“መናኸሪያ በሌለበት ከተማ የትራ ንስፖርት ሪፎርሙን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ነው” – አቶ ከሊፋ አባ ሳኒ በጅማ ከተማ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ኤጀንሲ ጽሕፈት ቤት የትራንስፖርት አቅርቦት አስተባባሪ

ለመንገደኞች ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ከሚያስችሉ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች መካከል ዘመናዊ መናኸሪያ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው:: አሁን ላይ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ ዲዛይን ያላቸው ዘመናዊ የአውቶቡስ ተርሚናሎች በመገንባት ላይ ናቸው:: ከእነዚህ መካከል የጅማ ከተማ ዘመናዊ አውቶቡስ ተርሚናል አንዱ ነው:: የዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ ዝግጅታችን የጅማ ከተማ ዘመናዊ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ መጓተት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ የሕዝብ ቅሬታ ያስመለከትናል::

በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የጅማ ከተማ ዘመናዊ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ ፕሮጀክት በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ቀን ቢቆረጥለትም በተባለው ጊዜ መጠናቀቅ አልቻለም:: ለዚህም ፕሮጀክቱን ለመገንባት በወሰደው ተቋራጭ እና ፕሮጀክቱን በሚቆጣጠረው የመንግሥት አካል ድክመት እንደሆነ ቅሬታ ይቀርባል:: የግንባታው መጓተት ለከፍተኛ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተዳርገናል ያሉት የጅማ ከተማ እና ዙሪያ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም አሽከርካሪዎች “የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደን” ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ክፍል አቤት ብለዋል:: የዝግጅት ክፍሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ያገኘውን ምላሽ እንዲህ አሰናድቶታል::

የአሽከርካሪዎች እና የህብረተሰቡ ቅሬታ

የጅማ መናኸሪያ በወቅቱ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ለእንግልት መዳረጋቸውን ለዝግጅት ክፍላችን አቤት ያሉት የአሽከርካሪዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ናቸው:: የሁሉንም ቅሬታ አቅራቢዎች አቤቱታ በዚህ ዝግጅት ብቻ ማስተናገድ ስለማይቻል እና ሃሳባቸው ተመሳሳይ በመሆኑ የሶስት አሽከርካሪዎችን እና የአንድ መንገደኛ አስተያየት ይዘናል::

በፕሮጀክቱ መዘግየት ችግር ያጋጠማቸው እና ለዝግጅት ክፍላችን ችግራቸውን ከነገሩን አሽከርካሪዎች መካከል ከጅማ አንድ ጊዜያዊ መናኸሪያ ወደ አጋሮ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት አቶ ሰኢድ ከማል አንዱ ናቸው:: እንደ አቶ ሰኢድ ገለጻ፤ የጅማ ዘመናዊ የአውቶብስ ተርሚናል ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ባለመሆኑ በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደረ ነው።

አሁን አገልግሎት እየሰጡበት ያለው ጊዜያዊ መናኸሪያ ከተማ አስተዳደሩ “ከጅንአድ” በትብብር ባገኘው ቦታ ላይ ነው:: ቦታው ለመናኸሪያ ታስቦ የተገነባ ባለመሆኑ በየጊዜው ይሰምጣል:: በዚህ የተነሳም በሳምንት ሁለት ጊዜ ድንጋይ እና ጠጠር ይሞላበታል:: ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ካላት ሀብት አንጻር ትክክለኛ ርምጃ አይደለም::

ቦታው ረግረጋማ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ተሽከርካሪዎች በጭቃ እየተያዙ እንደሚቸገሩ የሚናገሩት አቶ ሰኢድ፤ በዚህም ለበርካታ ጊዜያት የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚስተጓጐል ያስረዳሉ:: በጊዜያዊ መናኸሪያው ባለው ጭቃ ከተሽከርካሪዎች ባሻገር መንገደኞችም ለመሳፈር እንደሚቸገሩ አመላክተዋል::

እንደ አቶ ሰኢድ ገለጻ፤ በመናኸሪያው ውስጥ ምንም ዓይነት የመንገደኞች ማረፊያና መጸዳጃ ቤት የለም:: ሁሉም ሰው በመናኸሪያው ውስጥ በአገኘው አካባቢ ይጸዳዳል፤ ቆሻሻም ይጥላል:: ይህም ለከፍተኛ የጤና ችግር እየዳረገ ነው:: በተመሳሳይ በዚሁ ቦታ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት የሚቀመጡ መንገደኞች አሉ:: ይህም አሽከርካሪዎችን እና የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን ለከፋ የጤና ችግር እየዳረገ ነው::

በዘመናዊ አውቶብስ ተርሚናሉ ግንባታ መጓተት ምክንያት ለዝግጅት ክፍላችን ቅሬታ ካቀረቡት አሽከርካሪዎች መካከል ከአጋሮ ጅማ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት አቶ እንግዳወርቅ አብየ ሌላኛው ናቸው:: እንደ አቶ እንግዳወርቅ ገለጻ፤ ጊዜያዊ መናኸሪያው ጠዋት እና ማታ በጣም ስለሚጨናነቅ መኪና ለማስገባት እና ለማስወጣት ፈተና ነው። ብዙ ጊዜ የተሽከርካሪ ግጭት ይፈጠራል:: በዚህም በተደጋጋሚ የንብረት ውድምት እየደረሰ ነው::

ይገነባል የተባለው የአውቶብስ ተርሚናል በተባለለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ በጊዜያዊ መናኸሪያዎች ራሳቸውን በሕገወጥ የተደራጁ ወጣቶች ተሽከርካሪዎች ለመውጫ ከሚከፍሉት ክፍያ በተጨማሪ ለተራ እንደሚያስከፍሉ ይናገራሉ:: የመናኸሪያ ግንባታ ቢጠናቀቅ አሽከርካሪዎች እና ተሳፋሪዎችን ከሕገወጦች መጠበቅ እንደሚያስችል ያስረዳሉ:: ስለሆነም ከችግሮች ተደራራቢነት አንጻር የተጀመረው የአውቶቡስ መናኸሪያ በአስቸኳይ ሊጠናቀቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል::

ሌላኛው አቤቱታ አቅራቢ ደግሞ ከጅማ ወደ በደሌ አገልግሎት የሚሰጠው አቶ ሀኒ ተሰማ ነው:: አቶ ሀኒ ተሰማ በበኩሉ፣ አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለው ጊዜያዊ መናኸሪያ ጭቃ የሚበዛበት እና ረግረጋማ በመሆኑ ለተሽከርካሪ በጣም አስቸጋሪ ነው። ከዚህ ጭቃ ቦታ ለመራቅ ሲሉ አሽከርካሪዎች በሕገ ወጥ መልኩ መንገድ ላይ ይጭናሉ:: በዚህም በተሳፋሪዎች ላይ ከዝርፊያ ጀምሮ በርካታ ችግሮች ይፈጠራሉ:: አሁን ክረምት እየመጣ ነው:: በክረምት ደግሞ በዚህ ጊዜያዊ መናኸሪያ አገልግሎት ለመስጠት የማይታሰብ ነው:: ስለዚህ አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ሀኒ ጠቁመዋል::

ከመናኸሪያው ግንባታ መዘግየት ጋር ተያይዞ ከአሽከርካሪዎች በተጨማሪ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች እና ተሳፋሪዎችም ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ አቅርበዋል:: በአቤቱታ ያቀረቡ የከተማዋ ነዋሪዎች በርካታ ናቸው:: ይሁንና የሰጡን አስተያየት ተመሳሳይ በመሆኑ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብን ቅሬታ ብቻ መርጠን እንደሚከተለው አቅርበናል::

የከተማዋ ተፈጥሯዊ መገኛ ለፖለቲካል ኢኮኖሚ አመች ነው:: በዚህም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች ያርፉባታል፤ ይሳፈሩባታልም:: ከዚህ አኳያ የተጀመረው የዘመናዊ አውቶብስ ተርሚናል ፕሮጀክት በከተማዋ እና ዙሪያዋ ለሚደረጉት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል::

ነገር ግን አሁን ላይ የመናኸሪያው ግንባታ በመጓተቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ ይስተዋላል:: ከተማ አስተዳደሩም ማግኘት የነበረበትን ገቢ እያሳጣው ነው:: በጊዜያዊነት የመናኸሪያ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ቦታዎች የጅማ ከተማን ደረጃ የማይመጥኑ በመሆናቸው የከተማዋን ገጽታ እያበላሹ ነው:: በአጠቃላይ ከመናኸሪያ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ችግሮች አሳሳቢ በመሆናቸው በአስቸኳይ መፍትሔ እንደሚያሻቸው አመላክተዋል::

የጅማ ከተማ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ኤጀንሲ ጽሕፈት ቤት ምላሽ አቶ ባህሩ ጃድ የጅማ ከተማ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ኤጀንሲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው:: እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ የከተማው ማህበረሰብ የትራንስፖርት አገልግሎት የተሳለጠ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል:: ከዚህ አንጻር በከተማው ውስጥ የሚገኘው የዘመናዊ አውቶብስ ተርሚናል ግንባታ አንዱ ነበር:: ይሁን እንጂ ግንባታውን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ዘመናዊ የአውቶብስ ተርሚናል በታሰበው ልክ ግንባታው ሊከናወን አልቻለም::

የመናኸሪያ ግንባታ ፕሮጀክቱን ኦማ ኮንስትራክሽን የተሰኘ ተቋራጭ በ2011 ዓ.ም ውል ቢወስድም በተባለው ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ማስረከብ ስላልቻለ ውል እንዲቋረጥ ተደርጓል። አሁን ላይ ዘመናዊ የአውቶብስ ተርሚናል ግንባታ ፕሮጀክቱ “ኦቢኤም” ለተባለ ኮንስትራክሽን ድርጅት የተሰጠ ሲሆን የቁጥጥር ሥራውን የኦሮሚያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኤጀንሲ ያከናውናል::

መናኸሪያው ከፍተኛ የሕዝብ ጥያቄ ያለበት በመሆኑና እየተፈጠሩ ካሉ ችግሮች አንጻር በአጭር ጊዜ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው። አብዛኛው የፕሮጀክቱ ሥራዎች ተከናውነዋል:: አገልግሎት የሚሰጥበት የሕንፃ ሥራ ተጠናቋል:: አሁን ላይ የሚቀረው ሥራ ውስን ነው:: የቀረው የመናኸሪያው የቤዝ ኮርስ እና የአስፓልት ንጣፍ ሥራ ነው:: ይህን ለማጠናቀቅ የጠጠር እና አስፓልት ንጣፍ ሥራ እየተከናወነ ነው:: ከሁለት ወር በኋላ ተጠናቆ ለትራንስፖርት አገልግሎት ክፍት እንደሚሆን እንጠብቃለን::

ሌላው በጅማ ከተማ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ኤጀንሲ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን ጥያቄ የቀረበላቸው የትራንስፖርት አቅርቦት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ከሊፋ አባ ሳኒ ናቸው:: አቶ ከሊፋ አባ ሳኒ እንደሚሉት፤ በ2011 ዓ.ም የጅማ ከተማን ዘመናዊ የአውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ ፕሮጀክት ውል የወሰደው ኦማ ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ነበር:: ይህ ተቋራጭ ከአምስት ዓመት በፊት ሥራውን ሲጀምር ፕሮጀክቱን በሁለት ዓመት ሰርቶ ለማጠናቀቅ ውል ገብቶ ነበር:: ነገር ግን በግንባታ እቃዎች የዋጋ ንረት ሳቢያ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ገንብቶ ሊያስረክብ አልቻለም:: ብዙ መጓተቶችም ተፈጠሩ::

የመናኸሪያ ግንባታው በተባለው ጊዜ ባለመጠናቀቁ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ችግር አጋጥሟል:: አሽከርካሪዎችንና እና ሕዝቡን ለከፋ እንግልት ዳርጓል:: ተሽከርካሪዎቹ ቁመው የሚጭኑበት ምቹ ቦታ አጥተዋል:: ይህን ችግር ለመቅረፍ እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ በከተማዋ በሚገኙ መንገዶች (አስፓልት ዳር) የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ሲሞከር ቆይቷል::

ነገር ግን የአስፓልት ዳር አገልግሎቱ ተሳፋሪዎችን እና አሽከርካሪዎችን ለተለያዩ አስከፊ ችግሮች በመዳረጉ ኤጀንሲው ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልግ ተገዷል:: በዚህም በጊዜያዊነት ሶስት ቦታዎች ላይ የመናኸሪያ አገልግሎት እንዲጀመር አድርጓል:: እነዚህ ጊዜያዊ መናኸሪያዎች ሁለቱ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ከወሰዱት ቦታ ትብብር ተጠይቆ የተገኙ ሲሆን አንደኛው ደግሞ ከጅማ ከተማ “ጅንአድ” በትብብር የተገኘ ቦታ ነው:: እነዚህ መናኸሪያዎች ምቹ ባለመሆናቸው አሁንም ሕዝብ እየተሰቃየ ነው:: የተነሳው ቅሬታም ተገቢ እና ትክክል መሆኑን እንደሚረዱ ያምናሉ::

ከፕሮጀክቱ መጓተት ጋር ተያይዞ በተለያዩ ጊዜያት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ከሊፋ፤ ባደረጉት ውይይት ኦማ ኮንስትራክሽን ግንባታውን በተባለለት ጊዜ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ የወሰደው ውል እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን ይናገራሉ::

ከኦማ ጋር የነበረው ውል በመቋረጡ አሁን ላይ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ሥራ ለኦቢኤም ኮንስትራክሽን ተሰጥቷል:: አሁናዊ የግንባታ ሁኔታው ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነው:: አሁን ላይ ባለው የግንባታ ፍጥነት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል::

የኦ.ቢ.ኤም ኮንስትራክሽን ሥራው በምን ያህል ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተስማምታችሁ ነበር? ስንል ላነሳንላናቸው ጥያቄ የኦ.ቢ.ኤም ኮንስትራክሽን የፕሮጀክቱን ሥራ የወሰደው በ2015 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ነው:: ሥራውን በሶስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተስማምቶ ነበር:: ነገር ግን እስካሁን ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ሳይጠናቀቅ ከስምንት ወራት በላይ መቆጠራቸውን ተናግረዋል::

ቅሬታ አቅራቢዎች ለዝግጅት ክፍሉ ቅሬታቸውን ባሰሙበት ወቅት ላሉት ጊዜያዊ መናኸሪያዎች የመውጫ ይከፍላሉ ነገር ግን በመናኸሪያው ውስጥ በተመሳሳይ ለተራ ተብለው ገንዘብ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል:: ለዚህስ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል::

በመናኸሪያ ውስጥም እናንተ ያነሳችኋቸው ችግሮች አሉ:: እነዚህንም ቅሬታዎች ለመፍታት በየዕለቱ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረግን ነው:: ለዚህም እንደማሳያ የምናነሳው እንደ ጅማ 31 መስመሮች አሉን:: በ31 መስመሮች የዲጂታል ትኬት ሲስተሞችን ዘርግተን ሥራ እንዲጀምሩ አድርገናል:: በመናኸሪያዎቹ ውስጥም በታሪፍ ተሳፋሪዎችን ያስተናግዳሉ:: ነገር ግን ከመናኸሪያው ውጭ አንዳንድ አገልግሎት ሰጭዎች የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ::

ይህንንም ለመከላከል ኬላ ላይ ከሚቆጣጠሩ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው:: ይህ ማለት ግን አንዳንድ ክፍተት የለም ማለት አይቻልም:: የትራንስፖርት ሥራ አስቸጋሪ ነው:: ጠዋት ያለው እና ማታ የሚከሰተው ፈጽሞ የተለየ ነው:: ይሁን እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በየዕለቱ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ መሥራት ያስፈልጋል:: መኪኖች ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲወጡ ለከተማዋ ልማት በደረሰኝ የሚደረግ ክፍያ አለ:: አንዳንድ ሕግን የሚተላለፉትን ለማረም ኬላ ላይ ከሚቆጣጠሩ አካላት ጋር በመሆን ሥራዎችን እየሠራን ነው::

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የሚጠበቅባቸውን የመውጫ ክፍያ ቢፈጽሙም የተደራጁ ወጣቶች ደግሞ የተራ ካልከፈላችሁ መሥራት አትችሉም ብለው ክልከላ ያደርጋሉ:: ይህ አግባብነት ያለው ነገር አይደለም:: ይህንን ለመከላከል ምን እያደረጋችሁ ነው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ ሲመልሱ ችግሩ አለ:: ግን ማንም አካል በሰው ንብረት ላይ ተደራጅቶ መሥራት አይችልም:: በተለይ ከጊዜያዊ መናኸሪያዎች ውጭ በመንገድ ላይ ተደራጅተናል የሚሉ ሕገወጦች ʿሰው አምጥቼለሁ ወይም ሌላ ነገር አድርጌልሃለሁና ገንዘብ አምጣ’ በማለት ከአሽከርካሪዎች ጋር እስጣ ገባ ሲገቡ ይስተዋላል::

ነገር ግን በመናኸሪያ ውስጥ መሥራት የሚችሉት በማህበራት የተደራጁ ወጣቶች ናቸው:: እነሱም የትራንስፖርት አገልግሎቱን የተሳለጠ ማድረግ እንጂ የተራ ማስከፍል አይችሉም:: አልፎ አልፎ ግን ተሳፋሪ ላይ ዋጋ ጨምረው እንዲጫን የሚያደርጉ አሉ፤ እነሱንም በተጨባጭ የያዝናቸውን አባረናል:: ከኢ-ትኬት ጋርም እንዲሁ ተቀናጅተው ሕገወጥ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችን አባረናል:: በተጨማሪም ከአሠራሩ ውጭ ጅምላ ትኬት ሲሸጡ የተገኙትን ሁለት ሰዎች በአንድ ወር ውስጥ ከሥራ አሰናብተናል:: ህብረተሰቡም ሕጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ አገልግሎት ማግኘት እንዳለበት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራም ሰርተናል::

ከተለያዩ ተቋማት ጋር የፕሮጀክት አፈጻጸም ሂደት የልምድ ልውውጣችሁ ምን ይመስላል? ለተባሉትም ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል::

አሁን ላይ በዋናነት ግንባታውን በኃላፊነት እያሠራ ያለው የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ነው:: የሚቆጣጠረውም የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ነው:: እኛ እንደ ቢሮ የምናደርገው ፕሮጀክቱ በተያዘለት ገዜ እንዲያልቅ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ ብቻ ነው:: ይህ ሲባል በመናኸሪያ እጥረት ምክንያት እየተፈጠረ ያለውን ችግር በመጥቀስ ግንባታው እንዲፈጥን መጠየቅ ነው የምንችለው:: ከሚመለከተው አካላት ጋር በሃሳብ ደረጃ ውይይት እያደረግን ነው::

በመናኸሪያ አካባቢ የተሽከርካሪ አቅርቦት ችግር የለም:: ከ1100 በላይ የሚሆኑ በተለምዶ አጠራራቸው ኮስትር የሚባሉ ተሽከርካሪዎች አሉ:: 426 የሚሆኑ ታክሲዎች፤ 4400 የሚሆኑ ባጃጆችም እንዲሁ በከተማዋ አገልግሎት ላይ ይገኛሉ:: በባጃጅ ዙሪያ ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆነውን ለመለየት ውይይት በማድረግ ፖሊሲ በማርቀቅና የራሳችን ኮድ በማዘጋጀት ከ11 የባጃጅ ማህበራት ጋር በመሆን ከተለያዩ ቦታዎች በማምጣት ለመንግሥት የሚገባውን ክፍያ ሳይከፍሉና፤ ቦሎ ሳያድሱና መሥራት ካለባቸው አካባቢዎች ውጭ የሚሰሩትን የመለየት ሥራ ተሰርቷል::

በዚህም ሥራ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ1 ነጥብ 1ሚሊየን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ ተችሏል:: 4400 ባጃጆች ውስጥ ከ3150 የሚሆኑት ብቻ ህጋዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል:: ወደ 37 የሚሆኑ ባጃጆችም ሕገወጥ መሆናቸውን ማጣራት ተችሏል:: ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር አንድን ባጃጅ ሶስት እና አራት አሽከርካሪዎች ያሽከረክሩ ነበር:: አሁን ላይ ግን ባዘጋጀነው ባጅ መሠረት አንድን ባጃጅ ያለ ባለቤቱ የሚያሽከረክር ከሆነ ይቀጣል ይህ ወንጀልን ለመከላከል ረድቷል:: መናኸሪያ በሌለበት ከተማ የትራንስፖርት ሪፎርሙን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ነው:: ስለሆነም መናኸሪያ አካባቢ ያለውን ችግር መፍታት ለነገ ሊባል እንደማይገባ ጠቁመዋል::

በኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኦብኤም ኮንስትራክሽን አክስዮን ድርጅት አማካሪና የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ ምላሽ

በኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካሪ የጅማ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ ተቆጣጣሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኜ አራርሳ እንደገለጹት፣ የአውቶቡስ መናኸሪያውን በ318 ሚሊዮን ብር ለመገንባት በ2011 ዓ.ም ኦማ ኮንስትራክሽን ውል ወስዶ ግንባታ ቢጀምርም በገጠመው የአቅም ማነስ ምክንያት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ሳይከናወን ቀርቷል።

በዚህ የተነሳም ከተቋራጩ ጋር የነበረው ውል ተቋርጦ በ2015 ግንቦት ወር ላይ ግንባታን በ475 ሚሊዮን ብር ለኦቢኤም ኮንስትራክሽን ድርጅት ተሰጥቷል:: ድርጅቱም ግንባታውን በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል ገብቶ ወደ ሥራ ገብቷል::

ኦቢኤም ፕሮጀክቱን ከኦማ ሲረከብ የሲቪል ግንባታ ሥራው 42 በመቶ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር፣ አሁን ላይ የሲቪል ግንባታው ሥራ ከ78 በመቶ በላይ መድረሱን አመልክተዋል። አሁን ላይ የአስፓልት ጠጠር ምንጣፍ (base course) ግብዓት ላይ ችግር እንዳጋጠመ ገልጸዋል።

የአስፓልት ሥራው ለቻይና የኮንስትራክሽን ኩባንያ ለመስጠት ድርድር እየተካሄደ መሆኑን አመልክተው፤ የአስፓልት ንጣፍ ጠጠር (base course) ጥራትን ለማረጋገጥ (ሳምፕል) ለጅማ ዩኒቨርሲቲ መላኩን ጠቁመዋል። ግንባታውን በውሉ መሠረት እስከ ግንቦት ወር ድረስ አጠናቆ ለማስረከብ እየተሠራ መሆኑን፣ አልፎ አልፎ በሚዘንበው ዝናብና በግብዓት አቅርቦት እጥረት ምክንያት በተፈለገው ልክ እየተሠራ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ጥያቄ ያለበት በመሆኑ የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት የሚከታተለው ነው:: ፕሮጀክቱን በተገባው ውል መሠረት ለማጠናቀቅ ጥረት ሲደረግ ነበር:: ነገር ግን የቀረው ጊዜ አንድ ወር ነው:: ዝናብ ካለስቸገረ ምን አልባት አስፓልት ንጣፍ ሥራ ሊሠራ ይችላል:: ነገር ግን አንዳንድ ግብዓት ዕጥረት ሳቢያ ጊዜ ሊወስድ ይችላል:: እንደ እቅዳችን በ2016 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ነው::

የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ / ኮንትራክተር/ ምላሽ

አቶ ለማ ሶራ ይባላሉ የጅማ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ውል ወስዶ ግንባታ ከጀመረ 11ኛ ወሩ ላይ ደርሷል:: ውሉ ለአንድ ዓመት የተወሰደ ነው:: ከዚህ በፊት ከነበረው ኮንትራክተር ውል ስንወስድ በርካታ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ብዙ ጊዜ ወስዷል:: አሁን ላይ የሕንፃውን የአሉሚኒየምና የቀለም ሥራ ተሠርቷል::

የተርሚናሉ ሥራ ከአካባቢው የአየር ጸባይ ጋር ተዳምሮ ፈታኝ ነው። የሆነ ቦታ ሥራ ሲሰራ ውሃ ይመነጫል፤ ይህን እንደገና ለማድረቅ ጊዜ ይወስዳል:: አሁን ላይ ከፊል መሠረቱ ተጠናቋል:: የቀረው ትልቁ ሥራ ቤዝ ኮርስና አስፓልት ንጣፍ ነው:: ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የሕዝብ ጥያቄ ያለበት በመሆኑ ችግሩን የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት ርብርብ እየተደረገ ነው::

ውል የተወሰደው ለአንድ ዓመት ነው:: አሁን ላይ 11ኛ ወር ላይ ነን :: ስለዚህ በዚህ አንድ ወር ይህን ግንባታ ማጠናቀቅ ትችላላችሁ ተብለው የተጠየቁት አቶ ለማ በምላሻቸው፤ ቀድሞ ከነበረው ውል ተቋርጦ በአዲስ መልክ ውል ተይዞ ወደ ግንባታ ሲገባ ብዙ ፈተናዎች ነበሩ:: ለማስተካከል ብዙ ጊዜ ወስዷል:: አሁን ላይ የቀረው የጠጠርና የአስፓልት ንጣፍ ሥራ ነው::

ሕዝቡ የሚያነሳውን ችግር እንረዳለን:: እንደ ክልልም ችግሩን ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ ነው:: የቤዝ ኮርስ ዋጋ ከውሉ በላይ ገንዘብ የሚጠይቅ ሆኗል:: ይህን አቻችሎ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው:: የቀረው የውል ጊዜ አንድ ወር በመሆኑ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው::

የጋዜጠኞች ትዝብት

ፕሮጀክቱ ለሌላ ተቋራጭ ቢሰጥም አሁንም ከግብዓት እና መሰል ችግሮች ጋር ተያይዞ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ እንደማይችል ታዝበናል:: የአስፓልት ንጣፍ ሥራውንና የቤዝ ኮርስ ሥራው ገና አልተጀመረም:: አስፓልቱን ለማሠራት ከቻይና ድርጅት ጋር ድርድር አልተጀመረም:: ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ዘመናዊ የአውቶብስ ተርሚናሉ ግንባታ በቀሪው አንድ ወር ሊጠናቀቅ የሚችል አይደለም፣ አስፈላጊው ርብርብ ካልተደረገ መጪው የክረምት ወር ከመሆኑ አንጻር በዚህ ዓመት ስለመጠናቀቁ ርግጠኛ መሆን አይቻልም::

እንደ አማራጭ ተወስደው በጊዚያዊነት እያገለገሉ ያሉ መናኸሪያዎች ማረፊያና መጸዳጃ ቤቶች ባለመኖራቸው ለአሽከርካሪዎችም ሆነ ለመንገደኞች ጤንነት አደጋ ደቅነዋል::

ሞገስ ተስፋ፣ ሙሉቀን ታደገ እና መክሊት ወንድወሰን

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም

Recommended For You