ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ‹‹ሰርክ ኢትዮጵያን እናጽዳ›› የጽዳትና የመንጻት መርሃ ግብር በመንደፍ ህብረተሰቡን በመቀስቀስ ላይ ናቸው። ራሳቸውም አርአያ ሆኖ የማጽዳት እና የችግኝ ተከላ ትግበራ እያከናወኑ ይገኛሉ። ሌሎችም ሃሳቡን ተቀብለውት አካባቢን ማስዋብና የችግኝ ተከላ ከዘመቻ ወጥቶ ባህል እንዲሆን ለማድረግም የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ናቸው።
የመንግስት ተቋማትም ሆነ በግለሰቦች አካባቢን ከደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ለማጽዳት እና ችግኞች በየወቅቱ እንዲተከሉ በማድረግ አካባቢን የማስዋብ ስራ ትኩረት አግኝቶ እየተሰራ ነው። ይህም ስራ ከጅምሩ ተቀባይነቱ ከፍ ያለ ሆኗል ።
በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ውበትና መናፈሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ነጻነት ደረጄ፤ የጽዳትና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ይፋ መደረጉን ያስታውሳሉ። አረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር አሁን በአለም አቀፍ ደረጃ ችግር የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እና ህብረተሰቡ ንጹህ አየር እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ይጠቁማሉ። በመሆኑም ይህንን ለማስተግበር ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጥር ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪ ሆኑበትና በአርአያነት የተጀመረው ጥሩ ተግባር ነው። በወረዳው ወጣቶች በተለያዩ አልባሌ ቦታዎች ከሚያሳልፉ ይልቅ አካባቢን በማስዋብ የጥናት ቦታ ፣ ለሰርግና ለህጻናት መጫወቻ እንዲውሉ የማድረግ እንቅስቃሴም አለ ሲሉም ይጠቁማሉ። ‹‹የችግኝ ተከላ ከዚህ በፊት ክረምት ላይ የሚተገበር ነበር። አሁን እንደቋሚ ስራ ክትትል እየተደረገ ህብረተሰቡም ግንዛቤ በመፍጠር አሳታፊ የማድረግ አሰራር ተዘርግቷል›› በማለትም ወይዘሮ ነጻነት ያብራራሉ።
እንደ ወይዘሮ ነጻነት ገለጻ፤ ዘንድሮ የችግኝ ተከላ ስራው አብዛኛው ሰው ግንዛቤ አለው። መገናኛ ብዙሃንም ከበፊቱ የተሻለ ትኩረት ሰጥተውበት በመተግበሩ ህብረተሰቡ በየደጃፉ እና በተለያዩ ስፍራዎች ወጥቶ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ እየተሳተፈ ይገኛል። ጅምሩ ጥሩ ነው። ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲተገበር የሚፈለገው ውጤት እንዲገኝ ግንዛቤ ፈጠራው መቀጠል ይኖርበታል።
የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን መከላከልም ሆነ አካባቢን የተዋበ ስፍራ ማድረግ የሚጠቅመው ህብረተሰቡን ነው። አካባቢ ቢቆሽሽ፣ ጽዳት ቢጎድለው የሚጎዳውና ለበሽታ የሚጋለጠው ማህበረሰቡ ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ አካባቢ እንዲቆሽሽ የሚያደርጉ ችግር ፈጣሪዎች ሲያስተውል እንዳላየ ማለፍ ተገቢ አይደለም። ሁሉም አካባቢውን ጽዱ እና የተዋበ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት አለበት። መንግስት አካባቢን የማጽዳት እና የማስዋብ ስራን ትኩረት ሰጥቶ እየተገበረው ይገኛል። የተጀመረውን ስራ ህብረተሰቡ ተባባሪ ሆኖ ሊደግፈው ይገባል ይላሉ ወይዘሮ ነጻነት ።
የአካባቢን ንጽህና በመጠበቅ በኩል ብዙ ጉድለቶች አሉ። ባለሙያውም አንዳንዴ በጉዳዩ ትኩረት የማይሰጠውም ሆኖ ይታያል። አካባቢን መጠበቅ የሁሉም አካላት ድርሻ ነው። ንጽህናን ለመጠበቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሁሉም ድርሻ አለበት። ህብረተሰቡ ቆሻሻን በተገቢው ስፍራ ላይ በመጣል ብቻ ተባባሪ ሊሆን ይገባዋል። ህብረተሰቡ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ሲያይም የመከላከል ስራ መስራት ይኖርበታል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም መንግስት በየአካባቢው ህብረተሰቡ ሊጠቀምባቸው የሚችልበት የማረፊያ ቦታዎች ሊዘጋጁ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ።
አካባቢን መጠበቅም ሆነ አረንጓዴ ልማት ማካሄድ የሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ ዘሪሁን ጋሻው ናቸው። የጽዳትና የችግኝ ተከላው ቀደም ሲልም ጅምር እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም የተቀናጁ አልነበሩም። የአገሪቱ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጽዳት እና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን እንደ ዋና አጀንዳቸው አድርገው ይዘውት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍልም እንዲተገብረው ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛል። ይህ ከዚህ በፊት ሲደረግ ከነበረው የተለየ እንዲሆን ያደርገዋል። ህብረተሰቡም ይህንን ተከትሎ ጥሩ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ ነው። አካባቢን ማጽዳት አገር እንደሚጸዳ ግንዛቤ ለመፍጠር የተጀመረ ንቅናቄ አድርጌ እገነዘበዋለሁ። ህዝቡ በዚህ ማህበራዊ ኃላፊነት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት መትጋት ይኖርበታል ይላሉ ።
እርሳቸው እንደሚሉት ስራው ከወቅታዊ አጀንዳነት መውጣት አለበት። ከንቅናቄ እና ከዘመቻ ወጥቶ ተቋማዊ ሊሆን የሚችልበት እና በተቋም፣ በህግ የሚደገፍበት ስርዓት መዘርጋት አለበት። ከዚህ ባሻገርም እንደሌላው ዘርፍ በተጠያቂነት መንፈስ የሚፈጸም መሆን ይኖርበታል። ችግር ፈጣሪዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር መዘርጋት አለበት። አጠቃላይ ህብረተሰቡን ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረግ ይገባል። ይህንን በማስፈጸም ረገድም ጉድለቶች ይታዩበታል።
የአዲስ አበባ ከተማን አብነት ብንጠቅስ አብዛኛው አካባቢ ቆሻሻዎች ተከማችተው ይታያሉ ። የንጽህና እና የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች ይስተዋላሉ። እነዚህ ለምን ተከሰቱ? ብለን ብንጠይቅ በየደረጃው ያለው አመራር ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ስለማይሰጥ መሆኑን እንገነዘባለን። ትኩረት የማይሰጥበት ነገር ደግሞ ስለማይጠየቅበት ነው። በተሰጠው ኃላፊነት ልክ አመራሩ ተጠያቂ የሚደረግ ቢሆንና ‹‹ነገ ልጠየቅ እችላለሁ›› በሚል እሳቤ ቢሰራ አካባቢን ጽዱ የማድረግ እና አረንጓዴ የማልበስ ስራ ውጤታማ ይሆናል ሲሉም ያላቸውን ተስፋ ይጠቅሳሉ።
አሰራሩ ተጠያቂነት በሌለው እና ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ መተግበሩ ችግሮቹ ከቀን ቀን እየተደራረቡ እንዲቀጥሉ ነው ያደረገው። በመሆኑም በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ አካላትን መንግስት ተጠያቂ ማድረግ ካልቻለ ችግሩ እየጨመረ እና እየተወሳሰበ ይሄዳል የሚል ስጋትም አቶ ዘሪሁን አላቸው።
ጽዳትና አካባቢን የመጠበቅ ጉዳይ እንደሌሎቹ ችግሮች ሁሉ ያዝ ለቀቅ ሲደረግ የመጣ ጉዳይ ነው በማለት ይጠቁሙና፤ እስካሁን ተሰርቷል የተባለውም ቢሆን ያን ያህል አይደለም። ይህንን ስራ ውጤታማ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጀመሩት ስራ ባሻገር በተቋም፣ በህግና በፖሊሲ ደግፎ እንዲተገበር ማድረግ ወሳኝ ነው። አስቀድሞ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ከምንም በላይ ቀዳሚ አጀንዳ ማድረግ ያስፈልጋል። ጎን ለጎን ደግሞ አንዳንዴ በግንዛቤ የማይስተካከሉ ችግሮች ወይንም የማይገቡ ድርጊቶች ተፈጽመው በተገኙ ጊዜ ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው አቶ ዘሪሁን።
አጠቃላይ ስራው ዘላቂ መሆን አለበት። ህጻናቶች አካባቢን የማጽዳት አስፈላጊነትን ከታች ጀምሮ እየተማሩ የሚያድጉበትን ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ይህንንም በትምህርት ስርዓት ውስጥ አካትቶ ተማሪዎች አካባቢን የማስዋብ እና የማጽዳት ግንዛቤ በውስጣቸው እየሰረጸ የሚያድጉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ እና ከዚህ ቀደም እንደነበረው ያዝ ለቀቅ የማድረግ አዝማሚያ ከቀጠለ ዘላቂ አይሆንም።
አካባቢን መጠበቅ የህልውና ጉዳይ ነው። ይህ ሲባል ማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ የሚለማው አገር ውስጥ ባለው የተፈጥሮ ሃብት ላይ ተመስርቶ ነው። የአንድ አገር ሃብት በዋናነት መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ነው። የአካባቢ የጥበቃ ጉዳይ የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት ለመጠቀም የመታደግ ጉዳይ ቀዳሚ ነው። የተፈጥሮ ሃብት በተጎዳ መጠን የአንድ አገር ኢኮኖሚ መሰረቱን እያጣ ይሄዳል። በመሆኑም የተፈጥሮ ሃብትን መንከባከብ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ችግኝ መትከል ከዋናዎቹ ተግባራት መካከል የሚመደብ ነው ሲሉም አቶ ዘሪሁን ያብራራሉ።
አንድ አገር አድጓል ከተባለ በጽዳት እና አካባቢን በማስዋብ ትልቅ ጉዳይ ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ ከተሞች ለማጸዳትና ችግኞችን ለመትክል ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። በእነዚህ ጉዳዮች ህብረተሰቡ የባህል ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ አቶ ዘሪሁን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/ 2011
ዘላለም ግዛው