አዋጅ ያስፈልጋል ለማለት ነው።
ለመቆጣጠር የሚያስችል አንቀጾች አሉ። ሆኖም የሚያጠፉ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን ተቋማት ለሀገሪቱ ሕግ ተገዥ የሚሆኑበት ካልሆነ ግን ተጠያቂነትን ሊያሰፍን የሚችል የቴክኖሎጂውን ባህሪ ከግምት ያስገባ ማስፈፀሚያ ደንብ ያስፈልጋል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ክትትላችሁ ውጤት አምጥቷል ብላችሁ ታምናላችሁ?
አቶ ዮናታን፡- በእኔ እምነት አሁን ላይ በተለይ በዚህ አንድ ሁለት ዓመት ወዲህ ለውጥ መጥቷል እላለሁ። ባለው ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ማለትም በሪፎርሙ ሂደት ውስጥ ግጭትን የሚያነሳሱ መልዕክቶች ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ። እነዛን ተግዳሮቶች ሚዲያው ተፈትኖባቸዋል፤ ሚዲያው ሲፈተን እኛም ተፈትነናል። ሆኖም የከፋ ችግር ሳያስከትል ለመቆጣጠር ተሞክሯል።
ተቋሙ በቀጭን ገመድ ላይ ሚዛን ጠብቆ እየሠራ ያለ ተቋም መሆኑ ይሰማኛል። መርህ ላይ በተመሠረተ መልኩ ሚዲያው ስለሚመራ አሁን ላይ ሚዲያው በጤናማነት እየተመራ ያለ ነው። ከኢትዮጵያ የሥልጣን ወሰን ውጭ የሆኑት ብቻ ካልሆኑ በስተቀር እየተስተካከሉ እየታረሙ እየሄዱ ያሉበት ሁኔታ አለ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን አንድ ጥናት ይፋ አድርጋችሁ ነበር። ጥናቱ ምን አመላከተ?
አቶ ዮናታን፡- ቀደም ሲል በመሃል በመሃል ላነሳሳ ሞክሬ ነበር። የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል በወጣው አዋጅ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሁለት ኃላፊነቶችን ይጥልበታል። አንዱ ኃላፊነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ነው። እሱን ከማድረግ አንፃር ለተማሪዎች፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሚኒ ሚዲያ ላይ ለሚሰሩ፤ ለማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለሚሳተፉ ጥሪ በማድረግ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው። ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በሌላ በኩል የተሰጠው ኃላፊነት ደግሞ ሪፖርት ማውጣት ነው። መገናኛ ብዙኃን ባልሥልጣን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪ አውታሮች በሀገሪቱ ሕግ መሠረት እየሠሩ መሆኑን ክትትል አድርጎ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል የሚል ኃላፊነት ነው። ይህ ሁለት እንድምታ አለው። አንደኛው ራሳቸው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያ አውታሮቸ የሀገሪቱን ሕግ አክብረው እየሠሩ ነው አይደለም የሚለውን በመረጃ ፈትሸን ለረሳቸው ማሳወቅ ነው። እየሠራችሁ አይደለም ሕግ እየተላለፋችሁ ነው የሚል የማነቂያ ደውል ነው።
ሌላው ሕዝብም እንዲያውቀውና ግንዛቤ እንዲኖረው፤ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ማድረግ የሚችሉትንና መድረግ ያለባቸውን ነገር እንዲያወቁት ማሳወቅ ነው። ሲቪክ ማህበራት ሌሎች ሚዲያዎችና የሚመለከታቸው አካላትም ጉዳዩን መወያያ በማድረግ መፍትሔ እንዲሰጠው ማድረግ ነው።
በየነ መረብ ሚዲያን የሚከታተል ክፍል አለን፤ ይህንን በመከታተል ማህበረሰቡ የሚያቀርበውን ቅሬታ በመመልከት ለሁለተኛ ጊዜ ሪፖርት ወጥቷል። ከሕዝብ በተሰበሰበው መረጃም ሆነ ተቋሙ በቋሚነት ከሚያደርገው ክትትል በተገኘው መረጃ መሠረት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የንግግሮችና ጥላቻን ማስፋፋት ብቻ ላይ የተገደበ ነው።
በዚህ ስድስት ወር ላይ የታየው ደግሞ ዝም ብሎ ጥላቻን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን አመፅ መቀስቀስ፤ ግለሰቦችን ለጥቃት ማጋለጥ፤ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ መተማመን እንዳይኖር፤ የአብሮነት እሴቶች እንዲሸረሸሩና ወደ ተግባር ለጥፋት የሚነሳሱ ነገሮች በስፋት ተስተውሏል።
ተቋሙ እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች እያደረሱት ያለውን ጥፋት ለመከላከል ያደረገው ጥረት በሌሎች አካላት በበቂ ሁኔታ አልተደገፈም። ህብረተሰቡ ሪፖርት አድርገው ያልተመለሱ፤ ተቋሙም ሪፖርት አድርጎ የተሰጠው ምላሽ ደካማ መሆኑ ያሳያል። በሪፖርቱ እንደታየው ለኢትዮጵያ ገበያ ያለው ፍላጎት አነስተኛ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል። ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንፃርም ፌስቡክ ካልሆነ በስተቀር ሌሎቹ በኢትዮጵያ ቋንቋ ዜጎች እንዴት ሪፖርት እንደሚያደርጉ ግልፅ በሆነ መልኩ አይቀመጥም።
ከፌስ ቡክ ውጭ የእነሱን አገልግሎት የሚሰጡበት ዝርዝር ቋንቋዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያን በተመለከተ ግን አንድም ቋንቋ የለም። የኛ ሕዝብ ሁሉንም አውታሮች ይጠቀማል። ነገር ግን ራሱን መከላከልም ሆነ ሌሎችን ከጥላቻ ነገር መከላከል የሚችልበትና አግባብ መረጃዎችን በአግባቡ የሚረዳበት ቋንቋ አለመኖሩን በሪፖርቱ ተካቷል።
እነዚህ ማህበራዊ አውታሮች ከሀገሪቱ ሕግ ጋር እራሳቸውን አጣጥመው ለመሥራት የሚያስችል ውስንነት እንዳለባቸው ታይቷል። አጠቃላይ የሪፖርቱ መንፈስ ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማህበራዊ ሚዲያው በሚያስተላልፈው የጥላቻ ንግግር በሀገሪቱ ግጭትና አለመረጋጋት እንዲበራከት እያደረገ ያለውን አሉታዊ ሚና እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ዮናታን፡- ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለሌላው ማህበረሰብ አዲስ ነገር አይደለም። በየመሸታ ቤቱ የሚወሩ ነውረኛ ነገሮች በሌላውም ዓለም መኖሩ የተለመደ ነው። አሁን ፈታኙ ነገር በየጓዳው የሚወሩ ነገሮች አደባባይ መውጣታቸው ነው። ይህ ማለት በጓዳ መቅረት የነበረባቸው ነውረኛ ነገሮች ሚሊዮኖች በሰከንድ ያይዋቸዋል። የመዛመት አቅማቸውን ቴክኖሎጂው ቀላልና ፈጣን አድርጎታል። የዛሬ ሃያ ዓመት ወደኋላ ብንመለስ እንደዚህ ዓይነት ንግግሮች በስህተት በሚዲያ ቢሰሙ ቀውስ የሚፈጥሩ የነበረ ሲሆን አሁን አንድ ሰው በቀላሉ ከካሜራ ጀርባ ሆኖ የሚናገራቸውና በብዙ ዜጎች ላይ ጫና የሚፈጥር ሆኗል።
የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ በረጅም ጊዜ ዜጎች ላይ የሚፈጥረው ጫና ከባደ በመሆኑ መከላከል ግድ ነው። ሀሰተኛ መረጃው ዜጎች ከመንግሥት ጋር እንዳይተማመኑ የማድረግ አቅም ሁሉ አለው። ይህ ደግሞ ሥርዓት አልበኝነት እንዲበራከት ከማድረጉም በተጨማሪ፤ ሕዝብ ግራ እንዲገባ፤ እርስ በእርሱም እንዳይተማመን፤ ሥርዓቱን እንዳያምን የሚያደርጉ በመሆኑ ከባድ ጫና እየፈጠረ ነው። ይሄኛውን ትውልድ ብቻ ሳይሆን ተተኪው ትውልድ ላይም ጫናው ከባድ ነው።
ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር እንደ ሀገር ትልቅ ስጋት ነው። የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍና የሚኬድበት አካሄድን የሚያደናቅፍና ለሀገር መንግሥት ግንባታ ዋና እንቅፋት የሚሆን ነው። ያ ማለት ግን ማህበራዊ ሚዲያ የሚሰጠንን መልካም ነገር መካድ አይደለም። ማህበራዊ ሚዲያ ያለውን በጎ ነገር እያጎሉ መሄድና መጥፎውን እያቀጨጩ መጓዝ ያስፈልጋል። ማህበራዊ ሚዲያ እንደ ኒኩሌር ቦንብ ነው፤ በሰላም ከተጠቀምን ለኃይል አቅርቦት ከፍተኛ ጥቅም ያለው ለጦርነት ካዋልነው በርካቶችን ገዳይ ነው። ቃል ይሰብራል፤ ቃል ይሰራል ነውና የሚሰራጩ መረጃዎች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ማህበራዊ ሚዲያው በግጭት ወቅትም ሆነ በሌሎች ጊዚያት የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ዮናታን፡- በግጭቶች ወቅት የተለያዩ ዓይነት ያልተገቡ ዘገባዎች ይታያሉ። ይህ ማህበረሰብን የሚጎዳ እና ታሪክ ሰንዶ በማስቀመጥ ለተራዘመ ግጭት የሚጋብዝ ነው። አሁን ላይ ዋናዎቹ ሚዲያዎች ይህንን ተግባር ከማድረግ ተቆጠበዋል። ነገር ግን ሌሎች ከሀገር ውጭ ያሉና ዲጅታል ሚዲያ ላይ የሚረጩ መርዛማ ንግግሮች ለቀጣይ ጊዜ የሚያሳደረው ጫና ከባድ ነው።
ይህንን ለመከላከል ባለሥልጣኑ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎንም መንግሥትና የሲቪክ ማህበራት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ዮናታን፡- እኔም ሃሳቤን እንዳካፍል ስለጋበዛችሁኝ የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም